‘ከሰው ይልቅ ለአምላክ ልንታዘዝ ይገባል’
‘ከሰው ይልቅ ለአምላክ ልንታዘዝ ይገባል’
አዳም በ17 ዓመቱ የዩ ኤስ ሆሎኮስት ቤተ መዘክር ባዘጋጀው አንድ ውድድር ላይ ካሸነፉት ሦስት ተወዳዳሪዎች አንዱ ነበር። በጠቅላላው ወደ 500 የሚጠጉት ተወዳዳሪዎች ለውድድር ያቀረቡት በናዚ የጭቆና ቀንበር ስር የታየውን ጽናት የሚያሳይ የሥነ ጥበብ ወይም የሥነ ጽሑፍ ሥራ ነበር። የይሖዋ ምሥክር የሆነው አዳም በናዚ አገዛዝ ወቅት የእምነቱ አባላት የደረሰባቸውን መከራ የሚያሳይ የሥነ ጥበብ ውጤት ለውድድሩ ለማቅረብ ወሰነ። እንደ አዳም አባባል የሥነ ጥበብ ሥራው የሚያንጸባርቀው ሽንፈትን ወይም ሐዘንን ሳይሆን የይሖዋ ምሥክሮች በጨካኙ የናዚ አገዛዝ ሥር የደረሰባቸውን ግፍና መከራ በድል መወጣታቸው ያስገኘውን ደስታ ነው። በስዕሉ ላይ የአንዲት ልጅ ምስል ይታያል። ለምን? “ትናንሽ ልጆችም ጭምር የናዚን ስደት በጽናት እንደተወጡ ለማሳየት ነው” በማለት ተናግሯል።
በናዚ አገዛዝ ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች ሂትለርን የሚያወድሱ መፈክሮችን ለማለትም ሆነ ለፖለቲካ ፓርቲው ድጋፍ ለመስጠት ፈቃደኞች እንዳልነበሩ በስፋት የሚታወቅ ነው። አዳም ለውድድር ባቀረበው ሥራው ላይ ከላይ በስተቀኝ በኩል ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ጥቅምት 7, 1934 ለጀርመን ባለ ስልጣናት የላኩትን ደብዳቤ ጠቅሶ ያሰፈረው ሐሳብ ይህን አቋማቸውን ይገልጻል። ደብዳቤው በከፊል እንዲህ ይላል:- “የእርስዎ ሕግ ከአምላክ ሕግ ጋር በቀጥታ ይጋጫል፤ ስለዚህ የታማኝ ሐዋርያትን አርዓያ በመከተል ‘ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር መታዘዝ ይገባናል’፤ ይህን ለማድረግም ቆርጠናል። (ሥራ 5:29) . . . መንግሥትዎና ባለ ስልጣናትዎ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ሕግ እንድንጥስ ማስገደዳቸውን ስለገፉበት በእርሱ እርዳታ ይሖዋ አምላክን እንደምንታዘዝና ከማንኛውም ዓይነት ጭቆናና ከየትኛውም ጨቋኝ እንደሚታደገን በሰጠን ተስፋ ላይ እንደምንታመን ልናሳውቅዎ እንወዳለን።”
አዳም ይህንን የመሰለ መንፈሳዊ ውርሻ በማግኘቱ ይኮራል። “የይሖዋ ምሥክሮች ሌሎች ሰዎችን መጉዳት እንደሌለባቸው አጥብቀው የሚያምኑ ሲሆን ከፊታቸው የሚጠብቃቸው ቅጣት ሞት እንኳን ቢሆን ከአምላክ ሌላ ማንንም አያመልኩም” በማለት ይናገራል። የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸው ጠንካራ አቋም አዳም ለሥነ ጥበብ ሥራው በሰጠው “ከሰዎች ይልቅ ለአምላክ እንታዘዛለን!” የሚል ርዕስ በግልጽ ተንጸባርቋል።