በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ምርታማነት ጨምሯል?

ቫንኩቨር ሰን የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው “በአሁኑ ጊዜ ከአራት ካናዳውያን መካከል አንዱ በሳምንት ከ50 ሰዓት በላይ ይሠራል። ከአሥር ዓመት በፊት ግን ይህን የሚያክል ሰዓት የሚሠራው ከ10 ካናዳውያን መካከል አንዱ ብቻ ነበር።” መንግሥት 31, 500 በሚያክሉ ካናዳውያን ሠራተኞች ላይ ባደረገው ጥናት “ጥናት ከተደረገባቸው ሰዎች መካከል ግማሽ የሚሆኑት ማታ ማታ ወይም ቅዳሜና እሁድ እቤታቸው ሆነው በመሥራት በወር ውስጥ ተጨማሪ የ27 ሰዓት ሥራ ለአሠሪዎቻቸው እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል።” ለዚህ መንስኤ ከሆኑት ቁልፍ ምክንያቶች አንዱ ቴክኖሎጂ ነው። “ክፍያ ያልተገኘባቸውና በመኖሪያ ቤቶች የተከናወኑ የትርፍ ሰዓት ሥራዎች በሙሉ በኮምፒውተር አጋዥነት የተከናወኑ እንደሆኑ ጥናቱ አረጋግጧል” ይላል የጋዜጣው ዘገባ። ስለዚህ የቴክኖሎጂ እድገት “በሣምንት አራት ቀን ሠርቶ ሌላውን በእረፍት ማሳለፍ ከማስቻል ይልቅ ለውጥረት፣ ለበሽታ፣ ለድካም፣ ከሥራ ለመቅረትና ምርታማነትን ለሚቀንሱ በርካታ ችግሮች ዋነኛ ምክንያት ሆኗል።” ጋዜጣው በማከል “የቴክኖሎጂ እድገት በሥራቸው የሚያገኙትን ደስታና ምርታማነታቸውን እንደጨመረ አብዛኞቹ ተጠያቂዎች ተስማምተዋል። ቢሆንም አንዳቸውም ቢሆኑ የቴክኖሎጂ እድገት የሥራቸውን ጫና ወይም ሥራቸው የሚፈጥርባቸውን ውጥረት እንደቀነሰላቸው አልተናገሩም” ብሏል።

“ተናጋሪ” እጽዋት

በጀርመን አገር የቦን ዩኒቨርሲቲ የተግባራዊ ፊዚክስ ተቋም ተመራማሪዎች እጽዋትን “የሚያዳምጡ” በሌዘር ጨረር የሚሠሩ ማይክሮፎኖች ሠርተዋል። ማይክሮፎኖቹ እጽዋት በውጥረት ላይ በሚሆኑበት ጊዜ የሚያወጡት ኤትሊን የተባለ ጋዝ የሚያሰማውን ድምፅ ይቀርጻሉ። ዶክተር ፍራንክ ኩህነማን የተባሉት የቦን ዩኒቨርሲቲ ሳይንቲስት “ተክሉን ያጋጠመው ውጥረት በጨመረ መጠን ከማይክሮፎናችን የምናገኘው ድምፅም ይጨምራል” ብለዋል። በአንድ ወቅት ጤነኛ መስሎ የሚታይ አንድ የዱባ ተክል “በመጮህ ላይ እንዳለ” መሣሪያው አመለከተ። “ተክሉ በቅርብ ሲመረመር መሻገት ጀምሮ እንደነበረ ታየ። ሆኖም የበሽታ ምልክት ገና አልታየበትም ነበር።” ሻጋታ መታየት እስከሚችልበት ደረጃ ለመድረስ ስምንት ወይም ዘጠኝ ቀን ስለሚፈጅ ገበሬዎች ችግር መኖሩን ሊያውቁ የሚችሉት ይህን ከሚያክል ጊዜ በኋላ ነው። “እጽዋት ለሚያሰሙት ድምፅ ጆሮን ጣል በማድረግ” ይላል የለንደኑ ዘ ታይምስ “ተባይ ወይም በሽታ መኖሩን ቀደም ብሎ ለማወቅ መቻል ይኖርበታል። ፍራፍሬዎችና አትክልቶች የሚገኙበትን የውጥረት መጠን ማወቅ በጥሩ ሁኔታ ለማጓጓዝና ለማስቀመጥም ይረዳል።”

የመገናኛ ብዙኃን እድገት በሕንድ አገር

ብሔራዊ የአንባቢዎች ጥናት ጉባኤ ባደረገው ጥናት መሠረት ከ1999 እስከ 2002 ባለው የሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ የሕንድ ጋዜጣ አንባቢዎች ቁጥር ከ131 ሚልዮን ወደ 155 ሚልዮን አድጓል። ጋዜጦችን፣ መጽሔቶችንና ሌሎች ወቅታዊ ጽሑፎችን ጨምሮ ጠቅላላ የአገሪቱ የሕትመት አንባቢዎች ቁጥር 180 ሚልዮን ይደርሳል። አንድ ቢልዮን ከሚሆኑት የሕንድ ሕዝቦች መካከል 65 በመቶ የሚሆኑት ማንበብና መጻፍ የሚችሉ በመሆናቸው የአንባቢዎች ቁጥር ይበልጥ ሊጨምር እንደሚችል ይጠበቃል። የቴሌቪዥን ተመልካቾች ቁጥር 383.6 ሚልዮን የደረሰ ሲሆን 680.6 ሚልዮን የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ራዲዮ ያዳምጣሉ። የኢንተርኔት አገልግሎት ለማግኘት የሚችሉ ሰዎች ብዛት በ1999 1.4 ሚልዮን የነበረ ሲሆን አሁን ግን ከ6 ሚልዮን በልጧል። ከሕንዳውያን ቤቶች ግማሽ የሚያክሉት ቴሌቪዥን ያላቸው ሲሆኑ የኬብል ወይም የሳተላይት ስርጭት ደንበኞችም ናቸው። በዚህ ዘርፍ በሦስት ዓመት ውስጥ 31 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

የጠለፋ መስፋፋት

“ከአሥራ አምስት ዓመታት በፊት በሜክሲኮ ጠለፋ መኖሩ እንኳን አይታወቅም ነበር” ይላል የሜክሲኮ ሲቲው ዘ ኒውስ። “ይሁን እንጂ በ1980ዎቹ ዓመታት ወንጀል በመጨመሩና በ1994-95 የኢኮኖሚ ውድቀት በመከሰቱ በሜክሲኮ መሠረታዊ የሆነ ለውጥ ታይቷል። በዚህም ምክንያት ጠለፋና ወንጀል በአጠቃላይ በጣም እየጨመረ መጥቷል።” የጠለፋ ወንጀል አይቃጣብኝም ሊል የሚችል ሰው የሚኖር አይመስልም። “የቤት ሠራተኞች 500 ዶላር ካሣ እንዲከፍሉ ይታገታሉ። አንዲት የ12 ዓመት የቲጅዋና ልጅ ለትምህርት ቤታቸው የሚከፍሉት ገንዘብ ባጡ የኮሌጅ ተማሪዎች ታግታለች። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ከቤተሰቦቻቸው ወይም ከሚሠሩበት ድርጅት ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ በውሸት የተጠለፉ አስመስለዋል” ይላል ዘ ኒውስ። “ጠለፋ የተለመደ የሕይወት ገጠመኝ ሆኗል። በሜክሲኮ ለፖሊስ ሳያሳውቁ የታገቱ ሰዎችን ለማስለቀቅ ገንዘብ በአፋጣኝ መክፈል የተለመደ ሆኗል።” እንዲያውም የታገቱ ሰዎች፣ የደህንነት ሠራተኞችና የፍርድ ቤት መዝገቦች እንደሚናገሩት “ፖሊሶቹ ራሳቸው የጠለፋ ወንጀል ተባባሪዎች ናቸው። የፍትሕ ሥርዓቱ ደካማና በሙስና የተዘፈቀ በመሆኑ ፖሊሶቹን ይዞ የሚጠይቃቸው አይኖርም።”

የቋንቋ ችሎታ እያሽቆለቆለ መጥቷል

ዘ ዮሚዩሪ ሺምቡን የተባለው የጃፓን ዕለታዊ ጋዜጣ “ከአንደኛና ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት ለመዝናናት ሲሉ ምንም ዓይነት መጽሐፍ እንደማያነቡና ከመለስተኛና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት የተማሪዎቹ የጃፓንኛ ቋንቋ ችሎታ እያሽቆለቆለ መጥቷል ብለው እንደሚያስቡ” ገልጿል። በብሔራዊ የትምህርት ፖሊሲ ምርምር ተቋም የሚሠሩ ተመራማሪዎች “ከአራተኛ ክፍል እስከ አሥረኛ ክፍል በሚገኙ 2, 120 ተማሪዎች እንዲሁም በአንደኛ፣ በመለስተኛና በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሚሠሩ 259 መምህራን ላይ ጥናት አካሂደው እንደነበረ” ዘገባው ይገልጻል። “ተማሪዎቹ ብዙ ስለማያነቡ የመረዳትና የመጻፍ ችሎታቸው እንዲሁም የሚያውቁት የቃላት ብዛት እንደቀነሰ ተገንዝበዋል።” ጥናት የተደረገባቸው መምህራን ለዚህ ማሽቆልቆል ዋነኛው ምክንያት ከተማሪዎቹ ጋር ብዙ ግንኙነት ያላቸውን መምህራን ጨምሮ ትላልቅ ሰዎች ያላቸው የማንበብ ልማድ እየቀነሰ መምጣቱ ነው። በተጨማሪም “የቪዲዮ ጨዋታዎች አሉታዊ ተጽእኖ እንዳሳደሩ ጠቁመዋል።”

ለስላሳ መጠጦችና ሜክሲካውያን

ለስላሳ መጠጦችን በብዛት በመጠጣት ረገድ ከዩናይትድ ስቴትስ ቀጥሎ በዓለም የሁለተኛነቱን ደረጃ የያዘችው ሜክሲኮ ናት። ለስላሳ መጠጦች የሜክሲኮ ሰዎች አዘውትረው ከሚመገቧቸው አሥር የምግብ ዓይነቶች መካከል የሚመደቡ ሲሆን 60 በመቶ የሚሆኑ ቤተሰቦች አዘውትረው እንደሚጠጡ ሪፎርማ የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። ይህ ሁኔታ ለሕፃናት አካል መዳበርና እድገት አስፈላጊ የሆኑትን እንደ ወተት፣ ፍራፍሬና አትክልት የመሰሉ ምርቶችን እንዲገዙ የሚፈልጉትን የጤና ባለሞያዎች አሳስቧል። የቤተሰቡ ገንዘብ “ውሎ አድሮ ከማወፈር በስተቀር ምንም ዓይነት ገንቢ ንጥረ ነገር የሌለውን ሸቀጥ” ለመሸመት እንደሚውል ሪፎርማ ዘግቧል። ለስላሳ መጠጦችን በተለይም የኮላ መጠጦችን አብዝቶ መጠጣት ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች መካከል የጥርስ መበስበስና የአጥንት መሳሳት እንደሚገኙበት ዘገባው ገልጿል።

የራስ ምታት መድኃኒቶች ራስ ምታትን ያባብሳሉ

የሲድኒ፣ አውስትራሊያ ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ “በራስ ምታት ከሚሠቃዩ ሰዎች መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት የሚሠቃዩት የሥቃይ ማስታገሻ መድኃኒቶችን ‘አላግባብ በመውሰዳቸው’ ምክንያት በተፈጠረባቸው ራስ ምታት እንደሆነ ማይክል አንተኒ የተባሉት ኒውሮሎጂስት ገምተዋል” ይላል። “የሐኪም ትእዛዝ የማያስፈልጋቸውን መድኃኒቶች አዘውትሮ መውሰድ በሣምንት አንዴ የሚነሳውን ራስ ምታት በየቀኑ እንዲመላለስ ያደርጋል።” ፕሮፌሰር አንተኒ ከኒው ሳውዝ ዌልስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባደረጉት ጥናት “የራስ ምታት መድኃኒቶችን አብዝተው የሚወስዱ ሰዎች በጣም አነስተኛ የሆነ የሰሮቶኒን መጠን” እንዳላቸው ደርሰውበታል። ሰሮቶኒን የደም ሥሮች እንዳይለጠጡ የሚከላከል ቅመም ነው። “የሰሮቶኒን ማነስ ደም ሥሮች እንዲለጠጡ ሲያደርግ ይህ ደግሞ በተራው ራስ ምታት ያስከትላል” ብለዋል። አንተኒ የማይግሬን ወይም ከባድ ራስ ምታት ያለባቸው በሽተኞች የሐኪም ትእዛዝ የማያስፈልጋቸውን መድኃኒቶች ከመውሰድ ይልቅ ልዩ የሆኑ በሐኪም የሚታዘዙ መድኃኒቶችን ቢወስዱ ጥሩ እንደሚሆን ገልጸዋል። አክለውም “በሣምንት ውስጥ ከሦስት ጊዜ በላይ [የሕመም ማስታገሻ] እንክብል የሚወስዱ [ሰዎች] በጥቂት ወራት ውስጥ ራስ ምታታቸው ይባባስባቸዋል።”

እርጉዞች ጠዋት ጠዋት የሚሰማቸውን ሕመም ማስታገስ

“ከሰባ እስከ ሰማንያ በመቶ የሚሆኑ እርጉዝ ሴቶች ጠዋት ጠዋት የሕመም ስሜት ይሰማቸዋል” ሲል የአውስትራሊያው ሳን ሄራልድ ጋዜጣ ገልጿል። እነዚህ ሴቶች በመጀመሪያው የእርግዝናቸው ወቅት ጠዋት ሲነሱ ያቅለሸልሻቸዋል፣ ብዙ ጊዜም ያስመልሳቸዋል። ለዚህ ምክንያት ናቸው ተብለው ከሚጠረጠሩ ነገሮች አንዱ በእርግዝና ወቅት ፕሮጀስትሮን የተባለው ሆርሞን መጠን መጨ​መሩና በዚህም ምክንያት የጨጓራ አሲድ መብዛቱ ነው። በተጨማሪም “እርጉዝ ሴቶች የማሽተት ችሎታቸው ከፍ ስለሚል ለማቅለሽለሽ የተጋለጡ ይሆናሉ።” ለሁሉ ሰው የሚሠራ መድኃኒት አለ ብሎ መናገር ባይቻልም ጋዜጣው ሙቀት የማቅለሽለሽ ስሜት ስለሚያመጣ ከሞቃት አካባቢዎች መራቅ፣ በቂ እንቅልፍ ማግኘትና በቀኑ ውስጥ ለጥቂት ጊዜ ማሸለብ እንዲሁም የተቆረጠ ሎሚ ማሽተት እንደሚረዳ ይመክራል። “ከአልጋ ከመውረዳችሁ በፊት እንደ [ቆሎ] ያለ ጥሬ ነገር ለመብላት ሞክሩ። ሁልጊዜ ቀስ ብላችሁ ከአልጋ ውረዱ” በማለት ጋዜጣው ይመክራል። “በየጊዜው ፕሮቲን የሆነ ትንሽ ነገር ቀመስ አድርጉ።” ጋዜጣው “ይህ ሕመም በጎ ገጽታም አለው። በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶች ይህ የሕመም ስሜት የሚሰማቸው እናቶች ብዙ ጊዜ እንደማያስወርዳቸው አመልክተዋል” ይላል።

ቴሌቪዥን አመጣሽ የአመጋገብ ችግር

በለንደኑ ዚ ኢንዲፐንደንት ጋዜጣ ላይ የወጣ ሪፖርት እንዳመለከተው “በቴሌቪዥንና በአመጋገብ ችግሮች መካከል ጉልህ የሆነ ዝምድና አለ።” በዩናይትድ ስቴትስ የሀርቫርድ ሕክምና ትምህርት ቤት ባልደረባ የሆኑት ዶክተር አን ቤከር በ1995 ቴሌቪዥን ወደ ፊጂ እንደገባ በዚያ አገር ለሚኖሩ ወጣት ልጃገረዶች ቃለ መጠይቅ አድርገው ነበር። ቴሌቪዥን “ሊኖራቸው በሚፈልጉት ቁመናና በአመጋገብ ሥርዓት መዛባት ላይ የጎላ ተጽእኖ እንደሚያሳድር ተረድተዋል።” እንዴት? የፊጂ ባሕል ጠገብ ብሎ መብላትንና ውፍረትን ያበረታታ ነበር። ይሁን እንጂ ብዙ ወጣት ሴቶች ቀጠን ያሉትን የቴሌቪዥን ገጸ ባሕርያት ከተመለከቱ በኋላ እነርሱን መስለው ለመታየት ተነሳስተዋል። ለምሳሌ ያህል ቴሌቪዥን ወደ ፊጂ ከመግባቱ በፊት በጥናቱ ውስጥ ከተካተቱት ልጃገረዶች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ እንዳይወፍሩ ለመከላከል ሲሉ የበሉትን ለማስወጣት ሞክረው አያውቁም ነበር። ከሦስት ዓመት በኋላ ግን 11.3 በመቶ የሚሆኑት እንደዚያ እንዳደረጉ ተናግረዋል። በተጨማሪም በትምህርት ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ልጃገረዶች መካከል 69 በመቶ የሚሆኑት ክብደታቸውን ለመቀነስ ሲሉ አመጋገባቸውን እንደሚቆጣጠሩና ሦስት አራተኛ የሚሆኑት “በጣም ወፍራም” እንደሆኑ እንደሚሰማቸው መናገራቸውን ተመራማሪዎች ተገንዝበዋል።