በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመምረጥ ነፃነታችንን እንዴት ልንጠቀምበት ይገባል?

የመምረጥ ነፃነታችንን እንዴት ልንጠቀምበት ይገባል?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

የመምረጥ ነፃነታችንን እንዴት ልንጠቀምበት ይገባል?

አምላክ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች አዳምንና ሔዋንን የራሳቸውን ምርጫ የማድረግ ችሎታ አጎናጽፏቸዋል። ለአዳም ኤደን ገነትን የመንከባከብ ኃላፊነት ሰጥቶት ነበር። አዳም በገነት ውስጥ እንዲያከናውናቸው ከተሰጡት ሥራዎች መካከል አንዱ ለእንስሳት ስም ማውጣት ነበር። (ዘፍጥረት 2:15, 19) ከሁሉም በላይ አዳምና ሔዋን አምላክን ለመታዘዝ ወይም ላለመታዘዝ የመምረጥ መብት ነበራቸው።​—⁠ዘፍጥረት 2:17, 18

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሰው ልጆች በብዙ ቢልዮኖች የሚቆጠሩ ውሳኔዎችን አድርገዋል። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ጥሩ ውሳኔዎች የነበሩ ሲሆን አንዳንዶቹ ግን የተሳሳቱ አልፎ ተርፎም መጥፎ ውሳኔዎች ነበሩ። ሰዎች ያደረጓቸው አንዳንዶቹ የተሳሳቱ ምርጫዎች ይህ ነው የማይባል መጥፎ ውጤት አስከትለዋል። ቢሆንም አምላክ በመምረጥ ነፃነታችን ውስጥ ጣልቃ ገብቶ አያውቅም። ልክ እንደ አንድ አፍቃሪ አባት ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግ የሚያስችለንን እርዳታ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ይሰጠናል። እንዲሁም የተሳሳተ ምርጫ ማድረግ ስለሚያስከትለው ጉዳት በቅድሚያ ያስጠነቅቀናል። መጽሐፍ ቅዱስ የዘራነውን እንደምናጭድ ይናገራል።​—⁠ገላትያ 6:7

የግል ጉዳዮችን የሚመለከቱ ውሳኔዎች

አምላክ አንዳንድ ጉዳዮችን በሚመለከት ቀጥተኛ መመሪያዎችን በመስጠት ፈቃዱ ምን እንደሆነ ያሳውቀናል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እያንዳንዱን የግል ጉዳያችንን የሚመለከት ሕግ አስፍሯል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሰዎች የየራሳቸውን ምርጫዎችና ፍላጎቶች እንዲከተሉ የሚያስችሏቸውን ጠቅለል ያሉ መመሪያዎች ይሰጣል። ለምሳሌ ያህል በመዝናኛ ረገድ ምን እንደሚል እንመልከት።

በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ይሖዋ “ደስተኛ አምላክ” ተብሏል። (1 ጢሞቴዎስ 1:​11 NW ) ቃሉ “ለመሳቅም ጊዜ አለው፤ . . . ለመዝፈንም ጊዜ አለው” በማለት ይናገራል። (መክብብ 3:1, 4) መጽሐፍ ቅዱስ ንጉሥ ዳዊት ሌሎችን ለማዝናናት የሙዚቃ መሣሪያ ይጫወት እንደነበር ይገልጻል። (1 ሳሙኤል 16:16-18, 23) ኢየሱስ በሠርግ ግብዣ ላይ በተገኘበት ወቅት ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ በመለወጥ ለዝግጅቱ መሳካት አስተዋጽኦ አድርጓል።​—⁠ዮሐንስ 2:1-10

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል” በማለት ተገቢ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። (ምሳሌ 13:20) “ዋዛ ፈዛዛና” ከሥነ ምግባር ውጭ የሆኑ ድርጊቶች አምላክን የሚያሳዝኑ ከመሆናቸውም በላይ ከእርሱ ጋር ያለንን ዝምድና ሊያበላሹብን ይችላሉ። (ኤፌሶን 5:3-5 አ.መ.ት ) በግብዣዎች ላይ የአልኮል መጠጥ በገፍ የሚቀርብና ያለገደብ የሚጠጣ ከሆነ ከባድ ችግሮች ሊያስከትል ይችላል። (ምሳሌ 23:29-35፤ ኢሳይያስ 5:11, 12) በተጨማሪም ይሖዋ አምላክ ዓመጽን ይጠላል።​—⁠መዝሙር 11:5፤ ምሳሌ 3:31

እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አምላክ ስለ መዝናኛ ያለውን አመለካከት እንድናስተውል ይረዱናል። ክርስቲያኖች ምርጫ ሲያደርጉ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጉዳዩ ምን እንደሚል ግምት ውስጥ ያስገባሉ። እርግጥ ነው፣ ማናችንም ብንሆን ምርጫችን የሚያስከትለውን ጥሩም ሆነ መጥፎ ውጤት መቅመሳችን አይቀርም።​—⁠ገላትያ 6:7-10

ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ ክርስቲያኖች አለባበስን፣ ትዳርን፣ ልጆች ማሳደግንና፣ የንግድ ጉዳዮችን በሚመለከት ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማሙ የጥበብ ውሳኔዎችን እንዲያደርጉ ተበረታተዋል። እነዚህ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በቀጥታ ያልተጠቀሱ ጉዳዮችንም የሚጨምሩ ቢሆንም በሕሊናቸው ተመርተው ውሳኔዎችን ለማድረግ የሚረዷቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች በዚያው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ። (ሮሜ 2:14, 15) “የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” የሚለው መመሪያ ክርስቲያኖች የሚያደርጓቸውን የግል ውሳኔዎች ሁሉ በሚመለከት ይሠራል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 10:31

በዚህ ረገድ ‘በራሳችን ጉዳይ ላይ ብቻ ስለ ማተኮር’ የሚናገረውን መሠረታዊ ሥርዓት ማስታወስ አለብን። (1 ተሰሎንቄ 4:11 አ.መ.ት ) አብዛኛውን ጊዜ ክርስቲያኖች ከአምላክ ፈቃድ ጋር የማይጋጩ የተለያዩ ዓይነት ምርጫዎች ማድረግ የሚጠይቁ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። በመሆኑም የአንድ ክርስቲያን ምርጫ ከሌሎች የሚለይበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። አምላክ አገልጋዮቹ አንዳቸው በሌላው ላይ ሲፈርዱ ቢመለከት አይደሰትም። (ያዕቆብ 4:11, 12) መጽሐፍ ቅዱስ “ከእናንተ ማንም . . . በሌሎች ጉዳይ እንደሚገባ ሆኖ መከራን አይቀበል” በማለት ጥበብ ያዘለ ምክር ይሰጣል።​—⁠1 ጴጥሮስ 4:15

አምላክን ለማገልገል የሚደረገው ውሳኔ

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን መታዘዝ ያለውን ጥቅም አበክሮ ይገልጻል። ቢሆንም አምላክ ሰዎችን እንዲያመልኩት አያስገድዳቸውም። ከዚህ ይልቅ ሰብዓዊ ፍጡሮቹ እንዲያመልኩት ግብዣ ያቀርብላቸዋል። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ “ኑ፣ እንስገድ ለእርሱም እንገዛ፤ በእርሱ ባደረገን በእግዚአብሔር ፊት እንበርከክ” በማለት ይናገራል።​—⁠መዝሙር 95:6

በጥንት ጊዜ የነበሩት እስራኤላውያን እንዲህ ዓይነቱ ግብዣ ቀርቦላቸው ነበር። ከዛሬ 3, 500 ዓመት በፊት የእስራኤል ሕዝብ በሲና ተራራ ፊት ለፊት ሰፍሮ በነበረበት ወቅት አምላክ ለእነዚህ በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች በሙሴ ሕግ ውስጥ የተካተተውን የእውነተኛውን አምልኮ ሥርዓት ገለጸላቸው። ከዚያም አምላክን ለማገልገል ፈቃደኛ መሆናቸውን ወይም አለመሆናቸውን በሚመለከት ምርጫ ቀረበላቸው። ምን ምላሽ ሰጡ? በአንድ ልብ “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን እንታዘዛለንም” አሉ። (ዘጸአት 24:7) ይሖዋን ለማምለክ የወሰኑት በራሳቸው ፍላጎት ተነሳስተው ነበር።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን ምሥራች የመስበኩን ሥራ በግንባር ቀደምትነት ጀምሯል። (ማቴዎስ 4:17፤ 24:14) ሆኖም ይህን ሥራ አብሮት እንዲሠራ ማንንም አላስገደደም። ከዚህ ይልቅ ደግነት በተሞላበት መንገድ ‘ኑ፣ ተከተሉኝ’ በማለት ግብዣ ያቀርብ ነበር። (ማርቆስ 2:14፤ 10:21) ብዙዎች ግብዣውን ተቀብለው ከእርሱ ጋር አብረው መስበክ ጀመሩ። (ሉቃስ 10:1-9) ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን አንዳንዶቹ ትተውት የሄዱ ሲሆን ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ እስከመስጠትም ደርሷል። (ዮሐንስ 6:66፤ ሥራ 1:24, 25) ከጊዜ በኋላ ደግሞ በሐዋርያት አመራር ብዙ ሰዎች ደቀ መዛሙርት ቢሆኑም ይህን ምርጫ ያደረጉት በራሳቸው ፈቃድ እንጂ በኃይል ተገድደው አልነበረም። “ለዘላለም ሕይወትም የተዘጋጁ” ስለነበሩ “አመኑ።” (ሥራ 13:​48፤ 17:​34) ዛሬም በተመሳሳይ እውነተኛ ክርስቲያኖች የአምላክን ቃል የሚታዘዙትና የኢየሱስን ትምህርቶች የሚከተሉት በራሳቸው ምርጫ ነው።

እስካሁን እንደተመለከትነው አምላክ የራሳችንን ምርጫ የማድረግ ችሎታችንን እንድንጠቀምበት ይፈልጋል። እንዲሁም ጥበብ የታከለበት ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳንን መመሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስፍሮልናል። (መዝሙር 25:12) የግል ምርጫን በሚመለከት እያንዳንዱ ክርስቲያን የአምላክን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥንቃቄ ማገናዘብ አለበት። ‘በማመዛዘን ችሎታችን ተጠቅመን ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት’ ማቅረብ የምንችለው እንዲህ ስናደርግ ብቻ ነው።​—⁠ሮሜ 12:1 NW