በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የማንም ሰው ገመና መደፈር የለበትም

የማንም ሰው ገመና መደፈር የለበትም

የማንም ሰው ገመና መደፈር የለበትም

“የድሃ ሰው ጓዳ እንኳ በንጉሥ አይደፈርም”—⁠ዊልያም ፒት፣ ብሪታንያዊ የፖለቲካ ሰው 1759-1806

የፒት ቃላት እያንዳንዱ ሰው የየራሱን ገመና የማስከበር፣ ከሕይወቱ የተወሰነው ክፍል ካልተፈለጉ ሰዎች እይታ ውጭ እንዲሆንለት የማድረግ መብት እንዳለው ያመለክታሉ።

ገመና በተለያዩ ባሕሎች የተለያየ ትርጓሜ ይሰጠዋል። ለምሳሌ የፓስፊክ ደሴት በሆነችው በሳሞአ አብዛኛዎቹ ቤቶች ግድግዳ የሌላቸው ሲሆን በቤት ውስጥ የሚደረጉ አብዛኛዎቹ የቤተሰብ እንቅስቃሴዎች በውጭ ባለ ሰው በቀላሉ ሊታዩ ይችላሉ። ሆኖም በዚህም አገር ቢሆን ግቡ ሳይባሉ ሰው ቤት ዘው ብሎ መግባት ነውር ነው።

ሰዎች ጓዳቸው መከበር እንዳለበት ከተገነዘቡ ብዙ ዘመናት አልፈዋል። ዊልያም ፒት ከላይ የተጠቀሰውን ዝነኛ ቃል ከመናገራቸው ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት መጽሐፍ ቅዱስ የሌሎችን ጓዳ መዳፈር ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል። ንጉሥ ሰሎሞን “እንዳይሰለችህ እንዳይጠላህም እግርህን ወደ ባልንጀራህ ቤት አታዘውትር” ሲል ጽፏል። (ምሳሌ 25:​17) ሐዋርያው ጳውሎስም “በራሳችሁ ጉዳይ ላይ ብቻ አተኩሩ” በማለት መክሯል።​—⁠1 ተሰሎንቄ 4:​11 አ.መ.ት

የእያንዳንዱ ሰው ገመና መከበሩ አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሣ ዘ ዩኔስኮ ኩርየር “የዜጎች መሠረታዊ መብት” ብሎታል። በተመሳሳይም ተደማጭነት ያላቸው አንድ የላቲን አሜሪካ የፖለቲካ ሰውም “በአንድ በኩል ሁሉም ሰብዓዊ መብቶች የእያንዳንዱን ሰው ገመና ከማክበር ጋር የተያያዙ ናቸው” ብለዋል።

ይሁን እንጂ ወንጀል እየጨመረ በሄደበትና ዓለም አቀፍ አሸባሪነት በተስፋፋበት በዚህ ዘመን መንግሥታትና ሕግ አስከባሪ ባለ ሥልጣናት የዜጎቻቸውን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲሉ የሰዎችን ጓዳ መፈተሽ እንደሚያስፈልጋቸው እየተሰማቸው መጥቷል። ለምን? ምክንያቱም በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚኖሩ ወንጀለኞች ለክፉ ድርጊታቸው መሸፈኛ አድርገው የሚጠቀሙት ሰዎች ያላቸውን ገመናን የማስጠበቅ መብትን ነው። ስለዚህ መንግሥታት በተጣለባቸው የዜጎቻቸውን ደህንነት በመጠበቅ ኃላፊነትና ግለሰቦች ጓዳቸውን በማስጠበቅ መብት መካከል ያለው ሚዛን እንዲጠበቅ ትግል በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ገመናን የማስጠበቅ መብትና ደህንነት

መስከረም 11, 2001 የደረሰው መላውን ዓለም ያናወጠ የአሸባሪነት ድርጊት ብዙ ሰዎች መንግሥት በግለሰቦች የግል ሕይወት ውስጥ መግባት ስለመቻሉ የነበራቸውን አመለካከት እንዲለውጡ አድርጓል። አንድ የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ የፌደራል ንግድ ኮሚሽነር ቢዝነስ ዊክ ለተባለ መጽሔት “መስከረም 11 ሁሉን ነገር ለውጧል። አሸባሪዎች የጓዳ አለመደፈር መብትን በመጠቀም በማኅበረሰቡ ውስጥ እንደ ልባቸው ይፈነጫሉ። እነዚህን ወንጀለኞች ለማጋለጥ በተወሰነ ደረጃ የሰዎችን ጓዳ መፈተሽ አስፈላጊ ቢሆን አብዛኞቹ ሰዎች ፈቃደኛ እንደሚሆኑ የታወቀ ነው” ብለዋል። ይኸው መጽሔት “ከመስከረም 11 ወዲህ የተወሰዱ የሕዝብ አስተያየቶች እንደሚያመለክቱት 86 በመቶ የሚሆኑ አሜሪካውያን መልክ የሚለዩ መሣሪያዎች በብዛት ሥራ ላይ መዋላቸውን፣ 81 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በባንክና በክሬዲት ካርድ እንቅስቃሴዎች ላይ የቅርብ ክትትል መደረጉን እንዲሁም 68 በመቶ የሚሆኑት ብሔራዊ የመታወቂያ ወረቀት መታደሉን እንደሚደግፉ” ዘግቧል።

አንዳንድ ምዕራባውያን አገሮች ለዜጎቻቸው ለማደል የሚያስቡት መታወቂያ ካርድ የጣት አሻራና የዓይን ብሌን ምስል መዝግቦ ለማቆየት የሚችል ከመሆኑም በላይ በወንጀል ድርጊት ተካፍለው የሚያውቁ ስለመሆናቸውና ገንዘብ ነክ መዝገቦቻቸውን ለመመርመር ያስችላል። ከመታወቂያ ካርድ የሚገኘውን መረጃ ከክሬዲት ካርድ መረጃዎችና መልክ ሊለዩ ከሚችሉ የስለላ ካሜራዎች ጋር ማያያዝ የሚያስችል የቴክኖሎጂ አቅም አለ። በዚህ መንገድ ወንጀለኞችን ለወንጀል ሥራቸው የሚገለገሉበትን መሣሪያ እንደገዙ መያዝ ይቻላል።

ወንጀለኞቹ ቦምቦችን፣ ጠመንጃዎችን ወይም ጩቤዎችን ልብሳቸው ውስጥ ወይም እቤታቸው ውስጥ ቢደብቁ እንኳን ከመያዝ አያመልጡም። አንዳንድ የደህንነት ጥበቃ መሥሪያ ቤቶች ልብስ ውስጥ የተደበቁ ነገሮችን ሳይቀር የሚያሳዩ መሣሪያዎች አሏቸው። በቅርቡ የተሠሩ የራዳር መሣሪያዎች በሌላ ክፍል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ወይም የሚተነፍሱ ሰዎችን ማንነት ለመለየት ያስችላሉ። ይሁን እንጂ የስለላና የመከታተያ መሣሪያዎች መራቀቃቸው ወንጀል እንዲቀንስ አስችሏል?

ካሜራዎች ወንጀለኞችን ይቆጣጠራሉ?

ቡርክ በተባለው የአውስትራሊያ የገጠር መንደር ወንጀል እያሻቀበ በመሄዱ አራት የቴሌቪዥን ካሜራዎች ተተከሉ። ከዚያ በኋላ ወንጀሉ በከፍተኛ መጠን ቀነሰ። ይሁን እንጂ በሁሉም አካባቢዎች ይህን የመሰለ ውጤት ማግኘት አልተቻለም። በስኮትላንድ ግላስጎ ከተማ የሚፈጸመውን ወንጀል ለመቀነስ በ1994 32 የቴሌቪዥን ካሜራዎች ተተክለው ነበር። ስኮቲሽ ኦፊስ ሴንትራል ሪሰርች ዩኒት የተባለው መሥሪያ ቤት ባደረገው ጥናት መሠረት ካሜራዎቹ ከተገጠሙ ከአንድ ዓመት በኋላ አንዳንድ የወንጀል ዓይነቶች ቀንሰዋል። ይሁን እንጂ “ዝሙት አዳሪነትን የመሰሉ የብልግና ወንጀሎች በ120፤ የማጭበርበር ወንጀሎች በ2185፤ እንዲሁም ከሕገ ወጥ ዕፆች ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን ወንጀሎች ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ ወንጀሎች በ464 ጨምረዋል” ሲል ጥናቱ ዘግቧል።

የክትትል መሣሪያዎች አንዳንድ የወንጀል ዓይነቶችን ሊቀንሱ ይቻሉ እንጂ የወንጀል መጠን በአጠቃላይ እንዲቀንስ ለማድረግ አልቻሉም። ዘ ሲድኒ ሞርኒንግ ሄራልድ የተባለው ጋዜጣ ፖሊሶችና የወንጀል መርማሪዎች “ዞር ማለት” ስለሚሉት ዘዴ ዘግቧል። ጋዜጣው “ወንጀለኞች በካሜራ ወይም ሮንድ በሚዞሩ ፖሊሶች እንደሚያዙ ሲያውቁ ወደ ሌላ አካባቢ ይሄዱና ወንጀል ይፈጽማሉ” ብሏል። ምናልባት ይህ ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ ከብዙ ዘመናት በፊት “ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፣ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም” ሲል የተናገረውን ሳያስታውስህ አይቀርም።​—⁠ዮሐንስ 3:​20

ሕግ አስከባሪ መሥሪያ ቤቶች የተጋረጠባቸው ከባድ ፈተና በጣም የተራቀቀ ነው የሚባለው የራዳር ወይም የኤክስ ሬይ ስለላ መሣሪያ እንኳን በሰው ልብና አእምሮ ውስጥ ያለውን ነገር ማንበብ አለመቻሉ ነው። ወንጀልን፣ ጥላቻንና ጠበኝነትን ለመቀነስ ደግሞ ውጊያው መካሄድ ያለበት በሰዎች ልብና አእምሮ ላይ ነው።

ይሁን እንጂ የሰው ልጅ እስከ ዛሬ ካፈራቸው ከማንኛውም ቴክኖሎጂ ይበልጥ ጠልቆ የሚያይና የሁሉን ሰው ጓዳ የሚዳስስ የክትትል ዓይነት አለ። ስለዚህ ዓይነቱ የመከታተያ ዘዴና በሰዎች ባሕርይ ላይ ሊያሳድር ስለሚችለው በጎ ተጽዕኖ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ማብራሪያ ይሰጣል።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“አሸባሪዎች የጓዳ አለመደፈር መብትን በመጠቀም በማኅበረሰቡ ውስጥ እንደ ልባቸው ይፈነጫሉ።”

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የሕክምና መዝገቦች ምን ያህል ምሥጢርነታቸው የተጠበቀ ነው?

ብዙ ሰዎች ለዶክተሮቻቸውና ለሆስፒታላቸው የተናገሯቸው በሕክምና መዝገባቸው ላይ የሰፈሩት የሕክምና መረጃዎች ምሥጢርነታቸው የሚጠበቅ ይመስላቸዋል። ይሁን እንጂ ፕራይቨሲ ራይትስ ክሊሪንግሃውስ የተባለው ምሥጢር አስጠባቂ ድርጅት እንዳስጠነቀቀው “በዚህ ረገድ እርግጠኛ መሆናችሁ ስህተት ሊሆን ይችላል።” ሲምሰን ጋርፍንከል ዳታቤዝ ኔሽን​—⁠ዘ ዴዝ ኦቭ ፕራይቨሲ ኢን ዘ ትዌንቲ ፈርስት ሴንቸሪ በተባለው መጽሐፋቸው እንደሚከተለው ብለዋል:- “በዛሬው ጊዜ የሕክምና መዝገቦች የሚሰጡት አገልግሎት እየሰፋ መጥቷል። . . . ቀጣሪዎችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሊቀጥሯቸው የሚፈልጓቸውንና ኢንሹራንስ እንዲገቡ የሚፈቅዱላቸውን ሰዎች ለመወሰን በሕክምና መዛግብት ይጠቀማሉ። ሆስፒታሎችና ሃይማኖታዊ ድርጅቶች እርዳታ ለማሰባሰብ ይጠቀሙባቸዋል። ገበያ አፈላላጊዎች ሳይቀሩ ሸቀጦቻቸውን የሚቀበሏቸው ሰዎች ለመፈለግ የሕክምና መዝገቦችን ይገዛሉ።”

በተጨማሪም ጋርፍንከል “የሕክምና መዝገቦችን ምሥጢራዊነት መጠበቅ አስቸጋሪ የሚሆንበት አንዱ ምክንያት በአንድ የሆስፒታል ጉብኝት ወቅት የአንድን በሽተኛ መዝገብ የሚያዩ ሰዎች ቁጥር ከ50 እስከ 75 የሚደርሱ መሆናቸው ነው” ብለዋል። በአንዳንድ ቦታዎች በሽተኞቹ ራሳቸው ሆስፒታል በሚገቡበት ጊዜ አጠቃላይ የሆነ የስምምነት ውል በመፈረም ሳያውቁት ምሥጢራቸውን የማስጠበቅ መብታቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ። እነዚህን ቅጾች ስትሞሉ “የጤና አገልግሎት ሰጪው የሕክምና መረጃዎችን ለኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና ለሌሎች አሳልፎ እንዲሰጥ ፈቀዳችሁለት ማለት ነው” ይላል ፕራይቨሲ ራይትስ ክሊሪንግሃውስ።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

የገመና መደፈርና የነጋዴዎች ፍላጎት

በተለይ በኢንተርኔት የሚጠቀሙ ሰዎች ገመናቸው ባልተፈለጉ ሰዎች የመታየት ዕድሉ በጣም ከፍተኛ ነው። ፕራይቨሲ ራይትስ ክሊሪንግሃውስ የተባለው ድርጅት እንዲህ ብሏል:- “ሙሉ በሙሉ በሌሎች ሊታይ አይችልም የሚባል የኢንተርኔት እንቅስቃሴ ወይም ግብይት የለም። . . . የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ከዌብ ገጾች መረጃዎችን ወይም ሰነዶችን ሊወስዱ ይችላሉ። . . . አለበለዚያም ምንም ዓይነት ሌላ ግንኙነት ሳያደርጉ ገጾቹን ብቻ ይመለከቱ ይሆናል። ብዙ ሰዎች እንደነዚህ ያሉት ተጠቀሚዎች ማንነት ሊታወቅ የሚችል አይመስላቸውም። ግን ይታወቃል። አንድ ሰው የሚከታተለውን የዜና ማሠራጫ ወይም የሚያየውን የዌብ ገጽ ወይም የሚያነባቸውን ፋይሎች ጨምሮ የሚያደርጋቸውን የኢንተርኔት እንቅስቃሴዎች መመዝገብ ይቻላል። . . . አንድ የኢንተርኔት ደንበኛ የሚከታተላቸውን የዌብ ገጾች ዓይነት ማወቅ . . . ብዙ ገንዘብ ሊያስገኝ ይችላል። . . . እንዲህ ያለው መረጃ ገበያ አፈላላጊዎች ተመሳሳይ ጠባይና ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ለይተው እንዲያውቁና የማሻሻጥ ጥረታቸውን በእነዚህ ሰዎች ላይ እንዲያተኩሩ ያስችላቸዋል።”

ስማችሁ በሸቀጥ አሻሻጮች እጅ ሊገባ የሚችልበት ምን ሌላ መንገድ አለ? ከሚከተሉት አንዱን ካደረጋችሁ ስማችሁ በአሻሻጮች እጅ እንዲገባ ሊያደርግ ይችላል።

▪ የዋስትና ሰነድ ወይም የምዝገባ ካርዶችን በመሙላት።

▪ የክለቦች፣ የድርጅቶች ወይም የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አባል በመሆን ወይም ለእነዚህ ድርጅቶች የገንዘብ መዋጮ በመስጠት።

▪ የመጽሔት፣ የመጻሕፍት ወይም የሙዚቃ ክለቦች ደንበኛ በመሆን።

▪ ስማችሁና አድራሻችሁ በቴሌፎን ማውጫ ላይ እንዲመዘገብ በማድረግ።

▪ በሎተሪ ወይም በሌላ ውድድር በመካፈል።

በተጨማሪም የዱቤ ካርድ ወይም ገንዘብ ከባንክ የማውጫ ካርድ በመጠቀም ሸቀጥ የምትገዙ ከሆነ ገንዘቡን የሚቀበላችሁ ኩባንያ ስማችሁንና አድራሻችሁን ከገዛችኋቸው ዕቃዎች ጋር ማያያዝ ይችል ይሆናል። በዚህ መንገድ አዘውትራችሁ ስለምትገዟቸው ነገሮች በቂ ዝርዝር የያዘ መዝገብ ለማዘጋጀትና ሸቀጦችን ለመሸጥ ዓላማ ሊያገለግል ይቻላል። *

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.32 ፕራይቨሲ ዋች ክሊሪንግሃውስ ከተባለው ድርጅት የዌብ ገጽ የተወሰደ።

[በገጽ 6 እና 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሰዎችን በስውር መከታተል ወንጀል እንዲቀንስ ያደርጋል?