በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአካን ተረትና ምሳሌዎች—የማኅበራዊ ሥነ ምግባር ነጸብራቆች

የአካን ተረትና ምሳሌዎች—የማኅበራዊ ሥነ ምግባር ነጸብራቆች

የአካን ተረትና ምሳሌዎች—የማኅበራዊ ሥነ ምግባር ነጸብራቆች

ጋና የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ተረትና ምሳሌ ምንድን ነው? አንድ መዝገበ ቃላት “ሰዎች ብዙ ጊዜ የሚጠቅሱትና ስለ ሕይወት አንድ ዓይነት ምክር ወይም መረጃ የሚሰጥ አጭር አረፍተ ነገር ነው” የሚል ፍቺ ሰጥቷል። በናይጄሪያ የሚኖሩት የዮሩባ ጎሣዎች ለተረትና ምሳሌ ይበልጥ ሥዕላዊ የሆነ ፍቺ ሲሰጡ “ሐሳቦችን በትክክል ወደመረዳት የሚያደርስ ፈጣን ፈረስ ነው” ይላሉ።

“ለጠቢብ ሰው በተረትና ምሳሌዎች እንጂ በተራ አነጋገር አይናገሩም” የሚለው የጋናዎቹ የአካን ጎሣዎች ተረት የተረትና ምሳሌን አስፈላጊነት ይገልጻል። ለአዋቂ ሰው የአንድን ነገር ትክክለኛነት ለማሳመን ብዙ ቃል መደርደር አስፈላጊ አይሆንም ለማለት ነው። ተስማሚ የሆነ ተረትና ምሳሌ የማሰብ ችሎታን ይቀሰቅሳል፣ ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ ያነሳሳል፣ ነገሮችን ለመረዳት ያስችላል።

በጋና በጋብቻና በቀብር ሥነ ስርዓቶች እንዲሁም በባሕላዊ ዘፈኖች ተረትና ምሳሌዎችን መጠቀም የተለመደ ነው። በተጨማሪም በዲፕሎማሲያዊ ውይይቶች ወቅት መተኪያ የሌለው አገልግሎት ያበረክታሉ። አንድ መልእክተኛ ወይም ለሽምግልና የተላከ ሰው በተረትና ምሳሌ መጠቀሙ የተለመደ ነገር ነው።

በአካን ማኅበረሰብ ውስጥ በተረትና ምሳሌ ጥሩ አድርጎ መጠቀም የአዋቂነት ምልክት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም በአዋቂነቱ፣ በትምህርቱና በዲፕሎማሲያዊ ጥበበኛነቱ የታወቀው ንጉሥ ሰሎሞን 3, 000 ምሳሌዎችን እንደተናገረ ተገልጿል። እርግጥ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉና ምንጊዜም ትክክለኛና እውነት በመሆናቸው በሰብዓዊ ልምድና ማስተዋል ላይ ከተመሠረቱ ምሳሌዎች የተለዩ ናቸው። የሰዎች ተረትና ምሳሌዎች ምንም ያህል ጥበብ የተንጸባረቀባቸው ቢሆኑ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መተካከል አይገባቸውም። ቢሆንም እስቲ አንዳንዶቹን የአካን ተረትና ምሳሌዎች እንመልከት።

ስለ አምላክ ያላቸው ግንዛቤ

በጋና የአምላክን መኖር የሚቀበሉ ተረትና ምሳሌዎች አሉ። ይህም በብዙዎቹ የአካን ተረትና ምሳሌዎች ላይ ተንጸባርቋል። በአካን ፍልስፍና ውስጥ አምላክ የለሽነት ምንም ዓይነት ቦታ የለውም። ለምሳሌ ያህል አንድ ተረት “አምላክን ለሕጻን ልጅ እንኳን የሚያሳይ የለም” ይላል። የአምላክ መኖር ለሕጻን ልጅ እንኳን ሳይቀር ግልጽ ነው ማለት ነው። ይህ ተረት አንድ ልጅ እምብዛም ትምህርት ሳይሰጠው በራሱ ሊማርና ሊያውቅ የሚችላቸውን ነገሮች ለማመልከት ያገለግላል።

ሌላው የአካን ተረት “ከአምላክ ብትሸሽ ሁልጊዜም ከበታቹ ነህ” ይላል። አምላክን እንደሌለ መቁጠርና ችላ ማለት ራስን ማታለል መሆኑን ያመለክታል። መጽሐፍ ቅዱስም ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት “የእግዚአብሔር ዓይኖች በስፍራ ሁሉ ናቸው፤ ክፉዎችንና ደጎችን ይመለከታሉ” በማለት ተመሳሳይ ቁምነገር ያስጨብጣል። (ምሳሌ 15:3) ሁላችንም ሁሉን በሚችለው አምላክ ፊት ተጠያቂዎች ነን።

የማኅበራዊ እሴቶችና ምግባሮች መግለጫ

የአካን ተረትና ምሳሌዎች እንደሌሎቹ ባሕሎች የማኅበራዊ እሴቶችና ምግባሮች ማከማቻ ናቸው። ለምሳሌ ያህል የሚከተለው ተረት የምንናገረው ቃል ምን ያህል ኃይል እንዳለው ያሳያል። “የምላስ ወለምታ ከእግር ወለምታ ይከፋል።” ምላስ ልጓም ካልተደረገለት ከባድ ጉዳት ከማድረሱም በላይ ሕይወት እስከማሳጣት ሊያደርስ ይችላል።​—⁠ምሳሌ 18:​21

ይሁን እንጂ ተገቢ ቁጥጥር ከተደረገበት የሚከተለው ተረት እንደሚያረጋግጠው ምላስ ሰላም ፈጣሪ ሊሆን ይችላል። “ምላስ ባለበት ጥርሶች አይፋጩም።” ነጥቡ በባልና ሚስት ወይም በማናቸውም ሌሎች ሰዎች መካከል የሚፈጠር ውዝግብ ረጋ ያለ ውይይት ከተደረገበት ጠብ ላይ ሳይደርስ መፈታቱ አይቀርም ማለት ነው። ይህ የማይቻል ቢሆን እንኳን ምላሳቸውን በጥበብ የሚጠቀሙ ሰዎች በሚያደርጉት የሽምግልና ጥረት መፈታቱ አይቀርም።

ተግባራዊ ጥበብ

ተግባራዊ ጥበብን የሚያጎሉ በርካታ ምሳሌያዊ አነጋገሮች የአስተዋይነትንና የአርቆ ተመልካችነትን አስፈላጊነት በጥሩ ሁኔታ ይገልጻሉ። የሚያደርጋቸው ነገሮች ምን መዘዝ እንደሚያስከትሉ ሳያመዛዝን አንድ ነገር ውስጥ ዘው ብሎ የሚገባ ግድየለሽ ሰው ከሚከተለው ተረት ጥሩ ምክር ያገኛል። “እባቡን ከማስቆጣትህ በፊት መውጫህን አሰናዳ።” መጥፎ አዝማሚያ የሚታይበት ልጅ ያለው ወላጅ የሚከተለውን ተረት ልብ ማለት ያስፈልገዋል።

“የሚያድግ ቅርንጫፍ ዓይንህን ሊወጋ ከተቃረበ ንቀለው እንጂ አትመልምለው።” አዎን፣ ማንኛውም መጥፎ ባሕርይ ገና በእምቡጥነቱ መቆረጥ ወይም መነቀል ይኖርበታል እንጂ አቆጥቁጦ ችግር እስኪፈጥር ድረስ መታለፍ አይኖርበትም።

ጸንተው የኖሩ ወጎችንና ባሕላዊ ልማዶችን የሚያመላክቱ ተረትና ምሳሌዎች

አንዳንድ ጊዜ የተረትና ምሳሌዎችን ትርጉም ለመረዳት ባሕሉን ማወቅ አስፈላጊ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል ለአካን ጎሣዎች በሌሎች ፊት በተለይ ደግሞ በአረጋውያን ፊት ግራ እጅን እያነቃነቁ መናገር እንደ ነውር ይቆጠራል። “ወደ ትውልድ አካባቢህ የሚወስደውን መንገድ በግራ እጅህ አትጠቁም” የሚለው ተረት የሚያመለክተው ይህን የሥነ ምግባር ሕግ ነው። በሌላ አነጋገር አንድ ሰው የመጣበትን አካባቢ ጨምሮ ያለውን ነገር በአድናቆት መመልከት አለበት።

በአንድ የአካን ቤት ውስጥ የሚኖረውን ባሕላዊ የገበታ ሥርዓት የሚያመለክት ተረት ደግሞ “እጁን መታጠብ ያወቀ ልጅ ከታላላቆቹ ጋር ይበላል” በማለት ይናገራል። የአንድ ቤተሰብ አባላት ገበታ ላይ በሚቀርቡበት ጊዜ የሚቀመጡት እንደየዕድሜያቸው ነው። ይሁን እንጂ ጥሩ ምግባር ያለው በተለይ በአካላዊ ንጽሕናና ሥርዓት በመጠበቅ ረገድ ጠንቃቃ የሆነ ልጅ የደረጃ እድገት አግኝቶ ከአባቱና ከሌሎች ትላልቅ ሰዎች አጠገብ ተቀምጦ ሊመገብ ይችላል። ተረቱ አንድ ሰው የሚከበረው ከዕድሜው ይልቅ በጠባዩ ምክንያት እንደሆነ አጠንክሮ ያመለክታል።

ለማግባት አስበሃል? ከሆነ የሚከተለውን የአካን ተረት ልብ በል። “ጋብቻ እንደ ቴምር ጠጅ አይቀመስም።” የቴምር ጠጅ የሚሸጡ ሴቶች አብዛኛውን ጊዜ ከመሸጣቸው በፊት ገዥዎቻቸውን ያስቀምሳሉ። ገዥው ቀምሶ ካየ በኋላ ምን ያህል እንደሚገዛ ወይም ጭራሹን ላለመግዛት ይወስናል። ጋብቻ ግን በቅድሚያ ሊቀመስ አይችልም። ይህ ተረት የጋብቻ ሰንሰለት ዘላቂ መሆኑንና የሙከራ ጋብቻ ተቀባይነት እንደሌለው ያመለክታል።

ነገሮችን በጥንቃቄ ማየትና ማመዛዘን

የአካን አባቶች ሰዎችንና እንስሳትን በጥንቃቄ ይመለከቱና ያመዛዝኑ እንደነበረ የሚያሳዩ በርካታ ተረትና ምሳሌዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል የሚከተለው ተረት ዶሮንና ጫጩቶችዋን ልብ ብሎ ከመመልከት የተገኘ ነው። “ከእናቷ ያልራቀች ጫጩት የፌንጣ ጭን ታገኛለች።” ምን ማለት ነው? አንድ ሰው ራሱን ካገለለ ጥሩ ነገር በሚከፋፈልበት ጊዜ በቀላሉ ሊረሳና ሊታለፍ ይችላል።

የሞተች እንቁራሪት የተመለከተ ማንኛውም ሰው የሚከተለውን አባባል ትክክለኛነት መረዳት ከባድ አይሆንበትም። “የእንቁራሪት ሙሉ ቁመት የሚታወቀው ከሞተች በኋላ ነው።” ይህ ተረት የሚተረተው አብዛኛውን ጊዜ የአንድ ሰው ውለታ ሳይታወቅለት በሚቀርበት ጊዜ ነው። እንዲህ ያለው ሰው ጥቅሙና ማንነቱ የሚታወቅለት በሚታጣበት ጊዜ እንደሆነ በመረዳት ይጽናናል።

“በአህጽሮተ ጽሑፍ” የተገለጹ ተረትና ምሳሌዎች

የአካን ተረትና ምሳሌዎች ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የኖሩት በቃል ቢሆንም ምሳሌያዊነት ባላቸው የሥነ ጥበብ ሥራዎች ተጠብቀው የቆዩ ብዙ አባባሎች አሉ። እንደነዚህ ያሉትን የሥነ ጥበብ ሥራዎች በእንጨት ቅርጾች፣ በምርኩዞች፣ በወርቅ መመዘኛዎች፣ በባሕላዊና በዘመናዊ የልብስ ንድፎች ላይ ማየት ይቻላል። የጋና ሥነ ጥበብ አዳራሾችን የጎበኘ ሰው አንድ ሰው ዛፍ ላይ ሲወጣና ሌላው ሰው ሲረዳው የሚያሳይ ሥዕል ይመለከት ይሆናል። “ጥሩ ዛፍ ላይ ከወጣህ ወደላይ የሚገፋህ ሰው አታጣም” የሚለውን ተረት የሚያሳይ ሥዕል ነው። የዚህ ተረት መልእክት ግልጽ ነው። ጥሩና ተገቢ የሆነ ግብ ላይ ለመድረስ የምትጣጣር ከሆነ ድጋፍ ማግኘትህ አይቀርም ማለት ነው።

የቀብር ሥነ ሥርዓቶች አንድ ፀሐፊ እንዳሉት “የጨርቃ ጨርቅ ሥነ ቃል” የሚታይባቸው ጥሩ አጋጣሚዎች ናቸው። የሐዘን ወቅት በመሆኑ በሕይወት ምንነትና ትርጉም ላይ ለማሰላሰል ጥሩ አጋጣሚ ይሰጣሉ። ስለሆነም በቀብር ላይ በሚለበሱ ልብሶች ላይ የሚነደፉ ሥዕሎች ጠለቅ ያለ ፍልስፍና የሚንጸባረቅባቸው ናቸው። ለምሳሌ ያህል ደረጃ ወይም መሰላል የተሳለበት ልብስ “የሞትን መሰላል የሚወጣው አንድ ሰው ብቻ አይደለም” የሚለውን ተረት ያስታውሳል። * ይህ ተረት አንድ ሰው ራሱን ከፍ አድርጎ እንዳይመለከትና ሕይወቱን ሞት ሊደፍረው እንደማይችል በሚመስል ሁኔታ እንዳይመራ ያሳስበዋል።​—⁠መክብብ 7:​2

በአካን ማኅበረሰብ ውስጥ የባሕላዊ ገዥዎች ተወካዮች በተረትና ምሳሌ አጠቃቀም ረገድ በጣም የተካኑ ከመሆናቸውም በላይ ሕዝባቸው ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው የሥነ ምግባር እሴቶች የተቀረጸበት በትር ይይዛሉ። ለምሳሌ ያህል የእባብ ጭንቅላት የያዘች ወፍ የተቀረጸበት ከሆነ “የአንድን እባብ ጭንቅላት መያዝ ከቻልክ የቀረው አካሉ ልክ እንደ ገመድ ይሆንልሃል” የሚለውን አባባል የሚያመለክት አህጽሮት ነው። የሚያስተላልፈው መልእክት ምንድን ነው? ችግሮችህን ፊት ለፊት ተጋፈጥ የሚል መልእክት ያስተላልፋል።

ጨዋነት ያልተለየው የተረት አጠቃቀም

አንድን ተረት እንዴትና መቼ እንደምንጠቀም የሚወስነው እንደማንኛውም ምሳሌ የክርክሩና የአድማጮቹ ሁኔታ ነው። የተረቱ አጠቃቀም አግባብነት የሚጎድለው ከሆነ የክርክሩ አሳማኝነት ሊበላሽ ይችላል። በአንዳንድ ባሕሎች ተረቶችን በአግባቡ መጠቀም የአነጋገር ጨዋነት ከሚገለጥባቸው መንገዶች አንዱ ስለሆነ ተረትን ትክክለኛ በሆነ መንገድ አለመጠቀም ለተናጋሪው መጥፎ ግምት ሊያሰጥ ይችላል።

በጋና የማኅበረሰቡ ሽማግሌዎች የተረቶች ባለ አደራዎችና ደራሲዎች እንደሆኑ ይታሰባል። በዚህ ምክንያት አንድ ተረት ለመናገር ሲታሰብ “ሽማግሌዎቻችን እንደሚሉት . . .” ተብሎ ይጀመራል። ተናጋሪው የሚናገረው በዕድሜ ብዙ ለሚበልጡት ሰዎች ከሆነ ደግሞ “ . . . የምትሉት እናንተ ሽማግሌዎቻችን ናችሁ” ቢል ከጨዋነት ይቆጠርለታል። በዕድሜ የሚያንሰው ሰው በተረቱ ውስጥ የታቀፈውን ጥበብ ለሽማግሌዎች እንደሚያስተምር ሆኖ መታየት አይፈልግም።

ልብ ሊባሉ የሚገባቸው አንዳንድ አስተያየቶች

ተረትና ምሳሌዎች ከአንድ መከራከሪያ ነጥብ በፊትም ሆነ በኋላ ሊቀርቡ ይችላሉ። በተጨማሪም ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር በረቀቀ ሁኔታ ስለሚተሳሰሩ የተረቱ መልእክት ወይም ትርጉም ምን እንደሆነ ለመረዳት ጥሩ አስተዋይነት ይጠይቃል። ለምሳሌ ያህል አንድ የአካን ሰው ትሁትና ሰላም ወዳድ ስለሆነ ሰው ለመናገር ቢፈልግ “እንደ እገሌ ቢሆን ኖሮ በመንደሩ ውስጥ አንድም ተኩስ አይሰማም ነበር” ይላል። “ለቀንድ አውጣና ለዔሊ ብቻ ቢተው ኖሮ በዱሩ ውስጥ አንድም ተኩስ አይሰማም ነበር” የሚለውን ተረት የሚጠቅስ አባባል ነው። ሁለቱም እንስሳት የዋሆች፣ ሰላማዊና የጠበኝነት ባሕርይ የሌላቸው እንደሆኑ ይታሰባል። እንደነዚህ ያሉ ባሕርያት ያሏቸው ሰዎች ሰላም ፈጣሪዎች ናቸው።

ይሁን እንጂ አንድ የአካን ሰው ብዙ ተረቶችን እንዲናገር ብትጠይቅ ከሚከተለው ተረት ሌላ ለመስማት አትችል ይሆናል። “እንቅልፍ በሌለበት ሕልም አይታይም።” በሌላ አባባል እንቅልፍ ሳይወስደው ሕልም ሊያይ የሚችል ሰው እንደማይኖር ሁሉ ተረቶችንም በባዶ ሥፍራ የሚናገር አይኖርም። ተረት የሚነገረው በሁኔታዎች አስገዳጅነት ብቻ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.25 ይህ ሥዕል አብዛኛውን ጊዜ በቀብር ላይ በሚለበሱ ጥቁር ልብሶች ላይ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዓይነት ቀለም ባላቸው ልብሶች ላይ የሚገኝ መሆኑን መጥቀስ ተገቢ ነው።