በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጉዲፈቻ የተሰጠሁት ለምንድን ነው?

ጉዲፈቻ የተሰጠሁት ለምንድን ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

ጉዲፈቻ የተሰጠሁት ለምንድን ነው?

“ከአካል ጉዳተኛነት ተለይቶ አይታይም። የማይሽር የስሜት ጠባሳ ትቶ ያልፋል።”​—ሮበርት

ገና እንደተወለደ ጉዲፈቻ የተሰጠ አንድ ሰው ሕይወቱን የገለጸው ከላይ ባሉት ቃላት ነው። አክሎም እንዲህ ብሏል:- “በሕይወት ዘመናችሁ በሙሉ እውነተኛ ቤተሰቦቼ እነማን ናቸው? የት ነው የሚኖሩት? ጥለውኝ የሄዱት ለምንድን ነው? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ትጓጓላችሁ።”

አባቷ የማደጎ ልጅ የነበረው ሻንትየል እውነተኛ አያቶቿን ማወቅ ባለመቻሏ የሚሰማትን ቁጭት እንዲህ በማለት ገልጻለች:- “አጎቶቼን፣ አክስቶቼንና ልጆቻቸውን ሳላውቃቸው በመቅረቴ እንደተታለልኩ ሆኖ ይሰማኛል።” ጉዲፈቻ የተሰጡ ልጆች ሁሉ እንዲህ ዓይነት ስሜት ባይኖራቸውም አንዳንዶች ግን ቁጭት የሚያድርባቸው ለምንድን ነው?

የቁጣ መንስኤ ሊሆን ይችላል

አንድ ልጅ ያሳደጉት እውነተኛ ቤተሰቦቹ አለመሆናቸውን ሲያውቅ ከፍተኛ የስሜት ቀውስ ሊደርስበት ይችላል። ገና በሕፃንነቷ ጉዲፈቻ የተሰጠችው ካትሪና እንዲህ ትላለች:- “ወላጅ እናቴ ጉዲፈቻ የሰጠችኝ ለምን እንደሆነ ስላልገባኝ ነገሩ በጣም ያናድደኝ ነበር። እናቴ ጥላኝ የሄደችው አስቀያሚና አስቸጋሪ ስለነበርኩ እንደሆነ ተሰማኝ። ዕድሉን ሰጥታኝ ቢሆን ኖሮ እንድትኮራብኝ አደርጋት ነበር። ስለ ወላጅ እናቴ ባሰብሁ ቁጥር የበለጠ እናደዳለሁ።”

ካትሪና ከአሳዳጊ ወላጆቿ ጋር ያላት ግንኙነትም በጣም እየሻከረ ሄደ። “አሳዳጊ ወላጆቼ ከእናቴ ነጥቀው እንደወሰዱኝ ስለሚሰማኝ ንዴቴን የምወጣው በእነርሱ ላይ ነበር” በማለት ተናግራለች። በእርግጥም አንዳንድ ጊዜ የቁጡነት ባሕርይ ጉዲፈቻ የተሰጡ ልጆች ስሜታቸውን የሚገልጹበት መንገድ ነው።

እንዲህ ዓይነቱ የቁጣ ስሜት ጎጂ ሊሆን ይችላል። ከካትሪና ሁኔታ መመልከት እንደሚቻለው አንዳንድ ጊዜ በተሳሳተ መንገድ ወይም ምንም ባልበደሉህ ሰዎች ላይ ንዴትህን ትወጣ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ከንዴት ተቈጠብ፤ ቊጣንም ተወው” የሚል ምክር ይሰጣል። (መዝሙር 37:8 አ.መ.ት) እንደዚህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? የአምላክ ቃል “ሰውን ጠቢብ አእምሮው [“ማስተዋል፣” NW ] ከቍጣ ያዘገየዋል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 19:11) ያለህበትን ሁኔታ በማስተዋል መመልከትህ ያደረብህን ንዴት ለማብረድ ሊረዳህ ይችላል። እንዴት?

የተሳሳተ አስተሳሰብን ማስወገድ

ማስተዋል ንዴትህን የሚያባብሱትን ግምታዊ አስተሳሰቦች በጥንቃቄ እንድትገመግም ይረዳሃል። ለምሳሌ ያህል፣ የማደጎ ልጅ ከሆንህ እውነተኛ ወላጆችህ ጉዲፈቻ የሰጡህ አንድ ዓይነት ጉድለት ስለነበረብህ እንደሆነ ይሰማሃል? ካትሪና እንደዚህ ተሰምቷት ነበር። ይሁን እንጂ ሁኔታው ሁልጊዜ እንደዚያ ነው? ወላጆችህ ለምን ጉዲፈቻ እንደሰጡህ ማወቅ አስቸጋሪ ሊሆን ቢችልም እንዲህ ዓይነቱን አፍራሽ አስተሳሰብ እንድታስወግድ የሚረዱህ አጥጋቢ ምክንያቶች አሉ። ደግሞም አብዛኛውን ጊዜ ወላጆች ልጆቻቸውን ጉዲፈቻ የሚሰጡት ከዚህ የተሻለ ምርጫ እንደሌላቸው ስለሚሰማቸው ነው።

የሙሴን ምሳሌ ተመልከት። በዘጸአት ምዕራፍ 2 ላይ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የግብጹ ፈርዖን ወንድ የሆኑ እስራኤላውያን ሕፃናት በሙሉ እንዲገደሉ በደነገገ ጊዜ ዮካቤድ ሙሴ የተባለውን ሕፃን ልጅዋን ለሦስት ወራት እንደሸሸገችው ይናገራል። በኋላ ላይ ግን ልጁን ደብቃ ማሳደግ የማይቻል ነገር ሆነባት። የወላድ አንጀቷ ደግሞ ልጅዋ ሲገደል መመልከት አልቻለም። በመሆኑም “ልትሸሽገው ባልቻለች ጊዜ፣ የደንገል ሣጥን ለእርሱ ወስዳ ዝፍትና ቅጥራን ለቀለቀችው፤ ሕፃኑንም አኖረችበት፣ በወንዝም ዳር ባለ በቄጠማ ውስጥ አስቀመጠችው።”​—⁠ዘጸአት 2:3

በዚህ መንገድ ልጅዋን ትታ መሄዱ በጣም እንደሚከብዳት የታወቀ ነው። ሆኖም ሌላ ምን ምርጫ ነበራት? ለልጅዋ ያላት ፍቅር ከሁሉ የተሻለ አማራጭ ነው ያለችውን ነገር እንድታደርግ አነሳስቷታል። ሴት ልጅዋ በአካባቢው ቆማ ወንድሟን ሰው መጥቶ እስኪወስደው ድረስ ትጠብቀው ነበር። ልጅቷ እንዲህ ያደረገችው ተጨንቃ የነበረችው እናቷ እንድትጠብቀው ስለነገረቻት ሳይሆን አይቀርም።

እርግጥ ነው፣ ልጆቻቸውን ጉዲፈቻ የሰጡ ሁሉም ወላጆች እንደዚህ ዓይነት አስጨናቂ ሁኔታ ገጥሟቸው ላይሆን ይችላል። ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ ይህን የሚያደርጉበት ምክንያት ተመሳሳይ ነው። ሮበርት እንዲህ ይላል:- “እናቴ እኔን የወለደችኝ ሳታገባ ነው። በቤተሰቡ ውስጥ ሌሎች ልጆችም ስለነበሩ እኔን ማሳደግ በጣም ይከብዳት ነበር። በመሆኑም ጉዲፈቻ ብትሰጠኝ ጥሩ ሕይወት እንደምኖር አስባ ሊሆን ይችላል።”

ወላጆች ልጆቻቸውን ለሌሎች ቤተሰቦች እንዲሰጡ የሚያደርጓቸው በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ አይካድም። ሆኖም ከላይ የተገለጹት ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት አንዲት እናት ልጅዋን ጉዲፈቻ የምትሰጠው ስለጠላችው ወይም ደግሞ አንድ ዓይነት ጉድለት ስላየችበት አይደለም። ብዙውን ጊዜ እናትየው ልጁን ሌላ ቤተሰብ ቢያሳድገው የተሻለ እንክብካቤ እንደሚያገኝ ከልብ ታምናለች።

ተወዳጅ ነህ

ጉዲፈቻ ስለተሰጠህበት ምክንያት ስታስብ ጉዳዩን በማስተዋል መመልከትህም ሊጠቅምህ ይችላል። አሁንም የሙሴን ምሳሌ እንመልከት። ብዙም ሳይቆይ ‘የፈርዖን ልጅ እንዳነሳችውና ልጅም ይሆናት ዘንድ እንዳሳደገችው’ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይናገራል። (ሥራ 7:21) የፈርዖን ልጅ ሞት ከተፈረደባቸው ዕብራውያን ልጆች መካከል መሆኑን እያወቀች ሕፃኑን ወስዳ እንድታሳድገው የገፋፋት ምን ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ “እነሆም ሕፃኑ ያለቅስ ነበር፤ አዘነችለትም” ይላል። (ዘጸአት 2:6) በእርግጥም፣ ሙሴ የማደጎ ልጅ ለመሆን መብቃቱ የተጠላ ወይም የማይፈለግ መሆኑን ሳይሆን መወደዱን የሚያሳይ ነው።

ጉዲፈቻ የተሰጡ ብዙ ልጆች ወላጆቻቸው፣ በአሁኑ ጊዜ በስፋት እንደሚታየው እንዲሁ ሜዳ ላይ እንዳልጣሏቸው ከዚህ ይልቅ ተገቢውን እንክብካቤ ማግኘታቸውን ለሚከታተል ድርጅት እንደሰጧቸው ከጊዜ በኋላ ይገነዘባሉ። እንዲሁም እነርሱን ለማሳደግ ፈቃደኛ የሆነ ሰው ሊገኝ የቻለው ለእነርሱ ፍቅር ስላለው ነው። የአንተም ሁኔታ ተመሳሳይ ይሆን? አሳዳጊ ወላጆችህ ባሳዩህ ፍቅር ላይ ትኩረት ማድረግህና ይህንንም ከፍ አድርገህ መመልከትህ በውስጥህ ያለውን ቅሬታ ለማስወገድ ይረዳሃል።

ካሳደጉህ ቤተሰቦች በተጨማሪ ሌሎችም እንደሚወዱህ ትመለከት ይሆናል። የክርስቲያን ጉባኤ አባል ከሆንህ አፍቃሪ የሆኑ በርካታ መንፈሳዊ እናቶች፣ አባቶች፣ እህቶችና ወንድሞች ማግኘት ትችላለህ። (ማርቆስ 10:29, 30) ክርስቲያን ሽማግሌዎች “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ፣ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፣ በበረሀም አገር እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ” ሊሆኑ ይችላሉ። (ኢሳይያስ 32:2) የጎለመሱ ክርስቲያኖችን እርዳታ ከመጠየቅና ውስጣዊ ስሜትህን ለእነርሱ ከማካፈል ወደኋላ አትበል። የሚያሳስብህንና የሚሰማህን ሁሉ አውጥተህ ንገራቸው።

ሮበርት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማዋል። “አሁንም ቢሆን በውስጤ ባዶነት ይሰማኛል። ይሁን እንጂ ከመንፈሳዊ ቤተሰቤ የማገኘው ፍቅር ይህንን የባዶነት ስሜት እንድረሳው ረድቶኛል” በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል።

ሊሳካልህ ይችላል

እንግዲያው የተሳሳተና አሉታዊ አመለካከትን ለማስወገድ ጣር። ይህም የማደጎ ልጅ ስለሆንኩ በሕይወቴ ስኬት ማግኘት አልችልም የሚለውን አመለካከት ማስወገድንም ይጨምራል። እንደዚህ ዓይነቱ አሉታዊ አስተሳሰብ እጅግ ተስፋ አስቆራጭ ሊሆን ይችላል! (ምሳሌ 24:10) ደግሞም በእውነታ ላይ የተመሠረተ አይደለም።

ሙሴ በነበረው አጋጣሚ በሚገባ መጠቀሙን አስታውስ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሙሴም የግብፆችን ጥበብ ሁሉ ተማረ፣ በቃሉና በሥራውም የበረታ ሆነ” ይላል። (ሥራ 7:22) ከሁሉ በላይ ደግሞ በሰማይ የሚኖረው አባቱ ይሖዋ እውን ሆኖ እንዲታየው የሚያደርግ መንፈሳዊ ትምህርት ቀስሞ ነበር። (ዕብራውያን 11:27) ሕይወቱ የተሳካ ነበርን?

ከጊዜ በኋላ ሙሴ በግምት ሦስት ሚልዮን ወይም ከዚያ በላይ ብዛት ያለው የአንድ ኃያል ብሔር መሪ ሆኗል። ነቢይ፣ ዳኛ፣ የጦር መሪ፣ ታሪክ ጸሐፊና የቃል ኪዳኑ መካከለኛ ከመሆኑም በላይ የመጀመሪያዎቹ አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ጸሐፊ ለመሆን በቅቷል። ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፈ ኢዮብንና መዝሙር 90ን የጻፈው እርሱ እንደሆነ በስፋት ይታመናል። በእርግጥም ሙሴ ጥሩ ሕይወት አሳልፏል። ጉዲፈቻ የተሰጡ ብዙ ልጆችም እንዲሁ የተሳካላቸው ሲሆን አንተም ሊሳካልህ ይችላል።

ሮበርት ሁለት ልጆቹን ጥሩ አድርጎ ያሳደገ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግላል። የማደጎ ልጅ ሆኖ ያሳለፋቸውን ዓመታት መለስ ብሎ በማስታወስ እንዲህ ይላል:- “ላስተካክለው በማልችለው ነገር ላይ ከመብሰልሰል ይልቅ ላገኘኋቸው በረከቶች አመስጋኝ መሆን እንዳለብኝ ተምሬአለሁ።”

በአሁኑ ጊዜ እያሳደጉህ ያሉት ዘመዶችህ ከሆኑ አሊያም ደግሞ የማደጎ ልጅ ከሆንህ አልፎ አልፎ አሉታዊ አስተሳሰብ ይረብሽህ ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱን አስተሳሰብ ገንቢ በሆነ ነገር ለመተካት ጥረት አድርግ። ፊልጵስዩስ 4:8, 9 አምላክ የሚደሰትባቸውን ነገሮች ‘የምታስብ’ ከሆነ ‘የሰላምም አምላክ ከአንተ ጋር እንደሚሆን’ ተስፋ ይሰጣል። ይሁን እንጂ ከአሳዳጊ ቤተሰቦችህ ጋር ስትኖር ጥሩ ሕይወት ለመምራት የትኞቹን ተግባራዊ እርምጃዎች መውሰድ ትችላለህ? በቀጣዩ እትም ላይ የሚወጣው ርዕስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የማደጎ ልጅ መሆንህ አንድ ሰው ስለወደደህ ቤተሰቡ አድርጎ እንደተቀበለህና እንደሚያስብልህ የሚያሳይ ማስረጃ ነው