በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆችን መበዝበዝ በቅርቡ ያከትማል!

ልጆችን መበዝበዝ በቅርቡ ያከትማል!

ልጆችን መበዝበዝ በቅርቡ ያከትማል!

“የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ የልጅነት ጊዜ ልዩ ፍቅርና እንክብካቤ ሊቸረው እንደሚገባ አስታውቋል” በማለት ስለ ልጆች መብት የወጣው ስምምነት በመግቢያው ላይ ይገልጻል። የቤተሰብን አስፈላጊነት በተመለከተም የሚከተለውን አክሎ ተናግሯል:- “አንድ ልጅ የተሟላና ጥሩ ባሕርይ እንዲያዳብር ከተፈለገ ደስታ፣ ፍቅርና መግባባት በሰፈነበት ቤተሰብ ውስጥ ማደግ ይኖርበታል።” ሆኖም ይህ ግብ ሊደረስበት የሚችል አልሆነም።

ለልጆች የተሻለ ዓለም ስለማምጣት መናገሩ ብቻውን በቂ አይደለም። የሥነ ምግባር ብልሹነት እየተስፋፋ ያለ ቢሆንም ብዙ ሰዎች ይህን ችግር ከቁብ አይቆጥሩትም። በስፋት የተዛመተውን ብልሹነትና ስግብግብነት በሕግ መግታት አይቻልም። ሌላው ቀርቶ ወላጆች እንኳን ለልጆቻቸው ፍቅር ማሳየትና ጥበቃ ማድረግ ሲገባቸው አብዛኛውን ጊዜ መረን ይለቋቸዋል። ታዲያ የልጆችን ዝሙት አዳሪነት ለማስወገድ ምን ተስፋ አለ?

ይህ ብልሹ ዓለም ሁሉም ልጆች አፍቃሪ ቤተሰብና አስተማማኝ የወደፊት ተስፋ እንዲያገኙ ማድረግ ቢሳነውም ፈጣሪያችን የልጆች ዝሙት አዳሪነትን ጨምሮ ማንኛውንም ዓይነት ብልሹነትና ሴሰኝነት ያጠፋል። በቅርቡ ይሖዋ አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት በሰዎች ጉዳይ ጣልቃ ይገባል። ብልሹ ሰዎችና በዝባዦች ከመለኮታዊው ፍርድ አያመልጡም። በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ በሕይወት ለመኖር ከጥፋቱ የሚተርፉት ለሰዎች ፍቅር ያላቸው ብቻ ይሆናሉ። “ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና፣ ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉና፤ ኀጥአን ግን ከምድር ይጠፋሉ፣ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ።”​—⁠ምሳሌ 2:​21, 22

ልጆችም ሆኑ አዋቂዎች ከወራዳ ምግባርና የወሲብ መጠቀሚያ ከመሆን ነፃ ሆነው መኖር ሲችሉ የሚኖረውን እፎይታ ገምት! በብዝበዛና በዓመፅ ድርጊቶች ምክንያት የሚደርሰው ስሜታዊም ሆነ አካላዊ ጉዳት እንኳን የተረሳ ነገር ይሆናል። ቀደም ሲል የወሲብ ብዝበዛ ሰለባ የነበሩ ሰዎችም በደረሰባቸው በደል መጥፎ ትዝታ ሳይረበሹና በደሉ ካስከተለባቸው አካላዊም ሆነ ሥነ ልቦናዊ መዘዝ ነፃ ሆነው ይኖራሉ። “የቀደሙትም አይታሰቡም፣ ወደ ልብም አይገቡም።”​—⁠ኢሳይያስ 65:​17

በዚያን ጊዜ በደል የሚደርስበትና የወሲብ መጠቀሚያ የሚደረግ ልጅ አይኖርም። ደስታ፣ ፍቅርና መግባባት ሕልም ብቻ ሆነው አይቀሩም። በአምላክ አዲስ ዓለም የሚኖሩ ሰዎችን በሚመለከት ኢሳይያስ 11:​9 “አይጎዱም አያጠፉምም” በማለት ይናገራል።

በእርግጥም ድህነት፣ አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ፣ ደስታ ያጣ ቤተሰብና ሥነ ምግባራዊ ብልሹነት ተወግደው መመልከት ምንኛ የሚያስደስት ይሆናል! ሰላም፣ ጽድቅና ደህንነት ይሰፍናል። “ሕዝቤም በሰላም ማደሪያ በታመነም ቤት፣ በጸጥተኛ ማረፊያ ይቀመጣል።”​—⁠ኢሳይያስ 32:​18

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

የወላጅ አሳቢነት ቤተሰብን ከመፈራረስ ያድናል

“ወላጆቼ የትምህርት ዘመኔን በሚገባ ተጠቅሜ አንድ ዓይነት ሞያ እንድማር ያበረታቱኝ ነበር። የራሳቸውን ምርጫ እንድከተል ሊጫኑኝ ባይሞክሩም የሚያስፈልገኝን ሥልጠና የሚሰጥ ትምህርት ቤት እንድመርጥ ረድተውኛል።”​— ቴይስ

“እህቴና እኔ ልብስ ለመግዛት ወደ ገበያ ስንሄድ እናታችን አብራን ትሄድ ነበር። እናታችን ቆጣቢዎች እንድንሆን ብቻ ሳይሆን ከልክ በላይ የተንቆጠቆጡና ሰውነትን የሚያጋልጡ ልብሶችን እንዳንገዛም ትረዳን ነበር።”​— ቢያንካ

“ወደ ግብዣ ቦታዎች ስንሄድ ወላጆቼ ሁልጊዜ በግብዣው ላይ እነማን እንደሚገኙና ምን ዓይነት ሙዚቃ እንደሚኖር እንዲሁም ግብዣው ተጀምሮ የሚያልቅበትን ሰዓት ይጠይቁ ነበር። በአብዛኞቹ ግብዣዎች ላይ ቤተሰባችን አንድ ላይ ይገኝ ነበር።”​— ፕሪሲላ

“በልጅነትና በወጣትነት ዕድሜዬ ከወላጆቼ ጋር እንደ ልቤ እነጋገር ነበር። አንዲት የትምህርት ቤት ጓደኛዬ ይህን ተመልክታ ነበርና ‘ከወላጆችሽ ጋር ስለማንኛውም ነገር በነፃነት መነጋገር መቻልሽ ያስቀናኛል። እኔ ከእናቴ ጋር እንደ ልቤ ስለማልነጋገር ማወቅ የምፈልጋቸውን ነገሮች የምጠይቀው ከሌሎች ሰዎች ነው’ ስትል ተናግራለች።”​— ሳማራ

“ደስተኛ ወጣት ነበርኩ። ሰዎችን ስለማልጠራጠር ሁልጊዜ ሳቂታ ነበርኩ። ከጓደኞቼ ጋር ስሆን ምንም ሥጋት ስለማይሰማኝ ስለሚያስቁ ነገሮች ማውራት ያስደስተኝ ነበር። ወላጆቼም ይህ የእኔ ልዩ ባሕርዬ መሆኑን ስለተገነዘቡ ሊለውጡኝ አልሞከሩም። ይሁን እንጂ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ስሆን ጠንቃቃና ጨዋ መሆን እንዳለብኝ በደግነት አስገነዘቡኝ።”​— ቴይስ

“በብዙ ወጣቶች ላይ እንደሚታየው እኔም ለተቃራኒ ጾታ የፍቅር ስሜት አደረብኝ። አባቴ መጠናናት ለመጀመር ማሰብ ያለብኝ ዕድሜ መቼ እንደሆነ አሳወቀኝ። እኔም በዚህ አልተከፋሁም። ከዚህ ይልቅ ወላጆቼ እንደሚያስቡልኝና ወደፊት ሊገጥመኝ ከሚችል ጉዳት ሊጠብቁኝ ፈልገው መሆኑን ተረዳሁ።”​— ቢያንካ

“ወላጆቼ በትዳራቸው ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ ስለነበሩ እኔም ትዳር ጥሩ ነገር መሆኑን ተገንዝቤ ነበር። ወላጆቼ ስምም የሆኑና ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት የሚያደርጉ ባልና ሚስት ነበሩ። ከተቃራኒ ጾታ ጋር መቀጣጠር ስጀምር እናቴ ልጠነቀቅባቸው የሚገቡኝ አንዳንድ ሁኔታዎች ምን እንደሆኑና ይህም ለምመሠርተው ትዳር ምን ጥቅም እንዳለው የሰጠችኝን ምክርና ማብራሪያ አልረሳውም።”​— ፕሪሲላ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ልጆች ማንኛውም ዓይነት በደል አይፈጸምባቸውም