በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆችህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?

ልጆችህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?

ልጆችህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?

“ልጆች ሱስ የሚያስይዙ ነገሮችን እንዳይለምዱ በዋነኝነት መከላከል ያለባቸው ወላጆች ናቸው። ለልጆቻቸው ምሳሌና አስተማሪ መሆን ይገባቸዋል።”​—⁠ዶና ሻላላ የዩናይትድ ስቴትስ የጤናና የሰብዓዊ አገልግሎቶች ጸሐፊ

ወላጅ ከሆንክ ከአደገኛ ዕፅ ሱሰኝነት ጋር በሚደረገው ውጊያ የመጀመሪያው ተፋላሚ አንተ ነህ። የሚያሳዝነው ግን ይህን የሚገነዘቡት ሁሉም ወላጆች አለመሆናቸው ነው። ኢረናው የተባለ አንድ ብራዚላዊ ወጣት “አባቴ ሁልጊዜ እንደተጣደፈ ነው። ለአጭር ጊዜ ካልሆነ በቀር አነጋግሮን አያውቅም። ስለ አደገኛ ዕፆች ምንም ዓይነት ምክር ተሰጥቶን አያውቅም” ብሏል።

ከዚህ በተቃራኒ ግን አሌክሳንድሮስ የተባለ ሌላ ብራዚላዊ ወጣት ያለውን ልብ በል:- “አደገኛ ዕፆችን የሚመለከት ፕሮግራም ቴሌቪዥን ላይ ከቀረበ አባቴ እኔንና ወንድሞቼን ይጠራንና እንድንመለከት ያደርገናል። ሱሰኞቹ ምን ያህል በሚያሳዝን ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ያሳየናል። አንዳንድ ጊዜ አጋጣሚውን በመጠቀም በትምህርት ቤታችን አደገኛ ዕፅ የሚወስዱ ልጆች አይተን እናውቅ እንደሆነ ይጠይቀናል። በዚህ መንገድ አደገኛ ዕፅ መውሰድ አደገኛ መሆኑን ያስጠነቅቀናል።”

ከልጆችህ ጋር ስለ አደገኛ ዕፆች ተወያይተህ ታውቃለህ? ይህን ለማድረግ አንተ ራስህ በቂ እውቀት ማግኘት ሊያስፈልግህ ይችላል። ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው አደገኛ ዕፆችን ቢወስዱ በመንፈሳዊነታቸው ላይ ከባድ ጉዳት ሊያስከትልባቸው እንደሚችል እንዲገነዘቡ ሊረዷቸው ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ከማንኛውም ዓይነት ቆሻሻ ማለትም አካልንም ሆነ መንፈስን ከሚያቆሽሽ ነገር እንድንርቅ ይመክረናል። (2 ቆሮንቶስ 7:​1) መጽሐፍ ቅዱስን ከልጆች ጋር በቋሚነት ማጥናት እነርሱን ለመጠበቅ ጥሩ መሣሪያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። *

“የምሥጢር ወዳጅ”

በተጨማሪም ለልጆችህ የምሥጢር ወዳጅ መሆንህ በጣም አስፈላጊ ነው። ይሖዋ ለምድራዊ ልጆቹ “የምሥጢር ወዳጅ” ነው። (ኤርምያስ 3:​4 NW ) አንተስ ለልጆችህ የምሥጢር ወዳጅ ነህ? ልጆችህ የሚናገሩትን ታዳምጣለህ? ልጅህ ሳይሸማቀቅና ሳይሰጋ ችግሩን ያዋይሃል? ከማመስገን ይልቅ መንቀፍ ይቀናሃል? በቂ ጊዜ ወስደህ ልጅህን በደንብ እወቅ። ጓደኞች አሉት? ካሉትስ እነማን ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ “ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 15:​33) ለልጆችህ ገደብ ለማውጣት ወይም ፍቅራዊ ተግሣጽና እርማት ለመስጠት አትፍራ። መጽሐፍ ቅዱስ “ልጅህን ቅጣ ዕረፍትንም ይሰጥሃል፣ ለነፍስህም ተድላን ይሰጣታል” ይላል።​—⁠ምሳሌ 29:​17

ከዚህም በላይ ልጅህ ሊያጋጥመው የሚችለውን አደገኛ ሁኔታ አቅልለህ አትመልከት። አንዳንድ ወላጆች እነርሱ ጨዋዎች ስለሆኑ ልጆቻቸው ምንም ቢሆን አደገኛ ዕፅ አይወስዱም ብለው በማሰብ ቸልተኞች ይሆናሉ። ይሁን እንጂ ዶክተር ዦዜ ሄንሪኬ ሲልቬራ “ጥሩ ገበያ እንደሚያስገኝላቸው ስለሚያውቁ የአደገኛ ዕፅ ነጋዴዎች ከትላልቅ ሰዎች ልጆች ጋር መወዳጀት ይፈልጋሉ” ብለዋል። አዎን፣ ጨዋና የተከበረ ልጅ የአደገኛ ዕፅ ሱሰኛ ከሆነ ሌሎች እርሱን መከተላቸው የማይቀር ነው።

ስለዚህ የተሳሳተ ግምት አይኑርህ። ልጅህ አደገኛ ዕፅ መውሰድ መጀመሩን የሚጠቁሙ ምልክቶችን ቶሎ ብለህ ለማወቅ ሞክር። ለምሳሌ ያህል ልጅህ በድንገት ከሰው የሚርቅ፣ የሚጨነቅ፣ ሰው የሚጠላ ወይም የማይተባበር ሆኗል? አለምንም በቂ ምክንያት ከቀድሞ ጓደኞቹ ወይም ከቤተሰቡ አባሎች ይርቃል? ከሆነ አሳሳቢ የሆነ ሁኔታ ሊደቀንብህ ይችላል።

እጅግ የሚያሳዝነው ግን ወላጆች የሚያስመሰግን ጥረት ቢያደርጉም በሚደርስባቸው ተጽእኖ ተሸንፈው አደገኛ ዕፅ የሚወስዱ ወጣቶች መኖራቸው ነው። የአንተ ልጅ እንዲህ ያለ ሁኔታ ቢያጋጥመው ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

አንድ ወጣት አደገኛ ዕፅ መውሰድ በሚጀምርበት ጊዜ

ኢረናው “ወንድሜ አደገኛ ዕፅ እንደሚወስድ ወላጆቼ ያወቁት ዕፅ መውሰድ ከጀመረ ከብዙ ወራት በኋላ ነበር” በማለት ይናገራል። “የእነርሱ ልጅ የአደገኛ ዕፅ ሱሰኛ ይሆናል ብለው አስበው ስለማያውቁ መጀመሪያ ላይ የሚያደርጉት ጠፍቷቸው ተንቀጠቀጡ። አባቴ ወንድሜን ካልገደልኩ ብሎ ተነሳ።”

አንድ ወላጅ ልጁ አደገኛ ዕፅ እንደሚወስድ ሲያውቅ ቢቆጣ፣ ቢበሳጭና ድካሙ ሁሉ ከንቱ እንደሆነበት ቢሰማው እንግዳ ነገር አይደለም። ይሁን እንጂ የዩናይትድ ስቴትስ ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው አንድ መረጃ እንደሚከተለው በማለት ይመክራል:- “ግራ አትጋባ! ራስህንም ጥፋተኛ አድርገህ አትቁጠር። በዚህ ወቅት ልታደርግ የሚገባው አስፈላጊ ነገር መረጋጋትና ምን እየተከናወነ እንዳለ መከታተል ነው። . . . የአደገኛ ዕፅ ሱሰኝነት ሊወገድ የሚችል ልማድና ሊድን የሚችል በሽታ ነው።”

አዎን፣ ሁኔታው እንዳይባባስ ደግና ቆራጥ ሁን። ከልክ በላይ መቆጣትህ ወይም መበሳጨትህ ልጅህ ማገገም እንዳይችል ሊያደርገው ይችላል። በተጨማሪም ልጅህ አድጎ ስለ ራሱ የሚያስብና ኃላፊነት የሚሰማው ሰው እንዲሆን መርዳት ትፈልጋለህ። ስለዚህ በቂ ጊዜ ወስደህ ከአደገኛ ዕፅ ሱስ መላቀቅ ስለሚያስገኛቸው ጥቅሞች በሐቀኝነት አወያየው። መንገዱን በሳተው በዚህ ወጣት ልብ ውስጥ ምን እንዳለ ለማወቅ ሞክርና የሚለውን ለማዳመጥ ፈቃደኛ ሁን።​—⁠ምሳሌ 20:​5 አ.መ.ት

ኢረናው በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “በኋላ ግን ወላጆቼ ዘዴያቸውን ቀየሩና ወንድሜን በጥሞና መምከር ጀመሩ። አንዳንድ ቦታዎች እንዳይሄድ ገደብ አደረጉበት። ከክፍል ጓደኞቹ ጋር እንዳይገናኝ ሲሉም ክፍሉን እንዲቀይር አደረጉ። አብረውት የሚውሉትን ልጆች መቆጣጠርና ለእርሱም ሆነ ለሌሎቹ የቤተሰብ አባሎች የበለጠ ትኩረት መስጠት ጀመሩ።”

አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው አደገኛ ዕፅ እንደሚወስዱ ባወቁ ጊዜ ምን ዓይነት እርምጃዎችን እንደወሰዱ እንመልከት።

የተሳካ ውጤት ያስገኙ የእርምት እርምጃዎች

“እንዲህ ያለ ክፉ ነገር ገጥሞን አያውቅም” ይላል በሳኦ ፓውሎ፣ ብራዚል የሚኖረው ማርሴሎ። “እኔና ባለቤቴ በሁለቱ ልጆቻችን ጠባይ ላይ የተመለከትነው ምንም ነገር አልነበረም። ብዙ ጊዜ በደንብ እናውቃቸዋለን ብለን ከምናስባቸው ሰዎች ጋር ምግብ ቤቶች እየሄዱ ይመገቡ ነበር። ሁለቱ ልጆቻችን ማሪዋና እንደሚያጨሱ አንድ ወዳጃችን በነገረን ጊዜ ትልቅ ዱብ ዕዳ ሆነብን። ስንጠይቃቸውም አለምንም ማንገራገር አመኑ።”

ማርሴሎ ከገቡበት ችግር ውስጥ ልጆቹን ለማውጣት ምን አደረገ? “እኔና ባለቤቴ የተሰማንን ሐዘን  መደ​በቅ አልቻልንም” ይላል። “ይሁን እንጂ የዕፅ ሱሰኛ መሆናቸውን ብናወግዝም ዋጋ የሌላቸው ከንቱ ልጆች እንደሆኑ አድርገን አልተናገርንም። ከዚያ ቀን በኋላ ግባችን ልጆቻችንን ከዕፅ ሱሰኝነት ማውጣት እንደሆነ ተስማማን። ልናደርግ ስላሰብነው ነገር በግልጽ ተነጋገርን፤ ልጆቻችንም ያስቀመጥንላቸውን ቅድመ ሁኔታ ተቀበሉ። ትምህርታቸውንም ሆነ በትርፍ ጊዜያቸው የሚሠሩትን ሥራ ይቀጥላሉ። ከእንግዲህ ወዲያ የትም ቦታ ብቻቸውን አይሄዱም። ልዩ በሆኑ አጋጣሚዎች ብቻ ሳይሆን በየቀኑ እንደምንወዳቸው አሳየናቸው። የሕንፃ ሠራተኛ በመሆኔ በተቻለኝ መጠን ብዙ ጊዜ ወደ ሥራ ቦታ ይዣቸው መሄድ ጀመርኩ። ከቀድሞው ይበልጥ አብረን መጫወት፣ ስለ ወደፊቱ ሕይወታቸውና ሊኖራቸው ስለሚገባ ግብ ረዘም ላለ ጊዜ መነጋገር ጀመርን።” ማርሴሎ እና ባለቤቱ በዚህ መንገድ ልጆቻቸው ከዕፅ ሱሰኝነት እንዲላቀቁ መርዳት ችለዋል።

አሁንም የአንድ ሌላ ብራዚላዊ አባት ተሞክሮ እንመልከት። ልጁ ሮቤርቶ እንዲህ በማለት ይተርካል:- “አባቴ ወንድሜ አደገኛ ዕፅ እንደሚወስድ ባወቀ ጊዜ ኃይለ ቃል ከመናገር ወይም ከመቅጣት ይልቅ በወዳጅነት ቀረበውና የወንድሜን አመኔታ አተረፈ። ከወንድሜ ጓደኞችና ከሚያ​ዘወትሩባቸው ቦታዎች ጋር ተዋወቀና አደገኛ ዕፆቹም ሆኑ እንደነዚህ ያሉ ጓደኞች እንደማያስፈልጉት ጥሩ አድርጎ አስረዳው። ከእንግዲህ በኋላ አባቴ እንቅልፍ አጥቶ በየምሽቱ እሱን ሲፈልግ እንደማያድር ነገረው።” የእንጀራ እናቱም ይህን ችግር ላይ የወደቀ ወጣት ለመርዳት ለባለቤቷ ሙሉ ድጋፍ ሰጠች። ሁለቱም ምንም ጊዜ ማባከን እንደሌለባቸው ተስማሙና በቤታቸው እርሱን ለመርዳት ወሰኑ።​—⁠“እርዳታ ማግኘት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

ተስፋ አትቁረጥ!

በዚህ ‘አስጨናቂ ዘመን’ ልጆች ማሳደግ አድካሚና አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1) ሆኖም አንተም ስሜታዊና መንፈሳዊ እርዳታ ማግኘት እንዳለብህ ማወቅ ይኖርብሃል። (ማቴዎስ 5:​3) “በመከራ ቀን ብትላላ ጉልበትህ ጥቂት ነው” የሚሉት የምሳሌ 24:​10 ቃላት እዚህ ላይ ይሠራሉ። ከእውነተኛ ክርስቲያኖች ጋር መቀራረብ ብርታትና ኃይል ያስገኛል። የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ብዙ ድጋፍና ማበረታቻ ማግኘት ትችላላህ።​—⁠ዕብራውያን 10:​24, 25

ቤተሰብህ በአምላክ ላይ እምነት እንዲኖረው የማስተማርን ያህል ከዕፅ ሱሰኝነት የሚጠብቅ ነገር የለም። እርግጥ ነው፣ አምላክ ወጣቶች አንድ ዓይነት የአኗኗር ጎዳና እንዲከተሉ አያስገድድም። ቢሆንም አስተማማኝ የሆነ ምክር ይሰጣል። በመዝሙር 32:​8 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው አምላክ “አስተምርሃለሁ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ ዓይኖቼን በአንተ ላይ አጠናለሁ” ይላል። አምላክ አፍቃሪ የሰማይ አባት እንደመሆኑ ወጣቶች የስሜት፣ የአካልና የመንፈስ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ይፈልጋል። (ምሳሌ 2:​10-12) እንዲሁም አምላክ ልጆቻቸውን ‘በጌታ ምክርና ተግሣጽ ለማሳደግ’ የቆረጡ ወላጆችን እንደሚረዳና እንደሚደግፍ እርግጠኛ ሁን።​—⁠ኤፌሶን 6:​4

እንደዚያም ሆኖ በዚህ ዘመን ልጆችን ማሳደግ በጣም ከባድ የሚሆንባቸው ጊዜያት ይኖራሉ። ታዲያ መፍትሔ ማግኘት ይቻል ይሆን?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 ወላጆች አደገኛ ዕፆች ስለሚያስከትሉት ጉዳትና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ከልጆቻቸው ጋር ለመወያየት የሚረዱ መረጃዎችን የያዙ ጽሑፎችን የይሖዋ ምሥክሮች አዘጋጅተዋል። ለምሳሌ ያህል ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 33 እና 34ን ተመልከት።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“የአደገኛ ዕፅ ሱሰኝነት ሊወገድ የሚችል ልማድና ሊድን የሚችል በሽታ ነው።”—የዩናይትድ ስቴትስ ትምህርት ሚኒስቴር

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

እርዳታ ማግኘት

አንዳንድ ወላጆች ልጃቸው ከዕፅ ሱሰኝነት እንዲላቀቅ ለማድረግ የሕክምና ክትትል ቢደረግለት እንደሚበጅ ሊወስኑ ይችላሉ። ወላጆች የሚመርጡት የሕክምና ዓይነት በግል የሚወሰን ጉዳይ ነው። ይሁን እንጂ በሱስ ማላቀቂያ ክሊኒኮች የሚሰጠው እንክብካቤ ስለሚለያይ ወላጆች ውሳኔ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ዝርዝር ሁኔታዎችን ቢያጣሩ ጥሩ ይሆናል። በብራዚል የሳኦ ፓውሎ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት የሥነ ልቦና ሐኪም አርተር ጌራ ደ አንድራተ እንዳሉት ከሆነ በክሊኒኮች ክትትል ከተደረገላቸው የዕፅ ሱሰኞች መካከል ከሱሳቸው የተላቀቁት 30 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። ስለዚህ ወላጆች ለልጆቻቸው የሕክምና ባለሞያዎች ክትትል በሚያደርጉበት ጊዜም ጭምር የልጆቻቸውን ማገገም መከታተል ይኖርባቸዋል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ከዕፅ ሱሰኝነት በመላቀቅ ላይ ለሚገኙ ሰዎች የሚሆን እርዳታ

ከዕፅ ሱሰኝነት ለመላቀቅ በመታገል ላይ የምትገኝ ወጣት ነህ? ከሆንክ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ያነበብከውን ሥራ ላይ ማዋል በምታደርገው ጥረት በእጅጉ እንደሚረዳህ ትገነዘባለህ። በተለይ የመዝሙር መጽሐፍ አንተም በውስጥህ ሊሰማህ የሚችለውን የስሜት ቁስለትና ሥቃይ ስለሚገልጽ ብታነበው በጣም ይረዳሃል። በተጨማሪም ውስጣዊ ስሜትህን በመግለጽ ወደ አምላክ ከልብ መጸለይ ሊረዳህ ይችላል። (ፊልጵስዩስ 4:​6, 7) አምላክ በእርግጥ እንደሚያስብልህና እንዲሳካልህ እንደሚፈልግ ማስተዋል ትጀምራለህ። ይሁን እንጂ አምላክ ማንም ሰው ከፈቃዱ ውጭ ምንም ነገር እንዲያደርግ ስለማያስገድድ ከዕፅ ሱሰኝነት ነጻ ለመውጣት ከልብ መፈለግ ይኖርብሃል። ብዙ ጊዜ የአምላክን ድጋፍ ያገኝ የነበረው መዝሙራዊው ዳዊት “ቆይቼ እግዚአብሔርን ደጅ ጠናሁት፣ እርሱም ዘንበል አለልኝ ጩኸቴንም ሰማኝ። ከጥፋት ጉድጓድ ከረግረግም ጭቃ አወጣኝ፣ እግሮቼንም በድንጋይ ላይ አቆማቸው፣ አረማመዴንም አጸና” ብሏል። (መዝሙር 40:​1, 2) ዛሬም ቢሆን ራሳቸውን ለማጥራትና አምላክን ለማገልገል የሚፈልጉ ሁሉ በተመሳሳይ መንገድ እርዳታና ድጋፍ ያገኛሉ።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“አባቴ ስለ አደገኛነቱ ያስጠነቅቀን ነበር”​—⁠አሌክሳንድሮስ

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አደገኛ ዕፅ መውሰድ ስለሚያስከትለው አካላዊና መንፈሳዊ ጉዳት ጊዜ ወስዳችሁ ለልጆቻችሁ ንገሯቸው

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የልጃችሁ ጓደኞች እነማን እንደሆኑ በንቃት ተከታተሉ

[በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጉዳዩን ረጋ ባለ መንፈስ መያዝ ሁኔታው እንዳይባባስ ይረዳል