መልካም ቅዳሜና እሁድ!
መልካም ቅዳሜና እሁድ!
ሁሉም ሰው ለማለት ይቻላል ቅዳሜና እሁድ እስኪደርስ ይናፍቃል፤ አብዛኛውን ጊዜ የተለያየ ነገር ማድረግ የሚቻለው በእነዚህ ቀናት ነው። ቅዳሜና እሁድ ሲመጣ አንዳንዶች ሽርሽር ይሄዳሉ፣ አንዳንዶች የተለያዩ ነገሮችን በማድረግ ይዝናናሉ፣ ሌሎች ደግሞ አምልኳቸውን ያከናውናሉ፤ እቤታቸው ተኝተው የሚያሳልፉም አሉ።
በምዕራቡ ዓለም የሳምንቱ ዕረፍት ከዓርብ ጀምሮ እስከ እሁድ ይዘልቃል። ይሁንና ቅዳሜና እሁድ ማረፍ የሚለው ሐሳብ የመነጨው ከየት ነው? አምስት የሥራ ቀናት በተለመደበት አገር የምትኖር ከሆነ ቅዳሜና እሁድን በጥሩ ሁኔታ ማሳለፍ የምትችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
ቅዳሜና እሁድ የዕረፍት ቀናት ሊሆኑ የቻሉት እንዴት ነው?
ከ3, 500 ዓመታት በፊት ለእስራኤላውያን የተሰጣቸው የሰንበት ሕግ “ስድስት ቀን ሥራን ሥራ፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ የዕረፍት ሰንበት ነው፤ በሰንበት ቀን የሚሠራ ሁሉ ፈጽሞ ይገደል” የሚል ነበር። (ዘጸአት 31:15) ሰንበት እስራኤላውያን ወላጆች የቤተሰባቸውን መንፈሳዊ ፍላጎት የሚከታተሉበት አጋጣሚ ይሰጣቸው ነበር።
የአይሁድ ሰንበት የሚቆየው ዓርብ ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ጀምሮ ቅዳሜ ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ ነበር። ይሁን እንጂ ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔዲያ እንደሚገልጸው ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች “እሁድ ኢየሱስ ትንሣኤ ያገኘበት ቀን ነው ብለው ያምኑ ስለነበር ልዩ የአምልኮ ቀን አደረጉት። በ300 እዘአ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት በአንድነት እሁድ በአውሮፓ የዕረፍት ቀን እንዲሆን በይፋ ዕውቅና ሰጡት።”
የሚገርመው የሳምንቱ የዕረፍት ቀን ከአንድ ቀን በላይ የተራዘመው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው። በብሪታንያ ከ1870ዎቹ ጀምሮ የሥራ ሳምንት የሚያበቃው ቅዳሜ በምሳ ሰዓት ነበር። ስለዚህ የሳምንቱ ዕረፍት ቅዳሜ ከሰዓት በኋላና እሁድ ሙሉ ቀን ሆነ። አትላንቲክ መንዝሊ የተሰኘው መጽሔት እንደሚገልጸው ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ የቤተሰብ አባላት አንድ ላይ ሆነው ምሳ ይበሉና “በአካባቢው በሚገኝ ገላ መታጠቢያ ይታጠቡ ነበር።”
በዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ የሳምንቱ ዕረፍት ተራዝሞ ሁለት ቀን ሆኖ ነበር። አንድ ምንጭ እንደሚለው አምስት የሥራ ቀናትን የያዘው ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ በሥራ ላይ የዋለው በ1908 በኒው ኢንግላንድ በሚገኝ አንድ ፋብሪካ ነበር። ዝግጅቱ በአይሁድም ሆነ “በክርስቲያን” ሠራተኞች ዘንድ ተቀባይነት ነበረው፤ ምክንያቱም የአይሁዶች ዕረፍት ቅዳሜ ሲሆን “የክርስቲያኖች” ደግሞ እሁድ ስለነበረ ነው። ባለ አምስት ቀኑ የሥራ ሳምንት ወዲያው በሁሉም ዘንድ ተለመደ። የመኪና አምራች የሆኑት ሄንሪ ፎርድ ቅዳሜና እሁድ በቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ ለሽርሽር መውጣት እየተለመደ ከመጣ ብዙዎች መኪና መግዛታቸው አይቀርም ብለው ስላሰቡ ይህ አሠራር በሰፊው ተግባራዊ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።
ቅዳሜና እሁድ ምን ለማድረግ አስበሃል?
ዛሬ በምዕራቡ ዓለም ቅዳሜና እሁድ ቋሚ የዕረፍት ቀናት እየሆኑ መጥተዋል። በመሥሪያ ቤት የሳምንቱ የሥራ ቀናት ሊጠናቀቁ አካባቢ “ቅዳሜና እሁድ ምን ለማድረግ አስበሃል?” እያሉ እርስ በርስ መጠያየቅ የተለመደ ነው። ይህ ጥያቄ ቅዳሜና እሁድ ልታደርግ የምትችላቸውን ነገሮች በማሰብ እንድትደሰት ያደርግሃል።
ሳምንቱን ሙሉ በአሠሪህ ቁጥጥር ሥር ቆይተህ እንደልብህ መሆን የምትጀምረው ቅዳሜና እሁድ ሲመጣ ነው። ከተለመደው የሳምንቱ እንቅስቃሴህ ለየት ያለ ነገር ማድረግ
የምትችለው በእነዚህ ቀናት ነው። ማረፍ አሊያም ከወዳጅ ዘመዶችህ ጋር አብረህ መዋል ትችላለህ። ወይም ደግሞ ብዙዎች እንደሚያደርጉት ገበያ ወጥተህ በመዞር መዝናናት ትችላለህ። “ገበያ ወጥቶ በየሱቁ መዞር በጣም ያስደስታል” በማለት በጀርመን የምትኖረው ብሪጊቴ አስተያየቷን ሰጥታለች።ብዙ ሰዎች የዕረፍት ጊዜያቸውን እንዲሁ በመዝናናት ብቻ ማሳለፍ እንደሚመርጡ ጥናቶች ያሳያሉ። ቅዳሜና እሁድን ከቤታቸው መውጣት የማይፈልጉ ሰዎች ጊዜ የሚያሳልፉባቸው የተለያዩ ነገሮች አሉ። ከእነዚህም ውስጥ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል:- በቤትም ሆነ በግቢ ውስጥ ያሉ አትክልቶችን መንከባከብ፣ ቴምብሮችን መሰብሰብ፣ ሙዚቃ መጫወት ወይም ማዳመጥ፣ ፊልም መመልከት፣ ምግብ ማብሰል፣ ደብዳቤ መጻፍ፣ ማንበብ፣ ልብስ መስፋት፣ ሹራብ መሥራት፣ የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እና ሥዕል መሳል ናቸው። አንዳንዶች ደግሞ ከልጆቻቸውና ከትዳር ጓደኛቸው ጋር በመሆን እንደ ዳማና ቼዝ የመሳሰሉ ጨዋታዎችን መጫወት ይመርጣሉ። *
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በመሳሰሉ ቀላል መዝናኛዎች ጊዜ ማሳለፍን ያወግዛልን? እንደዚያ ማለት አይቻልም። ሰሎሞን “በድካምና ነፋስን በመከተል ከሁለት እጅ ሙሉ ይልቅ አንድ እጅ ሙሉ በዕረፍት ይሻላል” በማለት ጽፏል። (መክብብ 4:6) አንድ ክርስቲያን ሚዛኑን በጠበቀ ሁኔታ ማረፍ፣ መጫወትና መዝናናት እንደሚያስፈልገው ምንም ጥርጥር የለውም።
ከልክ ማለፍ
በሌላ በኩል ግን አንድ ጥሩ ነገር እንኳን ሲበዛ የታለመለትን ግብ አለመምታት ብቻ ሳይሆን ጎጂም ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የተወሰነ ጥቅም ሊኖረው ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 4:8) ነገር ግን አንዳንዶች ቅዳሜና እሁድ በመጣ ቁጥር ከስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ሌላ ምንም ነገር ማድረግ አይታያቸውም። በሚወዱት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ተፎካካሪ ለመሆን ሲሉ ለልምምድና ለስፖርት ትጥቆች ይህ ነው የማይባል ጊዜና ገንዘብ ያጠፋሉ።
ሰውነትን ከአቅሙ በላይ ማሠራትም ቢሆን የጤና እክል ያስከትላል። ቅዳሜና እሁድን ከባድ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ወጣትነታቸውን መልሰው ለማግኘት የሚጥሩ በመካከለኛ ዕድሜ የሚገኙ ሰዎች የሚያተርፉት ነገር ቢኖር ወለምታ፣ መቆሳሰል፣ የሰውነት መቀጥቀጥና መጓጎል ብቻ መሆኑን አንድ መጽሔት ዘግቧል። ሌሎች ደግሞ ጀብደኝነትን በሚጠይቁ አንዳንድ አደገኛ ስፖርቶች በመካፈል ለከፍተኛ የአካል ጉዳት እስከመዳረግ አልፎ ተርፎም ሕይወታቸውን እስከማጣት ይደርሳሉ። * በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “ልከኞች” ስለመሆን የሰጠው ምክር በጣም ተስማሚ ነው። (ቲቶ 2:2) ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያነቃቃ እንጂ ሰውነትን የሚያደክም ወይም ለአደጋ የሚያጋልጥ መሆን የለበትም።
ይህም በመሆኑ አንዳንዶች ቀለል ያሉ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ይመርጣሉ። ለምሳሌ ያህል በጀርመን አገር የእግር ጉዞ ማድረግና ሽርሽር በሰፊው የተለመዱ ነገሮች ናቸው። እንዲያውም በአውሮፓ ብዙዎች እንደ መዝናኛ የሚያዘወትሩት ነገር ፈጣን እርምጃ ነው። ማራኪ እይታ ወዳላቸው አካባቢዎች ወጣ በማለት በፈጣን እርምጃ በተወሰነ ሰዓት ውስጥ የተወሰነ ርቀት ለመሸፈን ጥረት ያደርጋሉ። ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለማድረግና በዚያውም ውብ የሆነ መልክአ ምድር በማየት ለመደሰት ይህ እንዴት ጥሩ አጋጣሚ ነው! መላው ቤተሰብ እንዲህ በማድረግ ሊዝናና ይችላል።
ሩጫ የበዛበት ቅዳሜና እሁድ
አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ቅዳሜና እሁድ ብዙ ነገር ለማከናወን ያቅዱና በአንዱም ሳይደሰቱ ሊቀሩ ይችላሉ። ስለዚህ አዲሱን ሳምንት የሚጀምሩት ታድሰውና ተዝናንተው ሳይሆን ዝለውና ተሰላችተው ይሆናል። ፎከስ የተሰኘው የጀርመን መጽሔት በአንድ ጥናት ላይ ጥያቄ ከቀረበላቸው ሰዎች መካከል 27 በመቶ የሚሆኑት የዕረፍት ጊዜያቸው ወከባና ውጥረት የበዛበት እንደሆነ መግለጻቸውን ዘግቧል።
ማርቆስ 6:31 ይገልጻል።ስለዚህ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ገበያ መውጣትና የመሳሰሉት ነገሮች የራሳቸው ቦታ ቢኖራቸውም ቁጭ ብሎ ለማንበብ፣ ለማረፍ ወይም ለመተኛት ጊዜ መመደብህ ኃይልህን በማደስ ረገድ ትልቅ ድርሻ አለው። ይሁን እንጂ ቅዳሜና እሁድን አስደሳች በሆነ ሁኔታ ለማሳለፍ የሚረዳ ሌላም ነገር አለ።
ታይም መጽሔት “በቂ ዕረፍት ካለ የሥራ ቅልጥፍና አለ” በማለት ጽፏል። ኢየሱስ ክርስቶስም የዕረፍትንና የመዝናናትን አስፈላጊነት ተገንዝቦ ነበር። ‘የሚመጡና የሚሄዱ ብዙዎች ነበሩና፣ ለመብላት እንኳ ጊዜ ስላጡ’ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “እናንተ ራሳችሁ ብቻችሁን ወደ ምድረ በዳ ኑና ጥቂት ዕረፉ” እንዳላቸውመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች
ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ “ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው” ብሏል። (ማቴዎስ 5:3 NW ) የቀድሞው የሰንበት ዕረፍት ቀን ከነበሩት ዓላማዎች አንዱ ሕዝቡ ለመንፈሳዊ ነገሮች ጊዜ እንዲያገኙ ማስቻል ነበር። በዛሬው ጊዜም ቅዳሜና እሁድን ለተመሳሳይ ዓላማ መጠቀም ይቻላልን? የይሖዋ ምስክሮች ምን እንደሚያደርጉ ተመልከት። አብዛኞቹ ጉባኤዎች ዋና ዋና ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻቸውን የሚያደርጉት ቅዳሜ ወይም እሁድ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ትላልቅ ስብሰባዎቻቸውንም የሚያደርጉት በእነዚህ ቀናት ነው። አብዛኞቹ የይሖዋ ምስክሮች ብዙውን ጊዜ ቅዳሜና እሁድን የሚያሳልፉት ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ከጎረቤቶቻቸው ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በመወያየት ነው።
እርግጥ ነው፣ የይሖዋ ምስክሮች እንደማንኛውም ሰው ሥራ፣ ቤትና የሚያስተዳድሩት ቤተሰብ አላቸው። ስለዚህ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን ዘና የሚሉበትን ጊዜ ያመቻቻሉ። ይሁን እንጂ ቅድሚያ የሚሰጡት ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ነው። እንዲህ ማድረጉን እንደ ሸክም ይቆጥሩታልን? ቀጥሎ የሚጠቀሱት ግለሰቦች ተሞክሮአቸውን ሲናገሩ ምን እንዳሉ ተመልከት።
በጀርመን አገር የሚኖሩት ጀርገንና ዶሪስ የተባሉ ባልና ሚስት የይሖዋ ምስክሮች ከመሆናቸው በፊት ቅዳሜና እሁድን የሚያሳልፉት በስፖርት ክበቦች ውስጥ ስፖርት በመሥራት ነበር። ሜላ እና ሄሌናም ቅዳሜና እሁድን የሚያሳልፉት የተለያዩ የሥነ ጥበብ አዳራሾችን በመጎብኘት ነበር። ሄልሙት የተባለው ሰው ደግሞ የዕረፍት ጊዜውን የሚያሳልፈው ውብ ወደሆኑ አካባቢዎች በመሄድና ተፈጥሮን በማድነቅ ነበር። ሲልቪያ የተባለች አንዲት ሴት ደግሞ ቅዳሜና እሁድን የምታሳልፈው በምሽት ክበቦች ነበር። እነዚህ ሰዎች የይሖዋ ምስክሮች ከሆኑ በኋላ ግን የዕረፍት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት መንገድ በሚያስደንቅ ሁኔታ ተለወጠ።
ጀርገንና ዶሪስ ሲናገሩ “የዕረፍት ጊዜያችንን የምናሳልፍባቸው ነገሮች ትንሽ ዘና እንድንል ያደርጉን የነበረ ቢሆንም ሕይወታችንን አበልጽገውት ነበር ብሎ መናገር ግን አይቻልም። አሁን ግን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲማሩ መርዳት መቻላችን ለእነሱ ሕይወት ብቻ ሳይሆን ለእኛም ሕይወት ትርጉምና ዓላማ የሚጨምር ሆኖ አግኝተነዋል” ብለዋል። ሜላ እና ሄሌናስ ምን ይላሉ? “መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉ የተሻለውን የአኗኗር መንገድ በተመለከተ መመሪያ ይሰጣል፤ ይህን ለሰዎች መናገር ደግሞ ከፍተኛ ደስታና እርካታ ያመጣል።” ሄልሙት አሁን ከበፊቱ ይበልጥ እርካታ ያገኘው ለምንድን ነው? “በመስክ አገልግሎት የማከናውነውን ነገር ይሖዋ በቁምነገር እንደሚመለከተው አውቃለሁ” ይላል። ሲልቪያም “መስበክ ማለት ሰዎችን ማነጋገርና ከእነሱ ጋር አስደሳች ውይይት ማድረግ ስለሆነ በጣም እወደዋለሁ” በማለት አስተያየቷን ሰጥታለች።
የይሖዋ ምስክሮች በሚቀጥለው ጊዜ እቤትህ ሲመጡ ብታነጋግራቸው ምን ይመስልሃል? ከእነሱ ጋር አጭር ውይይት ማድረግህ ቅዳሜና እሁድ ብቻ ሳይሆን በሕይወትህ ሙሉ ደስተኛ ወደምትሆንበት አቅጣጫ የሚመራ የመጀመሪያ እርምጃ ሊሆንልህ ይችላል።
በዕረፍት ጊዜህ ማድረግ የምትመርጠው ምንም ይሁን ምን፣ የቅዳሜና እሁድ ዕረፍትህን የሚያንጽና አስደሳች አድርገው። የምትኖረው የትም ይሁን የት፣ የምትሠራው ሥራ ምንም ይሁን ምን፣ መልካም ቅዳሜና እሁድ እንመኝልሃለን!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.12 አንዳንድ የኤሌክትሮኒክስ ጨዋታዎች ያላቸውን አደጋ በሚመለከት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “የወጣቶች ጥያቄ . . . የኮምፒውተር ወይም የቪዲዮ ጨዋታዎችን መጫወት አለብኝን?” የሚለውን የነሐሴ 22, 1996 ንቁ! መጽሔት (እንግሊዝኛ) እና “ኤሌክትሮኒክስ ጨዋታዎች—ጎጂ ጎን አላቸውን?” የሚለውን የታኅሣሥ 22, 2002 እትም (እንግሊዝኛ) ተመልከት።
^ አን.16 “የወጣቶች ጥያቄ . . . የጀብድ ስፖርቶች—መሞከር ይኖርብኛልን?” የሚለውን የሐምሌ 8, 1994 ንቁ! (እንግሊዝኛ) እና “ጀብድ አሳዳጆች—ሞት የሚያምራቸው ለምንድን ነው?” የሚለውን የጥቅምት 8, 2002 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ተመልከቱ።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ቅዳሜና እሁድ አስደሳች የሚሆነው ዕረፍትን፣ መዝናኛንና መንፈሳዊ እንቅስቃሴን በሚዛናዊነት የሚያካትት ሲሆን ነው