በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፈገግታ የሚያሳድረው ስሜት

ፈገግታ የሚያሳድረው ስሜት

ፈገግታ የሚያሳድረው ስሜት

ለአጭር ጊዜ ብልጭ ብሎ የሚጠፋ ቢሆንም ጥሎት የሚያልፈው ትዝታ ምንጊዜም የማይረሳ ሊሆን ይችላል። እጅግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ነገር ነው። ሆኖም ማንም ሰው እኔ እንኳ ድሀ ነኝ ከየት አመጣለሁ ሊል ወይም ደግሞ ማንም ሰው በጣም ሃብታም ስለሆንኩ ይህ ለእኔ አያስፈልገኝም ሊል አይችልም። ለመሆኑ ይህ ነገር ምንድን ነው? ፈገግታ ነው።

በውስጣችን የሚሰማንን ደስታ ለመግለጽ የፊታችን ጡንቻዎች ተኮማትረው ዓይናችን ሲፈካና ከንፈራችን ወደ ኋላ ሸሸት ሲል በፊታችን ላይ ፈገግታ ይነበባል። አንድ ሕፃን ከተወለደ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት ፈገግ ሲል ይታያል፤ ወላጆቹም ይህንን ሲመለከቱ መደሰታቸው የማይቀር ነው። ሕፃኑ በዚህ ወቅት የሚያሳየው ፈገግታ ሳይታሰብ የሚመነጭ ነው። እንደዚህ ዓይነት ፈገግታ የምናሳየው አብዛኛውን ጊዜ በሕልማችን እንደሆነና ይህም ከውስጣዊ ስሜታችንና ከማዕከላዊው የነርቭ ሥርዓት እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ጠበብት ይናገራሉ። አዋቂዎች ሆነንም እንኳ ምግብ ከበላን በኋላ ወይም ደግሞ ሙዚቃ ስናዳምጥ ሳናስበው ፈገግ ልንል እንችላለን።

ሕፃኑ ስድስት ሳምንት ገደማ ሲሆነው ግን በሌሎች ፊት ላይ በሚያየው ነገር ወይም በሚሰማው ድምፅ የተነሳ ፈገግ ማለት ይጀምራል። ሕፃናትም ሆንን አዋቂዎች በሌሎች ሰዎች ገጽታ ላይ ‘ወዳጃዊ ፈገግታ’ መመልከት ያስደስተናል። እንደዚህ ዓይነቱ ፈገግታ ለጤንነታችንም ጠቃሚ እንደሆነ ይነገራል። ፈገግታና ጤና የተባለ ክሊኒክ ባለቤት የሆኑት ሚርታ ማኖ እና ሩቤን ዴላውሮ የተባሉ የንግግር ሕክምና ባለሙያዎች እንደተናገሩት ፈገግታ በራሱ ፒቱታሪ የተባለውን እጢ ያነቃቃዋል። ይህ እጢ ደግሞ በምላሹ፣ ጥሩ ስሜት እንዲሰማን የሚያደርጉ በአእምሮ ውስጥ የሚገኙ ኢንዶርፊን የተባሉ ኬሚካሎችን ይረጫል።

ፈገግታ የሚያስገኘው ሌላው ጥቅም ደግሞ በሌሎች ላይ የሚያሳድረው በጎ ተጽዕኖ ነው። ለሰላምታም ይሁን፣ በአዘኔታ ወይም ለማበረታታት ብለን የምናሳየው ከልብ የመነጨ ፈገግታ በቃላት መግለጽ ሳያስፈልገን ውስጣዊ ስሜታችንን ይናገራል። አልፎ አልፎ በፎቶግራፍ የተመለከትነው የአንድ ሕፃን ማራኪ ፈገግታ ብቻ እንኳን ፈገግ እንድንል ሊያደርገን ይችላል።

አንድ ሰው የሚያሳየን ከልብ የመነጨ ወዳጃዊ ፈገግታ የበለጠ ዘና እንድንልና ያጋጠመንን የሚያበሳጭ ሁኔታ ወይም አስቸጋሪ ጉዳይ እንድንወጣ ሊረዳን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ለተቸገረው ሰው በጎ ነገርን ማድረግ አትከልክል፣ ልታደርግለት የሚቻልህ ሲሆን” ይላል። (ምሳሌ 3:27) አዎን፣ ፈገግታ በማሳየት ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን መጥቀም እንችላለን። ታዲያ ይህንን በጣም ውድ የሆነ ስጦታ ማለትም ወዳጃዊ ፈገግታ ለሌሎች ለመለገስ ለምን ጥረት አታደርግም?