አደገኛ ዕፅ የማይኖርበት ዓለም በቅርቡ ይመጣል
አደገኛ ዕፅ የማይኖርበት ዓለም በቅርቡ ይመጣል
አደገኛ ዕፅ ፈጽሞ የማይኖርበት ዓለም ይመጣል ብለህ ትገምታለህ?
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ኮፊ አናን ሁሉም ሰው እንዲህ ያለውን ዓለም እውን ለማድረግ የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። “ሁላችንም ብዙ ልጆቻችንን እስረኛ አድርጎ ያስቀረውን ይህን ክፉ ልማድ ለመዋጋት አዳዲስና ድፍረት የሚጠይቁ እርምጃዎችን መውሰድ ይገባናል” ብለዋል።
መሪዎች የሕገወጥ ዕፆችን ምርትና ስርጭት መቀነስ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይስማሙ እንጂ ይህን ማድረጉን ቀላል ሆኖ አላገኙትም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዚዳንት ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት የዩክሬኑ ሄናንዲ ኡዲቬንኮ “በዓመት እስከ 400 ቢልዮን ዶላር እንደሚያንቀሳቅስ የሚገመተው የናርኮቲክ ንግድ ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ እንስቅቃሴዎችን ሊበክልና ሊያናጋ የሚችል እጅግ አትራፊ ከሆኑ በሕቡዕ የሚከናወኑ የንግድ እንቅስቃሴዎች አንዱ ነው” ብለዋል። በመቀጠልም የአደገኛ ዕፆች ችግር “ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው በመሆኑ ይህ ችግር እኔን አይነካም ብሎ ሊናገር የሚችል አንድም አገር የለም” ብለዋል።
አደገኛ ዕፆች የማይኖሩበት ዓለም ይመጣል ብሎ ማሰብ በጣም ያስቸግራል። ሰብዓዊ መንግሥታት አደገኛ ዕፆችን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ እንደማይችሉ ተረጋግጧል። ይሁን እንጂ ሁሉን የሚችለው አምላክ ማንኛውም ስሜታዊ፣ አካላዊና መንፈሳዊ ፍላጎት የሚሟላበት ምድራዊ ገነት ለማምጣት ያወጣውን ዓላማ ሊያግድ የሚችል አንድም ኃይል የለም። (መዝሙር 145:16፤ ሉቃስ 23:43፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) ነቢዩ ኢሳይያስ እንደተናገረው የአምላክ ቃል ‘የሚሻውን ሳያደርግ የላከውንም ሳይፈጽም ወደ እርሱ በከንቱ አይመለስም።’—ኢሳይያስ 55:11
እንደነዚህ ባሉት ተስፋዎች መታመን ዛሬም ቢሆን አስደናቂ ጥቅሞች ያስገኛል። ለምሳሌ ያህል ኤድሙንዶ የዕፅ ሱሰኛ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ጽድቅ የሚኖርበት አዲስ ዓለም እንደሚመጣ የሚሰጠውን ተስፋ መቀበሉ ሕይወቱን መለስ ብሎ እንዲመለከት አደረገው። በአሁኑ ጊዜ ኤድሙንዶ “ሕይወቴን በከንቱ ማባከኔ እንዴት ያለ ሞኝነት ነበር!” ይላል። በአምላክ ዘንድ ያገኘውን ሞገስ እንዳያጣ ወደ ቀድሞ ልማዱ መመለስ አይኖርበትም። አዎን፣ አምላክንና አምላክ የሰጣቸውን ተስፋዎች ማወቃችን “ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው” እንድንለብስ ያነሳሳናል።—ኤፌሶን 4:24
የዕፅ ሱሰኞች የነበሩ ሌሎች ብዙ ሰዎች ከፈጣሪያቸው ጋር የተቀራረበ ዝምድና መመሥረት ችለዋል። እንደነዚህ ላሉት ሰዎች የሚከተሉት የመዝሙራዊው ቃላት ልዩ ትርጉም አላቸው:- “የልጅነቴን ኃጢአትና መተላለፍ አታስብብኝ፤ አቤቱ፣ ስለ ቸርነትህ ብዛት እንደ ምሕረትህ አስበኝ። እግዚአብሔር ቸር ቅንም ነው፤ ስለዚህ ኃጢአተኞችን በመንገድ ይመራቸዋል።” (መዝሙር 25:7, 8) መጥፎ አካሄድ የመረጡ ልጆች ያሏቸው ወላጆች ልጆቻቸው ሊለወጡ እንደሚችሉ ማወቃቸው ምንኛ የሚያጽናና ነው! ልባዊ ጥረት ካደረጉ ልጆቻቸው ዓለምን ያጥለቀለቀውን የአደገኛ ዕፅ ቸነፈር እንዲቋቋሙና በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ እውን የሚሆነውን ‘እውነተኛ ሕይወት እንዲይዙ’ ሊረዷቸው ይችላሉ።—1 ጢሞቴዎስ 6:18, 19
[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የመኖር ተስፋ ብዙ የዕፅ ሱሰኞች አኗኗራቸውን እንዲለውጡ አነሳስቷል