በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የልጆች ዝሙት አዳሪነት እየጨመረ የመጣው ለምንድን ነው?

የልጆች ዝሙት አዳሪነት እየጨመረ የመጣው ለምንድን ነው?

የልጆች ዝሙት አዳሪነት እየጨመረ የመጣው ለምንድን ነው?

ሰውን እንደ ሸቀጥ ማዘዋወር ከአደንዛዥ ዕፅና ከጦር መሣሪያ ዝውውር ቀጥሎ ሦስተኛውን ደረጃ የሚይዝ ወንጀል መሆኑን ታውቃለህ? የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው ዝሙት አዳሪነት በሁሉም መልኩ እየጨመረ ነው።

በአንድ የላቲን አሜሪካ አገር ዝሙት አዳሪነት ሕገ ወጥ ቢሆንም ከ500, 000 የሚልቁ ዝሙት አዳሪ ሴቶች ልጆች እንዳሉ የአገሪቱ ምርመራ ምክር ቤት ዘግቧል።

በአንድ ሌላ አገር ደግሞ 300, 000 የሚሆኑ የጎዳና ላይ ዝሙት አዳሪ ልጆች ያሉ ሲሆን በብዛት የሚገኙትም የዕፅ ዝውውር ባለባቸው አካባቢዎች ነው።

በእስያ አገሮች አንድ ሚልዮን የሚያህሉ ወጣት ልጃገረዶች ከባርነት በማይተናነስ ሁኔታ ዝሙት አዳሪዎች ሆነው ለመኖር እንደሚገደዱ ይነገራል። አንዳንድ አገሮች የልጆች ዝሙት አዳሪነትና የወሲብ ቱሪዝም መናኸሪያ እስከመባል ደርሰዋል።

እንደ ኤድስ ያሉ በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች በከፍተኛ ፍጥነት በመዛመት ላይ በመሆናቸው ምክንያት የወሲብ ደንበኞች ድንግል እንደሆኑና ኤድስ እንደሌለባቸው አድርገው ለሚያስቧቸው ወጣት ልጃገረዶች ከፍተኛ ዋጋ ለመክፈል ፈቃደኞች ናቸው። የብራዚል ፍትሕ ሚኒስትር የሆኑት ሉዌዛ ናዝሄብ ኤሉፍ “ወንዶች ኤድስን በመፍራት ትንንሽ ሴቶችና ወንዶች ልጆችን የሚፈልጉ መሆናቸው ችግሩን ይበልጥ አባብሶታል” በማለት ገልጸዋል። “በብራዚል ድሃ ሴቶችን በተመለከተ ያለው አሳሳቢ ማኅበራዊ ችግር ልጃገረዶችንና በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶችን የወሲብ መገልገያ ማድረግ ነው።”

ድህነትና የልጆች ዝሙት አዳሪነት

የልጆች ዝሙት አዳሪነት ይበልጥ ተስፋፍቶ የሚገኘው ችግርና ድህነት ባለበት አካባቢ ነው። አንዲት የመንግሥት ባለ ሥልጣን እንደገለጹት በአገራቸው ያለው “የልጆችን ጉልበት መበዝበዝና የልጆች ዝሙት አዳሪነት ከቤተሰብ መፈራረስ ጋር ተያይዞ የሚመጣ እንዲሁም የችግርና የድህነት ውጤት ነው።” አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን ለዝሙት አዳሪነት አሳልፈው እንዲሰጡ ያደረጋቸው ድህነት መሆኑን ይናገራሉ። ጎዳና ተዳዳሪ ልጆች ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ለማግኘት እንደብቸኛ አማራጭ አድርገው የያዙት ዝሙት አዳሪነትን ነው።

ኦ ኢስታዶ ደ ኤስ ፓውሎ የተሰኘው ጋዜጣ እንደገለጸው አንዲት ልጃገረድ ከጎዳና ዱርዬዎች ጋር ከገጠመች መጨረሻዋ ዝሙት አዳሪ መሆን ነው። የምትበላው ነገር ለማግኘት ስትል ልትሰርቅና አልፎ አልፎም ገላዋን ልትሸጥ ትችላለች። ቀጥሎም ዝሙት አዳሪነትን ሞያዋ ታደርገዋለች።

አንዳንድ ጊዜ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች ዝሙት አዳሪ ሆነው እንዲሠሩ ወደ ሌሎች አገሮች ይላካሉ። ዩኔስኮ ሶርስስ እንደዘገበው “ከአንዳንድ የእስያና የአፍሪካ አገሮች ድህነት አንፃር ሲታይ በስደት የሚኖሩ ዝሙት አዳሪዎች ለወላጆቻቸው የሚልኩት ገንዘብ ከፍተኛ መጠን ያለው ነው። የሚገርመው ነገር በእነዚህ አገሮች ውስጥ ወጣቶችና ልጆች የሚያቀርቡትን ‘ግልጋሎት’ ለማግኘት ከበለጸጉ አገሮች ከሚመጡ አገር ጎብኚዎች ጋር ዝሙት መፈጸም የሚደገፍ ተግባር ነው።”

ታይም መጽሔት በአንድ የላቲን አሜሪካ ከተማ ዝሙት አዳሪ የሆኑ የጎዳና ተዳዳሪ ልጆች ለምን ዓይነት አደጋ እንደሚጋለጡ ሲገልጽ “አንዳንዶቹ ዝሙት አዳሪዎች ገና የ12 ዓመት ልጆች ናቸው። በአብዛኛው ቤተሰባቸው የፈረሰባቸው እነዚህ ልጆች ቀን ባገኙበት ቦታ ሁሉ የሚተኙ ሲሆን ሌሊት ደግሞ የወሲብ ተጓዳኞች ወደሚያገኙባቸው የምሽት ክበቦች ይዘዋወራሉ።”

አንዲት ዝሙት አዳሪ አደንዛዥ ዕፅ ስትወስድ ሌላ ጊዜ ቢሆን እሺ የማትለውን ሰብዓዊ ክብሯን የሚያዋርድ ድርጊት ልትፈጽም ትችላለች። ለምሳሌ ያህል፣ ቬጃ የተሰኘው መጽሔት አንድ ሐኪም ከ50 የሚበልጡ ሴቶችን ሲያሰቃይ የሚያሳይ 92 የቪዲዮ ክሮች በፖሊስ እንደተገኘበትና ከእነዚህም ውስጥ አንዳንዶቹ ዕድሜያቸው ለወሲብ ያልደረሰ እንደነበሩ ገልጿል።

ሁኔታው አሰቃቂ ቢሆንም አንዲት ወጣት ዝሙት አዳሪ የሚከተለውን ተናግራለች:- “ሥራ ብፈልግ ሞያ ስለሌለኝ የምበላው አላገኝም። ቤተሰቦቼ ዝሙት አዳሪ እንደሆንኩ ያውቃሉ። ስለዚህ ይህን ሥራ መተው አልፈልግም። ገላዬ የራሴ ነው፤ ስለዚህ በገላዬ ያሻኝን አደርጋለሁ።”

ይሁን እንጂ እነዚህ ልጃገረዶች ዝሙት አዳሪነትን ግባቸው አድርገው አልተነሱም። አንድ ማኅበራዊ ሠራተኛ እንደተናገረው ብዙ ወጣት ዝሙት አዳሪዎች “ባል ማግባት ይፈልጋሉ” እንዲሁም “ፍቅረኛ የማግኘት” ሕልም አላቸው። ወደ ዝሙት አዳሪነት ሕይወት የመሯቸው ውስብስብ ሁኔታዎች ቢኖሩም በጉዳዩ ላይ ጥናት ያካሄዱ አንዲት ተመራማሪ እንዳሉት “በጣም ዘግናኝ የሆነው ነገር አብዛኞቹ በገዛ ቤታቸው ውስጥ ተገደው የተደፈሩ መሆናቸው ነው።”

የልጆች ዝሙት አዳሪነት ማብቂያ ይኖረው ይሆን?

የሆነ ሆኖ እነዚህ አሳዛኝ ፍጡራን ተስፋ አላቸው። በየትኛውም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ዝሙት አዳሪዎች ሕይወታቸውን መለወጥ ችለዋል። (ገጽ 7 ላይ የሚገኘውን “ሰዎች ሊለወጡ ይችላሉ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) መጽሐፍ ቅዱስ በመላው ዓለም የሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጥሩ ጎረቤቶችና ታማኝ የቤተሰብ አባሎች እንዲሆኑ ረድቷቸዋል። ቀደም ሲል አመንዝሮች፣ ዝሙት ፈጻሚዎች፣ ሌቦች፣ ስግብግቦችና ሰካራሞች የነበሩ ሰዎችን በሚመለከት “ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ ጸድቃችኋል” ይላል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 6:​9-11

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዛሬም በሕይወታቸው ላይ ጥሩ ለውጥ የሚያደርጉ ሰዎች አሉ። ቢሆንም የወሲብ ብዝበዛን ግስጋሴ ለመግታት ሌላም ነገር ያስፈልጋል። አንዳንድ መንግሥታትና ድርጅቶች የወሲብ ቱሪዝምንና የልጆች ዝሙት አዳሪነትን በመዋጋት ላይ ናቸው። ይሁንና ተጨባጩ ሐቅ እንደሚያሳየው ሰዎች ችግርንና ድህነትን ማጥፋት አይችሉም። ሕግ አውጭዎች ግብረ ገብነት የሌለው ተግባር ለመፈጸም የሚያነሳሱ አስተሳሰቦችንና ዝንባሌዎችን ማስቀረት አይችሉም።

እነዚህ ሁሉ ችግሮች የሚፈቱት በሰዎች ሳይሆን በአምላክ መንግሥት ነው። የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ያብራራል።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ድህነት ብዙውን ጊዜ የልጆች ዝሙት አዳሪነትን ያባብሳል

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ውድ ዋጋ

ዴዚ ገና የስድስት ዓመት ልጅ ሳለች በገዛ ወንድሟ ተነወረች። በዚህም ምክንያት ዕድሜዋ 14 ዓመት እስኪሆን ድረስ ከታላቅ ወንድሟ ጋር ቆየችና በአንድ የምሽት ክበብ ውስጥ መሥራት ጀመረች። ከጥቂት ቀናት በኋላ ዴዚ ታመመች። ከበሽታዋ ስታገግም የምሽት ክበቡ ባለቤቶች ዕዳ አለብሽ አሏትና በዝሙት አዳሪነት እንድትሠራ አስገደዷት። ከአንድ ዓመት በኋላም ዕዳዋን ከፍላ ስላልጨረሰች ከዕዳ ነፃ የምትሆንበት ጊዜ የሚመጣ አይመስልም ነበር። ይሁንና አንድ መርከበኛ ቀሪ ዕዳዋን ከፈለላትና ወደ ሌላ ከተማ ወስዶ እንደ ባሪያ ይገለገልባት ጀመር። እሱን ትታ ወጣችና ከአንድ ሌላ ሰው ጋር ለሦስት ዓመት ከኖረች በኋላ ተጋቡ። ከባድ የትዳር ችግሮች ስለነበሩባት ሦስት ጊዜ ራሷን ለመግደል ሙከራ አደረገች።

በመጨረሻም እሷና ባሏ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመሩ። ይሁንና ዴዚ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ብቃት እንደሌላት ሆኖ ተሰማት። ሆኖም ይሖዋ አምላክ በሕይወታቸው ውስጥ አስፈላጊውን ለውጥ የሚያደርጉ ሰዎችን እንደሚቀበል ከመጽሐፍ ቅዱስ ሲያሳዩአት ሕይወቷን ለይሖዋ ወሰነች። ዴዚ ትክክል የሆነውን ለማድረግ ብርቱ ጥረት ብታደርግም ይህ በቂ ሆኖ ስላልተሰማት የተስፋ መቁረጥ ስሜት አደረባት። ደስ የሚለው ግን በፆታ በመነወሯና በልጅነቷ ዝሙት አዳሪ በመሆኗ ምክንያት የደረሰባትን የስሜት ስብራት እንድትቋቋምና ስሜታዊ ሚዛኗን ጠብቃ መኖር እንድትችል የተደረገላትን እርዳታ ተቀበለች።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሰዎች ሊለወጡ ይችላሉ

ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር በነበረበት ጊዜ ለተጨነቁና ኃጢአተኛ ለሆኑ ሰዎች ያዝንላቸው ነበር። ዝሙት አዳሪዎች ዕድሜያቸው ምንም ይሁን ምን አኗኗራቸውን ሊለውጡ እንደሚችሉ ያውቅ ነበር። እንዲያውም ኢየሱስ ለሃይማኖት መሪዎች “እውነት እላችኋለሁ፣ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 21:​31) እነዚህ ልበ ቅን ሰዎች በአኗኗራቸው ይናቁ የነበረ ቢሆንም በአምላክ ልጅ በማመናቸው ምሕረትን ተቀብለዋል። ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞች የአምላክን መንግሥት በረከቶች ለማግኘት ሲሉ የዝሙት አዳሪነት ኑሯቸውን ለመተው ፈቃደኞች ነበሩ። ከዚያ በኋላ ከአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው ኖረዋል። ዛሬም ቢሆን ሁሉም ዓይነት ሰዎች የአምላክን ቃል እውነት ተቀብለው አኗኗራቸውን ለውጠዋል።

በመጀመሪያው ርዕስ ላይ የተጠቀሱት ማሪያ፣ ካሪና እና ኢስቴላ ምን እንደደረሰባቸው ተመልከት። ማሪያ ዝሙት አዳሪ እንድትሆን ከእናቷ የሚደርስባትን ግፊት ከመቋቋሟም በተጨማሪ ከአደንዛዥ ዕፅ ለመገላገል ብርቱ ጥረት ማድረግ ነበረባት። እንዲህ ትላለች:-“የዝሙት አዳሪነት ሕይወት በመምራቴ ምክንያት የሚደርስብኝን የዋጋ ቢስነት ስሜት ለማፈን አደንዛዥ ዕፅ እወስድ ነበር።” ማሪያ በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ የተደረገላትን አቀባበል ስትናገር:- “የጉባኤው አባላት ያሳዩኝ ፍቅር በጣም አስገረመኝ። ልጆችም ሆኑ አዋቂዎች ሁሉም በአክብሮት ያዙኝ። ያገቡት ወንዶች ለሚስቶቻቸው ታማኞች እንደነበሩ ተመለከትኩ። እንደ ጓደኛቸው አድርገው ስለተቀበሉኝ በጣም ደስተኛ ነኝ” ብላለች።

ካሪና 17 ዓመት ሲሆናት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤቷ መጡ። ለተወሰነ ጊዜ በዝሙት አዳሪነት ብትቀጥልም እሷም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። ቀስ በቀስም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች መረዳትና ማድነቅ ጀመረች። ስለዚህ ራቅ ወዳለ ከተማ ለመሄድ ወሰነችና እዚያም የይሖዋ ምሥክር ሆነች።

ገና በለጋ ዕድሜዋ በዝሙት አዳሪነት፣ በፈንጠዝያና የአልኮል መጠጦችን ከልክ በላይ በመጠጣት የተጠላለፈችው ኢስቴላ ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍላጎት አሳየች። ይሁን እንጂ አምላክ ፈጽሞ ይቅር አይለኝም ብላ አሰበች። ውሎ አድሮ ግን ይሖዋ አምላክ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን ይቅር እንደሚል ተረዳች። አሁን የክርስቲያን ጉባኤ አባል፣ ያገባችና የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ኢስቴላ “ይሖዋ ከጭቃ አውጥቶ በንጹሕ ድርጅቱ ውስጥ ስለተቀበለኝ በጣም ደስተኛና አመስጋኝ ነኝ” ትላለች።

እነዚህ ታሪኮች የአምላክ ፈቃድ ‘ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደማወቅ እንዲደርሱ’ መሆኑን የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ አባባል የሚደግፉ ናቸው።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 2:​4

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ዝሙት አዳሪ ልጆች ብዙውን ጊዜ የዕፅ ሱሰኞችም ናቸው

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የሥዕሎቹ ምንጮች]

© Jan Banning/Panos Pictures, 1997