ክርስቲያኖች በድህነት መኖር አለባቸውን?
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
ክርስቲያኖች በድህነት መኖር አለባቸውን?
በአንድ ወቅት ኢየሱስ ባለጠጋ ለሆነ አንድ ወጣት ባለ ሥልጣን ያለውን ሁሉ ሸጦ ለድሆች መስጠት እንዳለበት ይነግረዋል። ዘገባው እንደሚገልጸው ሰውየው ‘ብዙ ንብረት ስለነበረው’ በኢየሱስ አነጋገር አዝኖ ሄደ። (ማርቆስ 10:22) ከዚያም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል” አላቸው። አክሎም “ባለጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢገባ ይቀላል” አለ።—ማርቆስ 10:21-23፤ ማቴዎስ 19:24
ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? ሃብታም የሆነ ሰው በእውነተኛው አምልኮ መካፈል አይችልም ማለት ነውን? ክርስቲያኖች ሃብታም መሆንን እንደ ኃጢአት መመልከት ይኖርባቸዋልን? አምላክ የመናኝ ዓይነት ሕይወት እንዲኖሩ ይፈልግባቸዋልን?
አምላክ ‘ሰዎችን ሁሉ’ በደስታ ይቀበላል
በጥንት ጊዜያት አምላክ እስራኤላውያን በድህነት መኖር እንዳለባቸው አልተናገረም። ለምሳሌ፣ በርስት በተሰጣቸው መሬት ላይ መኖር ከጀመሩ በኋላ ሕዝቡ የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ቁሳዊ ፍላጎት ለማሟላት በእርሻና በንግድ ሥራ ተሰማርተው ነበር። በሥራቸው ስኬታማ መሆናቸው በኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች፣ በአየሩ ጠባይ፣ በጤንነታቸው ወይም በንግድ ችሎታቸው ላይ የተመካ ይሆናል። የሙሴ ሕግ እስራኤላውያን ከመካከላቸው አንዱ ቢደኸይ አሳቢነት እንዲያሳዩት ያዝዝ ነበር። (ዘሌዋውያን 25:35-40) በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዶች ባለጠጋ ሆነው ነበር። የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያት የሆነውና በጽኑ አቋሙና በእምነቱ የሚታወቀው ቦዔዝ “ባለጸጋ” እንደሆነ ተገልጿል።—ሩት 2:1 አ.መ.ት
በኢየሱስ ዘመንም ሁኔታው ተመሳሳይ ነበር። ኢየሱስ ማቴዎስ 19:26
በመግቢያው ላይ ለተጠቀሰው ሃብታም ሰው እንደዚያ ብሎ ሲናገር የመናኝ ዓይነት ሕይወት እንዲኖሩ ማበረታታቱ አልነበረም። ከዚያ ይልቅ አንድ ጠቃሚ ትምህርት እያስተላለፈ ነበር። ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ሲታይ ባለጠጋ የሆኑ ሰዎች ራሳቸውን ዝቅ አድርገው የአምላክን የመዳን ዝግጅት መቀበል የሚከብዳቸው ይመስል ይሆናል። ሆኖም ኢየሱስ “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል” ብሏል።—የመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ ‘ሁሉንም ዓይነት ሰዎች’ ያቀፈ ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) ከመካከላቸው ጥቂቶቹ ሃብታሞች፣ ሌሎቹ ደግሞ መካከለኛ ኑሮ ያላቸው ሲሆኑ አብዛኞቹ ግን ድሆች ነበሩ። አንዳንዶች ሃብታም የሆኑት ክርስቲያን ከመሆናቸው በፊት ሊሆን ይችላል። ሌሎቹ ደግሞ የሁኔታዎች መመቻቸትና ጥሩ የንግድ ችሎታ ክርስቲያን ከሆኑም በኋላ ሃብት አስገኝቶላቸው ሊሆን ይችላል።
በተመሳሳይም ዛሬ ያሉት ክርስቲያኖች የኑሮ ደረጃቸው አንድ ዓይነት አይደለም። ፍቅረ ነዋይ እገሌ ከገሌ ሳይል ሁሉንም ሰው ሊነካ ስለሚችል ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን በተመለከተ ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ ለመከተል ይጥራሉ። ኢየሱስ ባለጠጋ ለነበረው ወጣት ባለ ሥልጣን የሰጠው ትምህርት ገንዘብና ቁሳዊ ሃብት በሰዎች ላይ ከባድ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ለሁሉም ክርስቲያኖች ማስጠንቀቂያ ይሆናል።—ማርቆስ 4:19
ባለጠጋ ለሆኑት የተሰጠ ማሳሰቢያ
መጽሐፍ ቅዱስ ባለጠጋ መሆንን ባያወግዝም ገንዘብ ወዳድ መሆንን ግን ያወግዛል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ጳውሎስ “ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነው” ብሏል። አንዳንዶች ባለጠጋ ለመሆን ሲሉ መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ችላ በማለታቸው ‘ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን እንደወጉም’ ተናግሯል።—1 ጢሞቴዎስ 6:10
ጳውሎስ ባለጠጋ ለሆኑት ግልጽ መመሪያ መስጠቱ ትኩረት የሚስብ ነው። እንዲህ ብሏል:- “በአሁኑ ዘመን ባለ ጠጎች የሆኑት የትዕቢትን ነገር እንዳያስቡ፣ ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለ ጠግነት ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው።” (1 ጢሞቴዎስ 6:17) ከጳውሎስ ቃላት ለመረዳት እንደሚቻለው ባለጠጋ የሆኑ ሰዎች ሊታበዩና ራሳቸውን ከሌሎች ከፍ አድርገው መመልከት ሊጀምሩ ይችላሉ። ከዚህም በላይ ከአምላክ ይልቅ ሃብት የተሻለ መታመኛ እንደሆነ አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ።
ባለጠጋ የሆኑ ክርስቲያኖች ‘በበጎ ሥራ ባለ ጠጎች’ በመሆን እንደዚህ በመሰሉ ወጥመዶች እንዳይያዙ ራሳቸውን ሊጠብቁ ይችላሉ። እነዚህ በጎ ሥራዎች “ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ” በመሆን ለተቸገሩ ልግስና ማሳየትን ይጨምራሉ። (1 ጢሞቴዎስ 6:18) ከዚህም በላይ ሃብታም ድሃ ሳይል ሁሉም ክርስቲያኖች ዛሬ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች ትልቅ ቦታ የሚሰጡትን የመንግሥቱን ስብከት ሥራ በቁሳዊ መንገድ መደገፍ ይችላሉ። እንደዚህ የመሰለው የልግስና መንፈስ ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት እንዳለን የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ በደስታ የሚሰጥ ሰው በሚወዱት በይሖዋ አምላክና በኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ተወዳጅ ያደርገናል።—ማቴዎስ 24:14፤ ሉቃስ 16:9፤ 2 ቆሮንቶስ 9:7
ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች
በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ክርስቲያኖች በድህነት እንዲኖሩ አይጠበቅባቸውም። በሌላ በኩል ደግሞ ‘ባለጠጋ ለመሆንም ቆርጠው መነሳት’ አይኖርባቸውም። (1 ጢሞቴዎስ 6:9) መሠረታዊ የሆኑ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት ጠንክረው ይሠራሉ። ስኬታማ መሆናቸው በሚኖሩበት አገር የኢኮኖሚ ሁኔታና በተለያዩ ነገሮች ላይ የተመካ ይሆናል።—መክብብ 11:6
ክርስቲያኖች ምንም ዓይነት የኑሮ ደረጃ ይኑራቸው ‘ከሁሉ የሚሻለውን ለይተው ለማወቅ’ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። (ፊልጵስዩስ 1:10 አ.መ.ት ) ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ በመስጠት ‘እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ፣ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ ይሰበስባሉ።’—1 ጢሞቴዎስ 6:18, 19