በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰፊ የሆነው የኦቾሎኒ ዓለም

ሰፊ የሆነው የኦቾሎኒ ዓለም

ሰፊ የሆነው የኦቾሎኒ ዓለም

ኦቾሎኒ ትወዳለህ? እንዳንተው ኦቾሎኒ የሚወድዱ ብዙ ሰዎች አሉ። ለውዝ ተብሎም የሚጠራውን ኦቾሎኒ ለምግብነት የሚጠቀሙ ቤተሰቦች በጣም ብዙ ናቸው። በሕዝብ ብዛታቸው ግንባር ቀደሙን ቦታ የያዙት ቻይናና ሕንድ ከዓለም የኦቾሎኒ ምርት 50 በመቶ የሚሆነውን ያመርታሉ።

ዩናይትድ ስቴትስ ከጠቅላላው የዓለም ምርት 10 በመቶ የሚሆነውን ማለትም በቢልዮን ኪሎ ግራም የሚመዘን ኦቾሎኒ ታመርታለች። አርጀንቲና፣ ብራዚል፣ ማላዊ፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ደቡብ አፍሪካና ሱዳንም ዋነኞቹ ኦቾሎኒ አብቃይ አገሮች ናቸው። ኦቾሎኒ ይህን ያህል ተወዳጅነት ሊያተርፍ የቻለው እንዴት ነው? ኦቾሎኒ አለመብላት ተመራጭ የሚሆንባቸው ጊዜያት ይኖራሉ?

ረዥም ታሪክ

ኦቾሎኒ ከደቡብ አሜሪካ እንደተገኘ ይታሰባል። የሰው ልጅ የኦቾሎኒን ጠቀሜታ እንደተገነዘበ ከሚያሳዩ ጥንታዊ ቅርሶች መካከል በፔሩ የተገኘ አንድ የአበባ ማስቀመጫ ይገኝበታል። አበባ ማስቀመጫው በኦቾሎኒ ቅርፅ የተሠራ ሲሆን የኦቾሎኒ ቅርፅ ባላቸው ሥዕሎችም ያጌጠ ነው። ኦቾሎኒን ለመጀመሪያ ጊዜ በደቡብ አሜሪካ ያገኙት ስፔናውያን አሳሾች ለጉዞአቸው በጣም የሚጠቅማቸው ጥሩ ምግብ እንደሆነ በመገንዘባቸው ወደ አውሮፓ አመጡት። አውሮፓውያኑ ኦቾሎኒን ለተጨማሪ አገልግሎት ከማዋላቸውም በተጨማሪ የቡና ምትክ አድርገው እስከመጠቀም ደርሰው ነበር።

በኋላም የፖርቹጋል ተወላጆች ኦቾሎኒን ለአፍሪካ አስተዋወቁ። በአፍሪካም ሌሎች ሰብሎችን ሊያበቅሉ በማይችሉ የተራቆቱ ማሳዎች ላይ ሊበቅል የሚችል ጥሩ ምግብ መሆኑ በፍጥነት ታወቀ። የኦቾሎኒ ተክሎች ለምነቱ የተሟጠጠ ማሳ ተጨማሪ ናይትሮጂን እንዲያገኝ በማድረግ ያዳብሩታል። ከጊዜ በኋላም ኦቾሎኒ የባሪያ ንግድ ይካሄድ በነበረበት ዘመን ከአፍሪካ ወደ ሰሜን አሜሪካ ተዛመተ።

በ1530ዎቹ ዓመታት ኦቾሎኒ ከፖርቹጋል ተወላጆች ጋር ወደ ሕንድና ወደ ማካው፣ ከስፔናውያን ጋር ደግሞ ወደ ፊሊፒንስ አቅንቷል። ከዚያም ከእነዚህ አገሮች የተነሱ ነጋዴዎች ለቻይና አስተዋወቁት። በቻይናም ረሐብን ለመቋቋም የሚያስችል ጥሩ ሰብል መሆኑ ታወቀ።

በ1700ዎቹ ዓመታት በኦቾሎኒ ላይ ጥናት ያደረጉ የእጽዋት ተመራማሪዎች የመሬት ውስጥ አተር የሚል ስያሜ የሰጡት ሲሆን ለአሳማዎች ጥሩ ምግብ እንደሚሆን ተገነዘቡ። በ1800ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ ኦቾሎኒ በዩናይትድ ስቴትስ ደቡብ ካሮላይና በሰፋፊ እርሻዎች መመረት ጀምሮ ነበር። ከ1861 ጀምሮ በነበረው የአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት ኦቾሎኒ በሁለቱም ተዋጊ ወገኖች ለተሰለፉ ወታደሮች በምግብነት አገልግሏል።

ይሁን እንጂ በወቅቱ ብዙ ሰዎች ኦቾሎኒ የድሆች ምግብ እንደሆነ ያስቡ ነበር። የዘመኑ የአሜሪካ ገበሬዎች ለሰዎች ቀለብ እንዲሆን በብዛት ያላመረቱት በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም። ከዚህም በላይ የማምረቻ መሣሪያዎች ከተፈለሰፉበት ከ1900ዎቹ ዓመታት በፊት ኦቾሎኒ ማምረት ብዙ ልፋት የሚጠይቅ ሥራ ነበር።

በ1903 ግን ጆርጅ ዋሽንግተን ካርቨር የተባለ አሜሪካዊ የእርሻ ኬሚስት የኦቾሎኒ ተክሎችን ለሌሎች አገልግሎቶች ማዋል ስለሚቻልባቸው መንገዶች ምርምር ማድረግ ጀምሮ ነበር። እርሱም መጠጦችን፣ የመዋቢያ ቅባቶችን፣ ቀለሞችን፣ መድኃኒቶችን፣ የልብስ ማጠቢያ ሳሙናዎችን፣ ፀረ ተባይ መድኃኒቶችን፣ የማተሚያ ቀለሞችን ጨምሮ ከ300 የሚበልጡ የተለያዩ ምርቶችን ፈልስፏል። በተጨማሪም ካርቨር የአካባቢው ገበሬዎች የአፈሩን ለምነት የሚያሟጥጠውን ጥጥ ብቻ ከመዝራት ልማዳቸው ተላቅቀው ከኦቾሎኒ ጋር እያፈራረቁ እንዲዘሩ አበረታቷል። በወቅቱ ቦል ዊቭል የተባለው ተባይ የጥጥ ሰብሎችን በማውደም ላይ ስለነበረ ብዙ ገበሬዎች የካርቨርን ምክር ለመከተል ተነሳሱ። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ኦቾሎኒ በጣም ውጤታማ ሆኖ በመገኘቱ በደቡባዊ የአሜሪካ ክፍል ዋነኛ የገበያ ምርት ሆነ። ዛሬ በዶታን አላባማ ለካርቨር ሐውልት ቆሞለታል። በአላባማ ኢንተርፕራይዝ ከተማ ደግሞ ገበሬዎች ኦቾሎኒ እንዲዘሩ ያነሳሳቸው ቦል ዊቭል የተባለው ተባይ በመሆኑ ለዚሁ ተባይ ሐውልት ቆሞለታል።

የኦቾሎኒ አበቃቀል

ኦቾሎኒ ከለውዝ ተክል የሚገኝ ዘር ነው። ተክሉ እያደገ ሲሄድ እርስ በርሳቸው የሚዳብሩ ቢጫ አበቦች ያወጣል።

በግንዱ ጫፍ ላይ የሚገኘው የዳበረው የተክሉ ሴቴ ክፍል አፈሩን በስቶ ይገባል። ዘሩን የያዘው ክፍል ወደጎን መሬት ለመሬት ያድግና ሙሉውን የኦቾሎኒ ቅርፅ እስኪይዝ ድረስ ይጎመራል። በአንድ ተክል ላይ እስከ 40 የሚደርሱ የኦቾሎኒ ፍሬዎች ያድጋሉ።

ኦቾሎኒ ሞቃታማና ፀሐያማ እንዲሁም መጠነኛ ዝናብ የሚዘንብበት አካባቢ ይስማማዋል። ተዘርቶ ለምርት እስኪደርስ ድረስ የሚወስደው ጊዜ እንደ አካባቢው የአየር ሁኔታና እንደ ኦቾሎኒው የዘር ዓይነት የሚለያይ ቢሆንም ከ120 እስከ 160 ቀናት ሊቆይ ይችላል። የኦቾሎኒን ምርት ለመሰብሰብ አምራቾቹ ሙሉውን ተክል ከነሐረጉ ይቆፍሩትና ይገለብጡታል። ይህም እንዲደርቅና ሳይበላሽ መቆየት እንዲችል ይረዳዋል። በዛሬው ጊዜ ብዙ ገበሬዎች ሐረጎቹን በአንድ ጊዜ ለመንቀል፣ አፈሩን ከሥሮቹ ለማራገፍና ለመገልበጥ በሚያስችል መሣሪያ ይጠቀማሉ።

ከኦቾሎኒ የሚገኙ በርካታ ጥቅሞች

ኦቾሎኒ የሚሰጠው ጥቅም በጣም ከፍተኛ ነው። ብዙ አሰር ያለው ከመሆኑም በላይ 13 ዓይነት ቪታሚኖችና 26 ዓይነት ማዕድናት ይገኙበታል። ብዙዎቹ በዘመናዊው ምግብ ውስጥ የማይገኙ ናቸው። “በኦቾሎኒ ውስጥ የሚገኙት ማዕድናት፣ ቪታሚኖችና ፕሮቲን እኩል መጠን ባለው የበሬ ጉበት ውስጥ ከሚገኘው ይበልጣል” ይላል ዘ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ። መወፈር የማትፈልጉ ከሆነ ግን መጠንቀቅ አለባችሁ። በኦቾሎኒ ውስጥ የሚገኘው ቅባት “በወፍራም ክሬም ውስጥ ከሚገኘው ይበልጣል። በካሎሪ ይዘቱ ደግሞ ከስኳር ይበልጣል።”

ኦቾሎኒ የብዙ ብሔራዊ ምግቦች ክፍል ሆኗል። ልዩ የሆነውንም ጣዕም መለየት አስቸጋሪ አይሆንም። የምግብ አሠራር ጸሐፊ የሆኑት አንያ ፎን ብረምሰን “የኦቾሎኒ ጣዕም በጣም የተለየና ለመለየት የማያስቸግር በመሆኑ በኦቾሎኒ የተቀመሙ ምግቦች በሙሉ ተመሳሳይ ጣዕም አላቸው” ብለዋል። ‘ስለሆነም በኢንዶኔዥያ የኦቾሎኒ መረቅ፣ በምዕራብ አፍሪካ ሾርባ፣ በፔሩ ወጥና በኦቾሎኒ ቅቤ መካከል የጣዕም ተመሳሳይነት ይገኛል።’

በተጨማሪም ኦቾሎኒ በበርካታ የዓለም ክፍሎች ለመክሰስነት የሚመረጥ ምግብ ሆኗል። ለምሳሌ ያህል በሕንድ አገር ኦቾሎኒ ከሌሎች ጥራጥሬዎች ጋር ተደባልቆ በየመንገዱ ይሸጣል። በአንዳንድ አገሮች ዳቦ ላይ ተቀብቶ የሚበላው የኦቾሎኒ ቅቤ “አረጋውያን ቢመገቡት ለጤናቸው ጥሩ እንደሚሆን ታስቦ በ1890 አካባቢ በሴይንት ሉዊ [ዩ ኤስ ኤ] በሚኖር አንድ ሐኪም እንደተፈለሰፈ ይነገራል” በማለት ዘ ግሬት አሜሪካን ፒነት የተባለው ጽሑፍ ዘግቧል።

ይሁን እንጂ ኦቾሎኒ በምግብነት ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ብዙ ሌሎች ጥቅሞችም አሉት። በመላው እስያ ከኦቾሎኒ ዘይት ይወጣል። የኦቾሎኒ ዘይት ከፍተኛ በሆነ ሙቀት ምግብ ለማብሰል የሚያገለግል ሲሆን የሚበስለው ምግብ ጣዕም ወደ ዘይቱ አይጋባም።

በብራዚል ዘይት ከወጣ በኋላ የሚቀረው የኦቾሎኒ ፋጉሎ ለከብቶች መኖነት ያገለግላል። በተጨማሪም ከኦቾሎኒ በርካታ የዕለት ተዕለት መገልገያዎች ይመረታሉ።​—⁠ከላይ ያለውን ተመልከት።

ማስጠንቀቂያ​—⁠የኦቾሎኒ አለርጂ!

ኦቾሎኒን አለማቀዝቀዣ ለረዥም ጊዜ ማቆየት ይቻላል። ይሁን እንጂ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው። ሻጋታ ያለበት ኦቾሎኒ አፍላቶክሲን የተባለ ካንሰር አምጪ መርዝ ይኖረዋል። በተጨማሪም አንዳንድ ሰዎች ለኦቾሎኒ አለርጂክ ናቸው። የኦቾሎኒ አለርጂ “ከንፍጥ መብዛትና ከሽፍታ ጀምሮ ለሞት ሊዳርግ እስከሚችል ራስ መሳት የሚደርስ የጤና ችግር ሊያስከትል ይችላል” ይላል ፕሪቬንሽን የተባለው መጽሔት። ለኦቾሎኒ አለርጂክ የሆኑ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣ ብዙ ጥናቶች ያመለክታሉ።

ሁለቱም ወላጆች አስም፣ የአፍንጫ መዘጋት ወይም ችፌ የሚያስቸግራቸው ከሆነ ልጃቸው ለኦቾሎኒ አለርጂክ የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ እንደሚሆን ፕሪቬንሽን ዘግቧል።

የአለርጂ ችግር ያለባቸው እናቶች ልጆችና በአንደኛ ዓመት ዕድሜያቸው ለወተት አለርጂክ የሆኑ ሕፃናትም ተመሳሳይ የሆነ አዝማሚያ ይኖራቸዋል። በዩናይትድ ስቴትስ በጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ማዕከል የሕፃናት ሕክምና ፕሮፌሰር የሆኑ ሂው ሳምፕሰን “እንደነዚህ ያሉት ቤተሰቦች ልጆቻቸው ቢያንስ ሦስት ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ከኦቾሎኒ እንዲርቁ ቢያደርጉ ጥሩ ይሆናል” ብለዋል።

የኦቾሎኒ ወዳጅ ሆንክም አልሆንክ ከላይ የተመለከትነው ኦቾሎኒ ስለሚሰጣቸው በርካታ ጥቅሞች የሚናገረው ዘገባ ሰፊ እውቅና ስላገኘው ስለዚህ ተክል የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖርህ ሳያደርግ አልቀረም።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የኦቾሎኒ ተረፈ ምርቶች በብዙዎቹ የዕለት ተዕለት መገልገያ ዕቃዎች ውስጥ ሳይኖሩ አይቀሩም

• ፋይዚት

• ማገዶ

• የከብት ጉዝጓዝ

• ወረቀት

• ማጠቢያ

• ቅባት

• ብረት መወልወያ

• በረኪና

• ቀለም

• የዲፈረንሽያል ቅባት

• የጺም መላጫ ሣሙና

• የፊት ቅባት

• ሣሙና

• ሊኖልየም

• ጎማ

• የመዋቢያ ቅባት

• ፈንጂ

• ሻምፑ

• መድኃኒት

[ምንጭ]

ምንጭ:- ዘ ግሬት አሜሪካን ፒነት

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ቅጠል

ሴቴ የኦቾሎኒ ክፍል (ፔግ)

የመሬት ወለል |

ሥሮች ኦቾሎኒ

[ምንጭ]

The Peanut Farmer magazine

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለጆርጅ ዋሽንግተን ካርቨር የተሠራ ሐውልት

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዩናይትድ ስቴትስ

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አፍሪካ

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እስያ

[ምንጭ]

FAO photo/R. Faidutti

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከኦቾሎኒ የተሠሩ የቆሎ ዓይነቶች

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኦቾሎኒ ቅቤ በአንዳንድ አገሮች ተወዳጅነት ያተረፈ የምግብ ዓይነት ነው