በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የከፋ ወንጀል”

“የከፋ ወንጀል”

“የከፋ ወንጀል”

ማሪያ * ገና የ14 ዓመት ልጅ ሳለች ዝሙት አዳሪ ሆነች። ማሪያ ወደዚህ ሕይወት የገባችው በእናቷ ውትወታ ሲሆን ቆንጆ እንደሆነችና ወንዶች በጣም እንደሚወዷት አዘውትራ ትነግራት ነበር። በተጨማሪም ብዙ ገንዘብ ልታገኝ እንደምትችል ነገረቻት። እናቷ ማታ ማታ ወደ ሆቴሎች እየወሰደቻት ከወንዶች ጋር ታገናኛት ነበር። ከዚያም ራቅ ብላ ትጠብቃትና የተከፈላትን ገንዘብ ትቀበላት ነበር። ማሪያ በየቀኑ ከሦስት ወይም ከአራት ወንዶች ጋር ወሲብ ትፈጽም ነበር።

ማሪያ በምትኖርበት አካባቢ ካሪና የምትባል የ13 ዓመት ልጅም ተገዳ ወደ ዝሙት አዳሪነት ሕይወት ገብታለች። በሸንኮራ አገዳ ምርት የሚተዳደሩት የአካባቢው ማኅበረሰብ አባሎች የሆኑ ብዙ ቤተሰቦች እንደሚያደርጉት የካሪና ቤተሰቦችም ውስን የሆነውን ገቢያቸውን ለመደጎም የልጃቸውን ገላ ይሸጡ ነበር። በሌላ አካባቢ የምትኖረው ኢስቴላ ማንበብና መጻፍ እንኳን ሳትችል ትምህርቷን አቋርጣ የጎዳና ዝሙት አዳሪ ሆነች። ዴዚ በገዛ ወንድሟ ስትደፈር ገና የስድስት ዓመት ልጅ ነበረች። ከዚያ በኋላ በሥጋ ዘመዶቿ ከተፈጸሙባት በርካታ በጾታ የመደፈር ድርጊቶች መካከል ይህ የመጀመሪያው ብቻ ነበር። እሷም በ14 ዓመት ዕድሜዋ ዝሙት አዳሪ ሆነች።

በብዙ የዓለም ክፍሎች የልጆች ዝሙት አዳሪነት አስፈሪ እውነታ ሆኗል። ውጤቱም እጅግ አሳዛኝ ነው። ዝሙት አዳሪ የሆኑ ልጆች በወንጀልና በአደገኛ ዕፅም የተጠላለፉ ናቸው። ብዙዎቹ ከመጥፎ አኗኗራቸው የመላቀቅ ተስፋቸው ጨለማ ሆኖ ስለሚታያቸው ብስጭትና የዋጋ ቢስነት ስሜት ይሰማቸዋል።

ተደማጭነት ያላቸው ሰዎች የልጆች ዝሙት አዳሪነት ያለውን አጥፊ ውጤት ይገነዘባሉ። የብራዚል የቀድሞ ፕሬዚዳንት ፈርናንዶ ሄንሪክ “የልጆች ዝሙት አዳሪነት የከፋ ወንጀል ነው” በማለት በግልጽ ተናግረዋል። አንድ የብራዚል ጋዜጣ ስለ ልጆች ዝሙት አዳሪነት የሚከተለውን ስሜት የሚነካ አስተያየት ሰጥቷል:-“[ለገንዘብ] ሲባል እንዲህ ዓይነቱ ተግባር የሚዘወተርባቸው፣ በቸልታ የሚታለፍባቸው፣ ተቀባይነት ያገኘባቸውና አልፎ ተርፎም ሆን ተብሎ የሚስፋፋባቸው አገሮች ዝሙት አዳሪነት የሚያስከትለውን ገፈት በየዕለቱ እየቀመሱት ነው። ዝሙት አዳሪነት የሚያስገኘው ማንኛውም የገንዘብ ትርፍ ይህ ተግባር በግለሰቡ፣ በቤተሰቡና በኅብረተሰቡ ላይ ከሚያስከትላቸው ቀውሶች አኳያ ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።”

በቅን ልብ ተነሳስተው የልጆች ዝሙት አዳሪነትን ለማስቆም የሚጥሩ ሰዎች ቢኖሩም ችግሩ ግን እየጨመረ ነው። የዚህ አሳዛኝ ሁኔታ መንስኤ ምንድን ነው? እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት ብዙዎች በቸልታ የሚያልፉት አልፎ ተርፎም የሚያስፋፉት ለምንድን ነው?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 በዚህና በሚቀጥሉት ሁለት ርዕሶች ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተለውጠዋል።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“የልጆች ዝሙት አዳሪነት የከፋ ወንጀል ነው።”—የብራዚል የቀድሞ ፕሬዚዳንት ፈርናንዶ ሄንሪክ ካርዶሱ

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“የዝሙት አዳሪው ዕድሜ፣ ጾታ፣ ዘር፣ ብሔር ወይም ማኅበረሰባዊ ደረጃ ምንም ይሁን ምን አንድን ሰው ለወሲብ መጠቀሚያ ማድረግ ሰብዓዊ ክብርን መድፈር በመሆኑ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብትን መጣስ ነው።”​—⁠ዩኔስኮ ሶርስስ