በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከልክ ያለፈ ውፍረት ዓለም አቀፋዊ ችግር ነውን?

ከልክ ያለፈ ውፍረት ዓለም አቀፋዊ ችግር ነውን?

ከልክ ያለፈ ውፍረት ዓለም አቀፋዊ ችግር ነውን?

“ብዙውን ጊዜ የበለጸጉና ያደጉ አገሮች ዘመናዊ ኑሮ ውጤት እንደሆነ ተደርጎ ይታሰብ የነበረው ከልክ በላይ የመወፈር ችግር በታዳጊ አገሮችም እየታየ ነው” በማለት ዘ ላንሴት የተባለው በብሪታኒያ የሚታተም የሕክምና መጽሔት ዘግቧል። ከመጠን በላይ ከመወፈር ጋር የተያያዙ እንደ ስኳር፣ የደም ግፊት፣ ካንሰር እንዲሁም የደም ሥርና የልብ በሽታዎች “ዓለም አቀ​ፋዊ ወረርሽኝ” እንደሚሆኑ የምግብ ጥናት ባለሞያዎች እያስጠነ​ቀቁ ነው።

በቻይና ባለፉት ስምንት ዓመታት ከመጠን በላይ ወፍራም የሆኑ ወንዶች ቁጥር በሦስት እጥፍ የሴቶቹ ደግሞ በሁለት እጥፍ በመጨመሩ ምክንያት የደም ግፊት ታማሚዎች ቁጥር በአሜሪካ ካሉት ህመምተኞች ጋር ተመጣጣኝ ሆኗል። በዓለማችን ላይ የስኳር ሕመምተኛ መሆናቸው በቅርቡ በምርመራ ከታወቀው ሰዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሚገኙት በሕንድና በቻይና ነው። በግብፅ ያለው የስኳር ሕመምተኞች ቁጥር በአሜሪካ ካሉት ጋር ተመጣጣኝ ሲሆን ከአገሪቱ ሴቶች መካከል ግማሽ የሚሆኑት በጣም ወፍራሞች ናቸው። በሜክሲኮ በመላው የአገሪቱ ክፍል ከልክ በላይ ወፍራም የሆኑ ሰዎች ቁጥር በየትኛውም የኑሮ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረ ሲሆን ይህም የስኳር ህመምተኞች ቁጥር ከፍ እንዲል አስተዋጽኦ አድርጓል። ከሰሃራ በታች በሚገኙት ድሃ አገሮችም እንኳ ከልክ በላይ መወፈርና የስኳር ሕመም እየጨመረ ነው።

በአንዳንድ አገሮች ከልክ በላይ ለመወፈር መንስኤ የሚሆነው ቶሎ የሚደርሱ ቅባት የበዛባቸው ምግቦችን ማዘውተር ቢሆንም ዋነኛው ምክንያት ብዙ የምግብ አምራቾች ምግቡን “ለማጣፈጥ” ብዙ ስኳር ስለሚጨምሩበት ነው። ከዚህም በተጨማሪ የእስያና የአፍሪካ ምግቦች ብዙ ዘይት የሚጨመርባቸው በመሆኑ የሚይዙት የካሎሪ መጠን ከፍተኛ ነው። በፋብሪካዎችና በእርሻው መስክ የተገኘው የቴክኖሎጂ እድገት ሠራተኞች ብዙ ጉልበት ሳያጠፉ ምርት ለማግኘት አስችሏቸዋል። ሰዎች ትንሽ ሠርተው ብዙ ማረፍ ይፈልጋሉ። በዛሬው ጊዜ ኮምፒውተርና ቴሌቪዥን በስፋት ጥቅም ላይ በመዋላቸው ሠራተኞች እምብዛም አካላዊ እን​ቅስቃሴ ሳያደርጉ የሚውሉ ከመሆኑም በላይ “የኤሌክትሮኒክ መልእክት መለዋወጫ ዘዴ መልእክት ለማድረስና ከሥራ ባልደረባ ጋር ለማውራት ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስን አስቀርቷል።”

ከልክ በላይ መወፈር በተማሪዎችም ላይ በተለይ ደግሞ እም​ብዛም አካላዊ እንቅስቃሴ በማያደርጉት ላይ በስፋት እየታየ የመጣ ችግር በመሆኑ አመጋገብ በትምህርት ውጤት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንደሚኖረው መምህራን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። በካ​ሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ በሕዝብ ጤና አጠባበቅ ትምህርት መምህር የሆ​ኑት ጌይል ሃሪሰን ይህን ከልክ በላይ የመወፈር ችግርና ተዛማጅ በሽታዎችን ለመከላከል በትምህርት ቤት ደረጃ ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ “ዓለም አቀፋዊ ትኩረት ተሰጥቶት ፖሊሲዎች ሊረ​ቀቁለት፣ የተማረ የሰው ኃይል ሊመደብለትና የመሠረተ ልማት አው​ታሮች ሊዘረጉለት ይገባል” በማለት ያስጠነቅቃሉ።