በአደጋ ጊዜ ፍቅር ማሳየት
በአደጋ ጊዜ ፍቅር ማሳየት
ናይጄሪያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
እሁድ ጥር 27, 2002 በናይጄሪያ፣ ሌጎስ የሚታወሰው መዓተኛው እሁድ በመባል ነው። በዚያን ዕለት ከመሬት በታች የተሠራ የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት ሲፈነዳ ከተማዋ ተናወጠች። የፍንዳታው ብልጭታ የምሽቱን ሰማይ ወገግ አደረገው። ለሰዓታት የቀጠሉት ተከታታይ ፍንዳታዎች እስከ 3 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ የፈንጂ ፍንጥርጣሪዎችንና ፍርስራሾችን ሲያዘንቡ ከተማይቱ በሽብር ተዋጠች።
ወዲያው የተናፈሰው ያልተረጋገጠ ወሬ ሕዝቡን በፍርሃት አራደው። ከምን እንደሚሸሹም ሆነ ወዴት እንደሚሄዱ የማያውቁ በድንጋጤ የተዋጡ ሰዎች ጎዳናውን አጥለቀለቁት። በፍርሃት የሚገቡበት የጠፋቸውን ትንንሽ ልጆችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲሸሹ ጨለማ በዋጠው የውኃ ቦይ ውስጥ ገብተው ሰጠሙ። መኖሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶችና መሥሪያ ቤቶች በመውደማቸው ወይም በጣም በመጎዳታቸው የተነሳ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤታቸውንና ሥራቸውን አጥተዋል። በዚህ አሳዛኝ ገጠመኝ በግምት 1, 000 የሚያህሉ ሰዎች የሞቱ ሲሆን ከጊዜ በኋላ የወጡ ግምቶች ደግሞ የሟቾቹ ቁጥር ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ይጠቁማሉ።
ከጊዜ በኋላ ፍንዳታው በተከሰተበት ወታደራዊ ተቋም ዙሪያ በነበረው የመኖሪያ ሠፈር የወዳደቁ 1, 350 የሚያህሉ ያልፈነዱ ቦምቦች፣ ሮኬቶችና የእጅ ቦምቦች ተሰብስበዋል። አንድ ሰው ሳሎኑ ውስጥ አንድ ብረት አገኘ። ቦምብ መሆኑን ስላላወቀ በመኪናው የእቃ መጫኛ ውስጥ ከከተተው በኋላ ወስዶ ለፖሊሶች አስረክቧል።
ናይጄሪያ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የአደጋው ዜና እንደደረሰው ወዲያውኑ በሌጎስ ከሚገኝ አንድ ሽማግሌ ጋር ተገናኘና በአካባቢው ያሉት 16 ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሌጎስ የሚኖሩት 36, 000 ምሥክሮች የሚገኙበትን ሁኔታ እንዲያጣሩ ተነገራቸው። ቅርንጫፍ ቢሮው አንድ ሚልዮን ኒያራ (10, 000 የአሜሪካ ዶላር ገደማ ይሆናል) ላከና የእርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚቴ እንዲቋቋም መመሪያ አስተላለፈ።
በአካባቢው ከነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አንድ ወንድም በፈንጂ ፍንጣሪ ከባድ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን የሚያሳዝነው ሁለት ወጣት እህቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል። እንዲሁም ሁለት የመንግሥት አዳራሾችና የ45 ቤተሰቦች መኖሪያ ቤቶች እንዳልነበሩ ሆነዋል።
የመሣሪያው ግምጃ ቤት ከፈነዳ ከስድስት ቀናት በኋላ ማለትም የካቲት 2, 2002 በሌላ የከተማይቱ ክፍል የጎሳ ግጭት ተቀሰቀሰ። በቀይ መስቀል ዘገባ መሠረት በግጭቱ 100 የሚያህሉ ሰዎች ሲሞቱ 430 የሚያህሉ ቆስለዋል፤ 3, 000 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፤ እንዲሁም 50 ቤቶች በእሳት ተቃጥለዋል። “በመዓተኛው እሁድ” ዕለት በደረሰው ችግር የተጠቁትን ሰዎች ሲንከባከብ የነበረው የእርዳታ ኮሚቴ ወዲያውኑ የጎሳ ግጭቱ በተካሄደበት አካባቢ የሚኖሩትን ክርስቲያን ወንድሞች ማፈላለግ ጀመረ።
ግጭቱ በተቀሰቀሰበት ወቅት አብዛኞቹ የወረዳ ስብሰባ ለመካፈል ወደ ሌላ ቦታ ሄደው ስለነበር ከምሥክሮቹ መካከል ማንም አልሞተም። ይሁን እንጂ በአካባቢው ካሉት አምስት ጉባኤዎች አባላት ውስጥ አብዛኞቹ ተመልሰው የሚገቡበት ቤት አልነበራቸውም። ቢሆንም ክርስቲያን ወንድሞቻቸው ወዲያውኑ መጠለያ ሰጧቸው። የይሖዋ ምሥክር የሆነ አንድ ሐኪምና ሚስቱ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ 27 ሰዎችን ተቀብለው በቤታቸው አስጠልለዋል።
በፍንዳታውም ሆነ በጎሳ ግጭቱ ያልተጎዱት በሌጎስ የሚገኙ ምሥክሮች ምግብ፣ ልብስና የቤት ቁሳቁሶችን በልግስና ሰጡ። የከተማው የበላይ ተመልካች እንዲህ ሲል ሪፖርት አድርጓል:- “በሌጎስ የሚኖሩት ወንድሞች ያሰባሰቡት እርዳታ በአደጋው ለተጠቁት ምሥክሮች ከሚያስፈልገው በላይ ነበር።” ጉባኤዎች ተጨማሪ መዋጮ ማድረጋቸውን እንዲያቆሙ ለማድረግ ቅርንጫፍ ቢሮው ደብዳቤ መጻፍ አስፈልጎት ነበር። ሦስት የጭነት መኪና ሙሉ የተረፉ የእርዳታ ቁሳቁሶች በመጋዘን ውስጥ እንዲቀመጡ ለቅርንጫፍ ቢሮው ተላኩ።
የጉባኤ ሽማግሌዎች አብዛኞቹን የአደጋው ተጠቂዎችና የሟቾቹን ምሥክሮች የቤተሰብ አባላት በመጎብኘት ቅዱስ ጽሑፋዊ ማበረታቻ ሰጥተዋል። የእርዳታ ኮሚቴው ሰዎችን በማስተባበር ጉዳት የደረሰባቸው ቤቶች እንዲጠገኑ አድርጓል። በፍንዳታውም ሆነ በጎሳ ግጭቱ ለተጎዱት ሰዎች የቤት ቁሳቁሶች፣ አልባሳትና ምግቦችን ያከፋፈለ ሲሆን ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉትንም መጠለያ እንዲያገኙ በማድረግ ረድቷል። በድምሩ 90 የሚያህሉ ቤተሰቦችና ግለሰቦች በኮሚቴው እርዳታ ተደርጎላቸዋል።
በርካታ የአደጋው ተጠቂዎች በተደረገላቸው እርዳታ በጣም ተነክተዋል። አንድ ምሥክር ለእርዳታ ኮሚቴው እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “በሕይወት እስካለሁ ድረስ ይሖዋን ‘መጠጊያዬና ኃይሌ’ አደርገዋለሁ!”—መዝሙር 46:1, 2
በእነዚህ አደጋዎች ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች እንዴት እርስ በእርስ ይረዳዱ እንደነበር ምሥክር ያልሆኑ ሰዎችም አስተውለዋል። በአደጋው ሕይወቷን ያጣችው ምሥክር አጎት ለነበረችበት ጉባኤ ሽማግሌዎች “ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን ለመግለጽና ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት ተመልሼ እመጣለሁ” ብሏቸዋል። ለቤተሰቡም “ምሥክሮቹ በሌጎስ ያደረጉት በእርግጥም ተአምር ነበር። የስጋ ዘመዳሞች እንኳን እንደ እነሱ አላደረጉም” ብሏቸዋል።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የእርዳታ ቁሳቁሶችን የያዘ የጭነት መኪና
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እርዳታ ከተደረገላቸው መካከል አንዳንዶቹ
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እነዚህ ባልና ሚስት ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ 27 ሰዎችን በቤታቸው አስጠልለዋል
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ምሥክሮቹ በአደጋው የተጎዳ ቤት ሲጠግኑ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የሥዕሎቹ ምንጮች]
ከላይ:- Sam Olusegun - The Guardian