የማደጎ ልጅ መሆን የሚያስከትላቸውን ፈታኝ ሁኔታዎች መወጣት የምችለው እንዴት ነው?
የወጣቶች ጥያቄ . . .
የማደጎ ልጅ መሆን የሚያስከትላቸውን ፈታኝ ሁኔታዎች መወጣት የምችለው እንዴት ነው?
“ስለ ወላጆቼ ምንም የማውቀው ነገር የለም፤ ይህም በጣም ያበሳጨኛል።”—የ16 ዓመቷ ባርባራ
“የት እንደተወለድኩ ወይም ወላጆቼ እነማን እንደሆኑ ምንም ፍንጭ የለኝም። አንዳንድ ጊዜ ማታ ማታ ስለዚህ ጉዳይ ሳስብ አድራለሁ።”—የ9 ዓመቱ ማት
“ከአሳዳጊ ወላጆቼ ጋር ስጋጭ ምናልባት ‘እውነተኛ’ ወላጆቼ በተሻለ ሁኔታ ስሜቴን ይረዱልኝ ይሆን ብዬ አስባለሁ። እንደዚህ ማሰቤ በጣም ይጸጽተኛል፤ ይህን ፈጽሞ ነግሬያቸው አላውቅም።”—የ16 ዓመቱ ኪንታና
የማደጎ ልጅ መሆን ራሱን የቻለ ፈታኝ ሁኔታ እንደሚኖረው ጥርጥር የለውም። በርካታ ወጣቶች ከላይ እንደተገለጸው ዓይነት ጭንቀት ይሰማቸዋል። ብዙዎቹ እውነተኛ ወላጆቼን ባፈላልጋቸው ይሻል ይሆን? ከእነርሱ ጋር ብኖር ኖሮ ይበልጥ ደስተኛ እሆን ነበር? እያሉ ያስባሉ። የሚገጥሟቸው ፈታኝ ሁኔታዎች ግን እነዚህ ብቻ አይደሉም።
በዚህ ዓምድ በወጣው በፊተኛው ርዕስ ላይ የማደጎ ልጅ የሆኑ አንዳንድ ወጣቶች ስለ ራሳቸው ከሚኖሯቸው አሉታዊ አመለካከቶች ጥቂቶቹን ተመልክተን ነበር። * የማደጎ ልጆች በሕይወታቸው ደስተኛ መሆን ከፈለጉ እንደዚህ ዓይነት ተስፋ አስቆራጭ ሐሳቦችን መዋጋት ያስፈልጋቸዋል። ሆኖም ሊያጋጥሙህ የሚችሉ ሌሎች ፈታኝ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? እነዚህን ሁኔታዎች ለመቋቋምስ ተግባራዊ እርምጃዎች ልትወስድ የምትችለው እንዴት ነው?
እንደ “ወላጆቼ” አድርጌ ማየት ይኖርብኛል?
የ13 ዓመቱ ጄክ ስለ ወላጅ እናቱ በጣም ያስብ እንደነበረ ተናግሯል። ይህም ከአሳዳጊ ወላጆቹ ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ አንዳንድ ችግሮች አስከትሎበታል። “አንቺ እኮ እናቴ አይደለሽም። ለምን እንደዚህ ትመቺኛለሽ?” እላት ነበር በማለት ያስታውሳል።
ከዚህ መመልከት እንደምትችለው ጄክ “እናቴ” ማን ናት? ለሚለው አሳሳቢ ጥያቄ መልስ ማግኘት አስፈልጎት ነበር። የማደጎ ልጅ ከሆንህ አንተም ተመሳሳይ ጥያቄ ይኖርህ ይሆናል። በተለይ ደግሞ እውነተኛ ወላጆችህ ከአሳዳጊ ወላጆችህ በተሻለ መንገድ ሊንከባከቡህ እንደሚችሉ የምታስብ ከሆነ እንደዚህ ዓይነት ጥያቄ ማንሳትህ አይቀርም። ይሁን እንጂ መውለድ ብቻውን “ወላጅ” ያሰኛልን?
የጄክ አሳዳጊ እናት እንደዚህ አልተሰማትም። ጄክ እንዲህ ይላል:- “እሷም ‘አንተ የፈለግኸውን ብትልም እናትህ ነኝ። ባልወልድህም እንኳ እናትህ ነኝ’ ትለኝ ነበር።” ሰዎች አንድን ልጅ ወደ ቤታቸው አምጥተው መጠለያና ምግብ ለመስጠት እንዲሁም ለማሳደግ ኃላፊነት መውሰዳቸው ከዚያም የልጁን ፍላጎት ማሟላታቸው በእርግጥም “ወላጆች” ያስብላቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) በምትኖርበት አገር ያሉት የሕግ አካላትም አሳዳጊዎችህን እንደ ወላጆችህ አድርገው እንደሚመለከቷቸው ምንም ጥርጥር የለውም። በአምላክስ ዘንድ የሚታዩት እንዴት ነው?
ኢየሱስ ክርስቶስ የማደጎ ልጅ ሆኖ ስላሳለፈው ሕይወት የሚገልጸውን በሰፊው የሚታወቀውን ታሪክ ተመልከት። አናጺ የነበረው ዮሴፍ ኢየሱስን ባይወልደውም እንኳ እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ አሳድጎታል። (ማቴዎስ 1:24, 25) ኢየሱስ እያደገ ሲሄድ በዮሴፍ ሥልጣን ላይ ዓምጿልን? በፍጹም፤ ኢየሱስ አሳዳጊ አባቱን መታዘዙ የአምላክ ፈቃድ መሆኑን ተገንዝቧል። ይሖዋ ለእስራኤላውያን ልጆች የሰጠውን ሕግ ኢየሱስ በሚገባ ያውቅ ነበር። ሕጉ ምን ይላል?
አባትህንና እናትህን አክብር
ቅዱሳን ጽሑፎች ለልጆች “አባትህንና እናትህን አክብር” የሚል ምክር ይሰጣሉ። (ዘዳግም 5:16) “አክብር” የሚለው ቃል አብዛኛውን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት ከፍ አድርጎ መመልከትንና አሳቢነት ማሳየትን ለማመልከት ነው። ለአሳዳጊ ወላጆችህ ደግነት በማሳየት፣ ቦታቸውን በመጠበቅ፣ የሚሰጡህን ሐሳብ በማዳመጥና ምክንያታዊ እስከሆነ ድረስ ማንኛውንም የሚጠይቁህን ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ በመሆን እንዲህ ዓይነት አክብሮት ልታሳያቸው ትችላለህ።
ይሁን እንጂ አሳዳጊ ወላጆችህ ምክንያታዊ እንዳልሆኑ በሚሰማህ ጊዜ ምን ብታደርግ ይሻላል? እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሊያጋጥምህ እንደሚችል የታወቀ ነው። እውነተኛ ወላጆችም ሆኑ አሳዳጊ ወላጆች ፍጹማን አይደሉም። ጉድለቶቻቸውን ስለምትመለከት ለእነርሱ መታዘዝ ይከብድህ ይሆናል። እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠር የማደጎ ልጅ እንደሆንህ በማሰብ አንዳንድ ጊዜ ለእነርሱ መታዘዝ እንደሌለብህ ቢሰማህ የሚያስገርም አይሆንም። ሆኖም ይህ ትክክለኛ አመለካከት ነውን?
የኢየሱስን ሁኔታ ማሰብህ ሊረዳህ ይችላል። እርሱ ፍጹም እንደነበረ አስታውስ። (ዕብራውያን 4:15፤ 1 ጴጥሮስ 2:22) ሆኖም አሳዳጊ አባቱም ሆነ ወላጅ እናቱ ፍጹማን አልነበሩም። በመሆኑም ኢየሱስ ወላጆቹ ስሕተት ሲሠሩ የተመለከተባቸው ጊዜያት እንደሚኖሩ አያጠራጥርም። ፍጽምና የሚጎድለውን የዮሴፍን የራስነት አመራር ወይም ጉድለት ያለበት ቢሆንም ማርያም በእናትነቷ የምትሰጠውን መመሪያ ለመቀበል አሻፈረኝ ብሎ ይሆን? በፍጹም። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ እያደገ ሲሄድ ለወላጆቹ ‘ይታዘዝላቸው’ እንደነበረ ይናገራል።—ሉቃስ 2:51
በአንተና በአሳዳጊ ወላጆችህ መካከል የአመለካከት ልዩነት ሲፈጠር የተሳሳቱት እነርሱ እንደሆኑ በእርግጠኝነት ይሰማህ ይሆናል። ሆኖም አንተ ራስህ ፍጹም እንዳልሆንህ መቀበል ይኖርብሃል። በዚህም ምክንያት ምንጊዜም ቢሆን የተሳሳትከው አንተ ልትሆን የምትችልበት አጋጣሚ አለ። ያም ሆነ ይህ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ከሁሉ የተሻለ አይሆንም? (1 ጴጥሮስ 2:21) እንደዚህ ማድረግህ ታዛዥነት እንድታሳይ ይረዳሃል። ይሁን እንጂ ወላጆችህን እንድትታዘዝ የሚረዳህ ከዚህ የላቀ ምክንያት አለ።
መጽሐፍ ቅዱስ “ልጆች ሆይ፣ ይህ ለጌታ ደስ የሚያሰኝ ነውና በሁሉ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ” ይላል። (ቆላስይስ 3:20) አዎን፣ ታዛዥ መሆንህ በሰማይ የሚኖረውን አባትህን ያስደስተዋል። (ምሳሌ 27:11) እንዲሁም አንተም ደስተኛ እንድትሆን ስለሚሻ ታዛዥነትን እንድትማር ይፈልጋል። ቃሉ ወጣቶች ታዛዥ እንዲሆኑ የሚያበረታታ ከመሆኑም በላይ እንደዚህ ማድረግህ “መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም” እንደሚያደርግ ተስፋ ሰጥቷል።—ኤፌሶን 6:2, 3
ከአሳዳጊ ወላጆችህ ጋር ያለህን ዝምድና ማጠናከር
ከአሳዳጊ ወላጆችህ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት አክብሮትና ታዛዥነት ከማሳየት የበለጠ ነገርን ይጨምራል። በመካከላችሁ ጥሩ ቅርርብና ፍቅር እንዲሰፍን እንደምትፈልግ የታወቀ ነው። አሳዳጊ ወላጆችህ እንዲህ ዓይነት መንፈስ እንዲሰፍን የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። ሆኖም አንተም ጠቃሚ ድርሻ ልታበረክት ትችላለህ። እንዴት?
በመጀመሪያ ከአሳዳጊ ወላጆችህ ጋር ይበልጥ ለመቀራረብ የሚያስችሉህን መንገዶች ፈልግ። ስለ አስተዳደጋቸው፣ ስላሳለፉት ሕይወትና ስለሚወዷቸው ነገሮች ጠይቃቸው። ምሳሌ 20:5) በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አስታዋሽ ሳያስፈልግህ አንዳንድ የቤት ውስጥ ሥራዎች በመሥራት ጠቃሚ የሆነ አስተዋጽኦ ማበርከት የምትችልባቸውን መንገዶች ፈልግ።
የሚያስጨንቅህን ጉዳይ በተመለከተ ምክር ጠይቃቸው፤ ለዚህም ዘና የሚሉበትንና በደንብ ማዳመጥ የሚችሉበትን ጊዜ ምረጥ። (እውነተኛ ወላጆችህን በተመለከተስ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? እነርሱን ለማግኘት ከፈለግህ ወይም ደግሞ እነርሱ አንተን ለማግኘት ከፈለጉ ይህ ከአሳዳጊ ወላጆችህ ጋር ያለህን ዝምድና የግድ ያበላሻል ማለት ነውን? ቀደም ባሉት ዓመታት ለልጆች አሳዳጊ የሚያፈላልጉ ድርጅቶች ወላጆች ጉዲፈቻ የሰጡትን ልጃቸውን ለማግኘት የሚያስችላቸውን መረጃ ለመስጠት በአብዛኛው ፈቃደኛ አይሆኑም ነበር። እንዲሁም ጉዲፈቻ የተሰጡት ልጆች ወላጆቻቸውን ለማግኘት በሚፈልጉበት ጊዜ ተመሳሳይ ችግር ያጋጥማቸዋል። ዛሬ በአንዳንድ አገሮች ያሉት ሕጎች ያን ያህል ጥብቅ አይደሉም። በርካታ የማደጎ ልጆችም ፈጽሞ ከማያስታውሷቸው እውነተኛ ወላጆቻቸው ጋር መገናኘት ችለዋል። እርግጥ ነው፣ አንተ በምትኖርበት አገር ሕጉ የተለየ ሊሆን ይችላል።
ያም ሆነ ይህ እውነተኛ ወላጆችህን ለመፈለግ ወይም ላለመፈለግ የምታደርገው ውሳኔ ለአንተው የተተወ ከመሆኑም በላይ ቀላል ውሳኔ ላይሆን ይችላል። የማደጎ ልጆች በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያየ አመለካከት አላቸው። አንዳንዶች ወላጆቻቸውን ለማግኘት ይጓጓሉ፤ ሌሎች ደግሞ ከወላጆቻቸው ጋር ላለመገናኘት ወስነዋል። ሆኖም በርካታ የማደጎ ልጆች ከአሳዳጊ ወላጆቻቸው ጋር ያላቸው ጠንካራ ዝምድና ሳይበላሽ ከእውነተኛ ወላጆቻቸው ጋር መገናኘት እንደቻሉ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።
አሳዳጊ ወላጆችህና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ የጎለመሱ ወዳጆችህ ምክር እንዲሰጡህ ጠይቅ። (ምሳሌ 15:22) ያሉህን አማራጮች በጥንቃቄ አመዛዝን እንዲሁም ማንኛውንም ዓይነት እርምጃ ለመውሰድ አትቸኩል። ምሳሌ 14:15 “ብልህ . . . አካሄዱን ይመለከታል” ይላል።
ከእውነተኛ ወላጆችህ ጋር ለመገናኘት ከወሰንህ ለአሳዳጊ ወላጆችህ ያለህ ፍቅርና አክብሮት እንደማይቀንስ አረጋግጥላቸው። እንደዚህ ካደረግህ የወለዱህንና ከረጅም ጊዜ በፊት ጉዲፈቻ የሰጡህን ወላጆችህን ቀስ በቀስ እያወቅሃቸው ስትሄድ ካሳደጉህና ካስተማሩህ ወላጆችህ ጋር ያለህ የጠበቀ ግንኙነት እንደተጠበቀ ይቀጥላል።
በሰማይ ከሚኖረው አባትህ ጋር ያለህን ዝምድና አጠናክር
ጉዲፈቻ የተሰጡ ብዙ ወጣቶች ብቻዬን እቀር ይሆን የሚል ፍርሃት ይሰማቸዋል። በአንድ ወቅት እውነተኛ ቤተሰቦቻቸውን እንዳጡ ሁሉ አሁንም አሳዳጊ ቤተሰቦቻቸውን እንዳያጡ ይሰጋሉ። እንደዚህ ማሰባቸው የሚያስገርም አይሆንም። ሆኖም “ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል እንጂ በፍቅር ፍርሃት የለም” የሚሉትን ጥበብ ያዘሉ ቃላት አስታውስ። (1 ዮሐንስ 4:18) የምወዳቸውን ሰዎች አጣ ይሆን የሚል ፍርሃት እንዲቆጣጠርህ አትፍቀድ። ከዚህ ይልቅ በቤተሰብህ ውስጥ ያሉትን ጨምሮ ለሰዎች ሁሉ ያለህን ፍቅር ለማሳደግ ጥረት አድርግ። ከሁሉ በላይ ደግሞ በሰማይ ለሚኖረው አባትህ ለይሖዋ አምላክ የጠበቀ ፍቅር አዳብር። እርሱ ሙሉ በሙሉ እምነት የሚጣልበት በመሆኑ ታማኝ ልጆቹን ፈጽሞ አይተዋቸውም። ፍርሃትህን እንድታሸንፍ ሊረዳህ ይችላል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7
የማደጎ ልጅ የሆነችው ካትሪና መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቧ ወደ ይሖዋ ለመቅረብና ደስተኛና አርኪ የሆነ ሕይወት ለመምራት እንድትችል በጣም እንደረዳት ትናገራለች። “በሰማይ የሚኖረው አባታችን ስሜታችንን ስለሚረዳ” ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና መመስረታችን “በጣም አስፈላጊ” እንደሆነ ትናገራለች። ካትሪና በጣም የምትወደው ጥቅስ መዝሙር 27:10 ሲሆን ጥቅሱም “አባቴና እናቴ ትተውኛልና፣ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ” ይላል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.7 በግንቦት 2003 የንቁ! እትም ላይ የወጣውን “ጉዲፈቻ የተሰጠሁት ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከአሳዳጊ ወላጆችህ ጋር ለመቀራረብ የሚያስችሉህን መንገዶች ፈልግ