በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የደረሰብኝ የአካል ጉዳት ሕይወቴን ለወጠው

የደረሰብኝ የአካል ጉዳት ሕይወቴን ለወጠው

የደረሰብኝ የአካል ጉዳት ሕይወቴን ለወጠው

ስታንሊ ኦምቤቫ እንደተናገረው

በ1982 በአንድ እየበረረ በሚያልፍ መኪና ተገጨሁ። በጊዜው ታከምኩና ዕለታዊ ተግባሬን ማከናወን ጀመርኩ። በአንገቴና በደረቴ መካከል የሚገኝ አንድ ደንደስ ወልቆ ስለነበረ በየጊዜው የሚሰማኝ የሕመም ስሜት ቢኖርም ያን ያህል ከባድ ችግር አልፈጠረብኝም። ከ15 ዓመታት በኋላ ግን በሕይወቴ አጋጥሞኝ የማያውቅ እምነት የሚፈታተን ከባድ ሁኔታ አጋጠመኝ።

አደጋው በፊትም ሆነ፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ከአደጋው በኋላ ብርቱ ሰው ነበርኩ። ቅዳሜና እሁድ ከ10 እስከ 13 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ርቀት እሮጥ ነበር። ኳስ እጫወትና ከባድ የጉልበት ሥራ እሠራ ነበር። በምኖርበት በኬንያ የይሖዋ ምሥክሮች በገነቧቸው የመንግሥት አዳራሾችና የትላልቅ ስብሰባ አዳራሽ ሥራ ላይ ተካፍያለሁ።

ከ1997 ጀምሮ ግን የደረቴ ሕመም ይበልጥ እየጠነከረና ፋታ የማይሰጥ እየሆነብኝ መጣ። በተደረገልኝ ምርመራ አንድ የተዛነፈ አጥንት አከርካሪዬን እንደሚጫን ተረጋገጠ። ይህም በመግቢያው ላይ የተናገርኩት የመኪና አደጋ ያደረሰብኝ ጉዳት ነው።

ጤናዬ ከማሽቆልቆሉ በፊት በሽያጭ ሠራተኛነት ተቀጥሬ እሠራ ነበር። ሥራው ከሚያስገኝልኝ ጥቅማ ጥቅሞች አንዱ ነጻ ሕክምና ማግኘት ነበር። በሥራው ዓለም የተዘረጋልኝ ዕድል በጣም ብሩሕ ሆኖ ታይቶኝ ነበር። ከ1998 አጋማሽ ጀምሮ ግን ከደረቴ እስከ እግሬ ድረስ የመደንዘዝ ስሜት ይሰማኝ ጀመር። ከዕለት ወደ ዕለት የጤናዬ ሁኔታ ማሽቆልቆል ጀመረ።

ብዙም ሳይቆይ ሥራዬንና በሥራዬ ምክንያት አገኛቸው የነበሩትን ጥቅማ ጥቅሞች በሙሉ አጣሁ። በዚህ ጊዜ ሁለቱ ሴቶች ልጆቼ ሲልቪያ እና ዊልኸልሚና 13 እና 10 ዓመት ሆኗቸው ነበር። ከሥራ ከወጣሁ በኋላ ባለቤቴ ጆይስ በምታገኘው ደመወዝ መተዳደር ነበረብን። በዚህ ባጋጠመን አዲስ ሁኔታ የግድ አስፈላጊ ያልሆኑ ወጪዎችን ማስወገድ ነበረብን። በዚህ መንገድ ኑሯችንን ማሸነፍ ቻልን።

አሉታዊ የሆኑ ስሜቶች

ያለብኝ ችግር ከባድ መሆኑን ይበልጥ እየተገነዘብኩ ስመጣ በጣም የምበሳጭ፣ ስለ ራሴ ብቻ የማስብና አሉታዊ አመለካከት ያለኝ እንዲሁም በትንሽ በትልቁ የምቆጣና የምናደድ ሆንኩ። በጭንቀት የምዋጥባቸው ጊዜያት በጣም ብዙ ነበሩ። ችግሩ ያልነካው የቤተሰብ አባል አልነበረም። ባለቤቴና ሴቶች ልጆቻችን አይተው የማያውቁት ችግር ውስጥ ገቡ።

በወቅቱ ይሰማኝ የነበረው ስሜት ትክክል ነው ብዬ አስብ ነበር። ክብደቴ በጣም ጨመረ። ሽንቴንና ዓይነ ምድሬን መቆጣጠር ያስቸግረኝ ነበር። ይህም በጣም ያሳፍረኝ ነበር። ከሰው ነጠል ብዬ ማልቀስ የዕለት ተዕለት ተግባሬ እየሆነ መጣ። ለሚመለከተኝ ሰው አስቂኝ እስኪሆን ድረስ አምርሬ የምቆጣባቸው ጊዜያት ነበሩ። ያጋጠመኝን ሁኔታ የያዝኩበት መንገድ ጥሩ እንዳልነበረ ይገባኛል።

የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያን ጉባኤ ሽማግሌ እንደመሆኔ ክርስቲያን ባልደረቦቼን ምንም ዓይነት መከራ ቢደርስባቸው ይሖዋን እንዳያማርሩ ብዙ ጊዜ እመክራቸው ነበር። እኔ ግን አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ብዙ ጊዜ ‘ይሖዋ እንዲህ ያለው ነገር እንዲደርስብኝ የፈቀደው ለምንድን ነው?’ እያልኩ ከራሴ ጋር ተሟግቻለሁ። እንደ 1 ቆሮንቶስ 10:​13 ያሉትን ጥቅሶች ተጠቅሜ ሌሎችን ያጽናናሁባቸው ጊዜያት ቢኖሩም በኔ ላይ የደረሰውን ግን ማንም ሊሸከመው እንደማይችል ሆኖ ተሰማኝ።

ከባድ ሕክምና

ጥሩ ሕክምና ማግኘት ትልቅ ችግር ሆነብኝ። በአንድ ቀን ውስጥ በፊዝዮቴራፒስት፣ በካይሮፕራክተርና በአኩፓንቸሪስት ታይቻለሁ። ለቅጽበት ፋታ ከማግኘት ያለፈ ምንም ጥቅም አላገኘሁም። አንድ የአጥንት ቀዶ ሕክምና ሐኪምና ሌላ የነርቭ ቀዶ ሕክምና ሐኪምን ጨምሮ የተለያዩ ዶክተሮችን አማክሬአለሁ። ሁሉም ሕመሙን ለማስታገስና የተዛነፈውን አጥንት ለማውጣት ቀዶ ሕክምና እንደሚያስፈልገኝ ነገሩኝ። በመጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነቴ ምክንያት በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን ደም እንዲሰጠኝ እንደማልፈቅድ ለሕክምና ባለሞያዎቹ በግልጽ ነገርኳቸው።​—⁠ሥራ 15:​28, 29

የመጀመሪያው ሐኪም ጀርባዬን በመክፈት ቀዶ ሕክምና እንደሚያደርግልኝ ገለጸልኝ። ሕክምናው አደጋ ሊኖረው እንደሚችልም አልሸሸገም። ይሁን እንጂ ይህ ሐኪም ደም እንደማይሰጠኝ ቃል አልገባልኝም። ተመልሼ አልሄድኩም።

ሁለተኛው ሐኪም በአንገቴ በኩል አከርካሪ አጥንቴን ማከም እንደሚችል ነገረኝ። እንዲህ ያለውን ቀዶ ሕክምና ገና ስሰማው አስፈራኝ። ደም አልወስድም ማለቴን እንደ ችግር ባይቆጥረውም ወዲያው ኦፕራሲዮን መሆን እንዳለብኝ ከመናገር በቀር ዝርዝር ሁኔታዎችን ሊገልጽልኝ ፈቃደኛ አልሆነም። እርሱንም ተውኩት።

ይሁን እንጂ አገራችን ባለው የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ በሚሠሩ የይሖዋ ምሥክሮች እርዳታ ተባባሪ ዶክተር ለማግኘት ቻልኩ። ሦስተኛው ዶክተር ሊጠቀምበት ያሰበው ዘዴ ከሁለተኛው ብዙም የተለየ አልነበረም። ከአንገቴ ጀምሮ ወደታች ቀዶ ሕክምናውን እንደሚያደርግ ተናገረ። በዚህ ሁኔታ ሊደርስ የሚችለው አደጋ በጣም አነስተኛ እንደሚሆን ገለጸልኝ።

ቀዶ ሕክምናው ስለሚከናወንበት ሁኔታ የሰጠኝ ሥዕላዊ መግለጫ በጣም አስፈራኝ። እንዲህ ያለው ቀዶ ሕክምና የሚከናወነው እንደ ልብና ሳንባ ያሉት በቀላሉ ሊጎዱ የሚችሉ ብልቶች በሚገኙበት አካባቢ መሆኑን ማወቄ ደግሞ ፍርሃቴን ይበልጥ አባባሰው። በሕይወት እተርፍ ይሆን? እንዲህ ያለው አሉታዊ አስተሳሰብ ሥጋቴን እንደማይቀንስልኝ የታወቀ ነው።

ኅዳር 25 ቀን 1998 በናይሮቢ ሆስፒታል አራት ሰዓት የፈጀ የተሳካ ቀዶ ሕክምና አደረግሁ። ሕክምናው ከዳሌዬ ጥቂት አጥንት ቆርጦ መውሰድን የሚጠይቅ ነበር። ተቆርጦ የተወሰደው አጥንት ቅርጹ ከተስተካከለ በኋላ በሕመምተኛው ቦታ ላይ በብረት መያያዝ ነበረበት። ሕክምናው ችግሬን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ባይችልም ረድቶኛል። የምራመደው በብዙ ሥቃይ ነበር። አሁንም ቢሆን ሁልጊዜ ይደነዝዘኛል።

አዎንታዊ ዝንባሌ

ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ባጋጠመኝ ሁኔታ ምክንያት በሃዘንና በትካዜ ብዙ ጊዜ አሳልፌአለሁ። የሚያስገርመው ግን በርካታ የሕክምና ሠራተኞች ብሩሕ አመለካከትና እርጋታ አለህ እያሉ ያመሰግኑኝ ነበር። እንዲህ የተሰማቸው ለምን ነበር? በጣም ኃይለኛ የሆነ ሕመም ቢኖረኝም በአምላክ ላይ ስላለኝ እምነት እነግራቸው ነበር።

በደረሰብኝ ሁኔታ የምቆጣባቸውና የምማረርባቸው ጊዜያት ቢኖሩም በይሖዋ እታመን ነበር። የራሴ ደካማነት እስኪያሳፍረኝ ድረስ ሁልጊዜ ይረዳኝና ይደግፈኝ ነበር። እንደኔ ባለ ሁኔታ ውስጥ የሚኖርን ሰው እንደሚያጽናኑ የማውቃቸውን ጥቅሶች በሙሉ ለማንበብና ለማሰለሳል ቁርጥ ውሳኔ አደረግሁ። ከእነዚህ መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል:-

ራእይ 21:​4:- “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም።” መጽሐፍ ቅዱስ ልቅሶና ሕመም ለዘላለም የማይኖርበት አዲስ ዓለም እንደሚመጣ በሰጠው ተስፋ ላይ ማሰላሰል በእርግጥም ያጽናናል።

ዕብራውያን 6:​10:- “እግዚአብሔር፣ ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው፣ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና።” አቅሜ በእጅጉ የቀነሰ ቢሆንም ይሖዋ በአገልግሎቱ ለማደርገው ጥረት ከፍተኛ ግምት እንደሚሰጥ አውቅ ነበር።

ያዕቆብ 1:​13:- “ማንም ሲፈተን:- በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም።” ይህ ምንኛ እውነት ነው! ይሖዋ መከራ እንዲደርስብኝ ይፍቀድ እንጂ መከራው እንዲደርስብኝ ያደረገው እርሱ አይደለም።

ፊልጵስዩስ 4:​6, 7:- “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” ጸሎት በእጅጉ ያስፈልገኝ የነበረውን የአእምሮ ሰላም እንዳገኝ ረድቶኛል። ይህም ተረጋግቼ የደረሰብኝን ችግር እንድቋቋም አስችሎኛል።

እነዚህን ጥቅሶች ተጠቅሜ ችግር ያጋጠማቸውን ሌሎች ሰዎች አበረታትቻለሁ። ደግሞም ማበረታቻ አግኝተውባቸዋል። ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆኑ ግን ሙሉ በሙሉ የተገነዘብኩት አሁን ነው። ትሕትናን ለማወቅና በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ የመታመንን አስፈላጊነት ለመማር ይህን የመሰለ ሕመም መሸከም አስፈልጎኛል።

እንድበረታ የረዱኝ ሌሎች ነገሮች

የክርስቲያን ወንድማማች ማኅበር በችግር ጊዜ መደገፊያና ምሰሶ ሆኖ እንደሚያቆም የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው። ሆኖም የክርስቲያን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ዋጋማነት ችላ ብሎ ማለፍ በጣም ቀላል ነው። እኛን ለመርዳት ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር በጣም አነስተኛ ቢሆንም እንኳን ምንጊዜም ከጎናችን አይለዩም። በእኔ ሁኔታም ይህንን ለማየት ችያለሁ። ሁልጊዜ አንዳንድ ጊዜም በጣም ማልደው መጥተው አልጋዬ አጠገብ ቆመው ማየት ያልተለመደ ነገር አልነበረም። በሕክምና ወጪዬ ሊረዱኝ እስከመጠየቅ ደርሰዋል። ሁኔታዬን ተመልክተው ሊረዱኝ በተነሳሱት ወንድሞችና እህቶች ልቤ በጣም ተነክቷል።

በጉባኤያችን ያሉት ምሥክሮች አሁን ያለኝ አቅም በጣም ውስን እንደሆነ ያውቃሉ። በአሁኑ ጊዜ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች ሆኜ በማገልገል ላይ ስሆን በጣም ተባባሪ ከሆነ የክርስቲያን ሽማግሌዎች አካል ጋር እሠራለሁ። እስካሁን ሳላገለግል ያሳለፍኩት አንድም ወር የለም። ሕመሜ በጣም ተባብሶ በነበረበት ጊዜ ሁለት ሰዎች ሕይወታቸውን ለይሖዋ ወደመወሰን ደረጃ እንዲደረሱ ረድቼአለሁ። አንደኛው በአሁኑ ጊዜ ናይሮቢ በሚገኝ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ ያገለግላል።

በዚህ ሁሉ መከራዬ ያልተለየችኝን ባለቤቴን ለማመስገን የሚበቃ ቃል ማግኘት አልችልም። ቁጣዬን፣ ተለዋዋጭነቴን፣ ምክንያተ ቢስነቴንና ብስጭቴን ሁሉ ችላ ኖራለች። በጣም በሚያመኝና በማለቅስበት ጊዜ ታረጋጋኝና ታጽናናኛለች። ያላት ጥንካሬና መከራ ቻይነቷ በጣም ያስደንቀኛል። በእርግጥም ‘እውነተኛ ወዳጅ’ ሆናልኛለች።​—⁠ምሳሌ 17:​17

ልጆቼም ካጋጠመኝ ሁኔታ ጋር ተላምደዋል። የተቻላቸውን ያህል ሊረዱኝ ይጣጣራሉ። እናታቸው በማትኖርበት ጊዜ የሚያስፈልገኝን አውቀው ቶሎ ብለው ይረዱኛል። ሲልቪያ በጣም ደክሞኝ እቤት ውስጥ መንቀሳቀስ ሲያቅተኝ እንደ “ምርኩዝ” ሆና ትረዳኛለች።

ታናሿ ልጄ ሚናስ? እቤት ውስጥ ከወደቅሁ በኋላ መነሳት ያቃተኝን ጊዜ አስታውሳለሁ። ከእርሷ በስተቀር እቤት ማንም አልነበረም። ባለ በሌለ ጉልበቷ ብድግ ካደረገችኝ በኋላ ቀስ ብላ ወደ ክፍሌ አስገባችኝ። እንዴት እንዲህ ለማድረግ እንደቻለች እስከዛሬ ድረስ አይገባትም። የዚያን ዕለት ያሳየችው ጉብዝናዋ በአእምሮዬ ውስጥ ተቀርጾ ቀርቷል።

በሕይወቴ ውስጥ ይህን በአካሌ ላይ የደረሰብኝን ጉዳት ተቋቁሞ እንደመኖር ያለ ከባድ ትግል አጋጥሞኝ አያውቅም። አሁንም ገና እየታገልኩ ነው። ይህን ያህል ሕይወቴንና እምነቴን የተፈታተነ ችግር አጋጥሞኝ አያውቅም። ስለ ትሕትና፣ ምክንያታዊ ስለመሆንና ራስን በሌሎች ቦታ አድርጎ ስለማየት በጣም ብዙ ትምህርት አግኝቻለሁ። ሙሉ በሙሉ በይሖዋ መታመኔና በእርሱ መመካቴ ይህን የሚያህል ችግር እንድቋቋም አስችሎኛል።

“የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን” የሚለው የሐዋርያው ጳውሎስ ቃል ምን ያህል እውነት እንደሆነ ለማወቅ ችያለሁ። (2 ቆሮንቶስ 4:​7) አምላክ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” እንደሚመጣ የሰጠው ተስፋ በእጅጉ ያጽናናኛል። (2 ጴጥሮስ 3:​13) አሁንም በጣም አቅመ ቢስና በራሴ ምንም ላደርግ የምችል ባለመሆኔ ይሖዋ ራሱ ተሸክሞ ወደ አዲሱ ዓለም እንዲያስገባኝ እጸልያለሁ።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከቤተሰቤ ጋር በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች መካፈሌ እንድጸና ረድቶኛል