በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሒሳብ ለሁሉም ሰው የሚያገለግል መሣሪያ ነው

ሒሳብ ለሁሉም ሰው የሚያገለግል መሣሪያ ነው

ሒሳብ ለሁሉም ሰው የሚያገለግል መሣሪያ ነው

የሒሳብ አገልግሎት ለሳይንስ ሊቃውንት ብቻ የተወሰነ አይደለም። ለሁላችንም የሚጠቅም መሣሪያ ነው። ዕቃ በምትሸምትበት፣ ቤት በምታስጌጥበት ወይም የአየር ሁኔታ ትንበያዎችን በምታዳምጥበት ጊዜ ሁሉ በሒሳብ ሕግጋት ትጠቀማለህ።

ብዙ ሰዎች ሒሳብ አሰልቺ እንደሆነና ከዕለት ተዕለት ኑሮ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው ይሰማቸዋል። አንተስ እንዲህ ይሰማሃል? ሒሳብ ምን ያህል ጠቃሚ ወይም ለመረዳት የማያስቸግር ከዚያም አልፎ አስደሳች እንደሆነ እንመልከት።

ገበያ ስትወጣ

ገበያ ወጥተህ ዓይንህን ወዲያ ወዲህ ስታማትር ታላቅ ቅናሽ የሚል ጽሑፍ የሰፈረበት ሱቅ ትመለከታለህ። ሠላሳ አምስት ብር ይሸጥ የነበረ ዕቃ 25 በመቶ ቅናሽ እንደተደረገበት ትመለከታለህ። ይህማ ቀላል ቅናሽ አይደለም ብለህ ታስብ ይሆናል። ግን አዲሱ ዋጋ ስንት ይሆናል? አራቱን መደብ ጠንቅቀህ ካላወቅህ ትቸገራለህ። *

በመጀመሪያ ቅናሽ የተደረገበትን መቶኛ ከመቶ ስትቀንስ 75 መቶኛ ታገኛለህ። (100 መቶኛ - 25 መቶኛ = 75 መቶኛ) ከዚያም የቀድሞውን ዋጋ በ75 መቶኛ (0.75) ታባዛለህ። አዲሱ ዋጋ 26.25 (35 × 0.75 = 26.25) ይሆናል ማለት ነው። አሁን ቅናሽ የተደረገበት ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ አውቀሃል። ጥሩ ዋጋ መሆንና አለመሆኑን መወሰን ትችላለህ።

የሒሳብ መሥሪያ ማሽን ባይኖርህስ? በቃልህ ልታሰላ ትችል ይሆናል። ለምሳሌ ያህል የቀድሞ ዋጋው 45 ብር የነበረ ዕቃ 15 በመቶ ቅናሽ እንደተደረገበት ተጽፎ ይሆናል። ቀጥሎ የሰፈረውን ዘዴ በመጠቀም የመቶኛ ስሌቶችን በቃልህ ማስላት ትችላለህ። አሥር መቶኛን እንደመነሻ አድርገህ ተጠቀም። የአንድን ቁጥር 10 መቶኛ ለማወቅ ቁጥሩን ለ10 ታካፍላለህ። ይህን በቃል ለማስላት አስቸጋሪ አይሆንብህም። ከዚያም 15 የ10 እና የ5 ድምር ውጤት ስለሆነና 5 ደግሞ የ10 ግማሽ መሆኑን ስለምታውቅ ቅናሽ የተደረገበትን ዋጋ በመደመርና በመቀነስ በቀላሉ ማወቅ ትችላለህ። እስቲ እንሞክር።

የአርባ አምስት 10 መቶኛ 4.50 ሲሆን የአርባ አምስት 5 መቶኛ ደግሞ የዚህ ማለትም የ4.50 ግማሽ ስለሆነ 2.25 ይሆናል። ስለዚህ 15 መቶኛ የሁለቱ ማለትም የ4.50 እና የ2.25 ድምር ማለትም 6.75 ይሆናል። (4.50 + 2.25 = 6.75) በመጨረሻም 6.75ን ከ45 ስንቀንስ የተደረገበትን የዋጋ ቅናሽ ማለትም 38.25ን (45 - 6.75 = 38.25) እናገኛለን። በነገራችን ላይ አንድ ዕቃ ስትገዛ የሚያስጨምርህን የሽያጭ ታክስ መጠን ወይም ምግብ ቤት በሚያስከፍልህ ዋጋ ላይ ምን ያህል ጉርሻ እንደምትሰጥ ለማስላት በተመሳሳይ ዘዴ መጠቀም ትችላለህ። እርግጥ በእነዚህ ጊዜያት በመጀመሪያው ዋጋ ላይ ትደምራለህ እንጂ አትቀንስም።

በቃል በምታሰላበት ጊዜ ከተሳሳተ ድምዳሜ ላይ እንዳትደርስ መጠንቀቅ ይኖርብሃል። በመጀመሪያ 40 በመቶ ቅናሽ ከተደረገበት በኋላ ሌላ 40 በመቶ ዳግመኛ ቅናሽ የተደረገበት ቀሚስ ወይም ሱሪ፣ የተደረገበት ጠቅላላ ቅናሽ 64 በመቶ እንጂ 80 በመቶ አይደለም። ሁለተኛው ቅናሽ የተደረገው በመጀመሪያው ዋጋ ላይ ሳይሆን ቅናሽ በተደረገበት ዋጋ ላይ ነው። ቀላል ቅናሽ ባይሆንም ትክክለኛውን ቅናሽ ማወቁ አይከፋም።

ይሁን እንጂ በአራት መደብ ስሌት ብቻ ሊደረስባቸው የማይችሉ ጥያቄዎች ያጋጥማሉ። ለዚህ የሚያገለግሉን ሌሎች የሒሳብ ዘርፎች አሉን።

የቤት እድሳት

የቤትህን የወለል ንጣፍ መለወጥ አስፈልጎሃል እንበል። ሆኖም ይህን ለማድረግ ብዙም ገንዘብ አይኖርህ ይሆናል። ወደ ሱቅ ከመሄድህ በፊት ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያስፈልግህ ማስላት ይኖርብሃል። ትልቁ ጥያቄ ምን ያህል የወለል ንጣፍ ያስፈልግሃል የሚለው ነው። መሠረታዊ የሆነ የጂኦሜትሪ እውቀት ለዚህ በጣም ይረዳሃል።

አብዛኛውን ጊዜ የወለል ንጣፎች የሚሸጡት ሊሸፍኑ በሚችሉት ካሬ ሜትር ልክ ነው። ለምሳሌ አንድ ካሬ ሜትር ማለት አንድ ሜትር ወርድና አንድ ሜትር ቁመት ያለው ቦታ ነው። ምን ያህል ንጣፍ እንደሚያስፈልግህ ከመወሰንህ በፊት የእያንዳንዱን ክፍልና የመተላለፊያ ወለል ስፋት ማስላት ይኖርብሃል። የአብዛኞቹ ቤቶች ክፍሎች የአራት ማዕዘን ቅርፅ ያላቸው ናቸው። ስለዚህ በሚከተለው ቀመር መሠረት የየክፍሎቹን ስፋት ማስላት ትችላለህ:- ስፋት = ቁመት × ወርድ። በዚህ መንገድ አራት ማዕዘን ቅርፅ ያለውን የአንድ ቦታ ስፋት ማስላት ይቻላል።

ይህን የሒሳብ ስሌት እንዴት መጠቀም እንደሚቻል በምሳሌ ለማስረዳት ከወጥ ቤትህና ከመታጠቢያ ቤትህ ወለል በስተቀር የሁሉንም ክፍሎች የወለል ንጣፍ ለመለወጥ ፈልገሃል እንበል። የሁሉንም ክፍሎች መጠን ትለካና በገጽ 23 ላይ የሚታየውን የመሰለ የወለል ንድፍ ታወጣለህ። በንድፉ ውስጥ የሚታዩት አራት ማዕዘኖች የየክፍሉን መጠንና ቦታ የሚያመለክቱ ናቸው። ከላይ የሠፈረውን ቀመር በመጠቀም ምን ያህል ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ንጣፍ እንደሚያስፈልግህ ለማስላት ሞክር። የእያንዳንዱን ክፍል ስፋት ካሰላህ በኋላ የሁሉንም ውጤት መደመር ትችላለህ። አለበለዚያም የጠቅላላውን ቤት ስፋት ካሰላህ በኋላ የወጥ ቤቱንና የመታጠቢያ ቤቱን ስፋት ብትቀንስ ጥቂት ድካም ይቀንስልህ ይሆናል። *

“ጂኦሜትሪ” የሚለው ቃል ከግሪክኛ የተገኘ ሲሆን “መሬት መለካት” የሚል ትርጉም አለው። የቅርፆችና የመስመሮች ስፋት፣ ርዝመት፣ ይዘትና ሌሎች ጠባዮች የሚጠኑበት የሒሳብ ዘርፍ ነው። ማንኛውም ባለ ሁለትና ባለ ሦስት ጎን ቅርፅ የሚሰላበት የራሱ ቀመር አለው። ሳይንቲስቶች፣ መሐንዲሶችና ቤት አዳሾች በዕለት ተዕለት ተግባራቸው በእነዚህ ቀመሮች አማካኝነት የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ያሰላሉ። ይሁን እንጂ ሒሳብ በአራት መደብና በጂኦሜትሪ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ነገር አይደለም።

በየቀኑ በሒሳብ ተጠቀም

አልጀብራና ካልኩለስ የሚባሉም ሌሎች የሒሳብ ዘርፎች አሉ። ባለፉት መቶ ዓመታት ሒሳብ ማንኛውም ባሕል፣ ሃይማኖት ወይም ጾታ ያላቸው ሰዎች በጋራ ሊጠቀሙበት የሚችሉት ዓለም አቀፍ ቋንቋ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። በሳይንስ፣ በኢንዱስትሪ፣ በንግድና በሌሎች የዕለት ተዕለት ጉዳዮች በጣም ከባድ የሆኑ ጥያቄዎችን ለመፍታት የሚያስችል መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል። የአጽናፈ ዓለሙን ተፈጥሯዊ ምሥጢሮች ለመፍታትም ይሁን የቤተሰብህን ወጪና ገቢ ለማወራረድ የሒሳብን ቋንቋ ማወቅህ የግድ አስፈላጊ ነው።

ስለዚህ በትምህርት ቤት ሳለህ ሒሳብ የማትወድድ ከነበርክ ለምን አሁን በአዲስ መንፈስ አትመለከተውም? እንደ ማንኛውም ቋንቋ ሁሉ ሒሳብንም ብዙ በተጠቀምክበት መጠን ይበልጥ እያወቅኸው ትሄዳለህ። ስለዚህ በየቀኑ በሒሳብ ለመጠቀም ሞክር። የሒሳብ ጥያቄዎችንና እንቆቅልሾችን ለመፍታት ሞክር። ምናልባት ያጋጠመህ አንድ ጥሩ ተሞክሮ ስለ ሒሳብ ያለህን አመለካከት ያስለውጥህ ይሆናል። እነዚህን አስደናቂ ጽንሰ ሐሳቦች ከመጀመሪያ የፈጠረው ታላቁ የሒሣብ ሊቅ ይሖዋ አምላክ ስላለው ጥበብ የነበረህ አድናቆት እንዲጨምር ማድረጉ አይቀርም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 አራት መደብ ከሒሳብ ዘርፎች በሙሉ እጅግ ጥንታዊ የሆነ የሒሳብ ክፍል ነው። በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ያስቆጠረ ከመሆኑም በላይ የጥንት ባቢሎናውያን፣ ቻይናውያንና ግብጻውያን ይገለገሉበት ነበር። አራት መደብ በዙሪያችን ያለውን ገሐድ ዓለም ለመቁጠርና ለመለካት በየቀኑ የምንጠቀምበት መሠረታዊ መሣሪያ ነው።

^ አን.14 መልስ = 54 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ንጣፍ።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

3 ሜትር

3 ሜትር

ወጥ ቤት

ምግብ ቤት

መተላለፊያ

ሣሎን

መኝታ ቤት

መታጠቢያ ቤት

3 ሜትር

1.5 ሜትር

3 ሜትር

4.5 ሜትር

1.5 ሜትር

3 ሜትር

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሒሳብ የዕለት ተዕለት ተግባሮችን ለማከናወን ይረዳል