ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
ጨዋነት እየጠፋ መጥቷል
“ጃፓናውያን ጨዋነት እያጡና መልካም ጠባይ እየራቃቸው መጥቷል።” ይህ ዘ ዮምዩሪ ሺምቡን የተባለው ጋዜጣ 2 000 ለሚያክሉ ሰዎች ጥያቄ አቅርቦ 90 ከመቶ የሚሆኑት የሰጡት ምላሽ ነው። ይህን ያህል እንዲበሳጩ ያደረጋቸው ምንድን ነው? 68 ከመቶ የሚሆኑትን ያናደዳቸው “ብዙዎች የሲጋራ ቁራጮችን፣ ማስቲካዎችንና የመጠጥ ቆርቆሮዎችን ተገቢ በሆነ መንገድ አለማስወገዳቸው ነው።” ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ወላጆች ደግሞ ረባሽ ልጆቻቸውን ለመቆጣጠር አለመቻላቸው አሳዝኗቸዋል። ሌሎችን ያስመረረው ደግሞ ብዙ ሰው በሚገኝባቸው ቦታዎች ተንቀሳቃሽ ስልኮችን መጠቀም፣ የቤት እንስሳት የሚጥሉትን ኩስ አለማስወገድ እንዲሁም መኪናዎችንና ብስክሌቶችን አላግባብ ማቆም ነው። በዚህ ረገድ በይበልጥ የሚወቀሱት ወጣቶች ናቸው። “ከ20 እስከ 40 ዓመት የዕድሜ ክልል ከሚገኙ ተጠያቂዎች መካከል 66 በመቶ የሚሆኑት የመካከለኛና የከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጠባይ በጣም አሳስቧቸዋል።”
“አድመኝነት” በሥራ ቦታ
በስፔይን የሥራ ሰዓት የሚባክንበት ዋነኛ ምክንያት “ሥነ ልቦናዊ ጥቃት” እንደሆነ ኤል ፓይስ ሰማናል የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። ከሁለት ሚልዮን የሚበልጡ ስፔናውያን በሥራ ቦታቸው ብዙ ብሽቀትና ጥቃት ይደርስባቸዋል። የሥነ ልቦና ሊቅ የሆኑት ኢኛኪ ፒኝወል አብዛኛውን ጊዜ ለብሽቀትና ለሥነ ልቦና ጥቃት የሚጋለጡት የሥራ ባልደረቦቻቸው የሚቀኑባቸው ጎበዝ ሠራተኞች ናቸው። የሥራ ባልደረቦች አንድን ሠራተኛ የተመደበለትን ሥራ እንዳያገኝ በማድረግ፣ በማኩረፍ፣ አይተው እንዳላዩ ሆነው በማለፍ፣ ሁልጊዜ በመተቸት ወይም ክብሩን የሚነካ ሐሜት እንዲስፋፋ በማድረግ ለማብሸቅና ለማዋረድ ይሞክራሉ። “በአውሮፓ ራሳቸውን ከሚገድሉ አምስት ሰዎች መካከል አንዱ ራሱን የሚገድለው በዚሁ ምክንያት” እንደሆነ ዘገባው ይገልጻል። ታዲያ ምን ማድረግ ይቻላል? መጽሔቱ የሚከተለውን ምክር ይሰጣል:- “ምሥጢር አድርጋችሁ አትያዙት። ምሥክር ፈልጉ። ለመሥሪያ ቤቱ ባለ ሥልጣናት ሪፖርት አድርጉ። ራሳችሁን ጥፋተኛ አድርጋችሁ አትቁጠሩ። ሁኔታው ከተባባሰ ደግሞ የምትሠሩበትን ክፍል ወይም መሥሪያ ቤት ለውጡ።”
የአእምሮ ችግር በሕፃናት ላይ
“ከዓለም ሕፃናት መካከል ከአምስት አንዱ በወደፊት ሕይወቱ ላይ ጠባሳ ሊጥል የሚችል የአእምሮ ወይም የሥነ ልቦና ችግር” እንደሚደርስበት የለንደኑ ዚ ኢንዲፐንደንት ጋዜጣ ገልጿል። የዓለም ጤና ድርጅትና የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት በጋራ ባዘጋጁት ሪፖርት ጭንቀት፣ ራስን መግደልና በራስ ላይ ጉዳት ማድረስ በልጆችና በወጣቶች መካከል “በአስደንጋጭ ሁኔታ” እየጨመረ እንደመጣ አስጠንቅቀዋል። ከሁሉ በላይ የተጎዱት በጦርነት አካባቢዎችና ፈጣን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ በሚታይባቸው አገሮች የሚኖሩ ልጆች ናቸው። ዚ ኢንዲፐንደንት እንዳለው ከሆነ ሪፖርቱ ጭንቀት የነበረባቸው ልጆች “ዕድሜያቸውን ሊያሳጥሩ ለሚችሉ ሌሎች በሽታዎችና አደገኛ ልማዶች ተጋልጠዋል።” ጨምሮም “ሕይወትን በአጭሩ ከሚቀጩ ምክንያቶች መካከልም 70 በመቶ የሚሆኑት እንደማጨስ፣ መጠጣትና አደገኛ ዕፅ እንደመውሰድ ካሉት በጉርምስና ዕድሜ ከሚለመዱ መጥፎ ልማዶች ጋር ዝምድና ያላቸው ናቸው” ብሏል።
ጥሩ የአካል ብቃት ይዞ መኖር
“የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሰውነትን ክብደት ለመቆጣጠር ይረዳል፣ እንደ ስኳርና ኦስትዮፖሮሲስ ካሉት የጤና ችግሮች ይጠብቃል፣ ጠባይ ያሻሽላል እንዲሁም ጥሩ እንቅልፍ ያስወስዳል” በማለት ተፍትስ ዩኒቨርሲቲ ኤንድ ኒውትሪሽን ሌተር የተባለው ጽሑፍ ገልጿል። ከዚህ ሁሉ ይበልጥ ግን “የአካል ብቃት በዕድሜ ርዝመት ላይ ወሳኝ የሆነ ተጽዕኖ ያሳድራል።” የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲና የዩናይትድ ስቴትስ የአረጋውያን ጤና አጠባበቅ ድርጅት ተመራማሪዎች በመካከለኛ ዕድሜ ላይ በሚገኙ 6 000 ሰዎች ላይ ባደረጉት 13 ዓመት የፈጀ ጥናት አንድ ሰው ትንፋሽ ሳያጥረው ሊሠራ የሚችለው የእንቅስቃሴ መጠን የሚኖረውን የዕድሜ ርዝመት እንደሚጠቁም ደርሰውበታል። ጠንካራ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማድረግ አቅም ከዘር ውርሻ ጋር ከፍተኛ ዝምድና እንዳለው የሚጠቁሙ ሌሎች ጥናቶች ቢኖሩም በእግር እንደመጓዝ ያሉ “ቀላል” እንቅስቃሴዎች እንኳን በየቀኑ ከተደረጉ ጥሩ የአካል ብቃት ለማግኘት በጣም ይረዳሉ።
የአልኮል መጠጦችን ለወጣቶች ማስተዋወቅ
“ከአሥር አውስትራሊያውያን መካከል አንዱ የአልኮል ሱሰኛ ነው” ሲል የአውስትራሊያው ሳንደይ ቴሌግራፍ ዘግቧል። የአውስትራሊያ የአልኮልና ሌሎች ዕፆች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የሆኑት ኢያን ወብስተር በወጣቶች መካከል “ጥምብዝ እስኪሉ ድረስ” ካልጠጡ ጥሩ ቅዳሜና እሁድ አሳልፌያለሁ የማይባልበት አዲስ ዓይነት ባሕል እየተስፋፋ ነው ብለዋል። ዘ ሲድኒ ሞርኒንግ ሄራልድ ‘እያደገ የመጣው አልኮልን ለወጣቶች የማስተዋወቅ ኢንዱስትሪ’ ሊቃውንቱን እንዳሳሰበ ዘግቧል። አብዛኞቹ የአልኮል መጠጥ አሻሻጮች ለወጣቶች የተዘጋጁ የኢንተርኔት ገጾች እንዳሏቸው ተመራማሪዎቹ ደርሰውበታል። “እነዚህ ገጾች አልኮል ከማስተዋወቃቸው በተጨማሪ የሙዚቃ ዝግጅት መግቢያ ቲኬቶችን ያሻሽጣሉ፣ ፊልሞችን ያስተዋውቃሉ።” በሪፖርቱ መሠረት የዚህ ሁሉ ማስተዋወቂያ “ዓላማ አልኮል የወጣቶች ሕይወት ዋነኛ ክፍል እንዲሆን ለማድረግ” መሆኑ የዓለም ጤና ድርጅትን አሳስቦታል።
“ልባቸው ሙሉ ጭንቅላታቸው ግን ባዶ”
የጀርመኑ ሳምንታዊ ጋዜጣ ዲ ቮከ እንዳለው ባለሞያዎች በሆኑ ደብዳቤ ጸሐፊዎች የተጻፉ የፍቅር ደብዳቤዎች ተፈላጊነታቸው እየጨመረ እንደሄደ ገልጿል። ስሜታቸውን በቃላት መግለጽ ለተሳናቸው ሰዎች ምንም ዋጋ ሳያስከፍሉ ደብዳቤ የመጻፍ አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ ሰዎች አሉ። የደብዳቤው ይዘት እንደ ደንበኛው ፍላጎት ፍቅርን የሚገልጽ ወይም ቀጥተኛ የሆነ ጥያቄ የሚያቀርብ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም በድርድር የሚወሰን ዋጋ የሚከፈልባቸው ግጥሞችም አሉ። እነዚህ በሌላ ሰው እርዳታ የሚዘጋጁ ደብዳቤዎች የሚገኙበት መንገድ የተለያየ ነው። አንዳንዶቹ ጸሐፊዎች ጽሑፍ ማዘጋጀትን ሞያቸው ያደረጉና ጋዜጠኞች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ የፍቅር ደብዳቤ የሚጽፉት ጊዜ ማሳለፊያ እንዲሆናቸው ነው። እንዲያውም አንዳንዶቹ በኢንተርኔት አማካኝነት የሚሞላ መጠይቅ ያዘጋጁና በመጠይቁ መሠረት የተዘጋጀ ደብዳቤ ያቀርቡላቸዋል። ያም ሆነ ይህ ጸሐፊዎቹ አዎንታዊ ምላሽ እንደሚገኝ ዋስትና ሊሰጡ አይችሉም። የአንድ ደብዳቤ አዘጋጅ ታማኝ ደንበኛ ለሦስት ዓመታት ያህል “ልብ የሚነካ የፍቅር ጥያቄ” ሲልክ ቢቆይም የሴት ጓደኛው ጥያቄውን ለመቀበል እምቢተኛ ሆናለች።
የአካል ብቃትና በሕመም ምክንያት ከሥራ መቅረት
የፊንላንድ የአካል ብቃት ማኅበር ባደረገው ጥናት መሠረት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በሕመም ምክንያት ከሥራ መቅረትን ይቀንሳል። ብዙ የፊንላንድ አሠሪዎች ሠራተኞቻቸው ከሥራ እንዳይቀሩ ለማድረግ በዚህ ዘዴ እየተጠቀሙ ነው። ፊንፋክትስ የተባለው የፊንላንድ ኢንዱስትሪና አሠሪዎች ማኅበር ጽሑፍ “ከፊንላንድ ሠራተኞች መካከል ግማሽ የሚሆኑት የሚሠሩት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ፕሮግራም ላላቸው ድርጅቶች ነው።” “ድርጅቶች ማጨስ ለማቆምና ክብደት ለመቀነስ የሚያስችሉ ፕሮግራሞችና የተለያየ ዓይነት የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች በማካሄድ ላይ ናቸው።” የፊንላንድ ኩባንያዎች ለዚህ ተግባር በየዓመቱ 67, 000, 000 የአሜሪካ ዶላር የሚያክል ገንዘብ ያወጣሉ። ይህን የሚያደርጉት ሠራተኞች ከሥራ ባለመቅረታቸው የሚያገኙት ገቢ ከዚህ በብዙ እጥፍ እንደሚበልጥ ስለሚያውቁ ነው።
“መዋሸት አንጎልን ያደክማል”
በፔንሲልቫንያ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩ ተመራማሪዎች እውነት ከመናገር ይልቅ ውሸት መናገር የበለጠ አንጎል እንደሚያደክም ተረድተዋል። ዶክተር ዳንኤል ላንግልበን ፋንክሽናል ማግኔቲክ ሬሶናን ኢሜጂንግ የተባለ መሣሪያ በመጠቀም አንድ ሰው በሚዋሽበት ጊዜ የሚንቀሳቀሱት የትኞቹ የአንጎል ክፍሎች እንደሆኑ ሲከታተሉ ቆይተዋል። አንጎላችን አንድ ጥያቄ ሲቀርብለት በመጀመሪያ ጥያቄውን ይተነትናል። ከዚያም “የሚዋሸው ሰው በቅጽበት ውሸት የሆነ መልስ ከማዘጋጀቱ ወይም ከመመለሱ በፊት እውነተኛውን መልስ ያስባል” በማለት የሜክሲኮ ከተማው ዘ ኒውስ ዘግቧል። “በአንጎል ውስጥ ዋጋ ሳይከፈልበት እንዲሁ የሚገኝ ነገር የለም” ይላሉ ላንግልበን። “ውሸት መናገር እውነት ከመናገር የበለጠ ውስብስብ ስለሆነ የበለጠ የነርቭ እንቅስቃሴ ይጠይቃል።” ይህ ተጨማሪ የነርቭ እንቅስቃሴ በኤፍ ኤም አር አይ መሣሪያው ላይ እንደ መብራት ሆኖ ይታያል። ጋዜጣው “በጣም ቀልጣፋ ለሆነ ተናጋሪ እንኳን መዋሸት ለአንጎል በጣም ከባድ ሥራ ነው” ብሏል።