በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

የማያውቋቸውን ሰዎች መፍራት

የለንደኑ ዚ ኢንድፐንደንት የተባለው ጋዜጣ “ከሴት አሽከርካሪዎች ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት መኪናቸው ተበላሽቶ ቢቆም የማያውቁት ሰው የሚሰጣቸውን እርዳታ ከመቀበል እዚያው መኪናቸው ውስጥ ተቆልፈው ቢያድሩ ይመርጣሉ” ሲል ዘግቧል። ዳይረክት ላይን ረስኪው የተባለው ድርጅት 2, 000 በሚያህሉ አሽከርካሪዎች ላይ ባደረገው ጥናት ከሴት አሽከርካሪዎች መካከል 83 በመቶ ከወንድ አሽከርካሪዎች መካከል ደግሞ 47 በመቶ የሚሆኑት መኪናቸው ተበላሽቶ ቢቆም የማያውቁት ሰው እርዳታ ለመስጠት የሚያቀርበውን ጥያቄ ለመቀበል ፈቃደኛ እንደማይሆኑ አረጋግጧል። በተመሳሳይም አብዛኞቹ አሽከርካሪዎች መኪና የተበላሸበትን ሰው ለመርዳት እንደማይቆሙ ተናግረዋል። በተለይ ሴቶች መኪና የተበላሸበት ያስመሰለው አደጋ ለማድረስ አስቦ ቢሆንስ ብለው በመፍራት እርዳታ ከመስጠት ይታቀባሉ። የድርጅቱ ቃል አቀባይ የሆኑት ኒክ ኮል “ለብዙ አሽከርካሪዎች ከማያውቁት ሰው ጋር ፊት ለፊት ከመፋጠጥ ይልቅ መኪናቸው ውስጥ ተቆልፈው ሙሉ ሌሊት ማሳለፍ የሚመረጥ ነገር መሆኑ በጣም የሚያሳዝን ነው” ብለዋል።

እምነት የለሾች እምነት ያላቸውን ሲመሩ

የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ሴት ቀሳውስት “በአጠቃላይ ከወንድ ባልደረቦቻቸው ይበልጥ . . . ማዕከላዊ በሆኑ የክርስትና መሠረተ ትምህርቶች ላይ ጥርጣሬ አላቸው” ሲል የለንደኑ ዘ ታይምስ ዘግቧል። ሁለት ሺህ በሚያህሉ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስት ላይ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው “ከአሥር ወንድ ቀሳውስት መካከል ስምንቱ ኢየሱስ የዓለምን ኃጢአት ለማስወገድ እንደሞተ ሲያምኑ” ከአሥር ሴት ቀሳውስት መካከል በዚህ የሚያምኑት ስድስቱ ብቻ ናቸው። በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የሚያምኑት ከአሥሩ ወንዶች ሰባቱ ሲሆኑ ከሴቶቹ መካከል በዚህ የሚያምኑት ከአሥሩ አምስቱ ብቻ ናቸው። ጥናቱን ያካሄደው ኮስት ኦፍ ኮንሽየንስ የተባለ ድርጅት ቃል አቀባይ የሆኑት ሮቢ ሎው “በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁለት የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት እንዳሉ ግልጽ ነው። እነርሱም የሚያምነውና የማያምነው ቤተ ክርስቲያን ናቸው። በጣም የሚያሳፍር ነገር ነው። የሥልጣን ቦታዎች እያደር እምነት በሌላቸው ሰዎች እጅ እየገቡ ናቸው። እምነት ያላቸው እምነት በሌላቸው ሰዎች የሚመሩ መሆኑ ተቀባይነት ሊኖረው የማይገባ ሁኔታ ነው” ብለዋል።

ትዳር ለመምራት በቂ ሥልጠና አላገኙም

በሕግ ከመጋባታቸው በፊት አብረው መኖር ከጀመሩ ባልና ሚስት መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት አሥረኛ የጋብቻ ዓመታቸውን ከማክበራቸው በፊት እንደሚፋቱ የኒው ዮርኩ ዴይሊ ኒውስ ሪፖርት አድርጓል። የጤና ስታትስቲክስ ብሔራዊ ማዕከል ያጠናቀረው አኃዛዊ መረጃም እንደሚያመለክተው ሳይጋቡ እንደ ባልና ሚስት አብረው የሚኖሩና ከተጋቡ አሥር ዓመት የሆናቸው ባልና ሚስቶች ውሎ አድሮ የመፋታት ዕድላቸው በእጥፍ ይበልጣል። የሪፖርቱ ዋነኛ አዘጋጅ የሆኑት ማቲው ብራምሌት “በጋብቻ ለመጣመር የተሳሰቡና በሕግ ሳይጋቡ አብሮ መኖር ተገቢ እንዳልሆነ የሚያምኑ ወንዶችና ሴቶች ወደፊት በፍቺ ለመለያየት ያላቸው ዕድል በጣም የመነመነ ነው” ብለዋል። ከዚህም በላይ በሕግ ከመጋባታቸው በፊት አብረው መኖር የጀመሩ ሰዎች “ትዳሩ የተሳካ እንዲሆን የሚያስፈልገውን ድካምና ችግር ለመቀበል ፈቃደኛ” እንደማይሆኑ የጋብቻ አማካሪ የሆኑት አሊስ ስቲፈንስ ገልጸዋል።

የሟቾች ቁጥር ቀንሷል?

አሶሺዬትድ ፕሬስ ያቀረበው አንድ ሪፖርት “ባለፉት አርባ ዓመታት በድንገተኛ አደጋ ሕክምና ረገድ ብዙ መሻሻል በመደረጉ በሚፈጸምባቸው ጥቃቶች ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ሊቀንስ ችሏል” ይላል። ከ1960 እስከ 1999 ባለው ጊዜ ውስጥ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በወንጀለኞች የሚፈጸሙ ጥቃቶች በስድስት እጥፍ ያደጉ ቢሆንም በእነዚሁ ጥቃቶች ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር 70 በመቶ ያህል ቀንሷል። በተጨማሪም ጥናቱ በ1960 በተፈጸመባቸው ጥቃት ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር 5.6 በመቶ ሲሆን በ1999 የሞቱት ግን 1.7 በመቶ የሚሆኑት ብቻ እንደሆኑ አረጋግጧል። ተመራማሪዎቹ የሟቾቹ ቁጥር ሊቀንስ የቻለው የሕክምና ዘዴዎች በመራቀቃቸው፣ “ቀልጣፋ የሆነ የድንገተኛ አደጋ ጥሪ አገልግሎት በመኖሩ፣ አደጋ የደረሰባቸውን ሰዎች በአፋጣኝ ማጓጓዝና የሕክምና እርዳታ ለመስጠት በመቻሉ፣ የድንገተኛ አደጋ ሕክምና ሠራተኞች የተሻለ ሥልጠና በማግኘታቸውና ሆስፒታሎች በመብዛታቸው ምክንያት እንደሆነ” ሪፖርቱ ገልጿል። በአምኸረስት የማሳቹሰትስ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት አንተኒ ሐሪስ “ከ20 ዓመታት በፊት ወደ ሬሳ ቤት መሸኘታቸው የማይቀር የነበሩ በሽተኞች ዛሬ በጥቂት ቀናት ውስጥ ታክመውና ድነው ወደ ቤታቸው ለመመለስ ችለዋል” ብለዋል።

ሀብትና ጤና ቢኖርም ተስፋ ቢስነት በዝቷል

“ባለፉት ሦስት ዓመታት ተከታታይ የሆነ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሻሻል እንደነበረ” በ2001 ሪፖርት ላይ ቢገለጽም ካናዳውያን የወደፊቱ ኑሯቸው ብሩህ ሆኖ እንደማይታያቸው ዘ ቶሮንቶ ስታር ገልጿል። በካናዳ የማኅበራዊ እድገት ጉባኤ ባልደረቦች የሆኑ ተመራማሪዎች “ካናዳውያን ከቀድሞው ይበልጥ ባላቸው ገንዘብ እንደማይተማመኑ፣ በሥራቸው ላይ የበለጠ ውጥረት እንደሚያጋጥማቸው፣ ችግር ቢያጋጥማቸው የማኅበራዊ ዋስትና አገልግሎቶች ይደርሱልናል ብለው እንደማይተማመኑና ወንጀል ይፈጸምብናል የሚል ፍርሃት እንዳለባቸው” አረጋግጠዋል። አሳሳቢ ከሆኑባቸው ነገሮች መካከል “የደመወዝ ጭማሪ ከኑሮ ውድነት ጋር የሚመጣጠን አለመሆኑ፣ ከፍተኛ ዕዳ ውስጥ መዘፈቅ፣ . . . የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ብዙ ወረፋ ለመጠበቅ መገደድ፣ የመድኃኒቶች ዋጋ እያሻቀበ መሄድ፣ በትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚደርስ ጉዳት እየጨመረ መሄድ፣ በቂ ምክንያት ባይኖረውም በወንጀል ምክንያት አደጋ ይደርስብኛል የሚል ስጋት ከቀድሞው ይበልጥ መስፋፋቱ” ይገኙበታል። የሪፖርቱ አዘጋጆች “የደህንነት ስሜት የአስተሳሰብ ጉዳይ ነው ካልን የምንጓዘው ወደተሳሳተ አቅጣጫ ነው ማለት ነው” ብለዋል።

ቤተ ክርስቲያን ለማግኘት የሚደረግ ፍለጋ

“አንዴ ሜቶዲስት የሆነ ሁሌም ሜቶዲስት ነው የሚባል አባባል ነበረ። አሁን ግን ይህ የቀረ ነገር ሆኗል” ይላል ዘ ሳክራሜንቶ ቢ ያቀረበው ሪፖርት። በሳክራሜንቶ የሃይማኖቶች ውሕደት አገልግሎት ቢሮ ዳይሬክተር የሆኑት ማክናማራ “በአሁኑ ጊዜ የአንድ ሃይማኖት አባል መሆን አሳሳቢ ነገር መሆኑ እየቀረ መጥቷል። . . . ዛሬ ሰዎች የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናትን ለመሞከር ይበልጥ ፈቃደኞች እየሆኑ መጥተዋል” ብለዋል። ምዕመናኖች ቤተ ክርስቲያኖችን በሚያማርጡበት ጊዜ ሙዚቃውን፣ የአምልኮ ሥርዓቱን፣ አምልኮው የሚፈጀውን የጊዜ ርዝመት፣ ለወጣቶች የሚዘጋጀውን ፕሮግራም፣ የአባላቱን ብዛት፣ የቦታውን ርቀትና የመሳሰሉትን ነገሮች ግምት ውስጥ ያስገባሉ። የሐዋርድ የቤተሰብ፣ የሃይማኖትና የማኅበረሰብ ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት አለን ካርልሰን “እንደልብ ማማረጥ የሚቻልበት ሰፊ ገበያ አለ። በ1950 ለአቅመ አዳም ከደረሱ ሰዎች መካከል 85 በመቶ የሚሆኑት የወላጆቻቸውን ሃይማኖት የሚከተሉ ነበሩ።” አሁን ግን ‘ሌላ ብዙ ምርጫ አላቸው’ ብለዋል።

በጆርጅያ ሃይማኖታዊ ጥላቻ ተባብሷል

ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ላይ የወጣ አንድ ሪፖርት “የይሖዋ ምሥክሮች በአንድ ወንዝ አጠገብ በሚገኝ ሜዳ ላይ ሃይማኖታዊ ስብሰባ ለማድረግ አቅደው ነበር። ሆኖም በዋዜማው ምሽት ሴረኞች ጥቃት ፈጸሙባቸው” በማለት ይናገራል። “ሃያ አራት የሚያህሉ የጆርጅያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን መስቀል ያነገቱ ሰዎች በአውቶቡስ መጡና የስብሰባው አስተናጋጅ የነበረውን የኡሻንጊ ቡንቱሪን ቤት መበርበር ጀመሩ። መጽሐፍ ቅዱሶችን፣ ሃይማኖታዊ በራሪ ጽሑፎችንና የሚስተር ቡንቱሪን ንብረቶች ወደ ውጭ አውጥተው ከከመሩ በኋላ አቃጠሉ። . . . የመጠመቂያውን ገንዳ በናፍጣ ሞሉት። ፖሊሶችም፣ የጣቢያው አዛዥ ሳይቀር፣ ሄደው ነበር . . . ሆኖም አንድም የተያዘ ሰው አልነበረም . . . የተፈጸመው ጥቃት አስቀድሞ የተጠናና የተቀነባበረ ይመስል ነበር።” “ሩስያን ጨምሮ በብዙዎቹ የቀድሞዋ ሶቪዬት ኀብረት ሪፑብሊኮች” ሃይማኖታዊ ውጥረት እንደነበረ የሚታወቅ ቢሆንም ይላል ታይምስ “አናሳ በሆኑ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ላይ በሚፈጸመው ስደት መጠንና ባለ ሥልጣናት ጥቃቱን ከሚፈጽሙት ሰዎች ጋር ተባባሪ በመሆናቸው ረገድ ጆርጅያን የሚወዳደር አልተገኘም። ጆርጅያ በድኅረ ሶቭዬት ሕገ መንግሥትዋ የሃይማኖት ነጻነትን እንደምታከብር ደንግጋለች። ይሁን እንጂ እየጨመረ በሄደው ዓመፅ በደርዘን የሚቆጠሩ ከባድ ድብደባዎችና ጥቃቶች ተፈጽመዋል።”

ወጣቶች ወደ “መዝናኛ ቤተ ክርስቲያን” ይጎርፋሉ

ናሳውኢሸ ኖየ ፕሬሰ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ “ወጣቶች ‘ለመዝናኛ ቤተ ክርስቲያን’ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል” በሚል ርዕስ ሥር የሄሰ እና የናሳው ፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ ስላዘጋጀው የቤተ ክርስቲያን ወጣቶች ቀን ዘግቧል። ለአምስት ቀን በቆየው በዓል ላይ 4, 400 የሚያህሉ ወጣቶች ተገኝተዋል። በፕሮግራሙ ላይ ችግሮችን እንዴት መፍታት እንደሚቻል የሚያሳዩ ፕሮግራሞች፣ የቡድን ውይይቶች፣ በሻማዎችና በመዝሙሮች የታጀቡ የምሽት አገልግሎቶች፣ ብዙ የስፖርት ዓይነቶች፣ ድግሶችና የሙዚቃ ዝግጅቶች ተካተዋል። “ሁለት መቶ ሃያ ከሚያህሉት የተለያዩ ዝግጅቶች ውስጥ ያልተካተተው መደበኛ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና የተለመደው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ነበር” ይላል ጋዜጣው። አንድ ወጣት ቄስ በጣም በመገረም “አንዳንድ ወጣቶች አሰልቺ እንደሆነ የሚታወቀው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲዘጋጅላቸው ጠይቀዋል” ብሏል። አንድ ወጣት “መላው ፕሮግራም ከቤተ ክርስቲያን ጋር የሚዛመድበት አንዳች ነገር አይኑረው እንጂ የነበረው መንፈስ በጣም የሚያስደስት ነበር” ብሏል።

ሃይማኖትና ጦርነት

ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ የተባለው ጋዜጣ “በዛሬው ጊዜ ከሚካሄዱት ግጭቶች መካከል በጣም አደገኛና ደም አፋሳሽ የሆነው . . . ከሃይማኖት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጦርነቶች ናቸው” ብሏል። ለግልግልም በጣም የሚያስቸግሩ ሆነዋል። ጋዜጣው በማከል “ተዋጊ ወገኖች አምላክ ከጎናቸው እንደሆነ በሚያምኑበት ጊዜ ከእኔ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ እንደመሆንና የቆየ ቂምና በቀልን እንደመርሳት ያሉትን የታወቁ የዲፕሎማሲ ዘዴዎች ለመጠቀም አስቸጋሪ ይሆናል” ብሏል። “የግጭቱ ዋነኛ ምክንያት መሬት ወይም ሥልጣን ሆኖ ሃይማኖት የድጋፍ ማሰባሰቢያ መሣሪያ ብቻ በሚሆንበት ጊዜ እንኳን ይህ እውነት መሆኑ ታይቷል።” የሃይማኖት ልዩነት በሚኖርበት ጊዜ ጊዜያዊ የሆነ የተኩስ ማቆም ስምምነት ላይ እንኳን መድረስ አስቸጋሪ ይሆናል። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን በኮሶቮ የተደረገው ጦርነት ነው። በፋሲካ በዓል ወቅት የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ታስቦ ነበር። ይሁን እንጂ ካቶሊኮቹና ኦርቶዶክሶቹ ፋሲካን የሚያከብሩት በተለያየ ዕለት በመሆኑ ስምምነቱን ተግባራዊ ማድረግ አልተቻለም። “በመጨረሻ ተኩስ ለማስቆም ሳይቻል ቀርቷል” ይላል ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ።