በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በቂ እንቅልፍ ማግኘት ያስፈልግሃል!

በቂ እንቅልፍ ማግኘት ያስፈልግሃል!

በቂ እንቅልፍ ማግኘት ያስፈልግሃል!

ጤናማ ለመሆን ጥሩ እንቅልፍ መተኛት በጣም አስፈላጊ ነው ቢባል የማይስማማ ሰው ይኖራልን? ምናልባት ሁሉም ሰው ይስማማ ይሆናል። ያም ሆኖ ግን ብዙ ሰዎች ለእንቅልፍ እምብዛም ቦታ አይሰጡትም። ካናዳ በሚገኘው በካልጋሪ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ሐኪምና ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ሻውን ከሪ “በቂ እንቅልፍ ካላገኛችሁ በቀጣዩ ቀን ትቸገራላችሁ” ብለዋል። በቂ እንቅልፍ ካላገኘህ በቀላሉ ልትበሳጭና አንዳንድ ጊዜም በጭንቀት ልትዋጥ ትችላለህ።

ካልጋሪ ሄራልድ የተባለው ጋዜጣ “ሳይንቲስቶች እንቅልፍ አእምሯችን ራሱን የሚያድስበት ወቅት እንደሆነና በመኝታ ወቅትም ቢሆን መማራችንን እንደምንቀጥል ይናገራሉ” ብሏል። ፕሮፌሰር ከሪ እንዲህ ብለዋል:- “በእንቅልፍ ወቅት የማስታወስ ችሎታችሁን የምታጠናክሩ ሲሆን አእምሮም ቀን ያገኛቸውን አዳዲስ እውቀቶች ቦታ ቦታ የሚያስይዝበት ወቅት ነው። እንደዚህ ዓይነት እረፍት ካላገኘን የመማር ችሎታችን ይዳከማል።” አክለውም “በቂ እንቅልፍ ማግኘት የተረጋጋ ስሜት እንዲኖራችሁ ይረዳችኋል” በማለት ተናግረዋል።

ይህ ከሆነ ታዲያ በቂ የሚባለው እንቅልፍ ምን ያህል ነው? አብዛኞቹ ባለሞያዎች ስምንት ሰዓት በቂ መሆኑን ቢናገሩም ከሪ “እያንዳንዱ ሰው የሚያስፈልገው የእንቅልፍ መጠን የተለያየ ነው” ብለዋል። በዚህም ምክንያት ከሪ ጥሩ እንቅልፍ ለማግኘት ጥረት እንድናደርግ ያበረታታሉ። ይሁን እንጂ ጥሩ እንቅልፍ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው? በተለይም እንቅልፍ አልወስድ የሚላቸው ሰዎች ምን ማድረግ ይችላሉ? ከዚህ ቀጥሎ አንዳንድ ሐሳቦች ቀርበዋል:-

▪ ከመተኛታችሁ በፊት ሰውነታችሁን ሞቅ ባለ ውኃ ታጠቡ።

▪ በሳምንቱ ውስጥ በተደጋጋሚ መጠነኛ የአካል እንቅስቃሴ ሥሩ፤ ሆኖም ከመኝታ በፊት ከበድ ያለ የሰውነት እንቅስቃሴ አታድርጉ።

▪ የመኝታ ክፍላችሁ ፀጥታ የሰፈነበት፣ ጨለም ያለና ትንሽ ቀዝቀዝ ያለ እንዲሆን አድርጉ።

▪ ቋሚ የሆነ የእንቅልፍ ፕሮግራም እንዲኖራችሁ ሁልጊዜ ጠዋት ጠዋት በተወሰነ ሰዓት ላይ ለመነሳት ጥረት አድርጉ።

በጤና ረገድ የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ግምት ውስጥ በማስገባት ለእንቅልፋችን ከፍተኛ ቦታ ልንሰጠው ይገባል።