በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሶርያ—የጥንታዊ ታሪክ አሻራ

ሶርያ—የጥንታዊ ታሪክ አሻራ

ሶርያ—የጥንታዊ ታሪክ አሻራ

በጥንታዊው ዓለም ዋነኛ መተላለፊያ አገር ናት። ከሜዲትራንያን ወደ ቻይና እንዲሁም ከግብጽ ወደ አናቶልያ የሚያመሩ ቅፍለቶች ማለፊያ መንገድ ናት። የአካድ፣ የባቢሎን፣ የግብጽ፣ የፋርስ፣ የግሪክና የሮማ ጦር ሠራዊቶች የረገጧት ምድር ናት። ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላም ቱርኮችና የመስቀል ጦረኞች አልፈውባታል። በዘመናችን ደግሞ የፈረንሣይና የብሪታንያ ሠራዊቶች ቅኝ ግዛታቸው ለማድረግ ጦር ተማዘውባታል።

ዛሬ ይህ አካባቢ በከፊል ከሺህ ዓመታት በፊት ይታወቅበት የነበረውን ሶርያ የሚል ስያሜ እንደያዘ ይገኛል። አካባቢው ብዙ ለውጦችን ያሳለፈ ቢሆንም አሁንም የቀድሞ ታሪክ ጥሎት ያለፈው አሻራ አልጠፋም። ሶርያ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ የምትጫወተው ሚና ስለነበራት ይህ ምድር በተለይ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ትኩረት ይስባል።

ደማስቆ​—⁠ጥንታዊት ከተማ

የሶርያ ዋና ከተማ የሆነችውን ደማስቆን በምሳሌነት እንውሰድ። ከተቆረቆረችበት ጊዜ ጀምሮ ነዋሪ አጥታ የማታውቅ ጥንታዊት ከተማ እንደሆነች ይነገርላታል። ደማስቆ በሊባኖስ ትይዩ ከሚገኘው የተራራ ሰንሰለት በስተግርጌ የምትገኝና የበረዳ ወንዝ መሐል ለመሐል ሰንጥቆ የሚያልፋት ከተማ ስትሆን በሶርያ ምድረ በዳ ጠርዝ ላይ የምትገኝ ደስ የምትል የበረሐ ገነት ናት። የእስራኤላውያን አባት የሆነው አብርሃም ወደ ከነዓን በሚያመራበት ጊዜ በዚህች ከተማ ሳያልፍ አልቀረም። “የደማስቆ ሰው” የሆነውን ኤሊዔዘርን ያገኘውና ሎሌው አድርጎ የወሰደው ከዚህ ነበር።​—⁠ዘፍጥረት 15:​2

አንድ ሺህ ዓመት ከሚያህል ጊዜ በኋላ የሱባ ሶርያዊ ነገሥታት የእስራኤል ንጉሥ ከነበረው ከሳኦል ጋር ተዋግተዋል። (1 ሳሙኤል 14:​47) የእስራኤል ሁለተኛ ንጉሥ የነበረው ዳዊትም ከረአብ (ለሶርያ የተሰጠ የዕብራይስጥ ስም) ነገሥታት ጋር ተዋግቶ ድል ከነሳቸው በኋላ “በደማስቆ ሶርያ ጭፍሮች አኖረ።” (2 ሳሙኤል 8:​3-8) በዚህ መንገድ በእስራኤልና በሶርያ መካከል ለረዥም ዘመናት የቆየ ጠላትነት ሊኖር ችሏል።​—⁠1 ነገሥት 11:​23-25

በአንደኛው መቶ ዘመን እዘአ ላይ በሶርያውያንና በአይሁዳውያን መካከል የነበረው ጠላትነት ጋብ ያለ ይመስላል። እንዲያውም በዚህ ጊዜ በደማስቆ በርካታ የአይሁድ ምኩራቦች ነበሩ። በኋላ ጳውሎስ የተባለው የጠርሴሱ ሳውል ወደ ክርስትና በተለወጠ ጊዜ ከኢየሩሳሌም ወደ ደማስቆ በሚወስደው መንገድ ላይ እንደነበር ታስታውስ ይሆናል።​—⁠ሥራ 9:​1-8

በዘመናዊቷ ደማስቆ አብርሃም በዚያ ማለፉን ወይም ዳዊት ወርሯት እንደነበረ የሚያሳይ ማስረጃ አናገኝም። ይሁን እንጂ የጥንቱ የሮማውያን ከተማና በጥንት ሮማውያን ዘመን ቪያ ሬክታ የሚባለውና በአሮጌው ከተማ ያልፍ የነበረው ዋነኛ ጎዳና (ቅን የተባለ ጎዳና) ቅሬታዎች አሁንም አሉ። ሳውል ከደማስቆ ወጣ ብሎ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ወደ ክርስትና ከተለወጠ በኋላ ከሐናንያ ጋር የተገናኘው በዚህ ጎዳና ላይ በሚገኝ ቤት ውስጥ ነበር። (ሥራ 9:​10-19) ዛሬ ያለው ጎዳና በሮማውያን ዘመን ከነበረው ፈጽሞ የተለየ ቢሆንም ሐዋርያው ጳውሎስ የሰባኪነት ሥራውን የጀመረው በዚሁ ቦታ ነበር። ቅን ጎዳና የሚያልቀው በሮማውያኑ የባብ ሻርቂ በር ነው። የከተማይቱ ቅጥሮች ከአናታቸው ቤት የተሠራባቸው እንደነበሩ መገንዘባችን ጳውሎስ በቅርጫት ተደርጎ ከቅጥሩ እንዲወርድና እንዲያመልጥ የተደረገበትን ሁኔታ እንድንረዳ ያስችለናል።​—⁠ሥራ 9:​23-25፤ 2 ቆሮንቶስ 11:​32, 33

ፓልሚራ​—⁠ታሪካዊት የበረሐ ገነት

ከደማስቆ በስተሰሜን ምሥራቅ ለሦስት ሰዓት ያህል በመኪና ከተጓዝን በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተድሞር ተብላ ትጠራ የነበረችውን ፓልሚራን እናገኛለን። (2 ዜና መዋዕል 8:​4) በዚች ከተማ በርካታ የመሬት ቁፋሮ ጥናት ተደርጓል። ይህች የበረሐ ገነት በሜዲትራንያን ባሕርና በኤፍራጥስ ወንዝ አጋማሽ ላይ የምትገኝ ሲሆን በስተሰሜን ከሚገኙት ተራሮች የሚፈልቁት ምንጮች ያጠጧታል። በሜሶጶጣሚያና በስተምዕራብ በሚገኙት አገሮች መካከል የሚያልፈው የንግድ ጎዳና በስተ ሰሜን በሜዲትራንያን ባሕር ደቡባዊ ምሥራቅ ዳርቻዎች የሚገኙትን ለም መሬቶች ተከትሎ እስከ ፓልሚራ ሰሜናዊ ጫፍ ድረስ ይዘልቃል። ይሁን እንጂ በአንደኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በስተሰሜን ባሉት አገሮች በተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ይበልጥ አጠር ያለ ደቡባዊ መንገድ ማግኘት አስፈላጊ ሆነ። በዚህ የተነሣ ፓልሚራ ከፍተኛ ዝናና ብልጽግና አገኘች።

ፓልሚራ በምሥራቃዊው የሮማ ግዛት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በሩቁ ለመከላከል የምትጠቅም ከተማ በመሆኗ የሮማ ክፍለ ግዛት የነበረችው የሶርያ ክፍል እንድትሆን ቢደረግም የኋላ ኋላ ነጻ ግዛት ሆናለች። ትላልቅ ምሰሶዎች በተተከሉበት አስደናቂ ጎዳና ላይ ትላልቅ ቤተ መቅደሶች፣ ቅስቶች፣ መታጠቢያ ቤቶችና ቲያትር ቤቶች ተሠርተዋል። በጎዳናው ዳርና ዳር የተሠራው የእግረኛ መንገድ በደንብ የተነጠፈ ሲሆን ዋናው ጎዳና ግን ለግመሎች እንዲመች ተብሎ አልተነጠፈም። በምሥራቅ ከቻይናና ከሕንድ፣ በምዕራብ ደግሞ ከግሪክና ሮማ አካባቢ የሚነሱት የነጋዴ ቅፍለቶች በፓልሚራ ቆይታ ያደርጉ ነበር። እዚያም ሲቆዩ በሐር ጨርቆች፣ በቅመሞችና ባመጧቸው ሌሎች ሸቀጦች ላይ የሚጫነውን ቀረጥ እንዲከፍሉ ይገደዱ ነበር።

ፓልሚራ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰችበት በሦስተኛው መቶ ዘመን እዘአ ነዋሪዎቿ 200, 000 ደርሰው ነበር። የሥልጣን ጥመኛ የነበረችው ዘኖቢያ ከሮማ ግዛት ጋር ሰይፍ የተማዘዘችውና በመጨረሻም በ272 እዘአ ድል የተነሳችው በዚህ ጊዜ ነበር። ዘኖቢያ በዚህ መንገድ ነቢዩ ዳንኤል ከ800 ዓመታት በፊት የተናገረውን ትንቢት ሳታውቀው በከፊል ፈጽማለች። * (ዳንኤል ምዕራፍ 11) ዘኖቢያ ድል ከተነሳች በኋላ ፓልሚራ ስትራቴጅያዊ ጠቀሜታ ያላት የሮማ ግዛት ከተማ ሆና ብትቆይም የቀድሞ ኃያልነቷንና ግርማዋን ልታገኝ አልቻለችም።

ጉዞ ወደ ኤፍራጥስ

ከፓልሚራ ሰሜናዊ ምሥራቅ ከሦስት ሰዓት የመኪና ጉዞ በኋላ ዳይር አዝ ዛውር የተባለችው ከተማ ትገኛለች። እዚህ ሆኖ ታላቁን የኤፍራጥስ ወንዝ ማየት ይቻላል። ይህ ታሪካዊ ወንዝ በምሥራቅ አናቶልያ (እስያዊ ቱርክ) ከሚገኙት ተራሮች ይወጣና ከከርከሚሽ በስተሰሜን ወደ ሶርያ ገብቶ ወደ ደቡብ ምሥራቅ ካቋረጠ በኋላ ወደ ኢራቅ ይገባል። በኢራቅ ድንበር አካባቢ የሁለት ጥንታዊ የሶርያ ከተሞች ፍርስራሽ ይገኛል።

በደቡብ ምሥራቅ 100 ኪሎ ሜትር ያህል ወረድ ብሎ በኤፍራጥስ ወንዝ መጠምዘዣ ላይ ዱራ-ዩሮፖስ የተባለችው የጥንትዋ ባለ ቅጥር ከተማ ፍርስራሽ ይገኛል። አሁንም 25 ኪሎ ሜትር ያህል ወረድ ብሎ ደግሞ ማሪ የተባለችው ከተማ ትገኛለች። በአንድ ወቅት በጣም ባለጠጋ የነበረችውን ይህችን የንግድ ከተማ በ18ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ያወደመው ባቢሎናዊው ንጉሥ ሐሙራቢ ነበር። ከቤተ መንግሥቱ አብያተ መዛግብት ቢያንስ 15, 000 የሚያህሉ ጽሑፍ የሰፈረባቸው የሸክላ ጽላቶች የተገኙ ሲሆን በእነዚህ ጽሑፎች አማካኝነት በርካታ የታሪክ መረጃ ለማግኘት ተችሏል።

የሐሙራቢ ጭፍሮች ከተማይቱን ባወደሙበት ጊዜ የላይኞቹን ግድግዳዎች አፍርሰው የታችኞቹን ክፍሎች አፈርና ሸክላ ሞልተውባቸው ነበር። በዚህ ምክንያት የግድግዳዎቹ ቀለም ቅብ ሥዕሎች፣ ሐውልቶች፣ የሸክላ ዕቃዎችና ሌሎች በርካታ ቅርሶች ሳይበላሹ ቆይተው በ1933 አንድ የፈረንሣይ የመሬት ቁፋሮ ጥናት ቡድን ሊያገኛቸው ችሏል። እነዚህ ቅርሶች በደማስቆ፣ በአሌፖና በፓሪስ ሉቭር በሚገኙ ቤተ መዘክሮች ውስጥ ይታያሉ።

የሰሜናዊ ምዕራብ ሶርያ ጥንታዊ ከተሞች

የኤፍራጥስን ወንዝ ተከትለን ወደ ሰሜናዊ ምዕራብ በምናቀናበት ጊዜ አሌፖን (ሐለብ) እናገኛለን። አሌፖም እንደ ደማስቆ ለረዥም ዘመናት ነዋሪ አጥተው ከማያውቁ ጥንታዊ የዓለም ከተሞች አንዷ እንደሆነች ይነገርላታል። የአሌፖ ሱቆች በጣም ከሚያማምሩ የመካከለኛው ምሥራቅ ሱቆች የሚቆጠሩ ናቸው።

ከአሌፖ በስተደቡብ የጥንቷ የኤብላ ከተማ ግዛት የነበረችበት ቦታ ይገኛል። ኤብላ በሦስተኛው ሺህ ከዘአበ አጋማሽ ላይ ሰሜናዊ ሶርያን በበላይነት ትቆጣጠር የነበረች ኃያል የንግድ ከተማ ነበረች። በዚህ አካባቢ በተደረገ የመሬት ቁፋሮ አስታሮት ትባል የነበረችው የባቢሎናውያን ሴት አምላክ ቤተ መቅደስ ሊገኝ ችሏል። በተጨማሪም ቤተ መንግሥት የተገኘ ሲሆን በዚህ ቤተ መንግሥት አብያተ መዛግብት ውስጥ 17, 000 የሸክላ ጽላቶች ተገኝተዋል። ከኤብላ የተገኙ ቅርሶች 25 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኘው በኢድሊብ ቤተ መዘክር ውስጥ ይታያል።

በስተደቡብ ወደ ደማስቆ በሚወስደው መንገድ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ሐማት ብሎ የሚጠራት የሐማ ከተማ ትገኛለች። (ዘኍልቁ 13:​21) በመሐሏ የሚያልፈው የኦሮንተስ ወንዝ ሐማትን በጣም ከሚያምሩት የሶርያ ከተሞች አንዷ እንድትሆን አስችሏታል። ከዚያ በኋላ ደግሞ ኡጋሪት የተባለችው የጥንት ከተማ ትገኝ የነበረበት ራስ ሻምራ የሚባለው ቦታ ይገኛል። በሦስተኛውና በሁለተኛው ሺህ ዓመት ከዘአበ ኡጋሪት በጣም የበለጸገች የበዓልና የዳጎን አምልኮ በስፋት ይካሄድባት የነበረች የንግድ ወደብ ነበረች። ከ1929 ወዲህ የፈረንሳይ መሬት ቁፋሮ ተመራማሪዎች በርካታ የሸክላ ጽላቶችና ጽሑፍ የተቀረጸባቸው የነሐስ ዕቃዎች ያወጡ ሲሆን በእነዚህ ቅርሶች አማካኝነት የበዓል አምልኮ ምን ያህል አስነዋሪና ወራዳ እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል። ይህም አምላክ በዓል አምላኪ የነበሩትን ከነዓናውያን ያጠፋበትን ምክንያት እንድንረዳ ያስችለናል።​—⁠ዘዳግም 7:​1-4

አዎን፣ ዛሬም ቢሆን በዘመናዊቷ ሶርያ የጥንቱን ዘመን አሻራዎች ማየት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.12 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ጥር 15, 1999 መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚገኘውን “ባለ ሐር ፀጉሯ የሶርያ በረሐ እመቤት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 26 እና 27 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የሜዲትራንያን ባሕር

‐‐ አከራካሪ ድንበር

ግብጽ

እስራኤል

ዮርዳኖስ

ሊባኖስ

ሶርያ

ደማስቆ

ባራዳ

ኦሮንተስ

ሐማ (ሐማት)

ኡጋሪት (ራስ ሻምራ)

ኤብላ (ቴል ማርዲክ)

አሌፖ (ሐለብ)

ከርከሚሽ (ጀራብሉስ)

ኤፍራጥስ

ዘኖቢያ

ዳይር አዝ ዛውር

ዱራ-ዩሮፖስ

ማሪ

ፓልሚራ (ታድሞር)

ኢራቅ

ቱርክ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ደማስቆ (ከታች) እና የቅን መንገድ (ከላይ)

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የንብ ቀፎ የመሰሉ ቤቶች

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኡጋሪት

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሐማ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማሪ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አሌፖ

[ምንጭ]

© Jean-Leo Dugast/Panos Pictures

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቤተ መንግሥት፣ ኤብላ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እረኞች በዘኖቢያ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፓልሚራ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤፍራጥስ በዱራ-ዩሮፖስ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኙ የሥዕሎቹ ምንጮች]

Children: © Jean-Leo Dugast/Panos Pictures; beehive homes: © Nik Wheeler