በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጫማህ በእርግጥ ልክህ ነውን?

ጫማህ በእርግጥ ልክህ ነውን?

ጫማህ በእርግጥ ልክህ ነውን?

“ጫማ የቱ ላይ አጣብቆ እንደሚይዝ ከተጫማው በቀር የሚያውቀው የለም።”—⁠አንድ የሮማ ሊቅ እንደተናገረው።

በቅርቡ ጫማ የገዛኸው መቼ ነው? ስትለካው እንዴት ነበር? ልክህ ነበር? እነዚህን ጫማዎች ለመግዛት ምን ያህል ጊዜ ፈጅቶብሃል? ሻጩ ምን ያህል ተባበረህ? የገዛኸው ለምቾቱ ብለህ ነው ወይስ እንዲያው ሞዴሉን ስለወደድኸው ብቻ? ጫማዎቹን ለጥቂት ጊዜያት ካደረግካቸው በኋላ አሁን እንዴት ናቸው? የሚይዝህ ቦታ አለ?

ጫማ መግዛት የሚታሰበውን ያህል ቀላል አይደለም። ልክህ የሚሆን ጫማ ማግኘት አድካሚ ሊሆንብህ ይችላል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው?

ልክህን ማግኘት

በመጀመሪያ ትልቁ እግርህ የትኛው ነው? ቀኝህ ወይስ ግራህ? ሁለቱም እግሮችህ እኩል ይመስሉሃል? እስቲ በድጋሚ አስብ! ከግምት ውስጥ መግባት ያለበት ሌላው ነገር ደግሞ ጫማን በአራት መንገድ መለካት የሚቻል መሆኑ ነው። እነሱም ቁጭ ብሎ፣ ቆሞ፣ እየተንቀሳቀሱና በሙቀት ጊዜ ናቸው። ልዩነታቸው ምንድን ነው?

ፕሮፌሽናል ሹ ፊቲንግ የተሰኘው መጽሐፍ ተቀምጦ መለካትን በተመለከተ ሲናገር ‘ተቀምጦ መለካት ቆሞ ከመለካት ይለያል።’ አንድ ሰው ሲቆም የእግሩ መጠንና ቅርጽ ይለወጣል። ከላይ የተጠቀሰው ማመሳከሪያ ጽሑፍ “አንድ ሰው ቁጭ በሚልበት ጊዜ የእግር አጥንቶቹና አያያዥ አንጆ ሥጋዎቹ ዘና ይላሉ፤ ሲቆም ግን ተወጥረው ስለሚጠነክሩ የእግር መጠን ይለወጣል።” የሆነ ሆኖ ገና ሁለት የመለኪያ ዘዴዎች ቀርተውናል።

በእንቅስቃሴ ጊዜ የሚባለው ደግሞ አንድ ሰው በሚሄድበት፣ በሚሮጥበት፣ በሚዘልበት ወይም ሌላ እንቅስቃሴ በሚያደርግበት ጊዜ የሚኖረውን የእግር መጠን ነው። በዚህ ጊዜ እግር “የተለየ ስፋት፣ ቅርጽና መጠን ይኖረዋል።” አራተኛው ደግሞ ሙቀትና ቅዝቃዜ በእግር መጠን ላይ የሚያሳድሩት ለውጥ ነው። ሙቀትና ቅዝቃዜ በእግር ይዘት ላይ 5 በመቶ ጭማሪ ሊያመጡ ይችላሉ። ምሽት ላይ ጫማህን ስታወልቅ እፎይታ የሚሰማህ ለዚህ ነው። በተለይ ደግሞ ጠባብ ጫማ አድርገህ ከዋልክ ይህ ያጋጥማል።

እግር የሚለካው እንዴት ነው?

ኤሪክ ለዓመታት የሚገዛው 44 ተኩል፣ አነስተኛ ሞድ ያለው ከሆነ ደግሞ 45 ቁጥር ጫማ ነበር። በእነዚህ ጊዜያት በእግሩ መካከለኛ ጣት ላይ መጅ ወጥቶበት፣ አውራ ጣቱ ላይ ያለው ጥፍር ደግሞ ወደ ውስጥ ታጥፎ እያደገ ያስቸግረው ነበር። ሐኪሙ እግሩን በሠለጠነ ባለሞያ እንዲያስለካ ሐሳብ አቀረበችለት። ኤሪክ ማድረግ ያለበት ጫማ “ኤ” ተብሎ የሚታወቅ 47 ቁጥር መሆኑን ሲገነዘብ ተገረመ። “ኤ” የሚያመለክተው ቀጭን እግርን ነው። ይሁንና ምቹ ጫማ ለመግዛት የእግርን ርዝመትና ስፋት ማወቁ ብቻ በቂ ነውን? እግርህ መለካት ያለበት እንዴት ነው?

በአንዳንድ አገሮች የጫማ ቁጥር የሚወሰነው ብራኖክ በሚባል መሣሪያ ነው። (ፎቶውን ተመልከት።) ይህም ሦስት መሠረታዊ ልኬቶችን ለማግኘት ያገለግላል:- የእግርን አጠቃላይ ርዝመት፣ ከተረከዝ አንስቶ እስከ እግር መዳፍ ድረስ ያለው ርቀትና የእግር መዳፍ ስፋት ናቸው። ቢሆንም ግን እያንዳንዱ እግር የራሱ ቅርጽና ይዘት አለው። በዚህም ምክንያት ጫማ ከመግዛታችን በፊት ጫማዎቹን እያጠለቅን እንሞክራቸዋለን። እዚህ ላይም ልንሳሳት እንችላለን። አንድን ጫማ ወደኸው ስትለካው ትንሽ ያዝ አድርጎህ ያውቃል? ጫማ ሻጩ “ቆይቶ ይለቃል” ይልሃል። ጫማዎቹን ገዝተህ ትሄዳለህ። ሆኖም ጥቂት ቀናት ወይም ሳምንታት ካደረግካቸው በኋላ ምነው ባልገዛሁት እያልክ ትቆጫለህ። ይህም በጣትህ ላይ መጅ እንዲወጣና ጥፍርህ ወደ ውስጥ እንዲታጠፍ ሊያደርግ ይችላል እንዲሁም በአውራ ጣትህ አንጓ ላይ የሚያሠቃይ እብጠት ያስከትልብሃል!

ሙሉ በሙሉ የሚስማማ ጫማ ማግኘት ይቻላል?

ፍጹም ልክህ የሆነ ጫማ ማግኘት ይቻላል? ፕሮፌሽናል ሹ ፊቲንግ የተሰኘው መጽሐፍ ፈጠን ብሎ አይቻልም በማለት መልስ ይሰጣል። ለምን? “ምክንያቱም ምንም ልናደርጋቸው የማንችላቸው አያሌ እንቅፋቶች ስላሉ ነው። . . . አንድ ዓይነት ስፋት፣ ቅርጽ ወይም መጠን ያላቸው እግሮች ያሉት ሰው የለም።” ስለዚህ ጫማው ለትልቁ እግርህ ልክህ ከሆነ ለሌላው እግርህ ልክ አይሆንም። “ይህ ማለት ግን ልክህ የሚሆን ጫማ ማግኘት አትችልም ለማለት ሳይሆን ‘ፍጹም ልክ’ የሆነ ጫማ ማግኘት አይቻልም ለማለት ነው።”

በአብዛኛው ጫማህ የሚያልቀው የት ላይ እንደሆነ ለማወቅ ከምታደርጋቸው ጫማዎች ውስጥ አንዳንዶቹን ተመልከት። የጫማውን ገበር ተመልከት። ያለቀው የት ላይ ነው? አብዛኛውን ጊዜ ተረከዝህ የሚያርፍበት ቦታ፣ ከተረከዝህ ጀርባና የእግርህ መዳፍ የሚያርፍበት ቦታ አልቆ ታየዋለህ። ይህ ምን ያሳያል? ይህ ማለት “አንዳንዶቹ የጫማው ክፍሎች ከሌሎቹ የእግርህ ክፍል ጋር በተገቢው ሁኔታ አይገጥሙም። አንዳንዶቹ የጫማው ክፍሎች ምንም ሳይነኩ ሌሎቹ ከመጠን በላይ ተፋትገው ያልቃሉ።”

የጫማው ማስገቢያ እንኳን ሳይቀር ለምቾት አስፈላጊ ነው። የጫማው ማስገቢያ የተለያየ አሠራር ሊኖረው እንደሚችል ልብ ብለሃል? ከእነዚህም አንዱ ቤኤል የሚባለው ሲሆን የክር ማሠሪያዎቹ የተቀራረቡ ናቸው። እግርህ ወፍራም ከሆነ ደግሞ የሚመችህ ብላቸር የሚባለው የጫማ ማስገቢያ ያለው ጫማ ነው። (ሥዕሉን ተመልከት።) ይህ ዝርዝር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ከላይ የተጠቀሰው ምንጭ “በጫማ ምክንያት የሚከሰተው አብዛኛው የተረከዝ ችግር ብዙውን ጊዜ የጫማው ማስገቢያ በጣም ጠባብ በመሆኑና ተረከዝ ወደውጭ በመገፍተሩ ምክንያት የሚመጣ ነው” ይላል።

የሴቶች ባለ ረዥም ተረከዝ ጫማዎችስ?

ረዥም ተረከዝ ያለው ጫማ የሚያደርጉ ሴቶች በሰውነታቸው ላይ የተለያየ ጫና እንዲፈጠር ያደርጋሉ። ረዣዥም ተረከዝ ያላቸው ጫማዎች ሰውነት ወደፊት ዘንበል እንዲል በማድረግ የሰውነትን አቋም የሚለውጡ ሲሆን ይህም በምላሹ ሰውነት ቀና እንዲል ሲባል ከጉልበት አጠፍ ማለትን ያስከትላሉ። በተጨማሪም ባለ ረዣዥም ተረከዝ ጫማዎች የባትን ጡንቻ ስለሚያኮማትሩ ፈርጠም ብሎ እንዲታይ ሊያደርጉት ይችላሉ።

ይህም በመሆኑ ብዙውን ጊዜ ከሴት ጫማ ወሳኙ ክፍልና ለምቾትም ቁልፍ ድርሻ ያለው ተረከዙ ነው። ፕሮፌሽናል ሹ ፊቲንግ የተባለው መጽሐፍ ባለ ረዣዥም ተረከዝ ጫማ የሚመረጥባቸው ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች እንዳሉ ይናገራል:- ‘(1) “ጎላ ብሎ ለመታየት” ማለትም በቁመት ላይ ቁመት ለመጨመር፣ (2) ለጫማው ውበት ለመጨመር እንዲሁም (3) ውብ ሆኖ ለመታየት። ይኸውም የሴቶች ባለ ረዣዥም ተረከዝ ጫማዎች ለእግራቸው ቅርጽ ማማር አስተዋጽኦ ስለሚያበረክቱ ነው።’

በተለይ ሴቶች የሰውነታቸው ክብደት የሚያርፍበትን መሥመር የሚወስነው ተረከዛቸው ስለሆነ የሚያደርጉት ጫማ ተረከዝ ወደፊት የሚያቆለቁልበት መጠን ሊያሳስባቸው ይገባል። ይህ መሥመር ከተረከዛቸው በፊት በኩል የሚያርፍ ከሆነ አደጋ አለው። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ተረከዝን ወለም ሊለውና መጥፎ አወዳደቅ ሊያስከትል ስለሚችል ነው።

አንድ ጥሩ ጫማ ለመሥራት ጊዜ የሚጠይቅ በመሆኑ በልካችን የተሰሩ ጫማዎችን ለማግኘት ጊዜና ምናልባትም ተጨማሪ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑን እስካሁን ካደረግነው አጭር ውይይት በግልጽ ለማየት ይቻላል። የሆነ ሆኖ ጫማዎችህ በአጠቃላይ ምቾትህን በተለይ ደግሞ ጤንነትህን በእጅጉ ይነካሉ። ስለዚህ ረጋ ብለህ ልክህ የሆነውን ጫማ ምረጥ። ይህንንም ለማድረግ ትዕግስተኛ ሁን። በፋሽን ወይም በመልክ አትታለል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ጫማ ስትመርጥ ልታስብባቸው የሚገቡ ነገሮች

ዊልያም ኤ ሮዚ እና ሮዝ ቴናንት ፕሮፌሽናል ሹ ፊቲንግ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ የሚከተለውን ሐሳብ አቅርበዋል።

“እግር የሚለካበት ዓላማ እንደሚታሰበው የሚስማማንን ትክክለኛ ጫማ ለማግኘት አይደለም።” ይህ የሆነው ለምንድን ነው? የተረከዝ ቁመት፣ ሞድ፣ ንድፍ፣ ጫማው የተሠራበት ጥሬ እቃና ፋብሪካው የመሳሰሉ ምክንያቶች በጫማው መጠን ላይ ለውጥ ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ነው። በተለይ በብዙ አገሮችና በተለያዩ መሥፈርቶች ጫማ እየተመረተ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ይህ እውነት ሆኖ እናገኘዋለን።

የእግርህ ጣቶች እንዳይታጠፉና ጠባብ ጫማ እንዳትገዛ ጫማ በምትለካበት ጊዜ የእግርህን ሹራብ ከፊት በኩል ሳብ አድርገው።

ጫማ መለካት ያለብህ እንዴት ነው? ተቀምጠህ ወይስ ቆመህ? “ደንበኛ ተቀምጦ ጫማ እንዲለካ ማድረግ የስንፍና ሥራ ነው።” በዚህ መንገድ ልክህ የሆነውን ጫማ ለማግኘት ያስቸግራል። ስለዚህ የምትገዛውን ጫማ ቆመህ ለካው። ደግሞም ሁለቱንም ጫማዎች አድርጋቸው። ግራ እግር ትልቅ ነው ብለህ አታስብ። ሁለቱንም ለካ!

“ለእግር የሚስማማ ጫማ ማዘጋጀት በሞያው የተካኑ ጥቂት ባለሞያዎችና ተስማሚ የሆነ ጫማ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የሚገነዘቡ የጫማ ሱቆች የሚሰጡት አገልግሎት ነው።”

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የጫማ ክፍለ አካሎች

ሶል

ቫምፕ

ማስገቢያ

እግር ማረፊያ ገበር

ተረከዝ

ተረከዝ ክፈፍ

አፍንጫ

የውጭ ሶል

ደርዝ

ቫምፕ

መጋጠሚያ

ምላስ ማገጃ

የኋላ ሽፋን

ተረከዝ ማረፊያ

ተረከዝ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጫማ መለኪያ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሁሉም የጫማ ንድፎች በእነዚህ ሰባት መሠረታዊ ሞዶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጫማ ማስገቢያ ዓይነቶች

ብላቸር

ቤኤል