በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፍቅረ ንዋይ ምንድን ነው?

ፍቅረ ንዋይ ምንድን ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ፍቅረ ንዋይ ምንድን ነው?

ሰው በተፈጥሮው መንፈሳዊ ዝንባሌና አምላክን የማምለክ ፍላጎት አለው። ሆኖም ከቁስ አካል የተፈጠረ እንደመሆኑ መጠን ቁሳዊ ፍላጎቶችም ያሉት ሲሆን እነዚህ ፍላጎቶች ሲሟሉለት የመደሰት ባሕርይ አለው። አንዳንድ ክርስቲያኖች ከፍተኛ መጠን ያለው ቁሳዊ ሃብት አላቸው። ይህ በራሱ ፍቅረ ንዋይ እንደተጠናወታቸውና መንፈሳዊነት እንደሚጎድላቸው የሚያሳይ ማስረጃ ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላልን? በአንጻሩ ድሃ የሆኑ ሰዎች ፍቅረ ንዋይ እንደማያጠቃቸውና ይበልጥ መንፈሳዊ ዝንባሌ እንዳላቸው ተደርጎ ሊታሰብ ይገባልን?

ፍቅረ ንዋይ እንዲያው ከፍተኛ ሃብትና ንብረት ከማካበት የበለጠ ነገርን ይጨምራል ቢባል እንደምትስማማ አያጠራጥርም። ፍቅረ ንዋይ ሲባል ምን ማለት እንደሆነና በመንፈሳዊነታችን ላይ ምን አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል የሚያሳዩ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።

ሃብትና ክብር ነበራቸው

በጥንት ዘመን ከኖሩት ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች መካከል አንዳንዶቹ ሃብትና ክብር ነበራቸው። ለምሳሌ ያህል፣ አብርሃም ‘በከብት፣ በብርና በወርቅ እጅግ የበለጠገ’ ነበር። (ዘፍጥረት 13:2) ኢዮብ ብዙ ከብቶችና አገልጋዮች ስለነበሩት “በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ታላቅ ነበረ” ተብሎለታል። (ኢዮብ 1:3) ዳዊትንና ሰሎሞንን የመሳሰሉት የእስራኤል ነገሥታት ከፍተኛ መጠን ያለው ሃብት ነበራቸው።​—⁠1 ዜና መዋዕል 29:1-5፤ 2 ዜና መዋዕል 1:11, 12፤ መክብብ 2:4-9

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም ሃብታም ሰዎች ነበሩ። (1 ጢሞቴዎስ 6:17) ልድያ “ከትያጥሮን ከተማም የመጣች ቀይ ሐር [“ሐምራዊ፣” NW ] ሻጭ እግዚአብሔርን የምታመልክ” ክርስቲያን እንደነበረች ተገልጿል። (ሥራ 16:14) ሐምራዊ ቀለምና በሐምራዊ ቀለም የተነከሩ ልብሶች ዋጋቸው ውድ በመሆኑ መግዛት የሚችሉት ከፍተኛ ሥልጣን ወይም ሃብት ያላቸው ሰዎች ብቻ ነበሩ። በመሆኑም ልድያ ራሷ መጠነኛ ሃብት ሳይኖራት አይቀርም።

በተቃራኒው በጥንት ዘመን የኖሩ አንዳንድ ታማኝ የይሖዋ አምላኪዎች በጣም ድሃ ነበሩ። አንዳንድ ቤተሰቦች በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ አደጋዎች እንዲሁም በሞት ምክንያት ለድህነት ተዳርገዋል። (መክብብ 9:11, 12) ሌሎች ከፍተኛ ሃብት ወይም ንብረት ኖሯቸው ተንደላቅቀው ሲኖሩ መመልከት ችግረኛ ለሆኑ ቤተሰቦች ምንኛ ፈታኝ ሆኖባቸው ይሆን! ያም ሆኖ ግን ሃብታም የሆኑ ሰዎችን ፍቅረ ንዋይ አሳዳጆች፣ ሃብት የሌላቸውን ደግሞ አምላክን በተሻለ ሁኔታ የሚያገለግሉ እንደሆኑ አድርገው ካሰቡ በጣም ተሳስተዋል። ለምን? የፍቅረ ንዋይ ምንጭ ምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

የገንዘብ ፍቅር

አንድ መዝገበ ቃላት ፍቅረ ንዋይ ተብሎ ለተተረጎመው “ማቴሪያሊዝም” ለሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “በእውቀት ወይም በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ ቁሳዊ ነገሮችን ማሳደድ” የሚል ፍቺ ሰጥቶታል። ስለሆነም ፍቅረ ንዋይ በምኞቶቻችንና በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ በምንሰጣቸው ነገሮች ይንጸባረቃል። ከሚከተሉት ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ይህንን በግልጽ መመልከት ይቻላል።

ይሖዋ የነቢዩ ኤርምያስ ጸሐፊ ሆኖ ያገለግል ለነበረው ለባሮክ ጠንከር ያለ ምክር ሰጥቶት ነበር። ባሮክ ኢየሩሳሌም ከነበረችበት ሁኔታና በሕዝቡ ዘንድ እምብዛም ከማይወደደው ከኤርምያስ ጋር ከነበረው ቅርርብ አንጻር ድሃ የነበረ ይመስላል። ያም ሆኖ ይሖዋ “ለራስህ ታላቅን ነገር ትፈልጋለህን? . . . አትፈልገው” ብሎታል። ይሖዋ ምክር የሰጠው ባሮክ ሌሎች ባላቸው ሃብት ወይም በቁሳዊ ነገሮች ላይ የተመሠረተ ደህንነት በመቅናት ወደ ፍቅረ ንዋይ አዘንብሎ ስለነበረ ሊሆን ይችላል። በኢየሩሳሌም ላይ ከሚመጣው ጥፋት እርሱን ቢያድነውም ሃብቱ ግን ከጥፋት እንደማይተርፍ ይሖዋ አስጠንቅቆታል።​—⁠ኤርምያስ 45:4, 5

ኢየሱስ ቁሳዊ ሃብት የማካበት ከፍተኛ ፍላጎት አድሮበት ስለነበረ አንድ ሰው የሚገልጽ ምሳሌ ተናግሯል። ይህ ሰው ባለው ነገር አምላክን ከማገልገል ይልቅ ትኩረቱን ሃብት በማደለብ ላይ አድርጎ ነበር። “ጐተራዬን አፍርሼ ሌላ የሚበልጥ እሠራለሁ፣ . . . ነፍሴንም:- አንቺ ነፍሴ፣ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ፣ ብዪ፣ ጠጪ፣ ደስ ይበልሽ እላታለሁ አለ።” ኢየሱስ ቀጥሎ እንዲህ አለ:- “እግዚአብሔር ግን:- አንተ ሰነፍ፣ በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዱአት ይፈልጓታል፤ ይህስ የሰበሰብኸው ለማን ይሆናል? አለው። ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፣ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው።”​—⁠ሉቃስ 12:16-21

ከእነዚህ ሁለት ታሪኮች የምንማረው ትምህርት ምንድን ነው? አንድ ሰው ፍቅረ ንዋይ በማሳደድ የተጠመደ ነው የሚያሰኘው ያለው ሃብት ብዛት ሳይሆን ለቁሳዊ ነገሮች ቅድሚያ መስጠቱ እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዱናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፣ አንዳንዶችም ይህን ሲመኙ፣ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ።” (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ችግሩ ያለው ሃብታም ለመሆን ቆርጦ በመነሳትና ቁሳዊ ነገሮችን ከልክ በላይ በመውደድ ላይ ነው።

ራስን መመርመር ያስፈልጋል

በየትኛውም የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ክርስቲያኖች በፍቅረ ንዋይ ወጥመድ እንዳይያዙ ይጠነቀቃሉ። ሃብት የማታለል ኃይል ያለው ከመሆኑም ባሻገር መንፈሳዊነትን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል። (ማቴዎስ 13:​22) ለመንፈሳዊ ነገሮች ትኩረት እንሰጥ የነበርን ሰዎች እምብዛም ሳይታወቀን ቁሳዊ ነገሮችን ወደ ማሳደድ ልናዘነብልና አሳዛኝ ችግር ውስጥ ልንወድቅ እንችላለን።​—⁠ምሳሌ 28:​20፤ መክብብ 5:​10

በመሆኑም ክርስቲያኖች በሕይወታቸው ውስጥ የሚያስቀድሙትና ትልቅ ግምት የሚሰጡት ለምን ነገር እንደሆነ ራሳቸውን መመርመራቸው የተገባ ነው። መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ሃብታምም ሆኑ ድሃ ሐዋርያው ጳውሎስ “ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለ ጠግነት” ተስፋ እንዳናደርግ የሰጠንን ማሳሰቢያ ለመከተል ጥረት ያደርጋሉ።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 6:17-19