በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ድምፅ አልባው አደጋ” በቅርቡ ይወገዳል!

“ድምፅ አልባው አደጋ” በቅርቡ ይወገዳል!

“ድምፅ አልባው አደጋ” በቅርቡ ይወገዳል!

“ከጥቂት ዓመታት በፊት ከነበረው ይልቅ በአሁኑ ጊዜ የምንኖረው ምርት በተትረፈረፈበት ጊዜ ነው። . . . ለሁሉም ሰው ከበቂ በላይ ምግብ አለ የሚባልበት ጊዜ ነው።” ይህን ያለው የዓለም ጤና ድርጅት ነው። ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዲኖር ያደረገው ምንድን ነው?

“ችግሩ ምግብ የሚመረተውም ሆነ የሚከፋፈለው በትክክል ባለመሆኑ ነው” ይላል የዓለም ጤና ድርጅት። “የሚያሳዝነው በታዳጊ አገሮች ያሉ ድሆች ባዶ እጃቸውንና ባዶ ሆዳቸውን ሆነው ዓይናቸው እያየ ብዛት ያለው ምርትና ሰብል የገንዘብ ምንዛሪ እንዲያስገኝ ተብሎ ወደ ውጭ አገር ይላካል። ይህም ለጥቂቶች በአጭር ጊዜ ትርፍ የሚያስገኝ ሲሆን በብዙዎች ላይ ግን የረዥም ጊዜ ኪሳራ ያስከትላል።” በተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት በቅርቡ ያካሄደው ጥናት እንዳመለከተው ‘በምድር ላይ ካለው ሥጋና ዓሣ 45 በመቶውን የሚበሉት 20 በመቶ የሚሆኑት የዓለም ባለ ሃብቶች ሲሆኑ እጅግ ድሆች የሆኑት 20 በመቶ የሚሆኑት ግን የሚበሉት 5 በመቶውን ብቻ’ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት እንደሚለው “ጥሩ ትምህርትና በቂ መረጃ ማጣትም ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት አንዱ መንስኤ ነው። የመረጃ ስልት እንዲሁም የተሻለና ሊደረስበት የሚችል የትምህርት ፕሮግራም ሳይኖር የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለመዋጋት የሚያስፈልገው ግንዛቤ፣ ችሎታና ጠባይ ሊዳብር አይችልም።” ይሁንና የምግብ እጥረትም የአንድን ሰው ጤንነትና የተሻለ ትምህርት የማግኘት ችሎታውን ስለሚቀንስበት ችግሩ ማብቂያ አይኖረውም።

ፍትሕና ለሌሎች አሳቢነት ማሳየት

እንደዚህ ያሉ ተስፋ አስቆራጭ እንቅፋቶች ቢኖሩም በመስኩ የተሰማሩ አንዳንድ ባለሞያዎች አሁንም ገና ተስፋ አልቆረጡም። ለምሳሌ ያህል የምግብና እርሻ ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት ዣክ ጁፍ ይህን ተስፋ እንደሚከተለው በማለት ገልጸውታል:- “በዓለም ላይ ሴት፣ ወንድ፣ ሕፃን ሳይል ማንኛውም ሰው በእያንዳንዱ ቀን ገንቢና ለጤና ተስማሚ የሆነ ምግብ በበቂ መጠን የሚያገኝበት ጊዜ ይመጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። በሃብታምና በድሃ መካከል ያለው ሰፊ ልዩነት ሲወገድ ይታየኛል። መድሎ ተወግዶ መቻቻል ሲሰፍን፣ የእርስ በርስ ግጭት ተወግዶ ሰላም ሲሰፍን፣ የአካባቢ ውድመት ተወግዶ የተፈጥሮ ሃብት ሲጠበቅ፣ ድህነት ተወግዶ ብልጽግና ሲያብብ ይታየኛል።”

ይሁንና እስካሁን እንዳየነው እንዲህ ዓይነቶቹን ተስፋዎች እውን ለማድረግ ምርትንና የምርት ክፍፍልን ከማሳደግ የሚበልጥ ነገር ማድረግ ያስፈልጋል። ፍትሕን ማስፈንና ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ አሳቢነት ማሳየት ያስፈልጋል። ሆኖም እነዚህ በዚህ ትርፍ አሳዳጅ በሆነ ሕብረተሰብ ዘንድ ተወዳጅ ባሕርያት አይደሉም።

እንደ ስግብግብነት፣ ድህነት፣ ግጭትና ራስ ወዳድነት ያሉ ግዙፍ እንቅፋቶችን በማስወገድ ብቻ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ከምድረ ገጽ ማጥፋት ይቻላል? ወይስ ይህ እንዲያው የሕልም እንጀራ ብቻ ነው?

ብቸኛው እውነተኛ መፍትሔ

መጽሐፍ ቅዱስ በሚለው መሠረት የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን የሚያስከትሉ መሠረታዊ ችግሮች መኖራቸው ሊያስገርመን አይገባም። የአምላክ ቃል “በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ . . . ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ . . . መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ . . . የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል” በማለት ይናገራል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5

የሰው ልጅ ያለ አምላክ እርዳታ እንደዚህ ያሉትን ሥር የሰደዱ ዝንባሌዎች ማስወገድ ይችላል? ይህ የማይመስል ነገር ነው። ምናልባት አንተም በሥልጣን ላይ ያሉ አንዳንድ ሰዎች የሰው ልጆችን ችግሮች ለመቅረፍ እንደሚፈልጉ ሆኖም የሌሎች ራስ ወዳድነት፣ የገንዘብ ፍቅርና የሌሎች አለፍጽምና ጣልቃ ገብተው በቅን ልብ ያደረጉትን ጥረት ሁሉ መና ሲያስቀርባቸው ተመልክተህ ይሆናል።​—⁠ኤርምያስ 10:23

ሆኖም ችግሩ ምንም መፍትሔ የለውም ማለት አይደለም። የአምላክ መንግሥት የፍትሕ መጓደልንም ሆነ በዛሬው ጊዜ የሰው ልጆችን እያሠቃዩ ያሉ ሌሎች መከራዎችን እንደሚያስወግድ መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ይሰጣል።

ኢሳይያስ 9:​6-7 የሚከተለውን አስደናቂ ተስፋ ይዞልናል:- “ሕፃን ተወልዶልናልና፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፣ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፣ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም። የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል።”

ሰዎች የጌታን ጸሎት በመድገም “መንግሥትህ ትምጣ” እያሉ የሚጸልዩለት ይኸው መንግሥት ነው። (ማቴዎስ 6:​9, 10) “የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል” በማለት ኢሳይያስ የተናገረውን ልብ በል። አዎን፣ ይሖዋ አምላክ የሰው ልጆች ፍላጎቶች ተሟልተው መመልከት ይፈልጋል። ይህችን ምድር ለሁሉም በቂ ምርት እንድትሰጥ አድርጎ ፈጥሯታል።

መዝሙር 65:​9-13 ስለ ይሖዋ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “ምድርን ጎበኘሃት አጠጣሃትም፣ ብልጥግናዋንም እጅግ አበዛህ፤ የእግዚአብሔር ወንዝ ውኃን የተመላ ነው፤ ምግባቸውን አዘጋጀህ፣ እንዲሁ ታሰናዳለህና። ትልምዋን ታረካለህ፣ ቦይዋንም ታስተካክላለህ፤ በነጠብጣብ ታለሰልሳታለህ፣ ቡቃያዋንም ትባርካለህ። . . . የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፣ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ። ማሰማርያዎች መንጎችን ለበሱ፣ ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ።”

አዎን፣ ፈጣሪያችን ይሖዋ ለሰው ልጆች ከሁሉ የበለጠ መጋቢ ነው። እርሱ “ለሥጋ ሁሉ ምግብን የሚሰጥ፤ ምሕረቱ ለዘላለም” የሆነ አምላክ ነው።”​—⁠መዝሙር 136:​25

በክርስቶስ የሚተዳደረው የአምላክ መንግሥት ለሰዎች ሁሉ እንክብካቤ እንደሚያደርግ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “በምድር ውስጥ በተራሮች ላይ መጠጊያ ይሆናል።” በተጨማሪም “[ኢየሱስ ክርስቶስ] ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፣ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና። . . . የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል” ስለሚል ትክክለኛ የሆነ የምግብ ክፍፍልም ይኖራል። (መዝሙር 72:​12, 13, 16) ስለዚህ አይዞህ! “ድምፅ አልባው አደጋ” በቅርቡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይወገዳል።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በአፍ ሲናገሩት ረሃብንና የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ማስወገድ ቀላል ነው። ዘዴዎቹም አሉ። ፈታኙ ሁኔታ ግን . . . በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተባበረ እርምጃ መውሰዱ ላይ ነው።”​—⁠የዓለም ጤና ድርጅት

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]