በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ሳትሸማቀቅ አዛጋ

በማሕጸን ውስጥ ያለ ሕጻን በተጸነሰ በ11 ሣምንት ውስጥ ማዛጋት እንደሚጀምር ሳሉድ የተባለው የስፔን ሳምንታዊ ጋዜጣ ገልጿል። አብዛኞቹ አጥቢ እንስሳት፣ አንዳንድ አእዋፍና ተሳቢ እንስሳት የማዛጋት ባሕርይ ይታይባቸዋል። የምናዛጋበት ትክክለኛ ምክንያት እስካሁን በርግጠኝነት ያልታወቀ ይሁን እንጂ እንደ መንጠራራት ያሉት ድርጊቶች ከማዛጋት ጋር ተዛማጅነት እንዳላቸው ተመራማሪዎች አስተውለዋል። እነዚህ እንቅስቃሴዎች “የደም ግፊትና የልብ ምት ፍጥነት እንዲጨምር ከማድረጋቸውም በላይ ጡንቻዎችንና መጋጠሚያዎችን ያዝናናሉ።” አገጫችንን በግድ በመዝጋት የማዛጋት ፍላጎታችንን ስናፍን እነዚህን ጥቅሞች ሳናገኝ እንቀራለን። በዚህ ምክንያት ተመራማሪዎቹ ሁኔታው የሚፈቅድልን ከሆነ “አገጫችንንና የፊታችንን ጡንቻዎች በደንብ ለቀቅ አድርገን” እንድናዛጋ መክረዋል። ማን ያውቃል፣ ሙሉውን ቀን ነቃ ብለህ እንድትውል የሚያስፈልግህ ጥሩ አድርገህ ማዛጋት ሊሆን ይችላል።

“ዶክተሮች” የሆኑ እንስሳት

የለንደኑ ኢኮኖሚስት መጽሔት “ቁጥራቸው እየጨመረ የመጡ የእንስሳት ባሕርይ አጥኚዎች የዱር አራዊት የሚያጋጥማቸውን የጤና ችግር በራሳቸው የመፍታት ችሎታ እንዳላቸው ያምናሉ” በማለት ዘግቧል። በታንዛኒያ የሚኖሩ ቺምፓንዚዎች ትላትሎችን መግደል የሚችል ኬሚካል ያለበትን የእንጨት ቅርፊት በመብላት በአንጀታቸው ውስጥ የሚፈጠሩትን ትላትሎች ያስወግዳሉ። በመላው አፍሪካ የሚኖሩ ዝንጀሮዎች በጣም ጥቃቅን የሆኑ መንጠቆዎች ያሏቸውን ቅጠሎች በመብላት አንጀታቸው ውስጥ የሚኖሩትን ትላትሎች ጎትተው እንዲያወጡላቸው ያደርጋሉ። መርዝነት ያላቸውን የእፀዋት ዘሮች የሚበሉት ማካም የተባሉ የወፍ ዝርያዎችም ወደ ሆዳቸው የሚገባውን መርዝ የሚያረክስላቸው ሸክላ ይበላሉ። የአላስካ ቡናማ ድቦች፣ የካናዳ የበረዶ ዳክዬዎችና ተኩላዎች የአንጀት ትላትል የሚገድሉ እፀዋትን ይበላሉ። በተለያዩ እንስሳት ላይ የተደረጉ የደም ምርመራዎች እንዳሳዩት በዱር የሚኖሩ ብዙ እንስሳት ከአካባቢያቸው ርቀው እንዲኖሩ የተደረጉ እንስሳትን ሊገድሉ የሚችሉ በቫይረስና በባክቴርያ ምክንያት የሚመጡ በሽታዎችን ተቋቁመው መኖር ችለዋል። ዚ ኢኮኖሚስት “እንደነዚህ ያሉት አስተያየቶች የዱር እንስሳት ጤንነታቸውን ለመጠበቅ የሚያደርጉትና ከአካባቢያቸው ርቀው እንዲኖሩ የተደረጉት እንስሳት ግን ሊያደርጉ የማይችሉት ነገር እንዳለ ያመለክታሉ” ብሏል።

ጉርምስና የሚጀምርበት ዕድሜ ቀንሷል

በርሊነር ሳይቱንግ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ “ጉርምስና የሚጀምርበት ዕድሜ እየቀነሰ መጥቷል” በማለት ዘግቧል። የሕፃንነት ዕድሜ ቢያንስ በአካላዊ እድገት ረገድ ከ10 እስከ 12 ባለው ዕድሜ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ከዚያም በፊት ማብቃቱ የተለመደ ነገር እየሆነ መጥቷል። በመላው ዓለም የሚገኙ ተመራማሪዎች ይህን አዝማሚያ ቢያስተውሉም ምክንያቱ ምን እንደሆነ ግን እርግጠኞች አይደሉም። በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል የአመጋገብ መሻሻልና የተላላፊ በሽታዎች መቀነስ ይገኙበታል። ሌሎች ደግሞ በምክንያትነት የሚጠቅሱት አካባቢያችን በተለያዩ ቅመሞች በተለይም ኢስትሮጅን ከተባለው የሴቶች ሆርሞን ጋር የሚመሳሰል ውጤት ባላቸው ቅመሞች መበከሉን ነው። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ከትክክለኛው ዕድሜ ቀድሞ ለአካለ መጠን መድረስ አለ እድሜ ሩካቤ ሥጋ ወደመፈጸም ያመራል። “ብዙ ጊዜ ዕቃ ዕቃ የሚጫወቱበት ዕድሜና ለመጀመሪያ ጊዜ ሩካቤ ሥጋ የሚፈጽሙበት ጊዜ በጣም ተቀራርቧል” ይላል ጋዜጣው።

በቁጣ መገንፈል ለሞት ሊዳርግ ይችላል

ዲያሪዮ ሜዲኮ የተባለው የስፓንኛ ጋዜጣ “ግልፍተኛ የሆኑ ሰዎች አንጎላቸው ውስጥ ደም በመፍሰሱ ምክንያት ራሳቸውን የመሳት ዕድላቸው በጣም ከፍተኛ ነው” ይላል። ዶክተሮች በግልፍተኝነትና በልብ በሽታ መካከል የቅርብ ዝምድና መኖሩን ከተገነዘቡ ብዙ ጊዜ ሆኗቸዋል። በቅርብ የተደረጉ ጥናቶች ደግሞ ግልፍተኝነት ደም አንጎል ውስጥ በመፍሰሱ ምክንያት ራስ የመሳትን አጋጣሚ ከፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል። በ14, 000 ሰዎች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከ60 ዓመት በታች የሆናቸውና የግልፍተኝነት አዝማሚያ ያላቸው ሰዎች ደም አንጎላቸው ውስጥ በመፍሰሱ ምክንያት ራሳቸውን የመሳት አጋጣሚያቸው በሦስት እጥፍ ይበልጣል። እንዲህ የሆነው ለምንድን ነው? ቁጣ የደም ግፊት እንዲጨምር፣ የደም ሥሮች እንዲኮማተሩና ደም እንዲረጋ የሚያደርጉ ቅመሞች እንዲበዙ ስለሚያደርግና ይህም “ከጊዜ በኋላ በአንጎል ውስጥ የሚኖረውን የደም ዝውውር ስለሚቀንስ” ሳይሆን እንደማይቀር ይገምታሉ።

ዋነኛ ገዳይ

ኒው ሳይንቲስት “ኤድስ በታሪክ ውስጥ ከታዩት ወረርሽኝ በሽታዎች ሁሉ በመብለጥ ጥቁር ሞት የተባለው ወረርሽኝ እንኳን ሊወዳደረው አልቻለም” ብሏል። “ጥቁር ሞት የተባለው ወረርሽኝ በ14ኛው መቶ ዘመን አውሮፓንና እስያን በማዳረስ 40 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ጨርሷል። አሁን 700 ዓመታት ካለፉ በኋላ ደግሞ ታሪክ ራሱን እየደገመ ነው።” ብሪትሽ ሜዲካል ጆርናል እንደዘገበው በዚህ አሥርተ ዓመት መጨረሻ ላይ በኤች አይ ቪ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር 65 ሚልዮን ይደርሳል። ባሁኑ ጊዜ በሳንባ ነቀርሳና በወባ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ቢሄድም እነዚህ በሽታዎች የሚያስከትሉት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት ኤድስ ከሚያደርሰው ጋር ሊወዳደር የሚችል አይደለም።

ወላጆችና ወጣት ልጆች

የለንደኑ ታይምስ ባወጣው ዘገባ መሠረት የቤተሰብ ግጭት በሚኖርበት ጊዜ ከወጣት ልጆች ይበልጥ የሚጎዱት ወላጆች እንደሆኑ ገልጿል። ዘገባው በመቀጠል ወላጆች “ስሜታቸውን እንጎዳለን ብለው በመፍራት ግልፍተኛ ልጆቻቸውን ከመቅጣት ወደኋላ ማለት የለባቸውም” በማለት ይመክራል። ከዚህ ይልቅ “ወላጆች ሥልጣናቸው እንዲከበር በማድረግ . . . ራሳቸውን ከጉዳት መጠበቅ ይኖርባቸዋል።” በፊላደልፊያ፣ ፔንስልቫንያ፣ ዩ ኤስ ኤ በሚገኘው ቴምፕል ዩኒቨርሲቲ በአፍላ ጉርምስና ዕድሜ ላይ ስለሚገኙ ወጣቶች ምርምር የሚያደርጉት ፕሮፌሰር ሎረንስ ስታይንበርግ ልጆች የሚደርስባቸውን ጉዳት የመቋቋም ችሎታቸው ብዙ ሰዎች ከሚያስቡት በላይ ከፍተኛ ነው። ፕሮፌሰር ስታይንበርግ በሺህ በሚቆጠሩ ወላጆች ላይ ከአሥር ዓመት በላይ ጥናት ካደረጉ በኋላ “ሥልጣኑን የሚያስከብር ወላጅ አፍቃሪና አሳቢ ሲሆን የሚሰጣቸውን መመሪያዎች፣ ገደቦችና ትእዛዞች በማስከበር ረገድ ጥብቅ ነው” ብለዋል። እንዲህ ባለው ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ልጆች ከፍተኛ ውጤት የሚያገኙና ደስተኞች ሲሆኑ በዚህም ምክንያት በወንጀልና ፀረ ማኅበረሰብ በሆኑ ድርጊቶች የመካፈል ዕድላቸው በጣም አነስተኛ እንደሆነ ሪፖርቱ ይናገራል።

የመዳበስ አስፈላጊነት

ፖለቲካ የተባለው የፖላንድ ሳምንታዊ መጽሔት “መዳበስም የፀሐይን፣ የውኃንና የምግብን ያህል ያስፈልገናል” ይላል። ሁላችንም ከቆዳችን በታች የተለያዩ የዳበሳ ዓይነቶችን ባሕርይ ሊለዩ የሚችሉ የነርቭ አውታሮች አሉን። አንድ ሰው በሚዳብሰን ጊዜ “አንጎላችን ዳበሳውን ተረድቶ ፈገግ እንድንል፣ ደስ እንዲለን ወይም ወዳጃዊ ስሜት እንድናሳይ ሊያደርገን ይችላል።” ሕፃናት በተለይ በጨቅላነት ዕድሜያቸው መዳበስና መታቀፍ ያስፈልጋቸዋል። የሚያሳዝነው ግን ብዙ ወላጆች ልጆቻቸውን የሚዳብሱት ልብስ በሚያለብሷቸው፣ በሚያጥቧቸው፣ በሚመግቧቸው ወይም በሚቀጧቸው ጊዜ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ የሚታቀፉ፣ የሚሳሙና በእጅ የሚዳበሱ ልጆች ‘ወላጆቻቸው ከማያቀርቧቸው ልጆች’ ይበልጥ ጥሩ ጤንነትና እድገት እንደሚኖራቸው ፖለቲካ ዘግቧል።

የዓለም ሐይቆች አደጋ ተጋርጦባቸዋል

የዓለም ውኃ ጉባኤ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ዊልያም ኮስግሮቭ “በዓለማችን ላይ ሰዎች ከሚያደርሱበት ጉዳት የተጠበቀ አንድም ሐይቅ የለም” ብለዋል። “ሐይቆችን በማበላሸት ላይ ስንሆን ይህ ደግሞ ኑሯቸውን በእነዚህ ሐይቆች ላይ በመሠረቱት ማኅበረሰቦች ላይ ትልቅ አደጋ ያስከትላል።” ከኢንዱስትሪዎች፣ ከእርሻዎችና ከቤቶች የሚወጣው ፍሳሽ በአሁኑ ጊዜ ንጹሕ መስለው በሚታዩ ሐይቆች ላይ ጭምር ከባድ ጉዳት እያደረሰ ሊሆን ይችላል። ኮስግሮቭ በማከል “የባሕር ሙቀት እንደመለወጥ ያለ አንድ ዓይነት ለውጥ በሚደርስበት ጊዜ በድንገት ሐይቁ ከወትሮው የተለየ ይሆናል። ለውጡ አንዴ ከጀመረ ሂደቱን መግታት አስቸጋሪ ነው።” ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን ከአፍሪካ በትልቅነቱ አንደኛ የሆነው የቪክቶርያ ሐይቅ ነው። ባለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት በርካታ የዓሣ ዝርያዎች ወደ ሐይቁ በገባው ቆሻሻና ፍሳሽ ምክንያት ሞተዋል። በተጨማሪም በቻይና የሚገኘው ታይ ሁ ሐይቅ በአደገኛ ሁኔታ ላይ ይገኛል። የዓለም ውኃ ጉባኤ ያወጣው መግለጫ “ሐይቁ በቆሻሻ ከመሸፈኑ የተነሣ በውኃው ላይ በእግር መሄድ እንደሚቻል ጠበብት ይናገራሉ” ብሏል። የሮይተር ሪፖርት እንደሚያመለክተው የሰው ልጆች ከሚጠቀሙት ውኃ መካከል 90 በመቶ የሚሆነው የሚገኘው ከሐይቆች ነው።

ሳቅ ለጤንነት!

ከልብ የመነጨ ሳቅ ትካዜ ከማስወገድ የበለጠ ጥቅም አለው። አንዳንድ ጃፓናውያን ዶክተሮች እንደሚሉት የኢንዶክራይን እጢዎችን፣ የነርቮችንና የበሽታ ተከላካይ ሕዋሶችን አሠራር ያስተካክላል፤ የልብ ምትና የአተነፋፈስ ፍጥነትን ያስተካክላል፤ ለጊዜውም ቢሆን የቁርጥማት በሽታን ያስታግሳል። ሳቅ አንዳንድ ነርቮችን ስለሚያነቃቃ ወደ ጡንቻዎች የሚፈሰውን የደም መጠንና የአንጎልን እንቅስቃሴ እንዲጨምር ያደርጋል። ከልብ በምንስቅበት ጊዜ ጡንቻዎቻችን እንዲንቀሳቀሱ እናደርጋለን። አይ ኤች ቲ አሳሂ ሺምቡን በተባለ ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ጥናት እንዳመለከተው “አንድ ሰው በሚስቅበት ጊዜ የሆዱ ጡንቻዎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ቁጭ ብድግ የማለትን ያህል ጉልበት ይጠይቃል።”

የኦሳካ የሥነ አእምሮ ሐኪም የሆኑት ሚችዮ ታናካ የሳቅን ጠቃሚነት አወድሰዋል። ታናካ እንዳሉት ሳቅ “ምንም ዓይነት ጉዳት የማያስከትል ጥሩ መድኃኒት ነው።”