በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሙዝ እርሻ እንጎብኝ

የሙዝ እርሻ እንጎብኝ

የሙዝ እርሻ እንጎብኝ

ደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ሙዝ በጣም እወዳለሁ። ብዙ ሰዎች እንደኔው የሚወዱ ይመስለኛል። ሙዝ ጣፋጭ ከመሆኑም በላይ በቪታሚኖች፣ በማዕድናትና በአሰር የበለጸገ ነው። ስለዚህ ግሩም ፍሬ ይበልጥ ለማወቅ ትፈልጋለህ? በቅርቡ አንድ ገበሬና ባለቤቱ ስለ ሙዝ ተክል አበቃቀል አሳይተውኝ ነበር።

ቶኒና ማሪ የግብርና ሥራቸውን የሚያካሂዱት በደቡብ አፍሪካ ሰሜናዊ ክፍለ ሐገር ሌቩቡ በሚባለው አካባቢ ነው። ሃምሳ አምስት ሄክታር ስፋት ባለው እርሻቸው ላይ የተለያየ ሰብል ያመርታሉ። ዋነኛው ምርታቸው ግን ሙዝ ነው። ቶኒ በጣም ተወዳጅ ስለሆነው ስለዚህ ፍሬ ሊነግረን ይፈልጋል።

የሙዝ አስተዳደግና የሚስማማው የአየር ንብረት

“ለሙዝ የሚስማማው የአፈር ዓይነት” ይላል ቶኒ “አሸዋማ ወይም ድንጋያማ ሳይሆን ይበልጥ ሸክላማ የሆነ አፈር ነው። በተጨማሪም አፈሩ ጥልቅና ውሃ የማይቋጥር መሆን ይኖርበታል። ውርጭ የሌለበት አካባቢ በጣም ይስማማዋል። እንዲያውም ቆላማ የሆነ አካባቢ ይወድዳል። የሌቩቡ ዓመታዊ አማካይ የአየር ሙቀት ከ12 እስከ 35 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይደርሳል።” ስለ ዝናብ ስጠይቀው “ሙዝ በቂ ዝናብ ማግኘት ወይም በየሣምንቱ በመስኖ ውሃ መጠጣት ይፈልጋል” በማለት ገለጸልኝ።

የሙዝ ተክል ዛፍ ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ ግንዱ እንጨት ሳይሆን የተነባበረ ቅጠል ነው። ሙዝ ትልቅ ግንድ የለሽ ተክል ነው እንጂ ዛፍ አይደለም። ግንድ ሊባል የሚችለው መሬት ውስጥ ያለው የተክሉ ክፍል ነው። ከዚህ ክፍል ከታች ሥሮች ሲወጡ ከላይ በኩል ደግሞ ቅጠሎችና በመጨረሻም ወይን ጠጅ ቀለም ያለው አበባ ይበቅላል። በተጨማሪም ከመሬት በታች ካለው ከዚህ የተክሉ ክፍል አዳዲስ የሙዝ ተክሎች ያቆጠቁጣሉ።

የሙዝ ተክል ሦስት ዋና ዋና የእድገት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን እነዚህን ደረጃዎች የአካባቢው ገበሬዎች “አያት፣ ልጅ እና የልጅ ልጅ” ብለው ይጠሯቸዋል። (ፎቶግራፉን ተመልከት) “አያቲቱ” በዚህ ዓመት ፍሬ የሰጠች እንደሆነ “ልጂቱ” በሚቀጥለው ዓመት፣ “የልጅ ልጂቱ” ደግሞ በሦስተኛው ዓመት ይሰጣሉ። “የልጅ ልጆቹ” “ከእናቲቱ” ጎን ብዙ ሆነው ያቆጠቁጣሉ። የእነዚህ “ሕፃናት” ቁመት ጉልበት አካባቢ ሲደርስ ከመካከላቸው ሊያፈራ ይችላል ተብሎ የሚገመተው ብቻ ይተውና ሌሎቹ በሙሉ ይቆረጣሉ።

ውሎ አድሮ ዐበዛ ሙዝ የሚያወጣው ወይን ጠጅ ቀለም ያለው ትልቅ አበባ ከሥሩ ተነስቶ በተክሉ መሃል ለመሃል ካደገ በኋላ በመጨረሻዎቹ ሁለት ቅጠሎች መሃል ብቅ ይልና ቁልቁል ይዘቀዘቃል። አበቦቹ ሲረግፉ ከ10 እስከ 15 የሚደርሱ እንጭጭ የሙዝ ፍሬዎች የያዙ እጆች ያቆጠቁጣሉ። ስለ ሙዝ አበቃቀል ለማያውቅ ሰው ፍሬዎቹ ተዘቅዝቀው የበቀሉ ሊመስሉ ይችላሉ። በአንድ እጅ ላይ እስከ 20 የሚደርሱ ነጠላ የሙዝ ፍሬዎች ወይም ጣቶች ይኖራሉ።

ሲደርስ

አበቦቹ ከሚታዩበት ሙዙ ለመቆረጥ እስከሚደርስበት ጊዜ ድረስ እንደ ወቅቱ ሁኔታ ከሦስት እስከ ስድስት ወር ሊፈጅ ይችላል። የሚቆረጠው ገና አረንጓዴ ሳለ ቢሆንም ፍሬዎቹ እድገታቸውን የጨረሱና ፈርጠም ያሉ መሆን ይገባቸዋል። የአንድ ዐበዛ ሙዝ ክብደት እስከ 35 ኪሎ ግራም ሊመዝን ይችላል። ዐበዛው ከተቆረጠ በኋላ ወደሚታሸግበት ቦታ በሚጓጓዝበት ጊዜ እንዳይጋጋጥና እንዳይቆሳስል በፕላስቲክ ከረጢት ይሸፈናል። እዚያም ከደረሰ በኋላ ይገነጣጠልና (አንዱ ግንጣይ ከሦስት እስከ ስድስት የሚደርሱ ሙዞችን ሊይዝ ይችላል) እንዳይበሰብስ የሚከላከል መድኃኒት ይረጭበታል።

በደቡብ አፍሪካ ሙዙ ወደ ማብሰያ ቤት የሚገባው ሰም በተቀባና አየር በሚያስገባ ካርቶን ታሽጎ ነው። በዚህ ቤት ውስጥ ቶሎ እንዲበስል ኤትሊን የተባለ ጋዝ ይረጭበታል። * ካርቶኖቹ በተወሰነ የሙቀት መጠን ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን ከቆዩ በኋላ ለሸማች እንዲደርሱ ይጫናሉ።

“ለራስህ አድልተህ ነው ባትሉኝ” አለ ቶኒ ፈገግ እያለ “ምናልባት በአፈሩ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም የሌቩቡ ሙዝ ልዩ የሆነ ጣዕም አለው። ወደ ውጭ ለመላክ ከሚያስችል ከተማ የራቅን በመሆናችን ግን የዚህ አካባቢ ሙዝ በአገር ውስጥ ብቻ ተወስኖ ቀርቷል።”

ለጤና ጥሩ ነው

ሙዝ ፖታሲየም በተባለው ማዕድን የበለጸገ ነው። ኼልዝ የተባለው መጽሔት ስለ ሙዝ ባወጣው ርዕስ “በርካታ ጥናቶች ይህ ማዕድን አጥንት እንደሚያጠነክርና ከደም ብዛት እንደሚከላከል አረጋግጠዋል” በማለት ገልጿል። መጽሔቱ በማከል “ነፍሰ ጡር ለሆነች ወይም ለማርገዝ በሚያስችል ዕድሜ ላይ ለምትገኝ ሴት በጣም አስፈላጊ የሆነውና ጤናማ ሕፃን እንዲወለድ የሚረዳው የቪታሚን ቢ ክፍል የሆነው ፎሊክ አሲድ በሙዝ ውስጥ ይገኛል” ብሏል። በተጨማሪም በሙዝ ውስጥ ካልስየም ከአጥንት ጋር እንዲዋሃድና ጠንካራ እንዲሆን የሚረዳውን ማግኒዝየምን የመሰሉ ሌሎች አስፈላጊ ማዕድናት ይገኛሉ።

በሙዝ ውስጥ የሚገኘው ፕሮቲን ሰውነታችን በበቂ መጠን የማያመነጫቸውን ወይም ጭራሽ የማይሠራቸውን አስፈላጊ አሚኖ አሲዶች በሙሉ ጨምሮ 18 አሚኖ አሲዶችን ይዟል። በተጨማሪም ሙዝ 22 በመቶው ካርቦሃይድሬት ስለሆነና በቀላሉ የሚፈጭ ፍሬ በመሆኑ ቶሎ ብሎ ወደ ጉልበት ይለወጣል። ማሪም “ከሙዝ ቪታሚን ኤ፣ ቢ እና ሲ ማግኘት ይቻላል። በተጨማሪም በአንድ ጊዜ ብዙ ሙዝ መብላት ስለማይቻል የምግብ ፍላጎትን ለመቆጣጠር ይረዳል” በማለት አስተያየቷን አክላለች። ታዲያ ለምን አትበላም? ለጤና ጠቃሚ ነው፤ ደግሞም ሲበሉት ይጣፍጣል!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.12 ሙዝ በተፈጥሮ ሂደት በሚበስልበት ጊዜ የመብሰል ሂደቱን የሚያፋጥነውን ይህን ጋዝ ስለሚያመነጭ ጥቂት የበሰሉ ሙዞችን በመሃል በመሃሉ በማስቀመጥ አረንጓዴ የሆኑትን ሙዞች ማብሰል ይቻላል።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ቅጠል

አበባ/ሙዝ

የቅጠል አፎት

የመሬት ወለል

ከመሬት በታች ያለ ግንድ

ሥር

[ምንጭ]

ስዕል:- Based on drawing from The Complete Encyclopedia of Illustration/J. G. Heck

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

አያት

ልጅ

የልጅ ልጅ

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወይን ጠጅ ቀለም ያለው ትልቁ አበባ ውሎ አድሮ የሙዝ ዐበዛ ይሆናል

[ምንጭ]

Photo by Kazuo Yamasaki

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለመቆረጥ የደረሰ (በስተግራ)፣ አዲስ የሙዝ ተክል (ከላይ)