በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከትምህርት ሰዓት ውጭ ተቀጥሮ መሥራት የሚያስከትለው ኪሳራ

ትምህርት ቤት በሚዘጋበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን እየተማሩም ጭምር ተቀጥረው የሚሠሩ ጀርመናውያን ወጣቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። “በአገር አቀፍ ደረጃ 13 ዓመትና ከዚያ በላይ ከሆናቸው ልጆች መካከል ቢያንስ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት በአማካይ በሣምንት ውስጥ ሦስት ሰዓት ተቀጥረው ይሠራሉ” ሲል ደር ሽፒገል ዘግቧል። የጀርመን ክፍለ ሐገር በሆነችው በሄሰ ከከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መካከል ከ50 እስከ 80 በመቶ የሚሆኑት ተቀጥረው ይሠራሉ። እነዚህ ወጣቶች ሥራ የሚሠሩት አብዛኛውን ጊዜ የቤተሰባቸውን ወጪ ለመደጎም ብለው አይደለም። ከዚህ ይልቅ እንደ አዳዲስ ሞባይል ስልኮች፣ ውድ ልብሶችና መኪና ያሉትን ንብረቶች ለመግዛት እንዲሁም ሥራ መያዝ የሚያስገኘውን ነጻነት ስለሚፈልጉ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ፍላጎታቸው የሚያስከትልባቸው ኪሳራ አለ። የትምህርት ባለሞያ የሆኑት ቶማስ ሙለር “አንድ ተማሪ ባለፈው ቀን ወይም ማለዳ ተነስቶ ብዙ ሰዓት በመሥራቱ ምክንያት ዴስኩ ላይ ተደፍቶ ሲያንቀላፋ ማየት ያልተለመደ ነገር አይደለም። ለነገ የሚሆናቸውን ትምህርት ከመቅሰም ይልቅ የዛሬውን ቅንጦት ለማግኘት ይፈልጋሉ” ብለዋል። የእርሳቸው የሥራ ባልደረባ የሆኑት ክኑት ዲትማን በማከል “ልጆች አንድ ጊዜ ሸቀጥ የማግበስበስ ምኞት ከተጠናወታቸው ዝቅተኛ ውጤት ቢያገኙ እንዲያውም ክፍል ቢደግሙም ብዙ ቅር አይላቸውም” ብለዋል።

ትላልቆቹ የዝንጀሮ ዝርያዎች እያለቁ ነው

የሮይተር ዜና አገልግሎት “የሰው ልጅ አስቸኳይ የሆነ ሥር ነቀል እርምጃ ካልወሰደ የትላልቆቹ የዝንጀሮ ዝርያዎች መኖሪያ የሆኑ ደኖች በ30 ዓመት ጊዜ ውስጥ ፈጽሞ ይወድማሉ” ሲል ዘግቧል። በቅርቡ በጆሃንስበርግ፣ ደቡብ አፍሪካ ተደርጎ በነበረው በምድር ሥነ ምህዳር ጉባኤ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለ ሥልጣናት “የአውራ ጎዳናዎች፣ የማዕድን ቁፋሮ መንደሮችና የሌሎች ታህታይ መዋቅር ግንባታዎች አሁን ባለው ፍጥነት ከቀጠሉ ከአፍሪካ የትላልቅ ዝንጀሮዎች መኖሪያ አካባቢዎች ውስጥ እስከ 2030 ድረስ እንዳሉ የሚቆዩት ከ10 በመቶ ያነሱ ይሆናሉ።” አሁንም እንኳን ቢሆን የደኖች መመናመን የትላልቆቹ ዝንጀሮዎች ብዛት በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ አድርጓል። ቺምፓንዚ የተባለው የዝንጀሮ ዝርያ ከአንድ መቶ ዓመት በፊት 2, 000, 000 የነበረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ግን ከ200, 000 እንደማይበልጥ ይገመታል። በተጨማሪም ከቆላ ጎሪላዎች የቀሩት ጥቂት ሺህዎች ብቻ ሲሆኑ ከደጋ ጎሪላዎች ደግሞ የቀሩት ከጥቂት መቶዎች እንደማያልፉ ይገመታል። ሮይተርስ እንዳለው “የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ብዙ የትላልቅ ዝንጀሮ ዝርያዎች በሚገኙባቸው አሥራ ሁለት አገሮች ከተመራማሪዎች፣ ከዱር አራዊት ጥበቃ ሠራተኞች፣ ከመንግሥታትና ከአገሬው ሰዎች ጋር በመተባበር ቁጥራቸው እንዲያንሰራራ የሚያስችል ፕሮጀክት እያካሄደ ነው።”

መዝገብ የማያውቃቸው ልደቶች

“በየዓመቱ 50 ሚልዮን የሚያክሉ ሕፃናት ልደት ሳይመዘገብ እንደሚቀርና ይህም በመላው ዓለም ከሚወለዱት ሕፃናት 40 በመቶ እንደሚሆን” የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ሪፖርት አድርጓል። አክሎም “በ39 አገሮች 30 በመቶ የሚሆኑ ሕፃናት እንደተወለዱ እንደማይመዘገቡና በሌሎች 19 አገሮች ደግሞ ሳይመዘገቡ የሚቀሩት ሕፃናት ብዛት 60 በመቶ እንደሚደርስ” ገልጿል። ታዲያ ይህ ምን ትርጉም ይኖረዋል? ሕፃናት የልደት ምሥክር ወረቀት እንዲኖራቸው ካልተደረገ በሕግ ፊት በሕይወት እንዳሉ ስለማይቆጠር መሠረታዊ የሆኑ ሰብዓዊ አገልግሎቶችን ሳያገኙ ይቀራሉ። “ሕፃንን ማስመዝገብ መሠረታዊ የሆነ ሰብዓዊ መብት ከመሆኑም በላይ ትምህርትና የጤና እንክብካቤ እንደማግኘት . . . ከአድልዎ፣ ከግፍና ከብዝበዛ እንደመጠበቅ ላሉት ሌሎች መብቶች በር ከፋች ነው” ይላል ዩኒሴፍ። ልደት ባለመመዝገቡ የሚደርሰው ችግር በልጅነት ጊዜ ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም። “ያልተመዘገበው ልጅ በሚያድግበት ጊዜ . . . የጋብቻ ምሥክር ወረቀት ማግኘት አስቸጋሪ ሊሆንበት ይችላል” ይላል ዘገባው።

አብያተ ክርስቲያናትን ለሌላ አገልግሎት ማዋል

“ማርክ ቱዌይን በ1881 ሞንትሪያልን በጎበኘ ጊዜ ‘ከቤተ ክርስቲያኑ ብዛት የተነሣ ጠጠር መጣያ እንኳን ማግኘት አይቻልም’ ብሎ ነበር። ዛሬ ግን እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት በአብዛኛው የማኅበር መኖሪያ ቤቶች ሆነዋል” ይላል የሞንትሪያሉ ዘ ጋዜት የተባለው ጋዜጣ። ዛሬም በከተማይቱ ውስጥ 600 የሚያክሉ የአምልኮ ቦታዎች ቢኖሩም ጋዜጣው 100 የሚያክሉ በአብዛኛው የካቶሊክ የሆኑ አብያተ ክርስቲያናት በሚቀጥለው አሥር ዓመት ውስጥ ለሽያጭ መቅረባቸው አይቀርም ብሏል። “የሞንትሪያል ሐገረ ስብከት እንዳለው ከ1960 ወዲህ 25 የሚያክሉ የካቶሊክ ሰበካዎች ተዘግተዋል።” የካናዳ ካቶሊኮች ቁጥር በ1871 ከነበረበት 1.5 ሚልዮን በ1971 10 ሚልዮን የደረሰ ቢሆንም “በተለይ በኩቤክ የቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች ቁጥር በጣም አሽቆልቁሏል” ይላል ዘ ጋዜት። የሞንትሪያል ሐገረ ስብከት የስብከት ሥራ ኃላፊ የሆኑ በርናርድ ፎርቲን የቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች ቁጥር በ1970 ከነበረው 75 በመቶ አሽቆልቁሎ ዛሬ 8 በመቶ መድረሱን ለጋዜጣው ገልጸዋል።

ቀሳፊ ጭስ

“በከተሞች ውስጥ ለሞት ከሚያደርሱ የሳንባ ካንሰር በሽታዎች መካከል አንድ አምስተኛ የሚሆኑት በአብዛኛው ከመኪና ጭስ በሚወጡ ጥቃቅን በካይ ቅንጣቶች ምክንያት የሚመጡ ናቸው” ሲል ኒው ሳይንቲስት መጽሔት ዘግቧል። በካናዳና በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ተመራማሪዎች ግማሽ ሚልዮን የሚሆኑ አሜሪካውያንን ሕይወት ለ16 ዓመታት ተከታትለዋል። ተመራማሪዎቹ እንደ ዕድሜ፣ ጾታ፣ ዘር፣ የማጨስ ልማድ፣ አመጋገብ፣ አልኮል መውሰድና ሥራ ላይ መርዛማ ለሆኑ ንጥረ ነገሮች እንደመጋለጥ ያሉ በጤና ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ አስገብተዋል። “ጥናቱ ያተኮረው ከ2.5 ማይክሮ ሜትር ያነሰ ውፍረት ባላቸው ቅንጣቶች ላይ ነበር” ይላል ኒው ሳይንቲስት። “ምክንያቱም እነዚህ ቅንጣቶች ወደ ሳንባ ጠልቀው በመግባት ለሞት ያደርሳሉ ተብሎ ስለሚታሰብ ነው።” ለጭስ መጋለጥ የሚያስከትለው አደጋ “ከአጫሾች የሚወጣውን የትንባሆ ጭስ ለረዥም ጊዜ ከመተንፈስ እንደማይተናነስ” ጥናቱ ያረጋገጠ መሆኑን መጽሔቱ ዘግቧል።

ቴሌቪዥን ሰዎች ለታሪክ ያላቸውን አመለካከት እየቀረጸው ነው

የለንደኑ ዘ ታይምስ እንደዘገበው “ብሪታንያውያን ባለፈው አንድ መቶ ዓመት በአገራቸው ታሪክ ከተከናወኑት ነገሮች ከፍተኛ ግምት የሚሰጡት ለየትኛው እንደሆነ ሲጠየቁ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት መፈንዳትም ሆነ ከሴቶች የመምረጥ መብት መከበር ያስበለጡት የዌልስን ልዕልት የዳያናን ሞት ነው።” የታሪክ ፕሮግራሞችን ለሚያስተላልፍ አንድ የቴሌቪዥን ድርጅት በተደረገ ጥናት ከአንድ ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ባለፉት አንድ መቶ ዓመታት በብሪታንያ ታሪክ ከተከናወኑ አሥር ክስተቶች መካከል ከፍተኛ ግምት የሚሰጡት ለየትኛው እንደሆነ ተጠይቀው ነበር። የልዕልቲቱ ሞት 22 በመቶ የሚሆነውን ድምፅ ሲያገኝ፣ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጀመር 21 በመቶ፣ የሴቶች የመምረጥ መብት መከበር 15 በመቶ አግኝተዋል። በመላው ዓለም ስለተፈጸሙ ክስተቶች ሲጠየቁ ደግሞ 41 በመቶ የሚሆኑት መስከረም 11 ለደረሰው ጥቃት፣ 19 በመቶ የሚሆኑት በሂሮሺማ ላይ ለተጣለው አቶሚክ ቦምብ እንዲሁም 11 በመቶ የሚሆኑት ለበርሊን ግንብ መፍረስ ድምፅ ሰጥተዋል። ዘ ታይምስ ለአብዛኞቹ ሰዎች “ታሪክ የሚባለው በአብዛኛው በቅርብ ጊዜ በቴሌቪዥን የታየ ነገር ነው” ሲል አስተያየቱን ደምድሟል።

በፍቺና በትምህርት ቤት ውጤት መካከል ያለው ዝምድና

በቅርቡ በፈረንሳይ የሕዝብ ጉዳይ ጥናት ብሔራዊ ተቋም የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው ወላጆቻቸው የተፋቱባቸው ልጆች የሚያገኙት የትምህርት ውጤት አብረው የሚኖሩ ወላጆች ካሏቸው ልጆች ያነሰ ነው በማለት ለ ሞንድ የተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ ዘግቧል። ለአካለ መጠን ከመድረሳቸው በፊት ወላጆቻቸው የተለያዩባቸው ልጆች ማኅበራዊ ደረጃቸውም ሆነ ያደጉበት ባሕል ምንም ዓይነት ቢሆን ወላጆቻቸው ካልተለያዩባቸው ልጆች በአማካይ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ከሚደርስ ጊዜ በፊት ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ። ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ቤተሰቦች ውስጥ የሚኖሩ አብዛኞቹ ልጆች የሁለተኛ ደረጃ ፈተናቸውን የሚያልፉ ሲሆን በተመሳሳይ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ ወላጆቻቸው የተለያዩባቸው ልጆች ግን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ዲፕሎማቸውን የማግኘት ዕድላቸው ከእጥፍ በላይ ያነሰ ነው። በፈረንሳይ 40 በመቶ የሚሆኑት ጋብቻዎች ይፈርሳሉ።

ኤች አይ ቪ/ኤድስ “ከቁጥጥር ውጭ” ሆኗል

“በመላው ዓለም በየዓመቱ 40 ሚልዮን የሚያህሉ ሰዎች በኤች አይ ቪ ይያዛሉ፣ 20 ሚልዮን የሚያህሉ ደግሞ በኤድስ ምክንያት ይሞታሉ እንዲሁም 750, 000 የሚያህሉ ሕፃናት ኤች አይ ቪ ይዟቸው ይወለዳሉ” ይላል ዘ ላንሰት የተባለው የብሪታንያ ሕክምና መጽሔት። በ2001 ብቻ አምስት ሚልዮን የሚያህሉ አዳዲስ ሰዎች በኤች አይ ቪ ሲያዙ 3 ሚልዮን የሚያህሉ ሰዎች በኤድስ ምክንያት ሞተዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤች አይ ቪ/ኤድስ ፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት ፒተር ፒዮ ወረርሽኙ “ፈጽሞ ከቁጥጥር ውጭ” የመሆን ደረጃ ላይ ከመድረሱም በላይ “ከዚህ የሚብስበት ጊዜ ገና እየመጣ ነው” ብለዋል። በሚቀጥሉት 20 ዓመታት 70 ሚልዮን የሚያህሉ ሰዎች በኤድስ እንደሚሞቱ ገምተዋል። ከሰሐራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገሮች በአንዳንድ ከተሞች ከሚኖሩ ሰዎች መካከል ከ30 እስከ 50 በመቶ የሚደርሱት በኤች አይ ቪ የተያዙ ናቸው። በርካታ ወጣቶች እያለቁ በመሆናቸው እስከ 2020 ድረስ ለሥራ ከደረሰው ሕዝብ መካከል 25 በመቶ የሚሆነው እንደሚያልቅ ተሰግቷል። “በተለይ በሕፃናት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት በኢኮኖሚ በማገገም ረገድ ከፍተኛ የሆነ ተጽእኖ ይኖረዋል” ይላል ዘ ላንሰት። በዚምባብዌ “ከአምስት ሕፃናት መካከል አንዱ ወደ ጉርምስና ዕድሜ ከመድረሱ በፊት ቢያንስ ከወላጆቹ አንዱን ያጣል።”

ጡት የማጥባት ጥቅም

“ባጭሩ አዲስ ለተወለዱ ሕፃናት ከእናታቸው ጡት የተሻለ ምግብ አይገኝም” ሲሉ ኒውሮሰርጀን የሆኑት ዶክተር ሳንጄይ ጉፕታ ታይም መጽሔት ላይ ጽፈዋል። “የእናታቸውን ጡት የሚጠቡ ሕፃናት ታመው ሆስፒታል የመግባት፣ በጆሮ ኢንፌክሽን፣ በተቅማጥ፣ በቆዳ ሽፍታ፣ በአለርጂዎችና በሌሎች የጤና ችግሮች የመያዝ ዕድላቸው ጡጦ ከሚጠቡ ሕፃናት በጣም ያነሰ ነው።” በተጨማሪም ጡት ማጥባት ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተያያዙ በሽታዎችን እንደሚከላከል ተገልጿል። አንድ በዴንማርክ የተደረገ ጥናት “ሕፃን ሳሉ ከሰባት እስከ ዘጠኝ ለሚደርሱ ወራት ጡት የጠቡ ልጆች ለሁለት ሳምንታት ወይም ከዚያ ላነሰ ጊዜ ብቻ ጡት ከጠቡ ልጆች የበለጠ የማስተዋል ችሎታ እንዳላቸው” አረጋግጧል። የአሜሪካ የሕፃናት ሕክምና አካዳሚ አንድ ሕፃን ቢቻል ለአንድ ዓመት ወይም ከዚያ ለሚበልጥ ጊዜ ካልሆነም ለስድስት ወራት ቢጠባ ጥሩ እንደሚሆን ያሳስባል። “ጡት ማጥባት የሚጠቅመው ሕፃናቱን ብቻ አይደለም” ይላል ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት። በሠላሳ አገሮች በሚኖሩ 150, 000 ሴቶች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንደገለጸው “አንዲት ሴት ጡት ባጠባችበት አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድልዋን በ4.3 በመቶ ትቀንሳለች።” ይሁን እንጂ “ከአሜሪካ እናቶች መካከል በአማካይ ከሁለት እስከ ሦስት ወራት የሚያጠቡት ግማሽ የሚሆኑት ብቻ ናቸው።”