በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይቅር የማይባል ኃጢአት አለን?

ይቅር የማይባል ኃጢአት አለን?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ይቅር የማይባል ኃጢአት አለን?

ከሞት የከፋ ቅጣት ይኖራልን? አዎን፣ አንድ ሰው ይቅር የማይባል ኃጢአት በመሥራቱ ምክንያት ትንሣኤ የሌለው ሞት ከሞተ ቅጣቱ ከሞት የከፋ ነው። ኢየሱስ ‘ይቅር የማይባል’ ኃጢአት እንዳለ ተናግሯል።​—⁠ማቴዎስ 12:​31 አ.መ.ት

ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ይቅር ባይ እንደሆነ ይገልጻል። ምንም እንኳ ሰዎች ይቅር ከማለት ይልቅ ቂም መያዝ የሚቀናቸው ሊሆኑ ቢችሉም አምላክ ግን “ይቅርታው ብዙ ነው።” (ኢሳይያስ 55:​7-9) እንዲያውም በራሱ በኩል ምንም ያህል ከፍተኛ መሥዋዕትነት ቢጠይቅበትም ውድ ልጁ ለእኛ ቤዛ ሆኖ ኃጢአታችንን እንዲደመስስ ወደ ምድር ልኮታል።​—⁠ዮሐንስ 3:16, 17፤ ሥራ 3:19፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2

አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ በሕይወት ዘመናቸው ከባድ ኃጢአት ፈጽመው የነበሩ ሙታንን የሚያስነሳ ሲሆን ላለፈው ኃጢአታቸው ግን ተጠያቂ አያደርጋቸውም። (ሥራ 24:​15፤ሮሜ 6:​23) እንዲያውም ኢየሱስ ይቅር ከማይባለው ኃጢአት በስተቀር “ኀጢአት መሥራትና የስድብ ቃል ሁሉ መናገር ለሰዎች” ይቅር እንደሚባል ተናግሯል። (ማቴዎስ 12:​31 አ.መ.ት ) ስለዚህ ‘አምላክ ይቅር የማይለው ምን ያህል ከባድ ኃጢአት ቢሆን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።

ንስሐ የሌለው ኃጢአት

ኢየሱስ ያስጠነቀቀው የኃጢአት ዓይነት ሆን ብሎ ‘መንፈስ ቅዱስን መሳደብን’ የሚያመለክት ነው። ይህ ዓይነቱ ኃጢአት ይቅር አይባልም። ኢየሱስ “በዚህም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ይቅር አይባልም” በማለት አክሎ ተናግሯል። (ማቴዎስ 12:​31, 32 አ.መ.ት ) እንዲህ ዓይነቱን ኃጢአት የፈጸሙ ሰዎች ትንሣኤ አያገኙም።

መንፈስ ቅዱስን መሳደብ ምንድን ነው? መንፈስ ቅዱስን መሳደብ የሚመጣው ክፋትና ተንኮል ከተጠናወተው ልብ ነው። ይህን ኃጢአት የከፋ የሚያደርገው ሆን ብሎ የአምላክን ቅዱስ መንፈስ የመቃወም ዓላማ ይዞ የሚነሳ መሆኑ ነው። ይህ ምን ዓይነት ኃጢአት እንደሆነ በምሳሌ ለማስረዳት የሚከተለውን ተመልከት:- በአንዳንድ አገሮች ሰው የመግደል ወንጀል አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ በመባል የሚከፈል ሲሆን አንደኛ ደረጃ ሰው የመግደል ወንጀል የሚያመለክተው ሆን ተብሎ፣ ታስቦበት የተወሰደ እርምጃ መሆኑንና ግድያው የተፈጸመበት መንገድ ግምት ውስጥ የሚገባ ሲሆን ይህም ወንጀለኛው በሞት እንዲቀጣ የሚያስፈርድበት የግድያ ወንጀል ነው። ሁለተኛ ደረጃ ሰው የመግደል ወንጀል ግን ወንጀሉ በቅድሚያ ያልታሰበበትና በድንገት የተፈጸመ ነው።

ሐዋርያው ጳውሎስም አስቀድሞ ተሳዳቢ የነበረ ቢሆንም “ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረትን አገኘሁ” ብሏል። (1 ጢሞቴዎስ 1:​13) በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት መሥራት ማለት ሆን ብሎ መንፈስ ቅዱስን መቃወም ማለት ነው። እንደዚህ ዓይነቱ ኃጢአት ፈጽሞ ሊመለስ ከማይችል ክፉ ልብ የሚመነጭ ነው።

ጳውሎስ “አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱትን ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩትን መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና ሊመጣ ያለውን የዓለም ኃይል የቀመሱትን፣ በኋላም የካዱትን እንደ ገና ለንስሐ እነርሱን ማደስ የማይቻል ነው” ብሎ በጻፈ ጊዜ ያመለከተው እንዲህ ዓይነቱን ኃጢአት መሆኑ ግልጽ ነው። (ዕብራውያን 6:​4-6) በተጨማሪም ሐዋርያው “የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ወደን ኃጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አይቀርልንምና” ብሏል።​—⁠ዕብራውያን 10:​26

ኢየሱስ ይቅር ስለማይባል ኃጢአት እንዲያስጠነቅቅ ያነሳሳው በዘመኑ የነበሩት አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች ያሳዩት የነበረው ጠባይ ነው። ሆኖም ማስጠንቀቂያውን ሳይቀበሉት ቀሩ። ጭራሹንም አስገደሉት። ከዚያም መንፈስ ቅዱስ አሌ የማይባል ተአምር እንደሠራ ሰሙ። ኢየሱስ ከሙታን እንደተነሳ ተነገራቸው! ኢየሱስ መሲሕ መሆኑ ግልጽ ነበር! ከዚህ ሁሉ በኋላም ሮማውያን ወታደሮች ኢየሱስ እንዳልተነሳ የሚገልጽ የሐሰት ወሬ እንዲያናፍሱላቸው ጉቦ በመስጠት በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት ሠሩ።​—⁠ማቴዎስ 28:​11-15

ለእውነተኛ ክርስቲያኖች የሚሆን ማስጠንቀቂያ

እውነተኛ ክርስቲያኖች ይቅር ስለማይባል ኃጢአት የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ልብ ማለት ያለባቸው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ምንም እንኳ ስለ አምላክና መንፈሱ ስለሚያከናውነው ሥራ ትክክለኛ እውቀት ቢኖረንም ክፉ ልብ በውስጣችን ሊያቆጠቁጥ ስለሚችል ነው። (ዕብራውያን 3:​12) ይህ በእኔ ላይ ሊደርስ አይችልም ብለን እንዳናስብ መጠንቀቅ አለብን። የአስቆሮቱ ይሁዳን አስቡት። እሱ በአንድ ወቅት የኢየሱስ ታማኝ ተከታይ ነበር። ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ ሆኖ ተመርጦ ነበር፤ ስለዚህ መልካም ባሕርያት ኖረውት መሆን አለበት። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ክፉ ሐሳብና ምኞት እንዲያቆጠቁጥበት ፈቀደ፤ ይህም በመጨረሻ አሸነፈው። ኢየሱስ የፈጸማቸውን ድንቅ ተአምራት በገዛ ዓይኑ ቢያይም ገንዘብ ይሰርቅ ነበር። በዚህም ምክንያት ለገንዘብ ሲል የአምላክን ልጅ ሆን ብሎ አሳልፎ ሰጠ።

ቀደም ሲል ታማኝ ክርስቲያኖች የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ምናልባትም በቅሬታ፣ በኩራት ወይም በስስት ምክንያት ሆን ብለው ከአምላክ የራቁ ሲሆን አሁን የአምላክን ቅዱስ መንፈስ የሚዋጉ ከሃዲዎች ሆነዋል። መንፈስ ቅዱስ በግልጽ እያከናወነ ያለውን ነገር ሆን ብለው ይቃወማሉ። እነዚህ ግለሰቦች ይቅር የማይባል ኃጢአት ፈጽመዋልን? ፈራጁ ይሖዋ ነው።​—⁠ሮሜ 14:​12

በሌሎች ላይ ከመፍረድ ይልቅ እኛ በግላችን ቀስ በቀስ ልባችንን ሊያደነድኑ የሚችሉ ኃጢአቶችን በድብቅ እንዳንፈጽም ራሳችንን መጠበቅ አለብን። (ኤፌሶን 4:​30) ከዚህ በተረፈ ከባድ ኃጢአት ብንሠራ እንኳን ንስሐ ከገባን ይሖዋ በታላቅ ምሕረቱ ይቅር እንደሚለን በማወቃችን እንጽናናለን።​—⁠ኢሳይያስ 1:​18, 19

[በገጽ 12 እና 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዳንድ ፈሪሳውያን ይቅር የማይባል ኃጢአት ፈጽመዋል