ወጣቶችና አደገኛ ዕፆች
ወጣቶችና አደገኛ ዕፆች
“መሞት ነበረባቸውን?”
ቬጃ በተባለው የብራዚል መጽሔት ሽፋን ላይ የወጣ ጥያቄ ነበር። ከእነዚህ ቃላት በተጨማሪ በአደገኛ ዕፆች ምክንያት ሕይወታቸው በአጭሩ የተቀጨ የሚያማምሩ ወጣቶች ፎቶግራፍ ወጥቷል።
አደገኛ ዕፆች የሚያስከትሉት ጉዳት በሰፊው የሚታወቅ ቢሆንም ሰዎች አደገኛ ዕፆችን መውሰዳቸው አልቀረም፣ ዕፆቹም የሰዎችን ሕይወት ማበላሸታቸውን አላቆሙም። በአደገኛ ዕፆች ምክንያት በሚፈጠረው የምርታማነት መቀነስ፣ የሕክምና ወጪ፣ ወንጀልና የገቢ መቀነስ በዩናይትድ ስቴትስ በዓመት 100 ቢልዮን ዶላር ገደማ ኪሣራ እንደሚደርስ ይገመታል። ይሁን እንጂ ከሁሉ የበለጠ ከፍተኛ ኪሣራ የሚደርሰው በልጆች ላይ ሳይሆን አይቀርም። ዦርናል ዳ ታርድ በተባለ ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ በብራዚል የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው ከ10 እስከ 17 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ልጆች መካከል 24.7 በመቶ የሚሆኑት አንድ ዓይነት አደገኛ ዕፅ ወስደው የሚያውቁ ናቸው።
በዩናይትድ ስቴትስ ምንም እንኳ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ አደገኛ ዕፅ የሚወስዱ ወጣቶች ቁጥር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመጠኑም ቢሆን ቢቀንስም የአደገኛ ዕፅ ሱሰኞች የሆኑ ወጣቶች ብዛት አስደንጋጭ ደረጃ ላይ ደርሷል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሊያጠናቅቁ የደረሱ ወጣቶችን እንመልከት። አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው 37 በመቶ የሚሆኑት ባለፈው ዓመት ውስጥ ቢያንስ ማሪዋና ወስደው ያውቃሉ። ከአምስት ወጣቶች መካከል አንዱ ባለፈው ወር ውስጥ ማሪዋና ወስዷል። ከአሥር ወጣቶች አንዱ ባለፈው ዓመት ውስጥ ኤክስታሲ የተባለውን አደገኛ ዕፅ ወስዷል። ከስድስት በመቶ የሚበልጡት ኤል ኤስ ዲ የተባለውን ዕፅ ሞክረዋል።
ከሁሉም የዓለም ክፍሎች አሳሳቢ ሪፖርቶች ይቀርባሉ። የብሪታንያ ብሔራዊ ስታትስቲክስ ጽሕፈት ቤት “ከ11 እስከ 15 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ተማሪዎች መካከል 12 በመቶ የሚሆኑት ባለፈው ዓመት ውስጥ አደገኛ ዕፅ ወስደዋል . . . አብዛኞቹ የሚወስዱት ካናቢስ ወይም ማሪዋና እንደሆነ” ዘግቧል። በተለይ አስደንጋጭ የሆነው “ከአንድ ሦስተኛ የሚበልጡት (35 በመቶ የሚሆኑት) አንድ ወይም ከአንድ የሚበልጥ ዕፅ እንዲወስዱ ግብዣ ቀርቦላቸው የሚያውቅ መሆኑ ነው።”
በአውሮፓ ኅብረት ተዘጋጅቶ የቀረበ አንድ ሪፖርት ደግሞ በተመሳሳይ በወጣቶች መካከል “ሞቅ እስኪል መጠጣት በጣም የተለመደ እየሆነ መምጣቱን” ተናግሯል። በተጨማሪም ሪፖርቱ ይህ ዓይነቱ የአልኮል አወሳሰድ “እንደ ድንገተኛ አደጋ፣ ጠብና መመረዝ እንዲሁም ከሰዎች ጋር መጋጨትን ለመሳሰሉት ጉዳቶች እንደሚያጋልጥ” ገልጿል። “አብዛኛውን ጊዜ ወጣቶች ሱሰኛ የሚሆኑት እንደ ቤንዚንና ማስቲሽ የመሰሉትን በማሽተት ሲሆን ይህ ልማድ ደግሞ ሌሎች አደገኛ ዕፆችን ወደ መውሰድ ይመራል” የሚለው ደግሞ ከጃፓን የተገኘ ሪፖርት ነው።
ስለዚህ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ኮፊ አናን “አደገኛ ዕፆች የወንጀል መቀፍቀፊያ በመሆን፣ እንደ ኤድስ ያሉትን በሽታዎች በማዛመትና ወጣቶቻችንንና የወደፊት ሕልውናቸውን በመግደል ማኅበረሰባችንን እያፈራረሱት ነው” ማለታቸው የሚያስደንቅ አይደለም። አብዛኛውን ጊዜ ከአደገኛ ዕፆች ጋር ንክኪ የሚኖራቸው ሰዎች እንደ ዕፅ ማዘዋወርና ነፍስ መግደል የመሰሉትን ወንጀሎች ይፈጽማሉ። በተጨማሪም ብዙ ሰዎች ዕፅ በመውሰዳቸው ምክንያት ድብደባና የአካል ጉዳት ይደርስባቸዋል፣ ወይም ለአደጋ የሚያጋልጥና ቀደም ብሎ ያልታሰበበት ሩካቤ ሥጋ ይፈጽማሉ። እንዲህ ያለው ችግር በእኔ ቤተሰብ ላይ ፈጽሞ አይደርስም የምትል ከሆነ ቆም ብለህ አስብ! አንድ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ሪፖርት “አደገኛ ዕፅ የድሆች፣ የአናሳ ክፍሎች ወይም የአራዳ ነዋሪዎች ብቻ ችግር አይደለም . . . ከሁሉም የማኅበረሰብ
ክፍሎችና ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የአደገኛ ዕፅ ተጠቃሚዎችን ማግኘት ይቻላል። የአደገኛ ዕፅ ችግር የማይነካው ሰው የለም” ይላል።ይሁን እንጂ ወላጆች ችግር መኖሩን የሚያውቁት አብዛኛውን ጊዜ ችግሩ ሥር ከሰደደና ከተባባሰ በኋላ ነው። የአንዲት ብራዚላዊት ወጣት ሁኔታን እንመልከት። “የአልኮል መጠጦችን አዘውትራ ትጠጣ ነበር” ትላለች እህቷ ሬጂና። * “ቤተሰቡ ይህ ሁኔታ ያን ያህል ጉዳት ላይ ይጥላታል ብሎ አስቦ አያውቅም። ይሁን እንጂ በዚህ ልማዷ ምክንያት ከወንድ ጓደኞቿ ጋር አደገኛ ዕፆችን መሞካከር ጀመረች። ወላጆቼ የምታደርስብንን ችግር በጣም አቅልለው በመመልከታቸው ሁኔታዋ ከቁጥጥር ውጭ ሆነ። ብዙ ጊዜ ከቤት ትጠፋ ነበር። ፖሊሶች ሞታ የተገኘች ሴት በሚያጋጥማቸው ጊዜ ሁሉ ወደ አባቴ ይደውሉና እሷ አለመሆኗን ያጣሩ ነበር። ይህም በቤተሰቤ ላይ ከፍተኛ ጭንቀት አስከትሏል።”
የዓለም ጤና ድርጅት ወጣቶችን የዕፅ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ሊገፋፉ የሚችሉ አምስት መሠረታዊ ምክንያቶችን አቅርቧል።
(1) ትልቅ ሰው እንደሆኑ እንዲሰማቸውና በራሳቸው ውሳኔ መመራት ይፈልጋሉ።
(2) በጓደኞቻቸው ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ይፈልጋሉ።
(3) ዘና ማለትና ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው ይፈልጋሉ።
(4) ለማመፅና አደገኛ ለሆኑ ሁኔታዎች ራሳቸውን ማጋለጥ ይፈልጋሉ።
(5) የማወቅ ጉጉታቸውን ለማርካት ይፈልጋሉ።
በተጨማሪም የአደገኛ ዕፆች እንደ ልብ መገኘትና የእኩዮች ተጽእኖ አንድ ወጣት በዚህ የጥፋት ጎዳና የመቀጠል ዕድሉን ከፍ ያደርጉታል። ሉዊዝ አንቶኒዮ የተባለ አንድ ብራዚላዊ ወጣት “ወላጆቼ ስለ ዕፅ አንዳችም ነገር ነግረውኝ አያውቁም። በትምህርት ቤት መምህራን ስለ ችግሩ ጠቀስ ያድርጉ እንጂ በዝርዝር አላስረዱንም” ብሏል። አሥራ አራት ዓመት እንደሞላው በትምህርት ቤት ጓደኞቹ ገፋፊነት ዕፅ መውሰድ ጀመረ። ለመተው በሞከረ ጊዜ ግን ዕፅ የሚያመጡለት “ጓደኞቹ” በጩቤ በማስፈራራት እንዳያቆም አስገደዱት።
የራስህ ልጆች እንዲህ ላለው አደጋ ይጋለጡ ይሆናል ብለህ አስበህ ታውቃለህ? ከዕፅ ሱሰኝነት እንዲጠበቁ ለመርዳት ምን ያደረግኸው ነገር አለ? የሚቀጥለው ርዕስ ወላጆች ልጆቻቸውን ሊጠብቁ ስለሚችሉባቸው አንዳንድ መንገዶች ያብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.9 አንዳንዶቹ ስሞች ተለውጠዋል።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“አደገኛ ዕፆች የወንጀል መቀፍቀፊያ በመሆን፣ እንደ ኤድስ ያሉትን በሽታዎች በማዛመትና ወጣቶቻችንንና የወደፊት ሕልውናቸውን በመግደል ማኅበረሰባችንን እያፈራረሱት ነው”—ኮፊ አናን የተመድ ዋና ጸሐፊ
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕሎቹ ምንጮች]
© ቬጃ፣ ሚያዝያ 27, 1998 እትም