ከጥላቻ ሰንሰለት ተላቀቅኩ
ከጥላቻ ሰንሰለት ተላቀቅኩ
ሆዜ ጎሜዝ እንደተናገረው
የተወለድኩት መስከረም 8, 1964 በደቡባዊ ፈረንሳይ በምትገኝ ሮኛክ የተባለች አነስተኛ ከተማ ነበር። ወላጆቼና አያቶቼ በሰሜን አፍሪካ፣ በአልጄሪያና በሞሮኮ የተወለዱ የአንዱልዥያ ጂፕሲዎች ናቸው። በጂፕሲዎች ባሕል እንደተለመደው ቤተሰባችን ብዙ ዘመዳሞች አብረው የሚኖሩበት ሰፊ ቤተሰብ ነበር።
አባቴ በጣም ጠበኛ ሰው ነበር። እናቴን ይደበድብ እንደነበረ ትዝ ይለኛል። ከጊዜ በኋላ እናቴ በጂፕሲዎች ያልተለመደ ነገር ቢሆንም ከአባቴ ጋር ለመፋታት ወሰነች። ወንድሜን፣ እህቴንና እኔን ይዛ ወደ ቤልጅየም ሄደች፤ እዛም ለስምንት ዓመት ያህል በሰላም ኖርን።
ይሁን እንጂ ሁኔታዎች ተለወጡ። እኛ ልጆች አባታችንን ማየት ስለ ፈለግን ከእናታችን ጋር ወደ ፈረንሳይ ተመለስንና ሁላችንም አንድ ላይ መኖር ጀመርን። ከአባቴ ጋር መኖር አሁንም አስቸጋሪ ሆነብኝ። ቤልጅየም ሳለን ሁሉም ቦታ የምንሄደው ከእናታችን ጋር ነበር። በአባቴ ወገኖች በኩል ግን ወንድ መዋል ያለበት ከወንድ ጋር ብቻ ነው። የትምክህተኝነት አስተሳሰባቸው ጥሩው ነገር በሙሉ ለወንዶች ሆኖ ሴቶቹ ሥራ በመሥራት ብቻ ተወስነው እንዲኖሩ ያስገድድ ነበር። ለምሳሌ አንድ ቀን ገበታ ከተነሣ በኋላ ሳህን በማጠብና በማጸዳዳት አክስቴን ለመርዳት ስፈልግ አጎቴ ሴታሴት ብሎ ተቆጣኝ። በእርሱ ቤተሰብ ሳህን ማጠብ የሴቶች ሥራ ነው። እንዲህ ያለው ሚዛኑን የሳተ አስተሳሰብ ቀስ በቀስ ወደ እኔም ተጋባ።
ብዙም ሳይቆይ አሁንም አባቴ በቁጣ ገንፍሎ እናቴን ይደበድባት ጀመር። እኔና ወንድሜ ልንገላግል ስንሞክር ከአባታችን ቡጢ ለመዳን በመስኮት ዘለን ማምለጥ ነበረብን። እህቴም ብትሆን ከዱላ አላመለጠችም። በዚህ ምክንያት በተቻለ መጠን ጊዜዬን ከቤት ውጭ ማሳለፍ ጀመርኩ። አሥራ አምስት ዓመት ሲሞላኝ ለሕይወቴ ምንም ግድ የሌለኝ ወጣት ሆንኩ።
ከጊዜ በኋላ በጠበኛነቴ የታወቅሁ ሰው ሆንኩ። ጉልበተኛ መሆን ያስደስተኝ ነበር። ሌሎች ወጣቶች እንዲጣሉኝ ሆን ብዬ ጠብ የምጭርበት ጊዜ ነበር። ይሁን እንጂ ብዙ ጊዜ ጩቤ ወይም ሰንሰለት ስለምይዝ ብዙ የሚደፍሩኝ አልነበሩም። ብዙም ሳልቆይ መኪና መስረቅና መሸጥ ጀመርኩ። አንዳንድ ጊዜም መኪናዎችን አቃጥልና የእሳት አደጋ ተከላካዮች እሳቱን ለማጥፋት ሲሯሯጡ ማየት ያስደስተኝ ነበር። በኋላም ሱቆችንና መጋዘኖችን ሰብሬ መግባት ጀመርኩ። ብዙ ጊዜ ተይዤያለሁ። በተያዝኩ ቁጥር አምላክ እንዲረዳኝ እጸልያለሁ።
አዎን፣ በአምላክ አምን ነበር። ቤልጅየም ሳለን በአንድ የሃይማኖት ትምህርት ቤት ገብቼ እማር ነበር። ስለዚህ የማደርገው ሁሉ መጥፎ መሆኑን አውቃለሁ። ቢሆንም በአምላክ ላይ የነበረኝ እምነት ጠባዬን እንዳስተካክል አልረዳኝም። ኃጢአቴ እንዲሻር የአምላክን ይቅርታ መጠየቅ ብቻ ይበቃል ብዬ አስብ ነበር።
በ1984 ስሰርቅ ተይዤ 11 ወር ተፈረደብኝ። በማርሴይ
ወደሚገኘው የቦሜት እስር ቤት ተላክሁ። እዚያ ሳለሁ ሰውነቴን በተለያዩ ንቅሳቶች አዥጎረጎርኩት። አንደኛው ንቅሳት “ጥላቻና በቀል” ይላል። ከመታረም ይልቅ እስር ቤቱን ለባለ ሥልጣኖችና ለጠቅላላው ማኅበረሰብ ያለኝን ጥላቻ እንዲያጠነክርልኝ ፈቀድኩለት። ሦስት ወር ቆይቼ ከእስር ስፈታ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በጥላቻ ተሞልቼ ወጣሁ። በዚህ ጊዜ የደረሰብኝ አንድ አሳዛኝ ሁኔታ ሕይወቴን ለወጠው።ዋነኛ ግቤ በቀል ሆነ
ቤተሰቤ ከሌላ ጂፕሲ ቤተሰብ ጋር ተጣላ። እኔና አጎቶቼ ፊት ለፊት ልንገጥማቸውና ጠቡን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ወሰንን። ሁለቱም ቤተሰቦች መሣሪያ ታጥቀዋል። በጭቅጭቁ ምክንያት በተነሣው አምባጓሮ አጎቴ ፒየርና የአባቴ አጎት ልጅ በጥይት ተገደሉ። የማደርገው ጠፍቶኝ መሐል መንገድ ላይ ጠመንጃ እያወዛወዝኩ እንደ እብድ ጮህኩ። በመጨረሻ አንደኛው አጎቴ ጠመንጃውን ነጠቀኝ።
እንደ አባት አየው የነበረው የአጎቴ ፒየር መሞት በጣም አሳዘነኝ። በጂፕሲዎች ልማድ መሠረት ለቅሶ ተቀመጥኩ። ለብዙ ቀናት ጢሜን አልተላጨሁም ወይም ሥጋ አልበላሁም። ቴሌቪዥን ማየትም ሆነ ሙዚቃ ማዳመጥ አቆምኩ። የአጎቴን ገዳይ ለመበቀል ምዬ ተነሳሁ። ዘመዶቼ ግን ጠመንጃ እንዳላገኝ አደረጉ።
በነሐሴ ወር 1984 ለውትድርና አገልግሎት ተመለመልኩ። በ20 ዓመት ዕድሜዬ ሊባኖስ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ጦር ተመደብኩ። ለመግደል ወይም ለመሞት ዝግጁ ሆንኩ። በዚህ ጊዜ በጣም ብዙ ሐሺሽ አጨስ ነበር። ሐሺሹ ጥሩ ስሜት የሚሰጠኝ ከመሆኑም በላይ ሊጎዳኝ የሚችል ምንም ነገር እንደማይኖር ሆኖ እንዲሰማኝ ያደርግ ነበር።
በሊባኖስ ጦር መሣሪያ ማግኘት ቀላል ስለነበረ የአጎቴን ደም የመበቀል እቅዴን ለማሳካት የጦር መሣሪያ ወደ ፈረንሳይ ለመላክ ወሰንኩ። ከአገሩ ነዋሪዎች ሁለት ሽጉጥና ጥይቶች ገዛሁ። ሽጉጦቹን ፈታታሁና ራዲዮ ውስጥ ደብቄ ወደ አገሬ ላክሁ።
የውትድርና አገልግሎት ጊዜዬ ሊያልቅ ሁለት ሳምንት ብቻ ሲቀረው እኔና ሦስት ጓደኞቼ ከተመደብንበት ቦታ ጠፋን። ወደ ሠፈራችን ስንመለስ ታሰርን። እስር ላይ እንዳለሁ በቁጣ ገንፍዬ አንዱን ዘብ መታሁት። ለእኔ ጂፕሲ ባልሆነ ሰው መዋረድ የማይታሰብ ነገር ነበር። በማግስቱ ከአንድ መኮንን ጋር ተጣላን። የውትድርና አገልግሎት ጊዜዬን እስክጨርስ ድረስ በእስር እንድቆይ በሊዮን ወደሚገኘው የሞንትሉክ እስር ቤት ተላኩ።
በእስር ቤት ነጻነት አገኘሁ
ሞንትሉክ እስር ቤት እንደደረስኩ በመጀመሪያው ቀን አንድ ደስ የሚል ወጣት ሞቅ ያለ ሰላምታ ሰጠኝ። የይሖዋ ምሥክር እንደሆነና እርሱና ሌሎች የእምነት ባልንጀሮቹ የጦር መሣሪያ ለማንገብ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ብቻ እንደታሰሩ አወቅሁ። ነገሩ ግራ አጋባኝ። ይበልጥ ለማወቅ ፈለግሁ።
የይሖዋ ምሥክሮች ለአምላክ ልባዊ የሆነ ፍቅር እንዳላቸው ተገነዘብኩ። ከፍተኛ የሆነ የሥነ ምግባር ሕግ የሚያከብሩ መሆናቸው በጣም አስደነቀኝ። ቢሆንም ብዙ ጥያቄዎች ነበሩኝ። በተለይ ብዙ ጂፕሲዎች እንደሚያምኑት የሞቱ ሰዎች በሕይወት ከሚኖሩ ጋር በሕልም ይነጋገሩ እንደሆነ ለማወቅ ፈለግሁ። ዢን ፖል የተባለ ምሥክር በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስ ሊያስጠናኝ ፈቃደኛ እንደሆነ ነገረኝ። *
መጽሐፉን በአንድ ሌሊት አንብቤ ጨረስኩ። ባነበብኩት ነገር ልቤ በጣም ተነካ። እዚህ እስር ቤት ውስጥ እውነተኛ ነጻነት አገኘሁ! በመጨረሻ ከእስር ቤት ስለቀቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች የተሞላ ሻንጣ ተሸክሜ በባቡር ወደ ቤቴ ሄድኩ።
በአካባቢዬ ከሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመገናኘት በማርቲግ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ወደሚያደርጉበት መንግሥት አዳራሽ ሄድኩ። አሁንም ኤሪክ ከሚባል የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴን ቀጠልኩ። በጥቂት ቀናት ውስጥ ማጨስ አቆምኩ። ከወንጀል ግብረ አበሮቼ ጋር መገናኘቴንም አቆምኩ። “ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው፣ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ” ከሚለው የምሳሌ 27:11 ምክር ጋር ተስማምቼ ለመኖር ቆርጬ ተነሳሁ። ይሖዋ ላስደስተው የምፈልገው አፍቃሪ አባት ሆነልኝ።
ለውጥ ለማድረግ የገጠመኝ ችግር
በክርስቲያናዊ ሥርዓቶች መመራት ቀላል ሆኖ አላገኘሁትም። ለምሳሌ ያህል ለበርካታ ሳምንታት የዕፅ ሱሴ አገርሽቶብኝ ነበር። ከሁሉ ይበልጥ ያስቸገረኝ ግን የመበቀል ፍላጎቴን ማጥፋት ነበር። ሁልጊዜ ሽጉጥ እይዝ እንደነበረና አሁንም የአጎቴን ገዳዮች ለመበቀል የሚያስችለኝን ውጥን እያቀነባበርኩ መሆኔን ኤሪክ አያውቅም ነበር። እነርሱን ስፈልግ ሙሉ ሌሊት የማሳልፍበት ጊዜ ነበር።
ይህን ጉዳይ ለኤሪክ ስነግረው የጦር መሣሪያ እየያዝኩና በቀል ለመፈጸም እየፈለግሁ ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና ሊኖረኝ እንደማይችል በግልጽ አብራራልኝ። ከሁለት አንዱን መምረጥ ነበረብኝ። በሮሜ 12:19 ላይ “ተወዳጆች ሆይ፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፣ ለቁጣው ፈንታ ስጡ እንጂ” በሚለው የሐዋርያው ጳውሎስ ምክር ላይ በጥልቅ አሰላሰልሁ። ይህን ማድረጌና አጥብቄ መጸለዬ ስሜቴን እንድቆጣጠር ረዳኝ። (መዝሙር 55:22) በመጨረሻ መሣሪያዎቼን አስወገድኩ። መጽሐፍ ቅዱስን ለአንድ ዓመት ያህል ካጠናሁ በኋላ ታህሣሥ 26, 1986 ራሴን ለይሖዋ አምላክ መወሰኔን በውኃ ጥምቀት አሳየሁ።
ቤተሰቦቼም ተቀበሉ
ያደረግሁት የጠባይ ለውጥ ወላጆቼን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ ገፋፋቸው። እናቴና አባቴ እንደገና በሕግ ተጋቡና እናቴ በሐምሌ ወር 1989 ተጠመቀች። ከጊዜ በኋላ በርካታ የቤተሰቤ አባሎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ተቀብለው የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል።
በነሐሴ ወር 1988 የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ለመሆን ወሰንኩ። በዚህ ወቅት በጉባዬ ካለች ካትያ ከምትባል ወጣት እህት ጋር ተዋደድን። ሰኔ 10 ቀን 1989 ተጋባን። ለሴቶች በነበረኝ ዝንባሌ ረገድ ገና ማስተካከል የነበረብኝ የተሳሳተ ዝንባሌ ስለነበረኝ የመጀመሪያው ዓመት ቀላል አልሆነልንም። ባሎች ሚስቶቻቸውን እንዲያከብሩ የሚያዘውን የ1 ጴጥሮስ 3:7 ምክር ሥራ ላይ ማዋል በጣም ከብዶኝ ነበር። አስተሳሰቤን እንድለውጥና የኩራት መንፈሴን እንዳሸንፍ ደጋግሜ መጸለይ ነበረብኝ። ቀስ በቀስ ሁኔታዎች ተሻሻሉ።
አሁንም ቢሆን የአጎቴ ሞት በጣም ይሰማኛል። ስለ እርሱ ሳስብ እንባዬን መቆጣጠር የሚያቅተኝ ጊዜ አለ። የተገደለበት ሁኔታ የሚቀሰቅስብኝን ስሜት ለመቆጣጠር እታገላለሁ። ከተጠመቅሁ በኋላ ለበርካታ ዓመታት ደም ከተቃባናቸው ቤተሰቦች ጋር ድንገት እንዳልገናኝ እፈራ ነበር። ሊጣሉኝ ቢነሱ ምን አደርጋለሁ? የድሮ ጠባዬ ያገረሽብኝ ይሆን?
አንድ ቀን በጎረቤት ጉባኤ የሕዝብ ንግግር ሰጠሁ። እዚያም አጎቴን የገደሉት ሰዎች ቤተሰብ የሆነችውን ፔፓን አየሁ። እርሷን ማየቴ ክርስቲያናዊ ባሕርዬን በእጅጉ ተፈታትኖት እንደነበረ አልክድም። ቢሆንም ስሜቴን ተቆጣጠርኩ። በኋላም ፔፓ በተጠመቀችበት ዕለት አቅፌ ይሖዋን ለማገልገል በመወሰኗ እንኳን ደስ አለሽ ብያታለሁ። ያ ሁሉ ሆኖ መንፈሳዊ እህቴ አድርጌ ተቀብያታለሁ።
በየቀኑ ይሖዋ ከጥላቻ ሰንሰለት እንድላቀቅ ስለረዳኝ አመሰግነዋለሁ። ይሖዋ ምሕረት ባያደርግልኝ ኖሮ ዛሬ የት እሆን ነበር? ምሥጋና ይግባውና ደስታ የሰፈነበት የቤተሰብ ሕይወት አለኝ። በተጨማሪም ከጥላቻና ከጠብ ነጻ በሆነ አዲስ ዓለም ውስጥ የመኖር ተስፋ አለኝ። አዎን፣ አምላክ “የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር አፍም ተናግሮአልና ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም የለም” ሲል የሰጠው ተስፋ እንደሚፈጸም ሙሉ በሙሉ እተማመናለሁ።—ሚክያስ 4:4
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.18 በይሖዋ ምሥክሮች የታተመ መጽሐፍ ነው።
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1985 ሊባኖስ ከነበረው የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስጠባቂ ጦር ጋር ሆኜ
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከካቲያ እና ከልጆቼ ፒየር እና ቲሚዮ ጋር