በአውሮፓ በናዚ አገዛዝ ሥር በእምነት ላይ የደረሰ ፈተና
በአውሮፓ በናዚ አገዛዝ ሥር በእምነት ላይ የደረሰ ፈተና
አንቶን ሊቶኒያ እንደተረከው
መጋቢት 12, 1938 የሂትለር ወታደሮች የኦስትሪያን ድንበር አቋርጠው ገቡ። ሬዲዮዎች ወታደራዊ ማርሽና የፓለቲካ መፈክሮችን ማሰማት ጀመሩ። ብሔራዊ ስሜት የትውልድ አገሬን ኦስትሪያን እንደ ማዕበል አጥለቀለቃት።
ኦስትሪያ በሂትለር አገዛዝ ሥር ከወደቀች በኋላ ሕዝቡ የተሻለ ነገር ለማግኘት የነበረው ተስፋ አንሰራራ። ብዙዎች የሂትለር “የሺህ ዓመት ግዛት” ድህነትንና ሥራ አጥነትን ያስቀራል ብለው ተስፋ አደረጉ። የካቶሊክ ቄሶች እንኳን ሳይቀሩ አገሪቱን ባጥለቀለቀው ብሔራዊ ስሜት ተማርከው እንደ ናዚዎች ሰላምታ ይሰጣጡ ነበር።
ምንም እንኳን በወቅቱ ገና የ19 ዓመት ወጣት የነበርኩ ቢሆንም በሂትለር ተስፋዎች አልተማረክሁም ነበር። የትኛውም ሰብዓዊ መንግሥት ለሰው ዘር ችግሮች መፍትሄ ያስገኛል የሚል እምነት አልነበረኝም።
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መማር
የተወለድኩት ሚያዝያ 19, 1919 ኦስትሪያ በምትገኘው ዶናቪትስ በተባለች ከተማ ውስጥ ሲሆን ከቤተሰባችን ሦስተኛውና የመጨረሻው ልጅ ነበርኩ። አባቴ ትጉህ የከሰል ማዕድን አውጭ ነበር። በ1923 በፈረንሳይ የማዕድን ማውጫ ከተማ በሆነችው በሌቪን ሥራ አገኘና ቤተሰባችንን ይዞ ወደዚያው ተዛወረ። በፖለቲካዊ እምነቱ የተነሳ ለሃይማኖት በጎ አመለካከት አልነበረውም። እናታችን ግን ቀናተኛ ካቶሊክ ነበረች። እኛን በአምላክ እንድናምን አድርጋ ያሳደገችን ሲሆን ሁልጊዜ ማታ ማታ አብራን ትጸልይ ነበር። አባታችን ለሃይማኖት የነበረው ጥላቻ ከማየሉ የተነሳ እናታችንን ቤተ ክርስቲያን እንዳትሄድ ከለከላት።
በ1920ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ቪንኮ እያልን ከምንጠራው የዩጎዝላቪያ ተወላጅ ከሆነ ቪንሴንትስ ፕላታይስ ከተባለ ወጣት ጋር ተዋወቅን። በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ከሚጠሩት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ግንኙነት ነበረው። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ቤተሰባችንን መጎብኘት ጀመረ። እናታችን ቤተ ክርስቲያን እንዳትሄድ አባታችን ከልክሏት ስለነበር አምላክን እቤት ውስጥ ሆኖ ማምለክ ይቻል እንደሆነ ቪንኮን ጠየቀችው። አምላክ “እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም” የሚለውን ሥራ 17:24 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ አነበበላትና አምላክን በቤት ውስጥ ማምለክ ተገቢ መሆኑን አስረዳት። በዚህ ስለተደሰተች በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቤት ውስጥ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረች።
አባታችን ይህን በእርሱ አስተሳሰብ የማይረባ ድርጊቷን እንድታቆም ነገራት። ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር እንዳንሰበሰብ ለማድረግ እሁድ እሁድ በቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ እንድንገኝ አዘዘን! እናታችን ቤተ ክርስቲያን ላለመሄድ ባደረገችው ውሳኔ ስለገፋችበት አባቴ በቤተ ክርስቲያን በሚደረገው የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዳገለግል አደረገ። እናቴ ይህን ውሳኔውን ብታከብርለትም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ መመሪያዎች በልቤና በአእምሮዬ ውስጥ መቅረጿንና የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ወደሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ይዛኝ መሄዷን ገፋችበት።
በ1928 ቪንኮና ፒፔ ብለን የምንጠራት እህቴ ዮዜፌና ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው ተጠመቁ። ከዚያም ተጋቡና በቀጣዩ ዓመት ሴት ልጃቸው ፊኒ በሌቪን ተወለደች። ከሦስት ዓመት በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በታገደበት በዩጎዝላቪያ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ሆነው እንዲሠሩ ተጋበዙ። ብዙ ችግሮች የደረሱባቸው ቢሆንም ደስታቸውና ለይሖዋ አገልግሎት የነበራቸው ቅንዓት መቼም ቢሆን አልቀዘቀዘም። የእነርሱ መልካም አርአያ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የመሆን ፍላጎት እንዲያድርብኝ አድርጓል።
መንፈሳዊ እድገት
የሚያሳዝነው በወላጆቻችን መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በ1932 ለፍቺ አደረሳቸው። ታላቅ ወንድሜ ቪልኸልም እዚያው ፈረንሳይ ሲቀር እኔና እናቴ ወደ ኦስትሪያ ተመለስን። ከዚያ በኋላ ከአባቴ ጋር ብዙም አልተገናኘንም። እስከሞተበት ዕለት ድረስ ለእኛ ጥሩ አመለካከት አልነበረውም።
እኔና እናቴ ጋምሊትስ በተባለች የኦስትሪያ መንደር መኖር ጀመርን። በአቅራቢያችን ምንም ጉባኤ ስላልነበር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በመጠቀም ከእናቴ ጋር እንወያይ ነበር። ደስ የሚለው በግራዝ ከተማ የሚኖረው ኤድዋርት ቮሂንስ በወር ሁለት ጊዜ 100 ኪሎ ሜትር የሚያህል ርቀት በብስክሌት ተጉዞ እየመጣ መንፈሳዊ ማበረታቻ ይሰጠን ነበር።
በ1938 የሂትለር የሽብር አገዛዝ እንደ ጀመረ ወንድም ቮሂንስ ታሰረ። ከጊዜ በኋላ በሊንዝ በጋዝ ታፍኖ እንደተገደለ ስንሰማ በጣም አዘንን። ወንድም ቮሂንስ የነበረው አስገራሚ እምነት ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላችንን እንድንቀጥል አበረታቶናል።
1938—ለውጥ ያስከተለ ዓመት
የይሖዋ ምሥክሮች በኦስትሪያ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በ1935 ታግዶ ነበር። የሂትለር ወታደሮች በ1938 ኦስትሪያን ሲቆጣጠሩ አገልግሎታችንን ማከናወን ይበልጥ አስቸጋሪ ሆነ። ጎረቤቶቻችን እኔና እናቴ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን ያውቁ ስለነበር የሰዎችን ትኩረት ላለመሳብ ወሰንን። እንዲያውም ናዚዎች እንዳያገኙኝ ማታ ማታ በከብቶች በረት ውስጥ ማደር ጀመርኩ።
በ1938 መግቢያ ላይ መደበኛ ትምህርቴን አጠናቀቅሁና በዳቦ መጋገሪያ ቤት ተቀጥሬ መሥራት ጀመርኩ። ይሁን እንጂ “ሄይል ሂትለር” (ሂትለር አዳኝ ነው) ለማለትም ሆነ የሂትለር የወጣቶች ድርጅት አባል ለመሆን ፈቃደኛ ባለመሆኔ ከሥራዬ ተባረርኩ። ቢሆንም ራሴን ለይሖዋ ወስኜ ለመጠመቅ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ቆርጬ ነበር።
ሚያዝያ 8, 1938 እኔና እናቴ ተጠመቅን። አንድ ቀን ምሽት እኔና እናቴ ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር ጫካ ውስጥ ራቅ ብሎ በተሠራ ጎጆ ቤት ውስጥ ተሰበሰብን። የጥምቀት ንግግሩ ከተደረገ በኋላ በየአሥር ደቂቃ ልዩነት ተራ በተራ አንድ ቀጭን መንገድ ተከትለን ወደ ልብስ ማጠቢያው ክፍል ሄድንና ከሲሚንቶ በተሠራ ገንዳ ውስጥ ተጠመቅን።
ሚያዝያ 10 ቀን ኦስትሪያ ከጀርመን ጋር መቀላቀሏን በሚመለከት ለይስሙላ ሕዝባዊ ምርጫ ተደርጎ ነበር። “ሂትለርን ምረጡ” የሚለው ፖስተር መላ አገሪቷን አጥለቅልቋት ነበር። እኔና እናቴ ፈረንሳይ ረጅም ጊዜ ከመቆየታችን የተነሳ የየትኛውም አገር ዜጎች ስላልነበርን በምርጫው እንድንሳተፍ አልተጠበቀብንም። በፈረንሳይ ረዥም ጊዜ መቆየቴ በኋላ ላይም ሕይወቴን አድኖልኛል። ፍራንዝ ጋንስተር በደቡባዊ ኦስትሪያ ከሚገኘው ከክላገንፈርት የመጠበቂያ ግንብ ቅጂዎችን ይዞልን ይመጣ ነበር። በዚህ መንገድ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመፈንዳቱ በፊት የአምላክን ቃል በማጥናት መንፈሳዊ ጥንካሬ ማግኘት ችለን ነበር።
የወንድሜ የቪሊ ሁኔታ
እኔና እናቴ ፈረንሳይን ለቅቀን ከወጣንበት ጊዜ ጀምሮ በአራት ዓመት ከሚበልጠኝ ወንድሜ ከቪሊ ጋር ለዘጠኝ ዓመታት ያህል አልተገናኘንም ነበር። እናቴ በልጅነቱ መጽሐፍ ቅዱስን አስተምራው የነበረ ቢሆንም እንኳ የሂትለር የፖለቲካ ሥርዓት ከችግሮች ነጻ የሆነ ዓለም ያመጣል በሚለው እምነት ተታልሎ ነበር። ናዚን በመደገፍ
ባደረገው ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ግንቦት 1940 በአንድ የፈረንሳይ ችሎት ፊት ቀርቦ የሁለት ዓመት እስራት ተፈረደበት። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ የጀርመን ወታደሮች ፈረንሳይን ሲወርሩ ከእስር ተፈታ። በዚያ አጋጣሚ ከፓሪስ የሰላምታ ካርድ ላከልን። በሕይወት እንዳለ መስማታችን ቢያስደስተንም የናዚ ደጋፊ መሆኑን ማወቃችን ግን በጣም አስደነገጠን!ቪሊ ከኤስ ኤስ ወታደሮች (ሹትዝስታፈል፣ የሂትለር የተመረጡ ወታደሮች) ጋር ይግባባ ስለነበር በጦርነቱ ወቅት ብዙ ጊዜ እየመጣ ይጠይቀን ነበር። በሂትለር ወታደራዊ ድሎች በጣም ተማርኮ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተመሠረተው ተስፋችን ልነግረው ስሞክር “ይህን የማይረባ ወሬህን ወዲያ ተው! ሂትለር ያገኘውን ድል እስቲ ተመልከት። በቅርቡ ጀርመኖች የዓለም ገዢዎች መሆናቸው አይቀርም!” በማለት ያቋርጠኝ ነበር።
በ1942 የካቲት ወር ቪሊ እንደተለመደው ሊጠይቀን ሲመጣ በይሖዋ ምሥክሮች የታተመውን ኢነሚስ የተባለውን መጽሐፍ ሰጠሁት። ከተቀመጠበት ንቅንቅ ሳይል አንብቦ ጨረሰው። ከዚያም የሂትለር አገዛዝ መንኮታኮቱ እንደማይቀር ቀስ በቀስ መገንዘብ ጀመረ። እስካሁን ድረስ ሰብዓዊ ርኅራሄ የጎደለውን ሥርዓት ይደግፍ እንደነበር ሲገነዘብ ጊዜ ሳያጠፋ ስህተቱን ለማረም ቁርጥ ውሳኔ አደረገ።
ቪሊ ከእውነት ጎን ለመቆም የወሰደው እርምጃ
በሚቀጥለው ወር ቪሊ ሊጎበኘን ሲመጣ አመለካከቱ ፍጹም ተለውጦ ነበር። “አንቶን፣ እስከ አሁን ድረስ የተሳሳተ መንገድ ይዤ ነበር” አለኝ።
“ቪሊ፣ ይህን ለመገንዘብ ትንሽ ዘግይተሃል” አልኩት።
“በፍጹም፣ አሁንም ጊዜ አለኝ! መጽሐፍ ቅዱስ ‘በሕይወት እስካለህ ድረስ ማድረግ ያለብህን አድርግ’ ይላል። ደግሞም አምላክ የተመሰገነ ይሁን እስካሁን በሕይወት አለሁ!” ሲል መለሰልኝ።—መክብብ 9:10
“ታዲያ አሁን ምን ለማድረግ አስበሃል?” በማለት ጠየቅሁት።
“ወታደር ሆኜ የመቀጠል ፍላጎት የለኝም። ከናዚዎች ጋር ያለኝን ማንኛውንም ግንኙነት አቋርጥና የሚሆነውን አያለሁ” በማለት መለሰ።
ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ዩጎዝላቪያ የምትኖረውን እህታችንን ለመጎብኘት ወደ ዛግሬብ ሄደ። እዚያም የይሖዋ ምሥክሮች በድብቅ በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ ለተወሰነ ጊዜ ከተገኘ በኋላ በምስጢር ተጠመቀ። በመጨረሻ ኮብላዩ ልጅ ተመለሰ!—ሉቃስ 15:11-24
ቪሊ በፈረንሳይ ካሉት ናዚዎች ለማምለጥ በድንበር በኩል ወደ ስዊዘርላንድ ለመሻገር ሞከረ። ይሁን እንጂ የጀርመን ፖሊሶች ያዙት። ከዚያም በርሊን በሚገኘው ወታደራዊ ችሎት ፊት ቀረበና ሐምሌ 27, 1942 አገርን በመክዳት ወንጀል ሞት ተፈረደበት። በበርሊን ቴገል ወታደራዊ ወኅኒ ቤት ውስጥ በነበረበት ወቅት ሄጄ እንድጠይቀው ተፈቅዶልኝ ነበር። ወደ አንድ ጠባብ ክፍል ተወሰድኩና ብዙም ሳይቆይ ቪሊ ከአንድ ጠባቂ ጋር በሰንሰለት ተቆራኝቶ መጣ። እንደዚያ ተጎሳቁሎ ሳየው እንባዬ በዓይኖቼ ግጥም አለ። ተቃቅፈን ሰላምታ ለመለዋወጥ ያልተፈቀደልን ከመሆኑም በላይ ለመሰነባበት የተሰጠን ጊዜ 20 ደቂቃ ብቻ ነበር።
ቪሊ እንባዬን ሲመለከት እንዲህ አለኝ:- “አንቶን ለምንድን ነው የምታለቅሰው? መደሰት ነው ያለብህ! ይሖዋ እውነትን ዳግመኛ እንዳገኝ ስለረዳኝ በጣም አመሰግነዋለሁ! የምሞተው ለሂትለር ቢሆን ኖሮ ምንም ተስፋ አይኖረኝም ነበር። ለይሖዋ መሞት ማለት ግን በትንሣኤ የመነሳትና ከእናንተ ጋር በድጋሚ የመገናኘት ተስፋ አለኝ ማለት ነው!”
ቪሊ ለስንብት በጻፈልን ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር:- “የማገለግለው ውዱ አምላካችን የሚያስፈልገኝን ሁሉ ሰጥቶኛል፤ ወደፊትም በጽናት መቀጠልና ፈተናውን በድል መወጣት እንድችል ከጎኔ እንደሚቆም ፍጹም እርግጠኛ ነኝ። በዚህ ውሳኔዬ ምንም እንደማልጸጸትና እስካሁን ድረስ ታማኝነቴን እንደጠበቅሁ በድጋሚ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።”
ቪሊ በማግስቱ ማለትም መስከረም 2, 1942 በበርሊን አቅራቢያ በሚገኘው በብራንደንበርግ ወኅኒ ቤት ውስጥ የሞት ፍርዱ ተፈጸመበት። ገና 27 ዓመቱ ነበር። የእሱ ምሳሌነት በፊልጵስዩስ 4:13 ላይ ያሉትን ‘ኃይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ሁሉን እችላለሁ’ የሚሉትን ቃላት እውነተኝነት በግልጽ የሚያረጋግጥ ነው።
ቪንኮ እስከ ሞት ድረስ ያሳየው ታማኝነት
በ1941 የጀርመን ሠራዊት ዩጎዝላቪያን በቁጥጥሩ ስር ሲያደርግ ፒፔ፣ ባልዋ ቪንኮና የ12 ዓመት ልጅዋ ፊኒ ወደ ትውልድ አገራቸው ወደ ኦስትሪያ ለመመለስ ተገደዱ። በዚያን ጊዜ በኦስትሪያ ከነበሩት ምሥክሮች ውስጥ አብዛኞቹ
በወኅኒ ታስረው ወይም ወደ ማጎሪያ ካምፖች ተወስደው ነበር። እህቴ፣ ባልዋና ልጃቸው ግን የየትኛውም አገር ዜጎች ስላልነበሩ በደቡባዊ ኦስትሪያ ከእኛ ብዙም በማይርቅ በአንድ የእርሻ ማሳ ውስጥ የጉልበት ሥራ እንዲሠሩ ተመደቡ።ከዚያም ነሐሴ 26, 1943 ጌስታፖዎች (የናዚ የምስጢር ፖሊሶች) ቪንኮን አሰሩት። ፊኒ አባቷን ልትሰናበተው ስትል የፖሊሶቹ አዛዥ በኃይል ስለመታት ተሽቀንጥራ ወደቀች። ጌስታፖዎቹ ቪንኮን ተደጋጋሚ ምርመራ ካደረጉበትና በጭካኔ ከደበደቡት በኋላ ሙኒክ ወደሚገኘው የሽታደልሃይም ወኅኒ ቤት ወሰዱት።
ጥቅምት 6, 1943 ፖሊሶች የምሠራበት ቦታ ድረስ መጥተው ያዙኝና ቪንኮ ወደታሰረበት ወደ ሽታደልሃይም ወኅኒ ቤት ላኩኝ። ፈረንሳይኛ አቀላጥፌ መናገር ስለምችል ለፈረንሳይ የጦር ምርኮኞች ለማስተርጎም ይጠቀሙብኝ ነበር። በወኅኒ ቤቱ ግቢ ውስጥ በምንንሸራሸርበት ወቅት ከቪንኮ ጋር ለማውራት አጋጣሚ አግኝቼ ነበር።
በመጨረሻ ቪንኮ ሞት ተፈረደበት። ይህ ዓይነቱ ፍርድ የተላለፈበት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለይሖዋ ምሥክሮች ሰጥተሃል እንዲሁም ባሎቻቸው በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ለታሰሩባቸው የይሖዋ ምሥክር ሴቶች ገንዘብ ረድተሃል በሚል ክስ ነበር። በበርሊን አቅራቢያ ወደሚገኘው ቪሊ ወደተገደለበት ወኅኒ ቤት አዛወሩትና ጥቅምት 9, 1944 አንገቱ ተሰይፎ ተገደለ።
ቪንኮና ቤተሰቡ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙበት አጋጣሚ ልብ የሚነካ ነበር። ያገኙት በሰንሰለት ታስሮና ክፉኛ ተጎሳቁሎ ሲሆን በሰንሰለቶቹ ምክንያት አቅፎ ሊሰናበታቸው አልቻለም። ፊኒ ለመጨረሻ ጊዜ አባቷን ስታገኘው 14 ዓመቷ ነበር። “ፊኒ፣ እናትሽን አደራ!” የሚሉትን የስንብት ቃላት አሁን ድረስ ታስታውሳቸዋለች።
አባቷን ከገደሉባት በኋላ ፊኒን ከእናቷ ነጥቀው አመለካከቷን “እናስተካክላለን” ለሚሉ የናዚ ደጋፊ የሆኑ ቤተሰቦች ሰጧት። ብዙ ጊዜ በጭካኔ ይደበድቧት ነበር። የሩስያ ወታደሮች ኦስትሪያን ሲቆጣጠሩ ፊኒን ይበድሏት የነበሩትን የዚህን የጀርመን ቤተሰብ አባላት በሙሉ ረሸኗቸው። ቤተሰቡን አክራሪ ናዚዎች እንደሆኑ አድርገው ቆጥረዋቸው ነበር።
ከጦርነቱ በኋላ እህቴ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ቀጠለች። በ1998 እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ ከሁለተኛ ባልዋ ከሃንስ ፎርስተር ጋር በስዊስ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ አገልግላለች። ፊኒም የወላጆቿን አርአያ የተከተለች ሲሆን በአሁኑ ጊዜ እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን በስዊዘርላንድ በማገልገል ላይ ትገኛለች።
በመጨረሻ ነጻነት አገኘን!
በ1945 መጀመሪያ አካባቢ በቦምብ ከተደበደቡት ሕንጻዎች መካከል እኛ የታሰርንበት በሙኒክ የሚገኘው ወኅኒ ቤትም ይገኝበታል። ከተማይቱ በሙሉ የፍርስራሽ ክምር ሆና ነበር። ፍርድ ቤት ቀርቤ ጉዳዬ ከመታየቱ በፊት ለ18 ወራት ያህል ታስሬ ነበር። ጦርነቱ ሊጠናቀቅ ሁለት ሳምንት ብቻ ሲቀረው ማለትም ግንቦት 8, 1945 ፍርድ ቤት ቀረብኩ። ፍርድ ቤቱም “ወታደር ሆነህ ለማገልገል ፈቃደኛ ነህ?” የሚል ጥያቄ አቀረበልኝ።
“እስረኞች እኮ የወታደር ልብስ መልበስም ሆነ ‘ሄይል ሂትለር’ ማለት አይፈቀድላቸውም” በማለት መለስኩ። በጀርመን ሠራዊት ውስጥ ለማገልገል ፈቃደኛ መሆኔን ሲጠይቁኝ “ለውትድርና የምመለመልበትን ወረቀት ስጡኝና ውሳኔዬን አሳውቃችኋለሁ!” አልኳቸው።
ከጥቂት ቀናት በኋላ ጦርነቱ አበቃና ነጻ ነህ ተብዬ ተለቀቅሁ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ 35 የሚያህሉ ምሥክሮችን ያቀፈ አንድ ትንሽ ጉባኤ ወደሚገኝበት ወደ ግራዝ ተዛወርኩ። አሁን በዚያ አካባቢ ስምንት ጉባኤዎች ይገኛሉ።
አፍቃሪ ረዳት
ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሄሌነ ዱንሰት ከምትባል የናዚ ፓርቲ አባል የነበረች አንዲት ወጣት አስተማሪ ጋር ተገናኘን። የናዚን ሥርዓት እንደጠበቀችው ሆኖ ባለማግኘቷ ወሽመጧ ቁርጥ ብሎ ነበር። በመጀመሪያ ቀን ውይይታችን “የአምላክ ስም ይሖዋ መሆኑን እናንተ የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ እንዴት ልታውቁ ቻላችሁ?” በማለት ጠየቀችኝ።
“ምክንያቱም ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን አይመረምሩም” ብዬ መለስኩላትና የአምላክን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳየኋት።
“የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገር ከሆነ ይህን ሐቅ ለሰዎች ሁሉ ማሳወቅ አለብን!” አለች። ሄሌነ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሰዎች መስበክ ጀመረችና ከአንድ ዓመት በኋላ ራሷን ለይሖዋ ወስና ተጠመቀች። ሰኔ 5, 1948 ተጋባን።
ሚያዝያ 1, 1953 የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆንን። ከጊዜ በኋላ በኒው ዮርክ ግዛት በሳውዝ ላንሲንግ በሚገኘው የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በ31ኛው ክፍል እንድንሰለጥን ተጋበዝን። በዚያ ከ64 አገሮች ከመጡ ሌሎች ተማሪዎች ጋር በጣም አስደሳች ጊዜ ማሳለፍ ችለናል።
ከምረቃችን በኋላ በዚያው በኦስትሪያ እንድናገለግል ተመደብን። ለጥቂት ዓመታት ሥራችን ጉባኤዎችን እየጎበኙ በመንፈሳዊ ማበረታታት ነበር። ከዚያም በሉክሰምበርግ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እንድናገለግል ተጋበዝን። ከጊዜ በኋላ በኦስትሪያ፣ ቪየና በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ እንድናገለግል ጥያቄ ቀረበልን። በ1972 በዚያ እያገለገልን በቪየና ለሚኖሩ ከዩጎዝላቪያ ለፈለሱ ሠራተኞች ምሥራቹን መስበክ እንድንችል የሰርቦ-ክሮኤሺያን ቋንቋ መማር ጀመርን። በአሁኑ ወቅት በቪየና ከሁሉም የአውሮፓ ክፍሎች የመጡ ሰዎችን ያቀፉ ስምንት በሰርቦ-ክሮኤሺያ ቋንቋ የሚመሩ ጉባኤዎች አሉ።
ነሐሴ 27, 2001 ውዷ ሄሌነ በሞት ተለየችኝ። በ53 ዓመት የትዳር ሕይወታችን ወቅት እምነት የሚጣልባትና ውድ ረዳት ሆናልኝ ነበር። አሁን የትንሣኤን ተስፋ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በጉጉት እጠባበቃለሁ።
በአምላክ ፍቅር ረክቶ መኖር
ብዙ አሳዛኝ ገጠመኞች የደረሱብኝ ቢሆንም በኦስትሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በማከናውነው ሥራ ትልቅ እርካታ አገኛለሁ። በቅርቡ “በታሪክ የተረሱ የናዚ አገዛዝ ሰለባዎች” በተባለው ኤግዚቢሽን ላይ በግል የደረሰብኝን መከራ የመተረክ ልዩ መብት አግኝቼ ነበር። ከ1997 ጀምሮ ኤግዚቢሽኑ 70 በሚያህሉ የኦስትሪያ ከተሞችና መንደሮች ውስጥ የታየ ሲሆን ከናዚ ወኅኒ ቤቶችና ማጎሪያ ካምፖች በሕይወት የተረፉ የዓይን ምሥክሮች፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች በናዚ ስደት ወቅት የነበራቸውን እምነትና ድፍረት የሚናገሩበት አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል።
እንደነዚህ ያሉ ታማኝ ምሥክሮችን በግል ማወቄ ትልቅ መብት እንደሆነ ይሰማኛል። እነዚህ ምሥክሮች በሮሜ 8:38, 39 ላይ ያሉት “ሞት ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ ግዛትም ቢሆን፣ ያለውም ቢሆን፣ የሚመጣውም ቢሆን፣ ኃይላትም ቢሆኑ፣ ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ” የሚሉት ቃላት ያላቸውን እውነተኝነት በማያሻማ ሁኔታ ያረጋግጣሉ።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቤተሰባችን በ1930 (ከግራ ወደ ቀኝ ):- እኔ፣ ፒፔ፣ አባባ፣ ቪሊ፣ እናቴና ቪንኮ
በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወንድሜ ቪሊ ከመገደሉ ከጥቂት ጊዜ በፊት
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እኔና ቪንኮ በሙኒክ በሚገኘው የሽታደልሃይም ወኅኒ ቤት የተወሰነ ጊዜ አብረን አሳልፈናል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቪንኮ ልጅ ፊኒ ጨካኝ በሆነ የናዚ ቤተሰብ ውስጥ እንድታድግ ተደርጎ ነበር፤ እስካሁን ድረስ ታማኝነቷን ጠብቃለች
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሄሌነ ባሳለፍናቸው 53 የትዳር ዓመታት ውድ አጋር ሆናልኛለች
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“በታሪክ የተረሱ የናዚ አገዛዝ ሰለባዎች” በተሰኘው ኤግዚቢሽን ላይ ንግግር ሳቀርብ