በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰዎች በዓይነ ቁራኛ እየተከታተሉህ ነውን?

ሰዎች በዓይነ ቁራኛ እየተከታተሉህ ነውን?

ሰዎች በዓይነ ቁራኛ እየተከታተሉህ ነውን?

ኤልሳቤጥ በየቀኑ መሥሪያ ቤቷ እንደደረሰች የምታደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች በሙሉ አንድ ካሜራ ይከታተላል። ወደ ሕንጻው ስትገባ ፊቷ ላይ የሚያነጣጥር ሌላ ካሜራ አለ። በቀኑ በሙሉ ሌሎች በርካታ ካሜራዎች እንቅስቃሴዎቿን ይከታተሏታል። ኤልሳቤጥ የምትሠራው በየቀኑ በሚልዮን ዶላር የሚቆጠር ጥሬ ገንዘብ ለሚያንቀሳቅስ ኩባንያ ስለሆነ እንዲህ ያለ ክትትል መደረጉ የሚያስደንቅ አይደለም።

ኤልሳቤጥ የቅርብ ክትትል እንደሚደረግባት ታውቃለች። ሥራም ስትቀጠር ሁኔታው በግልጽ ተነግሯታል። ሆኖም በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች በየቀኑ የሚደረግባቸው ክትትል እንዲህ ግልጽ ሆኖ አይነገራቸውም።

ስለላ በሚካሄድበት ማኅበረሰብ ውስጥ መኖር

በሥራ ቦታህ ክትትል ይደረግብሃል? በመላው ዓለም በሚልዮን የሚቆጠሩ ተቀጣሪዎች ሥራቸው ላይ እንዳሉ የኢንተርኔትና የኢሜይል ግንኙነታቸው ክትትል ይደረግበታል። የአሜሪካ ማኔጅመንት አሶሴሽን ለ2001 ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት “ከዩናይትድ ስቴትስ ዋና ዋና ኩባንያዎች መካከል ሦስት አራተኛ ያህል (73.5 በመቶ) የሚሆኑት ሠራተኞቻቸው በሥራ ገበታቸው ላይ ሳሉ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ፣ የስልክ፣ የኢሜይልና የኢንተርኔት ግንኙነቶች እንዲሁም የኮምፒውተር ፋይሎቻቸውን እየመዘገቡ ይመረምራሉ” ብሏል።

መንግሥታት ለስለላ መሣሪያዎች በሚልዮን የሚቆጠር ዶላር ያወጣሉ። ሐምሌ 11, 2001 ለአውሮፓ ፓርላማ ቀርቦ የነበረ አንድ ሪፖርት “ዩናይትድ ስቴትስ፣ እንግሊዝ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያና ኒው ዚላንድ . . . በቅንጅት የሚያካሂዱት ሰዎች የሚያደርጓቸውን ግንኙነቶች የሚጠልፍ የክትትል መረብ አለ” ብሏል። እነዚህ መንግሥታት ኤቸሎን ተብሎ በሚጠራ እርስ በርሳቸው የተያያዙ የሳተላይት መቀበያ ጣቢያዎች መረብ አማካኝነት በሳተላይት የሚተላለፉ የስልክ ውይይቶችን፣ የፋክስ፣ የኢንተርኔትና የኢሜይል መልእክቶችን ለመጥለፍ እንደሚችሉ ይነገራል። አውስትራሊያን የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ መንግሥታት በዚህ የክትትል መረብ ሲጠቀሙ “የፈለጉትን የፋክስና የኢሜይል መልእክቶች እንዲሁም ድምፅ እንዲለይ ከተደረገ የፈለጉትን ሰው የስልክ ጭውውት ነጥለው መቅዳት ይችላሉ።”

ሕግ አስከባሪዎችም በዘመናዊ የክትትልና የስለላ ዘዴዎች ይጠቀማሉ። ቢዝነስ ዊክ የተባለው መጽሔት እንዳለው በዩናይትድ ስቴትስ ኤፍ ቢ አይ የተባለው የወንጀል ምርመራ መሥሪያ ቤት “ኢሜይሎችን፣ የኢንተርኔት ግንኙነቶችንና የስልክ ጭውውቶችን” ጠልፎ የሚከታተልበት ካርኒቮር የተባለ ቴክኖሎጂ አለው። ይህ በዚህ እንዳለ በብሪታንያ ሕግ አስከባሪዎች “በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ስልኮች፣ ፋክሶችና የኢንተርኔት ግንኙነቶች በምሥጢር እንዲከታተሉ የሚያስችል አዲስ ሕግ እንደወጣ ቢቢሲ የተባለው የዜና ማሠራጫ ዘግቧል።

ስውር ካሜራዎችና የመረጃ ቤተ መዛግብት

አንድ ሰው በስልክ፣ በፋክስ ወይም በኢሜይል የማይጠቀም እንኳን ቢሆን ከክትትል ላያመልጥ ይችላል። በአውስትራሊያ፣ በኒው ሳውዝ ዌልስ ክፍለ ሐገር በባቡር የሚጠቀሙ ሰዎችን በዓይነ ቁራኛ የሚከታተሉ 5, 500 ካሜራዎች ተተክለዋል። በዚሁ ክፍለ ሐገር 1, 900 በሚያክሉ የመንግሥት አውቶቡሶች ላይ የስለላ ካሜራዎች ተተክለዋል።

በስለላ ካሜራዎች ብዛት የአንደኛነቱን ቦታ የያዘችው ብሪታንያ ስትሆን አንድ ካሜራ ለ55 ሰዎች እንደሚደርስ አንድ ጥናት ገልጿል። በ1996 በዩናይትድ ኪንግደም የሰዎችን እንቅስቃሴ የሚከታተሉ የስለላ ካሜራዎች የነበሯቸው ከተሞች 74 ብቻ ነበሩ። በ1999 ግን 500 ትላልቅና ትናንሽ ከተሞች እነዚህን መሣሪያዎች ተክለዋል። እነዚህ የስለላ ካሜራዎች እንደ አውሮፕላን ማረፊያና የከተማ አደባባይ ባሉ ሕዝብ የሚበዛባቸው ቦታዎች ያለን ሰው ለይቶ ለማወቅ ከሚያስችል የኮምፒውተር ፕሮግራሞች ጋር እንዲቀናጁ ተደርጓል።

ዛሬ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ሳታውቀው ክትትል ሊደረግብህ ይችላል። ፕራይቨሲ ኢንተርናሽናል የተባለው የሰብዓዊ መብቶች አስከባሪ ድርጅት ዲሬክተር የሆኑት ሳይመን ዴቪስ “የዛሬውን ያህል ስለ እያንዳንዱ ሰው በርካታ መረጃ መሰብሰብ የተቻለበት የታሪክ ወቅት የለም። በበለጸጉ አገሮች ስለሚኖር አንድ ተራ ሸማች ወይም አምራች የሚገልጹ መረጃዎች 400 በሚያክሉ ዋና ዋና ቤተ መዛግብት ውስጥ ተሰባስቦ ይቀመጣል። በአንድ ሰው ላይ ብቻ የተሰበሰቡት መረጃዎች አንድ ላይ ቢጠቃለሉ አንድ ትልቅ መጽሐፍ ሊወጣቸው ይችላል።”

ታዲያ ከክትትል ለማምለጥ ምን ልታደርግ ትችላለህ?