ታላቁ ፍልሰት
ታላቁ ፍልሰት
ኬንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
ምድሪቱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ኮቴዎች እየጎደፈሩ በሚያሰሙት ድምፅ ተናውጣለች። የእንስሳቱ ጭፍራ ወደፊት ሲተምም ቀይ የአቧራ ደመና እየተግተለተለ ወደ ላይ ይወጣል። በቀጫጭን እግሮቻቸው እየጋለቡ ሸለቆዎችን፣ ኮረብቶችንና ለጥ ያሉ ሜዳዎችን፣ ወንዞችንና ጅረቶችን ያቋርጣሉ። እንደ ማዕበል በሚያልፉበት ቦታ ሁሉ ከሥራቸው ያለውን ሣር ከሥሩ ነቃቅለው ይጥላሉ። እነዚህ የሚያናፉና ተራጋጭ የሆኑ ፍጥረታት በጣም ያማረና ታይቶ የማይጠገብ ትርዒት ያሳያሉ። ይህ አስደናቂ ትርዒት የቶራ ፈረሶች (wildebeests) ታላቅ ፍልሰት ነው።
የአፍሪካ ኤደን ገነት
ሰሬንጌቲ ጠፍ የሆነ ምድር ነው። በታንዛንያና በኬንያ መካከል የሚገኘው ይህ ምድር 30, 000 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት የሚሸፍን የግጦሽ መሬት ነው። መሬቱ ከእሳተ ገሞራ በወጣ ለም አፈር የተሸፈነ በመሆኑ መሬቱን እንደ ምንጣፍ ለሸፈነው ሣር እድገት በጣም ምቹ ሆኗል። ለዝሆኖች ቀለብ የሚሆኑ የግራርና ሌሎች እሾሃማ ዛፎች በብዛት አሉ። የቀጭኔ መንጋዎች በረዥም ቅልጥማቸው ረጋ ብለው በታላቅ ግርማ ይንቀሳቀሳሉ።
በአንዳንድ አካባቢዎች በነፋስና በዝናብ ታጥበው የተወለወሉ ጥቁር አለቶች ለጥ ባለው ሜዳ ላይ ጉብ ጉብ ብለው ይታያሉ። አንበሶችና ነብሮች በእነዚህ ጉብታዎች ላይ ወጥተው አካባቢያቸውን ይቃኛሉ። እየተጠማዘዙ በሚፈሱት ፈጣን ጅረቶች
ውስጥ በርካታ ጉማሬዎችና አዞዎች ይተራመሳሉ። በመስኩ ላይ ደግሞ ቶራ ፈረሶች፣ ቆርኬዎች፣ ሳላዎችና ሌሎች የፍየል ዝርያ ያላቸው መንጎች ሣር ሲግጡ ይታያሉ። ውኃ የተጠሙ የሜዳ አህያዎች ኩሬዎችን እንደቀለበት ከብበው ውኃ ይጠጣሉ። የሜዳ ፍየሎችና ድኩላዎች ያለ ብዙ ችግር እመር ብለው እየዘለሉ ሜዳውን ያቋርጣሉ። ትላልቅ ጎባጣ ቀንዶችና ግዙፍ ቁመና ያላቸው በርካታ ጎሾች በሠፊው አፋቸው ሣሩን በእርጋታ ይግጣሉ።በሰሬንጌቲ በርካታ የአንበሳ መንጎችም ይታያሉ። የቀኑ ትኩሳት በሚያይልበት ጊዜ በዛፎችና በቁጥቋጦች ጥላ ውስጥ ተኝተው ለአደን የሚሰማሩበትን የቀኑን መምሸት ይጠባበቃሉ። ነብሮች ዛፎች ላይ ይወጡና ቅጠሎች በሚፈጥሩት ጥላ ተሸሽገው ይተኛሉ። ለጥ ያለው ሜዳ ለአቦ ሸማኔዎች እንደልባቸው ሮጠው ለማደን ያመቻል። የሚያድኑትን እንስሳ ለመያዝ በሚሮጡበት ጊዜ ቀጭን አካላቸው በረዥሙ ሣር ይደበቃል።
በእርግጥም በሰሬንጌቲ የሚታየው የእንስሳት ሕይወት በጣም ውብና የሚያስደንቅ ነው። ይሁን እንጂ በዚህ የእንስሳት ዓለም የቶራ ፈረሶችን ያህል የሚያምር ትርዒት አይታይም።
የዱሩ አስቂኝ ተዋናይ
በሰሬንጌቲ ውስጥ 1.5 ሚልዮን የሚደርሱ ቶራ ፈረሶች እንደሚኖሩ ይገመታል። ቶራ ፈረስ ያልተለመደ ዓይነት መልክ ያለው ፍጥረት ነው። ራሱ ረዥም ሲሆን፣ ዓይኖቹ የሚያብረቀርቁና ጭንቅላቱ ላይ ተራርቀውና ከፍ ብለው የሚገኙ ናቸው። ቀንዶቹ ከላም ቀንድ ጋር የሚመሳሰሉ ሆነው ወደታች ከጎበጡ በኋላ እንደገና ወደ ላይ ያቀናሉ። ጀርባው ወደታች ያቆለቆለ ሲሆን በጣም ጠንካራና ግዙፍ ከሆኑት አንገቱና ትከሻው ጋር ሲወዳደር ከሲታና ደካማ ይመስላል። ግዙፍ የሆነውን አካሉን የሚሸከሙት እግሮች ቀጫጭኖች ናቸው። ከአገጩ በታች ነጭ ጺም፣ ማጅራቱ ላይ ጥቁር ጎፈር እንዲሁም ከፈረስ ጋር የሚመሳሰል ጭራ ያለው ቶራ ፈረስ የተለያዩ እንስሳትን የሚመስል ቁመና አለው።
የቶራ ፈረሶች ባሕርይ አብዛኛውን ጊዜ የሚያስቅ ነው። በዛ ብለው በሚሰበሰቡበት ጊዜ በሺህ የሚቆጠሩ እንቁራሪቶች የሚያሰሙትን ዓይነት ጩኸት ያሰማሉ። ለጥ ባለው ሜዳ ላይ ቀጥ ብለው በሚቆሙበት ጊዜ አካባቢያቸውን በመገረምና በመደነቅ የሚመለከቱ ይመስላሉ።
አንዳንድ ጊዜ የቶራ ፈረስ ኮርማ ከመንጋው ነጠል ብሎ ሶምሶማ እየጋለበ ክብ ሲዞር ይታያል። አናቱን ወደታች ይደፋና በኋላ እግሮቹ እንጣጥ ብሎ እየዘለለ በሚያስቅ ሁኔታ አቧራ ያቦናል። እንዲህ የሚያደርገው እንስቶችን ለመማረክ ወይም ጉልበተኛነቱን ለሌሎች ተባዕቶች ለማሳየት ነው የሚሉ አሉ።
ሆኖም ኮርማው መጫወት ስለፈለገ ብቻ የሚቦርቅበት ጊዜ ይኖራል።ጠላት በበዛበት ዓለም ውስጥ መወለድ
ተስማሚው ጊዜ ሲደርስ ቶራ ፈረሶች መውለድ ይጀምራሉ። ብዙዎቹ የሚወልዱት በተመሳሳይ ወቅቶች መሆኑ የመውለጃ ጊዜያቸው አንድ ዓይነት ይመስላል። ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆኑት ጥጆቻቸውን የሚወልዱት በሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ነው። በዚህ ጊዜ የቶራ ፈረሶች መንጋ በግልገሎች ጩኸት ይሞላል። እናቶቹ ቶሎ ብለው ከግልገሎቻቸው ጋር መቆራኘት ይኖርባቸዋል። አለበለዚያ መንጋው በርግጎ በሚሸሽበት ጊዜ እናቲቱ ከግልገልዋ ልትነጠልና ግልገሊቱ በቀላሉ ልትሞት ትችላለች።
ግልገሎቹን በዓይነ ቁራኛ የሚከታተሉና የሚተናኮሉ በጣም ብዙ አዳኞች አሉ። እንስቶቹ ምንም የሚያሰጋ ነገር አለመኖሩን ካጣሩ በኋላ ግልገሎቻቸውን ይወልዳሉ። አዳኝ አውሬ ካስደነገጣቸው ግን የመውለዱን ሂደት አቋርጠው የመሸሽ ድንቅ ችሎታ አላቸው። አደገኛው ሁኔታ ካለፈ በኋላ ተረጋግተው ልጃቸውን ይገላገላሉ።
ግልገሉም ቢሆን የመጣበት ዓለም አደገኛ መሆኑን የሚገነዘብ ይመስላል። በተወለደ ጥቂት ደቂቃ ውስጥ ቀጥ ብሎ መቆም ይችላል። ከአንድ ሳምንት ጊዜ በኋላ በሰዓት 50 ኪሎ ሜትር በሚደርስ ፍጥነት ሜዳውን ማቋረጥ ይችላል።
ጉዞ የማድረግ ጊዜ ሲደርስ
ቶራ ፈረሶች በሰሬንጌቲ የሚጓዙት አንድ ላይ ሆነው ነው። የሚጓዙበት ዋነኛ ምክንያት ዝናብ ፍለጋ ነው። የዝናቡ አመጣጥ ዓመታዊ ኡደት ባለው በአየሩ ጠባይ ላይ የተመካ ነው። በዚህ ሰፊ የሣር ምድር ክልል ውስጥ በማንኛውም የዓመቱ ክፍል ዝናብ የሚዘንብበት ቦታ መኖሩ አይቀርም።
ቶራ ፈረሶች በየቀኑ የሚጠጡት ውኃና የሚመገቡት ግጦሽ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። ምግብና ውኃ ካላጡ በስተቀር ካሉበት አካባቢ አይሄዱም። ይሁን እንጂ የበጋው ጊዜ እየገፋ ሲሄድ የሜዳው ግጦሽ መመናመንና የውኃ ምንጮችም መድረቅ ይጀምራሉ። የቶራ ፈረሶቹ መንጋዎች አንድ ቦታ ቁጭ ብለው የዝናቡን መምጣት አይጠባበቁም። ዝናቡን መከተል ይኖርባቸዋል።
ዝናብ በሚጥልበት አካባቢ ደረቁ ሜዳ ወዲያው መለወጥ ይጀምራል። በጥቂት ቀናት ውስጥ ትናንሽ የሣር ቡቃያዎች ማቆጥቆጥ ይጀምሩና ሜዳው በለምለም ሣር ይሸፈናል። ገና
ያልጠነከረው ይህ የሣር ቡቃያ እርጥብና በንጥረ ምግቦች የተሞላ ነው። ይህም ቶራ ፈረሶች አጥብቀው የሚፈልጉት ነገር ነው።እነዚህ ፍጥረታት በጣም ሩቅ ሆነው እንኳን ዝናብ የሚጥልበትን ቦታ በትክክል የማወቅ ችሎታ አላቸው። በሌላው የሰሬንጌቲ ክፍል ዝናብ እንደሚጥል የሚያውቁት እንዴት እንደሆነ በትክክል የሚያውቅ ሰው የለም። የመብረቅ ብልጭታዎችን በመመልከት ይሁን የሚነፍሰውን እርጥበት አዘል አየር በማሽተት የሚታወቅ ነገር የለም። ያም ሆነ ይህ መንጋዎቹ በሕይወት ለመቆየት ከፈለጉ መጓዝ ይኖርባቸዋል። በእርግጥም ተጓዦች ናቸው!
አደገኛ የሆነ ጉዞ
ጉዞው በሚጀምርበት ጊዜ እንቅስቃሴው ዝግ ያለ ነው። ቶራ ፈረሶች መነጣጠል የማይወዱ እንስሳት ናቸው። አንድ እንስሳ ወደ አንድ አቅጣጫ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ሌሎቹ ሣር መጋጣቸውን ይተዉና ሊከተሉት ይሞክራሉ። ወዲያው መንጋው በሙሉ መንቀሳቀስ ይጀምርና አስደናቂ የሆነ ፍልሰት ይጀመራል። በረሐብና በጥማት እየተገፉ ወደፊት መጓዝ ይጀምራሉ። አንዳንድ ጊዜ ይሮጣሉ። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ተከታትለው በመሄድ ረዥም ቀጭን መሥመር ይፈጥራሉ።
ጉዟቸው ለአደጋ የተጋለጠ ነው። አዳኝ አራዊት ከመንጋው ኋላ እየሄዱ ደከም ያለ፣ የሚያነክስ ወይም የታመመ እንስሳ በዓይነ ቁራኛ ይከታተላሉ። ቶራ ፈረሶች በሚጓዙበት ጊዜ አንበሶች አድፍጠው በሚጠባበቁበት ክልል ውስጥ ይገባሉ። ሣር ውስጥ አድፍጠው የሚጠባበቁት አንበሶች ሣር በሚግጡት መንጋዎች መካከል ዘልለው በመግባት ያስበረግጓቸዋል። ነብሮች፣ አቦ ሸማኔዎች፣ ተኩላዎች፣ የበረሃ ውሾችና ጅቦች ሁሉ ወደኋላ የቀሩ ወይም ከመንጋው ተነጥለው የወጡ እንስሳትን ለማነቅ ይከታተላሉ። አንድ እንስሳ ከተገደለ ጥንብ አንሳዎች ከተፍ ይላሉ። በወዳደቀው ሥጋና አጥንት ሲጣሉና ሲሻኮቱ ከቆዩ በኋላ ነጭ አጥንት ብቻ አስቀርተው ይሄዳሉ።
ፈጣን ጅረቶች ለመንጋዎቹ አስቸጋሪ የጉዞ እንቅፋት ይሆኑባቸዋል። በሺህ የሚቆጠሩ እንስሳት ከወንዝ ዳርቻዎች ቁልቁል እየወረዱ ወንዝ ሲያቋርጡ ማየት በጣም አስደናቂ ነው። ብዙዎቹ አለምንም አደጋ መሻገር ይችላሉ። ሌሎች ደግሞ በውኃ ሙላት ይወሰዳሉ ወይም ወንዙ ውስጥ አድፍጠው በሚጠባበቁ አዞዎች ይበላሉ። ይህ አደገኛ ጉዞ በየዓመቱ ይደረጋል። ጉዞው ሲጠቃለል የተጓዙት ርቀት እስከ 3, 000 ኪሎ ሜትር ሊደርስ ይችላል።
ከሁሉ የሚከፋው አዳኝ ሰው ነው
የሰው ልጅ ለብዙ ሺህ ዓመታት በቶራ ፈረሶች ፍልሰት ላይ ያስከተለው ችግር አልነበረም። ባሁኑ ጊዜ ግን ትልቁን ስጋት የፈጠረው ሰው ነው። ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ የታንዛንያና የኬንያ መንግሥታት የሰሬንጌቲን እንስሳት ከአደጋ ለመጠበቅ ጥረት አድርገዋል። የቶራ ፈረሶች ፍልሰት የሚካሄደው በአብዛኛው ለዱር አራዊት በተጠበቀ ክልል ውስጥ ቢሆንም እንኳ በሺህ የሚቆጠሩ እንስሳት በሕገ ወጥ አዳኞች ይገደላሉ። እነዚህ አዳኞች በሽቦ ወጥመዶች፣ በመርዛማ ቀስቶችና በጠመንጃዎች እየተጠቀሙ እንስሳቱን በማደን ሥጋቸውንና በቅርስነት የሚያገለግሉ የአካል ክፍሎቻቸውን ይሸጣሉ። በጥብቅ ክልሉ ውስጥ የተሰማሩ በርካታ ጠባቂዎችና ዘበኞች ቢኖሩም ሰሬንጌቲ በጣም ሠፊ ክልል በመሆኑ ሙሉ በሙሉ መጠበቅ አልተቻለም። የነዋሪዎች ቁጥር እየጨመረ በመሄዱም ለም የሆነውን ይህን መሬት የሚፈልጉ ሰዎች ወደ ክልሉ ዘልቀው መግባታቸው አልቀረም። በጣም ሠፊ የሆነ መሬት ለእንስሳት ብቻ ከልሎ መስጠት መራራ ክርክር የሚደረግበት ጉዳይ ሆኗል።
በአንድ ወቅት በሰሜን አሜሪካ ሜዳዎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ጎሾች ይሰማሩ ነበር። አሁን ግን ጠፍተዋል። ምሥራቅ አፍሪካ በሚገኙ ቶራ ፈረሶችም ላይ ይኸው ዕጣ ይደርሳል ብለው የሚሰጉ አሉ። ይህን የመሰለው አስደናቂ የተፈጥሮ ትርዒት ቢጠፋ በእርግጥም በጣም የሚያሳዝን ነገር ይሆናል። ሰዎችና እንስሳት በአምላክ የጽድቅ አገዛዝ ውስጥ ፍጹም በሆነ ስምምነት የሚኖሩበትን ጊዜ በናፍቆት እንጠብቃለን። (ኢሳይያስ 11:6-9) እስከዚያ ጊዜ ግን በዚህ አስደናቂ የቶራ ፈረሶች ታላቅ ፍልሰት እየተደነቅን እንቆያለን።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መንጋዎቹ ፈጣን ጅረቶችን ማቋረጥ ይኖርባቸዋል