በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ገመና መጠበቅን በተመለከተ ምክንያታዊ የሆነ አመለካከት መያዝ

ገመና መጠበቅን በተመለከተ ምክንያታዊ የሆነ አመለካከት መያዝ

ገመና መጠበቅን በተመለከተ ምክንያታዊ የሆነ አመለካከት መያዝ

“የእግዚአብሔር ዓይኖች በስፍራ ሁሉ ናቸው፤ ክፉዎችንና ደጎችን ይመለከታሉ።”—⁠ምሳሌ 15:​3

የሚያደርገው እንቅስቃሴ በሙሉ በዓይነ ቁራኛ ክትትል እንዲደረግበት፣ የሚያስበውና የሚፈልገው ነገር ሁሉ እንዲመረመርበት የሚፈልግ ሰው እንደማይኖር የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ አምላክ ይህን ማድረግ እንደሚችል መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ በዕብራውያን 4:​13 ላይ “እኛን በሚቈጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቈተና የተገለጠ ነው እንጂ፣ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም” ይላል። ታዲያ ይህ የግለሰቦችን ገመና መዳፈር አይሆንም? በፍጹም አይሆንም። ለምን?

ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት በመዋኛ ገንዳ ውስጥ በምትዋኝበት ጊዜ የሕይወት አድን ሠራተኛው በዓይነ ቁራኛ ይከታተልሃል። ይህን በማድረጉ ቅር አትሰኝም። እንዲያውም የእርሱ መኖር የመተማመን ስሜት ያሳድርብሃል። በዋና ላይ እያለህ ችግር ቢገጥምህ ቶሎ መጥቶ እንደሚረዳህ ታውቃለህ። አንዲት እናትም በተመሳሳይ ሕፃን ልጅዋ የሚያደርገውን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በዓይኗ ትከታተላለች። ይህን ባታደርግ ግድየለሽ እንደሆነች ይቆጠራል።

በተመሳሳይም ይሖዋ አምላክ ከልብ ስለሚያስብልን የምናስበውንና የምናደርገውን ሁሉ ይከታተላል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢይ “እግዚአብሔር ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉ” ብሏል። (2 ዜና መዋዕል 16:​9) ይሁን እንጂ ይሖዋ አስተሳሰባችንንና ድርጊታችንን የሚመለከተው እስከ ምን ድረስ ነው? ይህን ለማስተዋል የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ያጋጠሙትን አንዳንድ ሁኔታዎች እንመልከት።

የሰዎችን ልብና አእምሮ የማንበብ ችሎታ

ኢየሱስ በአንድ ፈሪሳዊ ቤት ገበታ ላይ በነበረበት ጊዜ ኃጢአተኛ እንደሆነች የምትታወቅ አንዲት ሴት መጣችና በኢየሱስ እግር አጠገብ ተንበረከከች። ማልቀስ ጀመረችና በኢየሱስ እግር ላይ የፈሰሰውን እንባዋን በፀጉሯ ጠረገች። ታሪኩ “የጠራው ፈሪሳዊም አይቶ:- ይህስ ነቢይ ቢሆን፣ ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደ ሆነች እንዴትስ እንደ ነበረች ባወቀ ነበር፣ ኃጢአተኛ ናትና ብሎ በልቡ አሰበ” ይላል። ኢየሱስ ግን የሴቲቱን የቀድሞ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ፈሪሳዊው በልቡ የተናገረውን ጭምር አውቆ እንደነበረ የሰጠው መልስ ያመለክታል።​—⁠ሉቃስ 7:​36-50

በሌላ ጊዜ ደግሞ ኢየሱስ ያደረገውን ተአምር የተቃወሙ ሰዎች አጋጠሙት። በማቴዎስ 9:​4 ላይ የተመዘገበው ታሪክ እንዲህ ይላል:- “ኢየሱስም አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አለ:- ስለ ምን በልባችሁ ክፉ ታስባላችሁ?” ኢየሱስ የነበረው የሰዎችን አሳብ የማወቅ ችሎታ በብልጠትና በመላ ላይ የተመሠረተ አልነበረም።

አልዓዛር ከሞት የተነሣበትን ሁኔታ ብንመረምር ይህን መገንዘብ እንችላለን። የኢየሱስ የቅርብ ወዳጅ የነበረው አልዓዛር ከሞተ አራት ቀን ሆኖት ነበር። አሳቡ ሁሉ ጠፍቶ ሥጋው መበስበስ ጀምሮ ነበር። (መዝሙር 146:​3, 4) ኢየሱስ የአልዓዛር መቃብር የተዘጋበት ድንጋይ እንዲነሣ ባዘዘ ጊዜ የአልዓዛር እህት ማርታ “ጌታ ሆይ ከሞተ አራት ቀን ሆኖታልና አሁን ይሸታል” ስትል ተቃወመች። ኢየሱስ ግን በአምላክ ኃይል በመጠቀም ከመሞቱ በፊት የነበሩትን ትውስታዎች ጭምር በመመለስ የቀድሞውን አልዓዛር ለማስነሳት ችሏል።​—⁠ዮሐንስ 11:​38-44፤ 12:​1, 2

ይሖዋ አምላክ በውስጣችን የምናስበውን ሁሉ የማወቅ ችሎታ እንዳለው ኢየሱስ ስለ ጸሎት በተናገረው ቃል ላይ ተረጋግጧል። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ስለናሙና ጸሎት ከማስተማሩ በፊት “አንተ ግን ስትጸልይ፣ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል” ብሎ ነበር።​—⁠ማቴዎስ 6:​6, 8

አምላክ እንደሚያየን ማወቃችን ያለው ጥቅም

አምላክ ‘ልባችንን እንደሚመረምርና በውስጣችን ያለውን ሐሳብ ሁሉ እንደሚያውቅ’ መገንዘባችን እንቅስቃሴያችንን ወይም ነጻነታችንን አይገድብብንም? (1 ዜና መዋዕል 28:​9) አይገድብም። ከአምላክ ሊሰወር የሚችል ነገር እንደሌለ ማወቃችን መልካም እንድናደርግ ይገፋፋናል።

በመግቢያችን ላይ የተጠቀሰችው ኤልሳቤጥ ሐቀኛ ሆና ልትኖር የቻለችበት ዋነኛ ምክንያት በሥራ ቦታዋ ካሜራዎች ስለሚከታተሏት እንዳልሆነ ትናገራለች። ከዚህ ይልቅ “ይሖዋ የማደርገውን ሁሉ እንደሚመለከት ማወቄ በምሠራው ሁሉ፣ ከመሥሪያ ቤት ውጭ በምሆንበት ጊዜም ሐቀኛ እንድሆን ይገፋፋኛል” ብላለች።

ጂምም ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥቷል። የሚሠራው የሠራተኞች ስርቆት የተለመደ ችግር በሆነበት ፋብሪካ ውስጥ ነው። ጂም ግን ከአሠሪው ለመስረቅ ፈቃደኛ አልነበረም። እንዲህ ይላል:- “ሳልያዝ ከምሠራበት ኩባንያ መስረቅ እችላለሁ። ይሁን እንጂ ከአምላክ ጋር ላለኝ ዝምድና ትልቅ ቦታ እሰጣለሁ። የማደርገውን ሁሉ እንደሚያይ አውቃለሁ።”

አንድ ሰው አምላክ የምናደርገውን ሁሉ እንደሚያውቅ መገንዘቡና ከእርሱም ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረው መፈለጉ በሕይወቱ ውስጥ ከፍተኛ ለውጦች እንዲያደርግ ሊገፋፋው ይችላል። ለምሳሌ ዳግ ያደገው በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ቢሆንም አምላክ የሚያደርገውን ሁሉ እንደሚያይ አድርጎ አላሰበም ነበር። በዚህም ምክንያት ሁለት ዓይነት ኑሮ መኖር ጀመረ። ከቤተሰቡ ጋር በክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ ከተገኘ በኋላ ከጓደኞቹ ጋር ዕፅ ይወስድ ነበር። ለሞተር ብስክሌት በነበረው ፍቅር ተገፋፍቶ በተደባዳቢነቱ ከታወቀ የሞተር ብስክሌት ወንጀለኛ ቡድን ጋር ተቀላቀለ። የቡድኑን ተቀባይነት ለማግኘት ሲልም ከባድ ወንጀሎች ፈጸመ።

ከዓመታት በኋላ ዳግ መጽሐፍ ቅዱስ በድጋሚ ማጥናት ጀመረ። ይሖዋ እውን አካል እንደሆነና ሰዎች የሚሠሩትን ሁሉ የሚያይ፣ በዚህም የሚደሰትና የሚያዝን መሆኑን መገንዘብ ጀመረ። ዳግ ኑሮውን ከፍተኛ ከሆኑት የአምላክ የሥነ ምግባር ሕግጋት ጋር አስማምቶ ለመምራት ተነሳሳ። የወንጀለኞቹ ቡድን ከቡድኑ ተለይቶ የሚወጣን ሰው የመደብደብ ልማድ ቢኖረውም ዳግ በቡድኑ ስብሰባ ላይ ተገኝቶ በአባሎቹ ሁሉ ፊት ከቡድኑ መውጣቱን አስታወቀ። እንዲህ በማለት ትውስታውን ይተርካል:- “ለመናገር ብድግ ስል ልቤ ይመታ ነበር። ዳንኤል በአንበሳ ጉድጓድ ውስጥ እንደነበረ ሆኖ ተሰማኝ። ድምፄን ሳላሰማ ወደ ይሖዋ ጸለይኩና ረጋ ብዬ ከቡድኑ የምወጣበትን ምክንያት አስረዳሁ። ስወጣ ከአንዱ በስተቀር ሁሉም እጄን እየጨበጡና መልካም ምኞታቸውን እየገለጹ ተሰናበቱኝ። ኢሳይያስ 41:​13 እውነት መሆኑን በተግባር ለማየት ቻልኩ። ‘እኔ አምላክህ እግዚአብሔር:- አትፍራ፣ እረዳሃለሁ ብዬ ቀኝህን እይዛለሁ’” ይላል። ዳግ አኗኗሩን ለመለወጥ የሚያስፈልገውን ኃይልና ብርታት ከይሖዋ እንዳገኘ ይሰማዋል።

ምክንያታዊ የሆነ አመለካከት

አንዳንድ ነገሮችን ከአምላክ ልሸሽግ እችላለሁ ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ “ሰነፍ በልቡ:- አምላክ የለም ይላል” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 14:​1) ቀደም ባሉት ርዕሶች እንደተመለከተው የሰው ልጆች ከሕዝብ መካከል የአንድን ሰው መልክ ነጥሎ ሊያወጣ የሚችል የስለላ ካሜራ መሥራት ችለዋል። የስልክ መስመሮችን በመጠቀም በብዙ ሺህ ከሚቆጠሩ ሰዎች መካከል የአንድን ሰው ድምፅ ነጥሎ ሊቀዳ የሚችል የማዳመጫ መሣሪያ ሠርተዋል። የሰውን አንጎል የፈጠረው አምላክም ተገቢ ሆኖ ሲያገኘው የማንንም ሐሳብ ጠልቆ የመመርመር ችሎታ እንደሚኖረው የታወቀ ነው።

ፈጣሪያችን አንድ ሰው በምሥጢር የሚሠራውን ሁሉ የማወቅ መብት ያለው ቢሆንም ሰዎች ግን እንዲህ የማድረግ መብት የላቸውም። ሐዋርያው ጴጥሮስ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ለሚፈልጉ ሁሉ “ከእናንተ ማንም . . . ክፉ አድራጊ እንደሚሆን ወይም በሌሎች ጉዳይ እንደሚገባ ሆኖ መከራን አይቀበል” ሲል መክሯል። (1 ጴጥሮስ 4:​15) ሐዋርያው ጳውሎስም በሰው ‘ጉዳይ ገቢዎች እንዳንሆን’ አስጠንቅቋል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 5:​13

በአንዳንድ አገሮች በግለሰቦች ኑሮ ውስጥ መግባት እየተለመደ የመጣ ነገር በመሆኑ የሰዎችን እንቅስቃሴና ድርጊት ለመከታተል የድምፅና የምስል መቅረጫ መሣሪያዎችን በምሥጢር ይተክላሉ። ለምሳሌ ያህል በጃፓን አገር በሲድኒ ኦሎምፒክ ውድድር የወርቅ ሜዳልያ የተሸለመችው የማራቶን ሯጭ ናኦኮ ታካሺ በመታጠቢያ ቤቷ ውስጥ የምስል መቅረጫ መሣሪያ እንደተተከለና ሳታውቀው የምታደርገውን ሁሉ ሲቀዳ እንደነበረ ደርሳበታለች። የቪድዮ ፊልም ከተዘጋጀ በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ ቅጂዎች በሕገ ወጥ መንገድ ተሽጠዋል።

በተጨማሪም በተራቀቀ ቴክኖሎጂ የሰዎችን ማንነት መስረቅ እየተስፋፋ መጥቷል። ገመናችሁ ባልተፈቀደላቸው ሰዎች እንዳይታይ ለማድረግ ምክንያታዊ የሆኑ እርምጃዎች መውሰድ ያስፈልጋል። * መጽሐፍ ቅዱስ “ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፤ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይጐዳሉ” ይላል።​—⁠ምሳሌ 22:​3

በስውር የተደረገው ሁሉ በይፋ ፍርድ ያገኛል

ወንጀል፣ ጠበኝነትና አሸባሪነት እየጨመረ በሄደ መጠን መንግሥታት ዜጎቻቸውን በይበልጥ በዓይነ ቁራኛ መከታተላቸው አይቀርም። በቅርብ ጊዜ ግን የስለላ ካሜራም ይሁን የሰውን መልእክት መጥለፍ አስፈላጊ የማይሆንበት ጊዜ ይመጣል። መጽሐፍ ቅዱስ በቅርቡ ይሖዋ አምላክ መላውን የሰው ልጅ በስውርም ይሁን በግልጽ ላደረጋቸው ነገሮች ፍርድ እንደሚሰጥ ይናገራል።​—⁠ኢዮብ 34:​21, 22

ከዚያ በኋላ ምድር የሰውን ዘር ለብዙ ዘመናት አስጨንቆ ከኖረው ጠበኝነት፣ ጥላቻና ወንጀል ነጻ ትሆናለች። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? በዚያ ጊዜ ይሖዋ በሕይወት የሚኖሩትን ሰዎች በሙሉ አሳምሮ እንደሚያውቃቸው ሁሉ እነርሱም ይሖዋን በደንብ አድርገው የሚያውቁት ይሆናሉ። የነቢዩ ኢሳይያስ ቃላት በትክክል ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ:- “በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጐዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና።”​—⁠ኢሳይያስ 11:​9

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.21 “ተጠንቀቅ!” የሚለውን ሣጥን ተመልከት

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ከአምላክ ሊሰወር የሚችል ነገር እንደሌለ ማወቃችን መልካም እንድናደርግ ይገፋፋናል።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ተጠንቀቅ!

ገመናና የኢንተርኔት ሥራ ማፈላለጊያ ገጾች:- በኢንተርኔት አማካኝነት የሥራ ማመልከቻ የሚያቀርቡ ሥራ ፈላጊዎች ከፍተኛ የሆነ ምሥጢር የመባከን ችግር ያጋጥማቸዋል። ማመልከቻዎች በሥራ ማፈላለጊያ ገጾች ላይ ለበርካታ ዓመታት ተመዝግበው ሊቆዩና የግለሰቦችን ማንነት ለመስረቅ የሚያስችል መረጃ ለማግኘት ጭምር ሊያገለግሉ ይችላሉ። አንዳንድ ሥራ ማፈላለጊያ ገጾች የሥራ ፈላጊዎችን ስም፣ አድራሻ፣ ዕድሜና የሥራ ልምድ ከጠየቁ በኋላ ይህንን መረጃ ለሸቀጥ ሻጮች ወይም አስተዋዋቂዎች አሳልፈው ይሰጣሉ።

ምሥጢርና የተንቀሳቃሽ ስልክ ግንኙነት:- ባሁኑ ጊዜ በሞባይል ወይም በተንቀሳቃሽ ስልክ የሚደረግን ውይይት ምሥጢር ለመጠበቅ የሚያስችል አስተማማኝና ብዙ ወጪ የማይጠይቅ ዘዴ የለም። ምሥጢር የሆነ ነገር የምትነጋገር ከሆነ መደበኛውን በሽቦ የተገናኘ ስልክ መጠቀም የተሻለ ይሆናል። አንተም ሆንክ የምታናግረው ሰው በመደበኛው ስልክ የሚጠቀም መሆኑን አረጋግጥ። ከተንቀሳቃሽ ስልኮች የሚወጣው መልእክት የራዲዮ ጨረር በሚጠልፉ መሣሪያዎች፣ እንዲያውም በሌሎች ተንቀሳቃሽ ስልኮች ወይም ሕፃናት ከእንቅልፋቸው ሲነቁ ለወላጆች ምልክት በሚሰጡ መሣሪያዎች ሊጠለፍ ይችላል። በስልክ ዕቃ ብትገዛና የዱቤ ካርድ ቁጥርህንና ካርዱ የሚያበቃበትን ጊዜ በተንቀሳቃሽ ስልክ የምትናገር ከሆነ በሌሎች ሊጠለፍና ለአጭበርባሪዎች ሲሳይ ልትሆን ትችላለህ። *

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.32 ከፕራይቨሲ ዋች ክሊሪንግሃውስ ዌብ ገጽ የተወሰደ።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሕይወት አድን ሠራተኛው እያንዳንዱን ዋናተኛ በዓይነ ቁራኛ ቢከታተልም በሰው ጉዳይ ውስጥ እንደሚገባ ተደርጎ አይቆጠርም

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳግ አምላክ የምናደርገውን ሁሉ እንደሚያውቅ መገንዘቡ በአኗኗሩ ላይ ለውጥ እንዲያደርግ አነሳስቶታል