በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሥር የሰደዱ መንስኤዎችና ዘላቂ መዘዞች

ሥር የሰደዱ መንስኤዎችና ዘላቂ መዘዞች

ሥር የሰደዱ መንስኤዎችና ዘላቂ መዘዞች

“እኔ ርቦኝ ሳለ እናንተ ግን ስለ ረሃቤ የሚያጠና ኮሚቴ አቋቋማችሁ። እኔ ቤት አጥቼ ሳለ እናንተ ችግሬን የሚገልጽ ዘገባ አጠናቀራችሁ። እኔ ታምሜ ሳለ እናንተ በችግረኞች ሁኔታ ላይ ለመወያየት ተሰበሰባችሁ። ሁኔታዬን በሙሉ መረመራችሁ፤ እኔ ግን አሁንም እንደተራብኩ፣ ቤት እንዳጣሁና እንደታመምኩ ነኝ። ”—ተናጋሪው አይታወቅም

የዓለም ድርጅቶች የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለማስቆም በርካታ ጥረቶች ቢያደርጉም የተገኘው ስኬት ግን ተስፋ የተጣለበትን ያህል አልሆነም። ለምሳሌ ያህል በተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት በ1996 በዓለም ምግብ ላይ ባደረገው የመሪዎች ጉባኤ ላይ በ2015 የዓለምን ራብተኞች በግማሽ ማለትም በ400 ሚልዮን ለመቀነስ ግብ አውጥቶ ነበር። *

አንዳንድ መሻሻሎች መደረጋቸው የሚያስመሰግን ቢሆንም የምግብና እርሻ ድርጅት በቅርቡ ያወጣው የዓለም ምግብ ዋስትና ማጣት 2001 በተሰኘው ሪፖርት እንዳስታወቀው “በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚሠቃዩትን የዓለም ሕዝቦች ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት አዝጋሚ መሆኑ በግልጽ የሚታይ ነው።” የመሪዎቹ ጉባኤ ያወጣው ግብ ሊደረስበት የሚችል አይመስልም። እንዲያውም “በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚሠቃዩት ሰዎች ቁጥር በአብዛኞቹ ታዳጊ አገሮች ውስጥ እየጨመረ እንዳለ” ሪፖርቱ አምኗል።

የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያስከተለውን ችግር ማስወገድ ይህን ያህል አዳጋች የሆነው ለምንድን ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት በመጀመሪያ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እንዲሁም ያስከተለው መዘዝና ሥር የሰደዱ መንስኤዎቹ ምን እንደሆኑ እንመርምር።

የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መንስኤው ምንድን ነው?

የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሰውነታችን ሴሎች ወደ ውስጥ የሚያስገቡት ገንቢ የምግብ መጠን በሚያንስበት ጊዜ የሚፈጠር ችግር ነው። ለዚህም ሁለት መንስኤዎች አሉ:- (1) ፕሮቲን፣ ሙቀት ሰጪ ምግቦችና ቫይታሚኖች እንዲሁም ማዕድኖችን በበቂ መጠን አለመመገብ እና (2) በተደጋጋሚ በበሽታ መጠቃት ናቸው።

ተቅማጥ፣ ኩፍኝ፣ ወባና የመተንፈሻ አካል በሽታዎች ሰውነትን በጣም የሚያዳክሙ ከመሆኑም በላይ በውስጡ ያሉትን ገንቢ ምግቦች ያሳጡታል። የምግብ ፍላጎትን ያሳጡና የመመገብ አቅምን ይቀንሳሉ። በውጤቱም የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ይከሰታል። በሌላ በኩል ደግሞ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተጠቃው ሕፃን ለተላላፊ በሽታ ይጋለጣል። ይህም በፕሮቲንና ኃይል ሰጪ ምግብ እጥረት ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር በማብዛት ማቆሚያ የሌለው እሽክርክሪት ያበጃል።

ሕፃናት ከሌሎች በበለጠ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚጠቁት ለምንድን ነው? ይህ የሆነበት ምክንያት ኃይል ሰጪና የፕሮቲን ምግቦችን መመገብ በሚያስፈልጋቸው ፈጣን የእድገት ወቅት ላይ ስለሚገኙ ነው። በተመሳሳይም እርጉዞችና እመጫት ሴቶች በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ይጠቃሉ።

ብዙውን ጊዜ ሕፃኑ በዚህ ችግር መጠቃት የሚጀምረው ገና ከመወለዱ በፊት ነው። እናቱ ከማርገዟ በፊትና ካረገዘችም በኋላ የተመጣጠነ ወይም በቂ ምግብ የማትመገብ ከሆነ ልጁ አነስተኛ ክብደት ኖሮት ይወለዳል። አለጊዜው ጡት መጣል፣ ደካማ የአመጋገብ ልማድና የንጽሕና ጉድለትም የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ሊያስከትሉ ይችላሉ።

አስፈላጊ የሆኑ ገንቢ ምግቦች እጥረት የሕፃኑ እድገት እንዲገታና በተገቢው መንገድ እንዳይፋፋ ሊያደርገው ይችላል። ሕፃኑ አልቃሻና በቀላሉ የሚታመም ይሆናል። ሁኔታው እየተባባሰ ሲሄድ ደግሞ ጉልህ የሆነ የክብደት መቀነስ የሚታይበት ከመሆኑም በላይ ዓይኖቹና የጭንቅላቱ አናት ይጎደጉዳል፤ እንዲሁም ቆዳውና ሥጋው የመለጠጥ ችሎታቸውን ያጡና አካሉ ይሸበሸባል፤ ሰውነቱ ሙቀት የመጠበቅ አቅሙ ይቀንሳል።

የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሌሎች ገጽታዎችም አሉት። እነዚህም ቢሆኑ ሕፃናትን ያጫጫሉ። ለምሳሌ ያህል በምግቡ ውስጥ በተለይም እንደ ብረት፣ አዮዲንና ዚንክ ያሉ በቂ ማዕድናት፣ ከቫይታሚኖች ደግሞ እንደ ቫይታሚን ኤ ያሉ ንጥረ ነገሮች በሚጎድሉበት ጊዜ መጫጫት ያጋጥማል። የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት እንዳመለከተው የቫይታሚን ኤ ጉድለት የዓለምን 100 ሚልዮን ሕፃናት የሚያጠቃ ሲሆን ይህም ዓይነ ስውርነት ያስከትልባቸዋል። የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም በማዳከም ሕፃናቱ በቀላሉ በተላላፊ በሽታዎች እንዲጠቁ ያደርጋል።

ብዙ መዘዝ ያለው ችግር

የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በአካል በተለይም በሕፃን አካል ላይ ከፍተኛ ቀውስ ይፈጥራል። ልብን፣ ኩላሊትን፣ ጨጓራን፣ አንጀትን፣ ሳንባንና አንጎልን ጨምሮ በሁሉም የሰውነት የውስጥ ክፍሎች ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችላል።

የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የሕፃን መጫጫት ከአእምሮ መጎዳትና ደካማ ከሆነ የትምህርትና የማሰብ ችሎታ ጋር ግንኙነት አለው። ከዩናይትድ ስቴትስ የተገኘ አንድ ዘገባ ይህን ሁኔታ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ የሚመጣ በጣም አሳሳቢ የሆነ ዘላቂ ችግር በማለት ጠርቶታል።

የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ከሚያስከትለው ሞት የተረፉ ሕፃናት ካደጉ በኋላም ቢሆን መዘዙ አብሯቸው ይኖራል። የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት “ሙሉ በሙሉ መከላከል ሲቻል አሁን በሚታየው መጠን የሰዎች የማሰብ ችሎታ መዳከሙ ብኩንነት ብሎም ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ አውዳሚነት ነው” በማለት በምሬት የተናገረው ለዚህ ነው። በመሆኑም የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ዘላቂ መዘዝ የሚያስከትል መሆኑ እጅግ የሚያሳስብ ነው። በቅርብ ጊዜ የተካሄደ አንድ ጥናት በጨቅላነት ወራት የተመጣጠነ ምግብ አለማግኘትን በአዋቂዎች ላይ ከሚታየው የልብ በሽታ፣ የስኳር በሽታና ከፍተኛ የደም ግፊት ከመሳሰሉ ሥር የሰደዱ ሕመሞች ጋር አዛምዷቸዋል።

ሆኖም አብዛኛው ችግር የሚፈጠረው ከፍተኛ በሚባለው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አይደለም። የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት እንዳሳወቀው ‘በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ ከሚሞቱት ሰዎች መካከል ሦስት አራተኛ የሚሆኑት የሚሞቱት ከፍተኛ በሚባለው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ ሳይሆን ቀላል እና መካከለኛ በሚባለው ዓይነት ነው።’ ቀላል ወይም መካከለኛ በሚባለው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ የሚሠቃዩ ሕፃናት ዘላቂ የጤና መዘዝ ሊያጋጥማቸው ይችላል። ስለዚህ ሕፃናት ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳለባቸው የሚያሳዩ ምልክቶችን ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል።​—⁠በገጽ 7 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።

ሥር የሰደዱ መንስኤዎች

ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት አንደኛው መንስኤ የምግብ እጦት ነው። ሆኖም ዋነኞቹ መንስኤዎች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባሕላዊና አካባቢያዊ ችግሮች ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ ዋነኛው ድህነት ሲሆን ይህም በሚልዮን የሚቆጠሩ በተለይም በታዳጊ አገር የሚኖሩ ሰዎችን ያጠቃል። ድህነት ግን ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት መንስኤ ብቻ ሳይሆን ውጤትም ጭምር ነው። ምክንያቱም በቂ ምግብ አለመመገብ የሰዎችን ምርታማነት ስለሚያዳክም ድህነትን ያባብሳል።

ሌሎች ምክንያቶችም አሉ። የእውቀት ማነስ ደካማ የአመጋገብ ልማድን ያስከትላል። ቀደም ብለን እንዳየነው በበሽታ መጠቃትም የራሱ የሆነ ድርሻ አለው። ምግብ ለሁሉም በእኩል ደረጃ አለመዳረሱ እና በሴቶች ላይ አድልዎ መፈጸምን የመሰሉ ማኅበራዊና ባሕላዊ ምክንያቶችም አሉ። ብዙውን ጊዜ ሴቶች የሚበሉት “መጨረሻና የተራረፈውን” ማለትም ወንዶች ከበሉ በኋላና ከወንዶች ያነሰ ነው። ሴቶች ለልጆቻቸው የተሻለ እንክብካቤ ማድረግ እንዲችሉ የሚያግዛቸውን የትምህርት አጋጣሚ ይነፈጋሉ።

በተጨማሪም አካባቢያዊ ምክንያቶች የምግብ ምርት እንዲቀንስ ሊያደርጉ ይችላሉ። ከእነዚህም ውስጥ የተፈጥሮ አደጋዎችና ጦርነቶች ይገኙበታል። ዓለም የምግብ ዋስትና ማጣት 2001 እንደገለጸው ከጥቅምት 1999 እስከ ሰኔ 2001 ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ 22 አገሮች በድርቅ፣ 17 አገሮች በአውሎ ነፋስ ወይም በጎርፍ፣ 14 አገሮች በእርስ በርስ ጦርነት ወይም ግጭት፣ 3 አገሮች በከባድ የክረምት ቅዝቃዜ፣ 2 አገሮች ደግሞ በምድር መናወጥ ተጠቅተዋል።

ሕክምናና መከላከያው

በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተጠቃ አንድ ሕፃን በሕክምና እርዳታ ሊያገኝ የሚችለው እንዴት ነው? ሕፃኑ ከፍተኛ በሚባለው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተጠቃ ከሆነ ሐኪም ቤት ገብቶ ሕክምና ቢሰጠው የተሻለ ሊሆን ይችላል። የዓለም ጤና ድርጅት ለሐኪሞች ባሳተመው አንድ መምሪያ ላይ እንደገለጸው ሐኪሞቹ የሕፃኑን ሁኔታ በመገምገም በበሽታ ተለክፎ ወይም የሰውነቱ ውኃ አልቆ ከሆነ ሕክምና ያደርጉለታል። ሕፃኑን መመገብ ቀስ በቀስ የሚጀመር ሲሆን ብዙውን ጊዜም በአፍንጫው በሚከተት ላስቲክ አማካኝነት ሊጀመር ይችላል። ይህ የመጀመሪያ ምዕራፍ ለአንድ ሳምንት ያህል ሊቀጥል ይችላል።

ከዚያም የተሃድሶ ፕሮግራም ይቀጥላል። ሕፃኑ እንደገና የእናቱን ጡት እንዲጠባና በተቻለ መጠን ምግብ እንዲበላ ይበረታታል። በዚህ ወቅት ስሜታዊና አካላዊ ማነቃቂያ መስጠት አስፈላጊ ነው። እንክብካቤና ፍቅር ማሳየት ለሕፃኑ እድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። ሕፃኑ እንደገና እንዳያገረሽበት ተገቢ ምግብ በመስጠትና ንጽሕናውን በመጠበቅ እንዴት መንከባከብ እንደምትችል እናቲቱ ትምህርት ማግኘት የሚኖርባትም በዚህ ጊዜ ነው። ከዚህ በኋላ ሕፃኑ ከሐኪም ቤት ይወጣል። ቢሆንም የሕክምና ክትትል እንዲደረግለት ሕፃኑን ወደ ሐኪም ቤት ወይም ክሊኒክ መውሰድ አስፈላጊ ነው።

ያም ሆኖ ግን ሕፃኑ እዚህ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት መከላከል ከሁሉ የተሻለ አካሄድ ነው። ለዚህም ሲባል በብዙ አገሮች መንግሥታትና የግል ድርጅቶች አጠቃላዩን የምግብ አቅርቦት ለማጠናከር ሲሉ የምግብ ድጎማ ፕሮግራሞችን አቋቁመዋል። ማኅበረሰቦችም አመጋገብን የሚመለከቱ የትምህርት ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት፣ ለመጠጥ ውኃ ጥበቃ በማድረግ፣ መጸዳጃ ቤቶችን በመሥራት፣ የአካባቢን ንጽሕና በመጠበቅ፣ ለክትባት ዘመቻዎች ድጋፍ በመስጠትና ትኩረት ሰጥቶ የልጆችን እድገት በመከታተል የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በሽታን ለመከላከል ብዙ እገዛ ማድረግ ይችላሉ።

ሆኖም የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለመከላከል በግለሰብ ደረጃ ምን ማድረግ ይቻላል? ገጽ 8 ላይ የሚገኘው ሣጥን አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦችን ይዟል። ከዚህም ጋር የሕፃናት አመጋገብ ሐኪም የሆኑት ጆርጂያ ታውሴንት የተባሉ ሴት አንዲት እናት ከወለደች ከሰባት ቀን በኋላ፣ ሕፃኑ አንድ ወር ሲሆነውና ከዚያም በኋላ በወር አንድ ጊዜ ልጅዋን ወደ ሕፃናት ሐኪም ቤት ወይም ወደ ጤና ጣቢያ ይዛ መሄድ እንዳለባት ሐሳብ አቅርበዋል። በሕፃኑ ላይ የሰውነት መሟሸሽ፣ ኃይለኛ ተቅማጥ ወይም ትኩሳት የመሳሰሉ ምልክቶች ከታዩበት እናቲቱ የሕክምና ባለሞያ ማማከር ይኖርባታል።

እነዚህ ሁሉ የመፍትሔ ሐሳቦች የልጆችን አመጋገብ ልማድ ለማሻሻል የሚረዱ ቢሆንም የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በሰው ጥረት ብቻ ሊፈታ የማይችል ትልቅ ችግር እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ “ለሁሉም ሰው በቂ የምግብ አቅርቦትና የአመጋገብ ትምህርት ዝግጅት ማድረግ አንገብጋቢ ችግር ሆኖ ይቀጥላል” በማለት አስታውቋል። ስለዚህ ይህ “ድምፅ አልባ ችግር” ይወገዳል የሚል ተስፋ ይኖር ይሆን?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 በዓለም ምግብ ላይ የተደረገውን የመሪዎች ጉባኤ በሚመለከት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የነሐሴ 8, 1997 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 12-14ን ተመልከት።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ልጃችሁ በቂ ምግብ ይመገባልን?

የጤና ባለሞያዎች አንድ ሕፃን ከተመጣጠነ ምግብ አንጻር ጤንነቱ የተጠበቀ መሆኑን የሚገመግሙት እንዴት ነው? ልዩ ልዩ ምልክቶችን ሊመረምሩ፣ ስለ አመጋገብ ልማዱ ጥያቄዎችን ሊጠይቁና የላብራቶሪ ምርመራ እንዲደረግ ትዕዛዝ ሊሰጡ ይችላሉ። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ የሚንተራሱት በማያወላውሉ መለኪያዎች ላይ ነው። የልጁን ሰውነት ይለኩና ከማመሳከሪያ መሥፈርቶች ጋር ያነጻጽሩታል። ይህም የተመጣጠነ ምግብ እጥረቱን ዓይነትና ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ ለመወሰን ይረዳቸዋል።

በመጀመሪያ የልጁን ክብደት፣ ቁመትና የእጅ ዙሪያ ይለካሉ። የልጁን ክብደትና ዕድሜ ማነጻጸር በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምን ያህል እንደተጎዳ ለማወቅ ይረዳቸዋል። ሕፃኑ በጣም ተጎድቶ ከሆነ ሰውነቱ የሟሸሸና በጣም የከሳ ይሆናል። የሕፃኑ ክብደት ከተለመደው ክብደት ጋር ሲነጻጸር ከ40 በመቶ በላይ ያነሰ ከሆነ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ የደረሰበት ጉዳት በጣም ከባድ እንደሆነ የሚቆጠር ሲሆን ከ25 እስከ 40 በመቶ ካነሰ መካከለኛ፣ ከ10 እስከ 25 በመቶ ካነሰ ደግሞ አነስተኛ እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል። ከዕድሜው አንጻር ሲታይ ቁመቱ በጣም አነስተኛ ከሆነ ሕፃኑ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ቀጫጫ እንደሆነና ችግሩም ሥር የሰደደ እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ ይችላል።

በጣም ከባድ የሆኑት የፕሮቲንና የኃይል ሰጪ ምግቦች እጥረት ማራስመስ እና ክዋሸኮር የሚባሉ ወይም የሁለቱም ጥምረት በሽታ ሊያስከትሉ ይችላሉ። ማራስመስ (ቀስ በቀስ እየሟሸሹ መሄድ) የሚከሰተው ከ6 እስከ 18 ወር ዕድሜ ባላቸው በሚጠቡ ሕፃናት ላይ ነው። ይህም የሚከሰተው ሕፃናትን በቂ የጡት ወተት ካለማጥባት ወይም በእናት ወተት ምትክ በውኃ የቀጠነ ወተት በማጠጣት ካሎሪና የተመጣጠነ ምግብ በመጉደላቸው ምክንያት የሚከሰት ሥር የሰደደ ችግር ነው። የሕፃኑ ክብደት በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስ ሲሆን ቆዳው ከአጥንቱ ጋር እስኪጣበቅ ድረስ ጡንቻዎቹ በጣም የከሱ ናቸው። እድገቱም በጣም የተገታ ነው። የሕፃኑ “ፊት የአዋቂ ሰው መልክ” ያለው ሲሆን ነጭናጫና አልቃሻ ነው።

ክዋሸኮር የሚለው አጠራር “የተነጠለ ልጅ” የሚል ትርጉም ካለው ከአንድ የአፍሪካ ቋንቋ የተወሰደ ነው። ይህም የሚያመለክተው በላዩ ላይ ሌላ ልጅ በመወለዱ ምክንያት ከእናቱ ጡት የተነጠለ ልጅን ነው። ይህ ሁኔታ የሚከሰተው ሕፃኑ ጡት በሚጥልበት ጊዜና የካሎሪ ጉድለትን ጨምሮ ከፍተኛ የሆነ የፕሮቲን እጦት ሲያጋጥም ነው። ሰውነቱ ውኃ ይቋጥርና በልጁ እጆችና እግሮች ላይ የእብጠት እንዲሁም በሆዱ ላይ የመነፋት ሁኔታ ይታይበታል። አንዳንድ ጊዜ ፊቱንም ያሳብጠውና እንደ ሙሉ ጨረቃ ክብ ፊት ይኖረዋል። ቆዳው ይቆስላል፣ የፀጉሩ ቀለም ይለወጣል እንዲሁም ይሳሳል። ይህ ሁኔታ ያለባቸው ልጆች የጉበት እብጠት የሚታይባቸው ከመሆኑም በላይ የፈዘዙ ናቸው። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ኤሪክም የገጠመው ሁኔታ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነው። የክዋሸኮር በሽታ ሊይዘው የቻለው ከተወለደ በኋላ እናቱ ለአንድ ወር ብቻ ጡት ካጠባችው በኋላ ብዙ ውኃ የተበረዘበት የላም ወተት ትሰጠው ስለነበር ነው። በሦስት ወሩ የአትክልት ሾርባና የስኳር ውኃ እየተሰጠው አንዲት ጎረቤት እንድትጠብቀው ይደረግ ነበር።

ሦስተኛው ዓይነት የፕሮቲንና የኃይል ሰጪ ምግቦች እጥረት የማራስመስን እና የክዋሸኮርን ባሕርይ አጣምሮ የያዘ ነው። ለሦስቱም በሽታዎች በጊዜው ሕክ​ምና ካልተደረገላቸው ሞት የሚያስከትሉ ሊሆኑ ይችላሉ።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ልጃችሁን ከተመጣጠነ ምግብ እጥረት ጠብቁ!

▪ የእናቲቱን ምግብ ማሻሻል በጣም አስፈላጊ ነው። ነፍሰ ጡሮችና የሚያጠቡ እናቶች ተጨማሪ ካሎሪና ፕሮቲን ያስፈልጋቸዋል። በተለይ ደግሞ ፕሮቲን ያላቸው ምግቦች እናቲቱ ብዙ ወተት እንዲኖራት ይረዳሉ። ስለዚህ ያላችሁ ምግብ ጥቂት በሚሆንበት ጊዜ ልጅ በመውለጃ ዕድሜ ላይ ለሚገኙ ሴቶችና ለትንንሽ ልጆች ቅድሚያ ስጡ።

▪ በሁሉም ሁኔታዎች ለማለት ይቻላል ለሕፃን ልጅ ከሁሉ የተሻለው ምግብ የእናቱ ጡት ነው። የእናት ጡት ወተት ሕፃኑን ከበሽታ ለመከላከል የሚያስችሉ ፀረ ተሕዋስያን ያሉት በመሆኑ አንድ ሕፃን በተለይም ደግሞ ከተወለደ በኋላ ባሉት ጥቂት ቀናት የእናቱን ጡት መጥባቱ አስፈላጊ ነው። በመጀመሪያዎቹ አራት ወራት የጡት ወተት ሕፃኑ በተገቢው ሁኔታ ለማደግና ለመፋፋት የሚያስፈልጉት ሁሉም ዓይነት ተመጣጣኝ ምግቦች አሉት።

▪ በአራትና በስድስት ወር መካከል የእናቱ ወተት ዋና ምግብ ሆኖ ቢቀጥልም ሕፃኑ ሌላ ዓይነት ምግቦችንም ለመመገብ ዝግጁ ይሆናል። ቀስ በቀስ የተፈጩ ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን እንዲሁም አዳዲስ ምግቦችን መብላት አስለምዱት። ከአንድ ምግብ ጋር ከተዋወቀ ከሁለት ወይም ከሦስት ቀን በኋላ ሌላ እንዲቀምስ አድርጉ። እርግጥ ነው ሕፃኑ አንድን ምግብ ከመውደዱ በፊት በትዕግሥት ተደጋጋሚ ሙከራ ማድረግ ያስፈልጋል። እንዲህ ያለውን ምግብ ከማዘጋጀት በፊት ሁሉም ነገር በጣም ንጹሕ መሆን እንዳለበት አትዘንጉ! ምግቦቹንና ዕቃዎቹን በሚገባ እጠቡ!

▪ በአምስትና በዘጠኝ ወር ዕድሜ መካከል ያሉ ሕፃናት በአጠቃላይ የእናት ጡት ወተት ከሚሰጠው በላይ ካሎሪና ፕሮቲን ያስፈልጋቸዋል። ተስፋ ሳትቆርጡ አለማቋረጥ አዳዲስ ምግቦችን አስተዋውቁት። ለሕፃናት ተብለው የተዘጋጁ የጥራጥሬና የአትክልት ምግቦችን በማስቀደም ሥጋና የላም ወተት ውጤቶችን ማስከተል ይቻላል። የጥራጥሬና አትክልት ምግቦችን ከፈጩ በኋላ በማጥለል ከአሰራቸው መለየት የሚያስፈልግ ሲሆን ሕፃኑ ስድስት ወር ከሆነው በኋላ ግን በደቃቁ መክተፍ ይቻላል። ጨውና ስኳር መጨመር አስፈላጊም የሚደገፍም አይደለም።

▪ ከስምንት ወር በኋላ የእናት ጡት ወተት ለሕፃኑ መሠረታዊ ምግብ መሆኑ ቀርቶ ማሟያ ብቻ ይሆናል። ሕፃኑ ቤተሰቡ የሚመገበውን ምግብ መብላት ይችላል። ምግቡ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ በንጽሕና መዘጋጀት ያለበት ሲሆን በቀላሉ እንዲታኘክለት በደቃቁ የተከተፈ መሆን አለበት። ተስማሚ የሆነው ምግብ ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን፣ እህልንና ጥራጥሬዎችን፣ ሥጋና የወተት ውጤቶችን ይጨምራል። * በተለይ ልጆች በቫ​ይታሚን ኤ የበለጸጉ ምግቦች ያስፈልጓቸዋል። በቫይታሚን ኤ ከበለጸጉ ምግቦች ውስጥ ለአብነት ያህል የእናት ጡት ወተት፣ ጠቆር ያሉ አረንጓዴ ቅጠላቅጠሎችና ብርቱካንማ ወይም ቢጫ ቀለም ያላቸው ፍራፍሬዎች እንዲ​ሁም እንደ ማንጎ፣ ካሮትና ፓፓያ ያሉት አትክልቶች ይገኙበታል። ከሦስት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት በቀን ውስጥ አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መመገብ አለባቸው።

▪ የተቻለውን ያህል በተለያየ መልክ የቀረቡ ብዙ ዓይነት ምግቦች ልጃችሁን ከበሽታ ለመጠበቅ የሚያስፈልጉ ገንቢ ምግቦችን ይሰጣሉ። እናትዬው ልጅዋ ከጠገበ በኋላ አስገድዳ ከመመገብ ወይም ልጅዋ ለመብላት በሚፈልግበት ጊዜ ከመከልከል በመቆጠብ ልጅዋን ጥሩ ምግብ ለመመገብ ጥረት ማድረግ ይኖርባታል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.43 ለተጨማሪ ማብራሪያ የሰኔ 2002 ንቁ! መጽሔት እትም ላይ የወጣውን “የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት ይቻላል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[ሥዕል]

ምንጊዜም ለማለት ይቻላል፣ አዲስ ለተወለደ ሕፃን ከእናቱ ጡት ወተት የተሻለ ምግብ እንደሌለ ስለ ምግብ ያጠኑ ባለሞያዎች ይናገራሉ

[ምንጭ]

© Caroline Penn/Panos Pictures

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቡታን በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ልጆች የስንዴ ቆሎና አትክልት ሲመገቡ

[ምንጭ]

FAO photo/WFP Photo: F. Mattioli

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የልጃችሁን የአመጋገብ ልማድ ለማሻሻል በግለሰብ ደረጃ እርምጃ መውሰድ ትችላላችሁ

[ምንጭ]

FAO photo