ታላቁ ጉማሬ እነሆ!
ታላቁ ጉማሬ እነሆ!
ኬንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደ ጻፈው
በተንጣለለው የማሳይ ማራ የአራዊት ጥብቅ ክልል ውስጥ የሚገኘው ሰፊ ኩሬ በምሽቷ ጀምበር አብረቅርቋል። ጀምበሯ ወደ አድማሱ እያዘቀዘቀች ስትሄድ የኩሬው ውኃ ቀይ ሆኖ ይታያል። ጥቂት ሜትሮች ራቅ ብሎ የሜዳ አህዮችና የቶራ ፈረሶች መንጋ ወደ ኩሬው ያዘግማል። እንስሳቱ በድንገት እንደ መበርገግ አሉና ቀጥ ብለው ቆሙ። ዓይኖቻቸው በኩሬው ጫፍ ላይ በሚገኝ ቋጥኝ በመሰለ ግዙፍ ነገር ላይ ተተክሏል። “ቋጥኙ” ውኃውን ካተራመሰ በኋላ ወደ ውስጥ ገባና ተሰወረ። የሜዳ አህዮቹና የቶራ ፈረሶቹ የበረገጉት ጉማሬ የሚባለውን በውኃ ውስጥ የሚኖር አስፈሪ እንስሳ ስለተመለከቱ ነው።
በምሥራቅ አፍሪካ በሚገኙ ኩሬዎች፣ ወንዞችና ሐይቆች የሚገኘውን ጉማሬ በትልቅነቱ የሚወዳደረው ቢገኝ ዝሆን ብቻ ነው። ጉማሬ ሙሉ እድገት ላይ ሲደርስ የ4 ሜትር ርዝመትና የ1.5 ሜትር ቁመት ይኖረዋል። ክብደቱ ደግሞ እስከ 40 ኩንታል ይደርሳል። በመጽሐፍ ቅዱሱ የኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ “ብሄሞት” ተብሎ የተጠራው እንስሳ ጉማሬ ሳይሆን እንደማይቀር ይታሰባል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ግዙፍ አውሬ ኢዮብ 40:15-18
በተመለከተ “አጥንቱ እንደ ናስ አገዳ፣ አካላቱ እንደ ብረት ዘንጎች” በማለት መናገሩ አያስደንቅም።—ይህ ባለ ወፍራም ቆዳ፣ ፀጉር የለሽና በርሜል መሰል ቅርፅ ያለው ከርፋፋ መሳይ እንስሳ ለቁንጅና ውድድር ቢቀርብ የመጨረሻ እንደሚሆን የታወቀ ነው። የጉማሬ እግሮች አጫጭሮች በመሆናቸው ያን የሚያክል ግዙፍ አካል መሸከም መቻላቸው ያስደንቃል። ይሁን እንጂ የእነዚህን ድንክዬ እግሮች አቅም እንደ ቀላል አትቁጠር። ጉማሬ በመሬት ላይ ሲሮጥ ከሰው ይፈጥናል። በውኃ ላይ ደግሞ በሞተር ወይም በሰው ጉልበት የሚነዳ አነስተኛ ጀልባ እንደሚቀድም ይታወቃል።
የውኃ ላይ ኑሮ
ጉማሬዎች በአንድ ወይፈን የሚመሩ ከ10 እስከ 15 የሚደርስ አባላት ባሉት መንጋ የሚኖሩ ማኅበራዊ እንስሳት ናቸው። እስከ 150 የሚደርሱ አባላት ያሏቸው መንጋዎች የታዩባቸው ጊዜያትም አሉ። ጉማሬዎች በየብስም ሆነ በውኃ ውስጥ መኖር የሚችሉ ሲሆኑ አብዛኛውን ጊዜ ማታ ማታ ከውኃ ወጣ ብለው በዳርቻው ላይ ያሉትን እጽዋት ይመገባሉ። ብዙውን ጊዜ ከሚኖሩበት ውኃ ርቀው መሄድ አይፈልጉም። ይሁን እንጂ በደረቅ ወራት አንዳንድ ጉማሬዎች እስከ 10 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ርቀት ተጉዘው ምግባቸውን እንደሚቃርሙ ታውቋል።
ጉማሬዎች ድንበራቸውን እንዴት እንደሚከልሉ በግልጽ አይታወቅም። በሚያስገርም ሁኔታ ፋንድያቸውን በጅራታቸው የሚበትኑት እንስት ጉማሬዎችን ለመማረክ ወይም ወደረኞቻቸውን ለማስፈራራት እንደሆነ የሚያስቡ አሉ። ጥቃት ሲሰነዘርባቸው እንደ ፈረስ ያሽካካሉ። በሚጣሉበት ጊዜ ደግሞ ያጓራሉ ወይም ይጮሃሉ። ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በሚጠልቁበት ጊዜ እንኳን የሚያስገመግም ድምፅ ይሰማል። አውራው ጉማሬ ሙህ -ሙህ የሚል ድምፅ በማሰማት ማንነቱን ያሳውቃል።
ጉማሬ ሙሉውን ቀን የሚያሳልፈው ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በውኃ ተሸፍኖ ነው። ግዙፍ የሆነው አካላቱ ይህን ለማድረግ ያመቸዋል። እንደ ሌሎቹ አራዊት ጥሩ ዋናተኛ ነው ባይባልም እስከ 15 ደቂቃ ውኃ ውስጥ ተቀብሮ ሊቆይ ይችላል። አፍንጫዎቹ፣ ዓይኖቹና ጆሮዎቹ በአንድ አካባቢ ያሉ በመሆናቸው የቀረውን የአካል ክፍል ውኃ ውስጥ ሊሰውር ይችላል። መዳራትንና ተራክቦን ጨምሮ አብዛኞቹ የጉማሬ እንቅስቃሴዎች የሚከናወኑት በውኃ ውስጥ ነው።
ከስምንት ወር የእርግዝና ጊዜ በኋላ ብዙ ጥልቀት በሌለው ውኃ ውስጥ አንድ ጥጃ ይወለዳል። ጥጃው መሬት ላይ ወይም ከቁርጭምጭሚት የማያልፍ ጥልቀት ባለው ውኃ ውስጥ ሆኖ ይጠባል። ጉማሬ በጣም ጠንካራ እንስሳ ይሁን እንጂ ልጅ የማሳደግ ኃላፊነቱን አቅልሎ አይመለከትም። እናቲቱ ልጅዋን በከፍተኛ ጥንቃቄ ትንከባከባለች። ልጅዋን በጀርባዋ ላይ አዝላ ውኃ ላይ የምትንሳፈፍ ጉማሬ ማየት በእርግጥም የሚያስደስት ትዕይንት ነው። ገራም የምትመስለው ይህች እንስሳ ልጅዋን ከጀርባዋ ለማውረድ የሚቃጣ ፍጡር ቢኖር አምርራ ትጣላለች።
የጉማሬ ቆዳ ለውኃ ውስጥ ኑሮ በጣም የተመቸ ነው። እንስሳው ደረቅ መሬት ላይ ሲወጣ ግልጽ የሆኑ ለውጦች ይታዩበታል። ከቆዳው ሥር ያሉ እጢዎች ቡናማ ቀይ ቀለምና ከፍተኛ የጨው ይዘት ያለው ቀጭን ዝልግልግ ፈሳሽ ያመነጫሉ። እንስሳው ከሩቅ ሲታይ ደም የሚያልበው መስሎ ይታያል። ይሁን እንጂ ይህ ፈሳሽ የእንስሳውን ቆዳ * የግዝሂመክ አኒማል ላይፍ ኢንሳይክሎፒዲያ የጉማሬ ቆዳ ቢያንስ ስድስት ወር ለሚያክል ጊዜ ከለፋ በኋላ “እንደ ድንጋይ የጠነከረና አራት ሴንቲ ሜትር ተኩል የሚያክል ውፍረት ያለው ይሆናል።”
በውኃ ውስጥም ሆነ በደረቁ መሬት ላይ ከጉዳት ይጠብቃል። በጥንቶቹ የአፍሪካውያን ማኅበረሰቦች የጉማሬ ቆዳ በቀጭን በቀጭኑ ይቆራረጥና ዘይት ውስጥ ይዘፈዘፋል። ከዚያም ተገምዶ ከደረቀ በኋላ ለውጊያ የሚያገለግል ጅራፍ ይሆን ነበር።የሚያስደንቀውና አስፈሪ የሆነው ማዛጋት
ከጉማሬ የአካል ክፍሎች በሙሉ በጣም አስደናቂ የሆነው አፉ ነው። ይህ እንስሳ መሬት ላይ ሲሆን ግማሽ ሜትር ስፋት ባላቸው ከንፈሮቹ በባሕር ዳርቻ ያለውን ሣር ይግጣል። ይሁን እንጂ አፉ የሚያገለግለው ለመብያነት ብቻ አይደለም። መንጋጋውን በ150 ዲግሪ ስፋት ሲከፍት ማዛጋቱ ብቻ ሳይሆን በጣም መቆጣቱንም ማሳየቱ ነው። የመኖሪያ ድንበር ለማስከበር ሲባል በተቀናቃኞች መካከል በጣም ከባድ የሆነ ጠብ ይፈጠራል። አፉ ሲከፈት በጣም ትላልቅ የሆኑ የክራንቻ ጥርሶች ይታያሉ። እነዚህ የመከላከያ መሣሪያዎች ከድዱ በላይ እስከ 30 ሴንቲ ሜትር የሚደርስ ቁመት ሊኖራቸው ይችላል።
የጉማሬ አፍ ለሌሎች ጉማሬዎች ብቻ ሳይሆን ለሰዎችም ጭምር አደገኛ ነው። የሰው ልጅ ከጉማሬ ጋር ለመላመድ ያደረገው ጥረት በሙሉ ሳይሳካ ቀርቷል። ይህ እንስሳ ወደ መኖሪያ ክልሉ አለአግባብ በተጠጉ ሁሉ ላይ ጥቃት ይሰነዝራል። ከዚህም በላይ ጉማሬ ከቆሰለ የበለጠ ስለሚቆጣ ከፊቱ ያገኘውን ሁሉ ያጠቃል። ጀልባዎች ሳይቀሩ በተቆጣ ጉማሬ መንጋጋዎች ተሰባብረዋል።
ጉማሬ መሬት ላይ በሚሆንበት ጊዜም ከውኃ ውስጥ ባልተናነሰ መጠን ግልፍተኛ ነው። ለምሳሌ ያህል ሣር በሚግጥ ጉማሬና በውኃ መካከል በሚገኝ ቦታ ላይ መቆም በጣም አደገኛ ነው። በአንዳንድ የአፍሪካ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች ሳያስቡት የጉማሬዎቹን ወደ ውኃ መመለሻ መንገድ በመዝጋታቸው ጉዳት ደርሶባቸዋል። ይህ አውሬ ሰዎችንም ሆነ አራዊትን የሚያስፈራ በመሆኑ በከፍተኛ ጥንቃቄና አክብሮት መያዝ ይኖርበታል።
ጉማሬ ከጥፋት ይተርፍ ይሆን?
ጉማሬ ብቻውን ሆኖ ሣር በሚግጥበት ጊዜ አንበሶች ሊያጠቁት ይችላሉ። ይሁን እንጂ ከሁሉ የሚከፋው የጉማሬ ጠላት የሰው ልጅ ይመስላል። ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ “ሰዎች የጉማሬዎችን ቁጥርም ሆነ የመኖሪያ አካባቢያቸውን ስፋት በእጅጉ ቀንሰዋል” ይላል። “ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጉማሬዎች በአዳኞች ከመገደላቸውም በላይ በአንድ ወቅት የጉማሬዎች መኖሪያ የነበሩ አካባቢዎች ዛሬ የእርሻ ማሳዎች ሆነዋል።”
አዎን፣ የጉማሬዎች የመኖሪያ አካባቢዎች በሰው ልጆች በመወረራቸው እንስሳቱ በጣም ጠባብ በሆነ ክልል ለመወሰን ተገድደዋል። በዚህም ምክንያት የመንቀሳቀስና የመራባት ነጻነታቸው ተገድቦባቸዋል። ይሁን እንጂ ፈጣሪ በአምላክ መንግሥት ግዛት ውስጥ በእንስሳትና በሰው ልጆች መካከል ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖርና ተመልሳ በምትቋቋመው ምድራዊ ገነት ውስጥ ‘ጉዳት ወይም ጥፋት’ እንዳይኖር ለማድረግ ቃል መግባቱ በጣም ያስደስታል።—ኢሳይያስ 11:9
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.11 ጉማሬ በስዋሂሊ ቋንቋ ኪቦኮ ሲባል ትርጉሙም “ጅራፍ” ማለት ነው።
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የሥዕሎቹ ምንጭ]
Elizabeth DeLaney/Index Stock Photography