በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጋሊልዮና የቤተ ክርስቲያን ግጭት

የጋሊልዮና የቤተ ክርስቲያን ግጭት

የጋሊልዮና የቤተ ክርስቲያን ግጭት

ኢጣሊያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ዕለቱ ሰኔ 22, 1633 ነው። ዕድሜው በመግፋቱ ምክንያት አቅሙ የተዳከመ አንድ አረጋዊ መናፍቃንን ለመዳኘት በተቋቋመ የሮማ ሸንጎ ፊት ተንበርክኳል። ሰውዬው ሳይንቲስትና በዘመኑ ከነበሩት ዝነኛ ሊቃውንት መካከል አንዱ ነው። የያዘው ሳይንሳዊ እምነት ከበርካታ ዓመታት ጥናትና ምርምር በኋላ ያገኘው ነው። አሁን ግን ሕይወቱን ማዳን ከፈለገ እውነት እንደሆነ የሚያውቀውን ነገር መካድ ሊኖርበት ነው።

ይህ ሰው ጋሊልዮ ጋሊሌ ይባላል። ብዙዎች የጋሊልዮ ክስ ብለው የሚጠሩት ይህ ጉዳይ ዛሬ 370 ዓመታት ካለፉ በኋላ እንኳን ጋብ ያላለ ጥርጣሬ፣ ውዝግብና ጥያቄ አስነስቷል። ይህ ክስ በሃይማኖትና በሳይንስ ታሪክ ላይ የማይድን ጠባሳ ጥሎ አልፏል። ይህን ያህል ትልቅ ግምት የተሰጠው ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው? የጋሊልዮ ክስ በዚህ በዘመናችን ዳግመኛ ብዙዎችን የሚያነጋግር ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው? አንድ ጸሐፊ እንዳሉት በእርግጥ “በሳይንስና በሃይማኖት መካከል ትልቅ ገደል እንዲፈጠር” ያደረገ ነውን?

ጋሊልዮ በብዙዎች ዘንድ “የዘመናዊ ሳይንስ አባት” እንደሆነ ይቆጠራል። የሂሣብ፣ የሥነ ፈለክና የፊዚክስ ሊቅ ነበር። ጋሊልዮ የጠፈር አካላትን አቅርቦ በሚያሳይ መነጽር ምርምር ያደረገ የመጀመሪያው ሰው ሲሆን የተመለከተውን ነገርም በዘመኑ እጅግ አወዛጋቢ የሆነውን አስተሳሰብ ለመደገፍ ተጠቅሞበታል። ይህም ምድር በፀሐይ ዙሪያ ስለምትዞር ዓለማችን የጽንፈ ዓለሙ እምብርት አይደለችም የሚለው አስተሳሰብ ነበር። ጋሊልዮ አንዳንድ ጊዜ መላ ምቶችን በሙከራ የማረጋገጥ አሠራር አባት እንደሆነ መነገሩ የሚያስደንቅ አይደለም።

ከጋሊልዮ ግኝቶችና ፈጠራዎች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? የሥነ ፈለክ ተመራማሪ እንደመሆኑ ጁፒተር ጨረቃዎች እንዳሏት፣ ፍኖተ ሐሊብ (Milky Way) የብዙ ከዋክብት ስብስብ መሆኑን፣ በጨረቃ ላይ ተራሮች መኖራቸውን፣ ቬነስ እንደ ጨረቃ አንሳና ተልቃ የምትታይበት ጊዜ እንዳላትና ሌሎች ተጨማሪ ነገሮችን አውቋል። የፊዚክስ ሊቅ በመሆኑም የግድግዳ ሰዓት ዘንግ ውዝዋዜን እና ከላይ ወደ ታች የሚወድቅ ነገር የሚገዛበትን ሕግ አጥንቷል። ለስሌት ሥራ የሚያገለግል የጂኦሜትሪ ኮምፓስንና ሌሎች መሣሪያዎችን ፈልስፏል። ከሆላንድ ያገኘውን መረጃ በመጠቀም የጽንፈ ዓለምን መስኮት የከፈተለትን አቅርቦ የሚያሳይ ቴሌስኮፕ የሚባል መነጽር ሠርቷል።

ከቤተ ክህነት ባለ ሥልጣናት ጋር ባጋጠመው ረዥም ጊዜ የፈጀ ግጭት ምክንያት ግን የዚህ ታላቅ ሳይንቲስት የሥራ እድገት ባጭሩ ተቀጭቶ ወደ ጋሊልዮ ክስ አመራ። ይህ ግጭት የጀመረው እንዴትና ለምንድን ነው?

ከሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር የተደረገ ግጭት

ጋሊልዮ ምድር የምትዞረው በፀሐይ ዙሪያ ነው እንጂ ፀሐይ ምድርን አትዞርም የሚለውን የኮፐርኒከስ ንድፈ ሐሳብ የተቀበለው ከ16ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ጀምሮ ነበር። ይህ ንድፈ ሐሳብ ሄልዮሴንትሪክ ወይም “የፀሐይ ማዕከልነት” የሚል ስያሜም ተሰጥቶታል። ጋሊልዮ በ1610 አቅርቦ የሚያሳይ መነጽሩን በመጠቀም ከዚህ በፊት ታይተው የማያውቁ የጠፈር አካላትን ካገኘ በኋላ የፀሐይ ማዕከልነትን ንድፈ ሐሳብ የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዳገኘ እርግጠኛ ሆነ።

ግራንዴ ዲትስዮናሪዮ ኤንቺክሎፔድኮ ዩ ቲ ኢ ቲ እንደሚለው ጋሊልዮ እነዚህን ግኝቶች በማግኘት ብቻ ተወስኖ ለመቅረት አልፈለገም። የኮፐርኒከስ ንድፈ ሐሳብ ትክክለኛ መሆኑን “የዘመኑን ከፍተኛ ባለ ሥልጣናት (መሣፍንቱንና ጳጳሳቱን)” ለማሳመን ፈለገ። ተደማጭነት ባላቸው ወዳጆቹ አማካኝነት የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቃውሞ ማርገብና እንዲያውም ድጋፏን ማግኘት እንደሚችል ሆኖ ተሰማው።

በ1611 ጋሊልዮ ወደ ሮም ሄደና ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያን ባለ ሥልጣናት ጋር ተገናኘ። አቅርቦ በሚያሳየው መነጽሩ በመጠቀም የሥነ ፈለክ ግኝቶቹን አሳያቸው። ይሁን እንጂ ነገሮች እሱ እንደተመኘው ሆነው አላገኛቸውም። በ1616 ጋሊልዮ ባለ ሥልጣናት በዓይነ ቁራኛ የሚከታተሉት ሰው ሆነ።

የሮም የመናፍቃን ፍርድ ቤት የፀሐይ ማዕከልነትን ንድፈ ሐሳብ “የቅዱሳን ጽሑፎችን ዓረፍተ ነገሮች፣ የተለመዱ ማብራሪያዎች፣ የቅዱሳን አባቶችንና የሥነ መለኮት ዶክተሮችን ግንዛቤ በብዙ ቦታዎች የሚቃረን ከመሆኑም በላይ ለማመን የሚያዳግትና መናፍቃዊ ትንታኔ ነው” ብሎታል።

ጋሊልዮ የዘመኑ ታላቅ የካቶሊክ ሃይማኖት ሊቅና “የመናፍቃን መዶሻ” የሚል ዝና ካተረፉት ከካርዲናል ሮበርት ቤሎርሚን ጋር ተገናኘ። ቤሎርሚን ጋሊልዮ ይህን የፀሐይ ማዕከልነትን አስተሳሰብ ማስፋፋት እንዲያቆም አጥብቀው እንደመከሩት ይነገራል።

መናፍቃንን በሚዳኘው ሸንጎ ፊት

ጋሊልዮ የኮፐርኒከስን ንድፈ ሐሳብ እንደቀድሞው በይፋ ከማስተጋባት ይቆጠብ እንጂ ጨርሶ አልካደውም። ከአሥራ ስድስት ዓመታት በኋላ ማለትም በ1633 ጋሊልዮ መናፍቃንን በሚዳኘው ሸንጎ ፊት ቀረበ። በዚህ ጊዜ ካርዲናል ቤሎርሚን በሕይወት የሌሉ ቢሆንም ከዚህ በፊት እርሱን የመደገፍ አዝማሚያ የነበራቸው ጳጳስ ኡርባን ስምንተኛ ዋነኛ የጋሊልዮ ተቃዋሚ ሆነው ቀረቡ። ይህን የፍርድ ሂደት በርካታ ጸሐፊዎች በሶቅራጥስና በኢየሱስ ላይ ከተፈጸመው ፍርደ ገምድልነት ጋር የሚተካከልና በጥንቱ ዓለም ፍትሕ የለሽነት የታየበት አጋጣሚ እንደሆነ ገልጸዋል።

ለዚህ ክስ መቀስቀስ ምክንያት የሆነው ምን ነበር? ጋሊልዮ ሁለቱን ዋነኛ የዓለም ሥርዓቶች በሚመለከት የተደረገ ውይይት የተባለ መጽሐፍ ጽፎ ነበር። የፀሐይን ማዕከልነት ንድፈ ሐሳብ የሚደግፍ መጽሐፍ ነበር። ጸሐፊው በ1632 ሸንጎው ፊት እንዲቀርብ ታዘዘ። የ70 ዓመቱ አዛውንት ጋሊልዮ ታምሞ ስለነበር ሳይቀርብ ዘገየ። በግድ ታስሮ እንደሚቀርብ ከተነገረው በኋላ ግን በሚቀጥለው ዓመት ወደ ሮም ተጓዘ። በሊቀ ጳጳሱ ትእዛዝ ምርመራ ተደረገበትና እንደሚሠቃይም ተዛተበት።

ይህ አቅመ ቢስና ሕመምተኛ ሽማግሌ እንዲሠቃይ ተደርጎ ይሆን? የሚለው ጥያቄ ብዙ አወዛግቧል። የፍርድ መዝገቡ እንደሚያሳየው ጋሊልዮ “ከባድ ምርመራ” ተደርጎበት ነበር። የኢጣሊያ ሕግ ታሪክ ጸሐፊ የሆኑት ኢታሎ ሚራው እንደሚሉት “ከባድ ምርመራ” የሚለው ሐረግ ማሠቃየትን የሚያመለክት የዘመኑ አነጋገር ነው። ከዚህ አተረጓጎም ጋር በርካታ ምሁራን ይስማማሉ።

ያም ሆነ ይህ ጋሊልዮ ሰኔ 22 ቀን 1633 በአንድ አነስተኛ አዳራሽ ውስጥ መናፍቃንን በሚዳኘው ሸንጎ አባላት ፊት ቀርቦ ፍርድ ተሰጠው። “ቅዱሳንንና መለኮታዊ ጽሑፎችን በመቃወም ፀሐይ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ አትንቀሳቀስም፣ የምትንቀሳቀሰው ምድር ስትሆን የዓለማት ማዕከልም አይደለችም የሚል የሐሰት መሠረተ ትምህርት በመከተሉና በማመኑ” ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

ጋሊልዮ በሰማዕትነት የመሞት ፍላጎት ስላልነበረው እምነቱን ለመካድ ተገደደ። የተላለፈበት ፍርድ ከተነበበ በኋላ ይህ አረጋዊ ሳይንቲስት መጸጸቱን የሚያሳይ ልብስ ለብሶና ተንበርክኮ “ቀደም ሲል የተጠቀሱትን ስህተቶችና የመናፍቅነት ትምህርቶች [የኮፐርኒከስን ንድፈ ሐሳብ] እንዲሁም በአጠቃላይ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የማትቀበላቸውን ስህተቶች፣ ኑፋቄዎች ወይም ትምህርቶች በሙሉ ክጃለሁ፣ አወግዛለሁ፣ እጸየፋለሁ” በማለት ተማጸነ።

ጠንካራ ማስረጃ አልተገኘለትም እንጂ ጋሊልዮ የክህደት ቃሉን ከተናገረ በኋላ የቆመበትን መሬት በእግሩ መትቶ “ቢሆንም ትንቀሳቀሳለች!” እንዳለ የሚገልጹ አፈ ታሪኮች አሉ። ተንታኞች እንደሚሉት የራሱን ግኝቶች መልሶ መካዱ ያሳደረበት ውርደት እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ሲያሠቃየው ቆይቷል። እስር ቤት እንዲገባ ቢፈረድበትም ፍርዱ ተለውጦ ዕድሜ ልኩን በገዛ ቤቱ በቁም እስር እንዲኖር ተበይኖበታል። ዓይኑም በመታወሩ ከሰው ተገልሎ ኖረ።

የሳይንስና የሃይማኖት ግጭት?

ብዙ ሰዎች ሳይንስና ሃይማኖት ፈጽሞ ሊታረቁ እንደማይችሉ የጋሊልዮ ምሳሌ ያረጋግጣል የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። በዚህም የተነሣ ባለፉት መቶ ዘመናት የጋሊልዮ ክስ ብዙ ሰዎችን ከሃይማኖት እንዲርቁ አድርጓል። ሃይማኖት በባሕርዩ ለሳይንሳዊ እድገት ፀር ነው ወደሚል መደምደሚያ እንዲያመሩ አድርጓቸዋል። ታዲያ ይህ እውነት ነው?

ፖፕ ኡርባን ስምንተኛና የሮም የመናፍቃን ፍርድ ቤት ሃይማኖታዊ ሊቃውንት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይጋጫል በማለት የኮፐርኒከስን ንድፈ ሐሳብ አውግዘዋል። የጋሊልዮ ጠላቶች የጠቀሱት “ፀሐይ ትቁም” የሚለውን የኢያሱን ቃል ሲሆን ይህንን ጥቅስ ቃል በቃል መቀበል አለብን የሚል አቋም ነበራቸው። (ኢያሱ 10:​12) ይሁን እንጂ እውነት መጽሐፍ ቅዱስ ከኮፐርኒከስ ንድፈ ሐሳብ ጋር ይጋጫልን? በፍጹም።

ግጭቱ የተፈጠረው በሳይንስና ትክክል ባልሆነ የቅዱሳን ጽሑፎች አተረጓጎም መካከል ነው። ጋሊልዮም ሁኔታውን የተመለከተው ከዚህ አንጻር ነበር። ለአንድ ተማሪው እንደሚከተለው በማለት ጽፎ ነበር:- “ቅዱስ ጽሑፉ ሊሳሳት አይቻል እንጂ ተርጓሚዎቹና ተንታኞቹ ግን በተለያዩ መንገዶች ይሳሳታሉ። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለውን ስህተት የሚፈጽሙት ቃል በቃል ለመረዳት በሚሞክሩበት ጊዜ ነው።” ማንኛውም መጽሐፍ ቅዱስን ከልቡ የሚያጠና ሰው ከዚህ ጋር ለመስማማት ይገደዳል። *

ጋሊልዮ በዚህ ብቻ አላቆመም። ሁለቱ መጻሕፍት ማለትም መጽሐፍ ቅዱስና የተፈጥሮ መጽሐፍ በአንድ ደራሲ የተዘጋጁ በመሆናቸው እርስ በርሳቸው ሊጋጩ አይችሉም ብሏል። አክሎም “ሁሉም ተርጓሚዎች በመለኮት ተመርተው ይናገራሉ” ብሎ በእርግጠኝነት ሊናገር የሚችል አንድም ሰው የለም ብሏል። የሮማ የመናፍቃን ሸንጎ ዳኞች ሳይንቲስቱን እንዲያወግዙ ያነሳሳቸው ይህ በቤተ ክርስቲያን አተረጓጎም ላይ የተሰነዘረው ትችት ሳይሆን አይቀርም። የሥነ መለኮት ትምህርት የሌለው አንድ ተራ ሰው የቤተ ክህነትን የመተርጎም ሥልጣን እንዴት ሊጋፋ ይችላል?

በርካታ ምሑራን የጋሊልዮን ክስ በማስረጃነት በመጥቀስ ቤተ ክርስቲያንና ሊቀ ጳጳሱ ፈጽሞ አይሳሳቱም የሚለውን መሠረተ ትምህርት ተጠራጥረዋል። ሃንስ ኩንግ የተባሉ የካቶሊክ እምነት ሊቅ “የጋሊልዮን መወገዝ ጨምሮ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ባለ ሥልጣናት በፈጸሟቸው በርካታና የማይካዱ ስህተቶች ምክንያት” ቤተ ክርስቲያንና ሊቀ ጳጳሱ ሊሳሳቱ አይችሉም የሚለው ቀኖና ትልቅ ጥያቄ ወድቆበታል ሲሉ ጽፈዋል።

በጋሊልዮ ላይ የተሰነዘረው ውንጀላ ተነስቷል?

ዳግማዊ ዮሐንስ ጳውሎስ በተመረጡ በዓመቱ ይኸውም በኅዳር 1979 “ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሰዎችና ድርጅቶች ታላቅ መከራ ደርሶበት ነበር” በማለት የጋሊልዮ አቋም እንደገና እንዲታይ እንደሚፈልጉ ተናገሩ። ከአሥራ ሦስት ዓመታት በኋላ ማለትም በ1992 በእኚሁ ሊቀ ጳጳስ የተሰየመ ኮሚሽን “በጋሊልዮ ዘመን የነበሩ አንዳንድ የሃይማኖት ሊቃውንት ስለ ግዑዙ ጽንፈ ዓለም በሚናገሩበት ጊዜ የቅዱሳን ጽሑፎችን ጥልቅና ምሳሌያዊ ትርጉም መረዳት አቅቷቸዋል” ብሏል።

እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የፀሐይ ማዕከልነት ንድፈ ሐሳብ የተተቸው በሃይማኖት ሊቃውንት ብቻ አልነበረም። በዚህ ጉዳይ ግንባር ቀደም ሚና የነበራቸው ጳጳስ ኡርባን ስምንተኛ ጋሊልዮ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለብዙ መቶ ዘመናት አጽንታ የያዘችውን ምድር የጽንፈ ዓለሙ ማዕከል ነች የሚለውን ትምህርት ከማዳከም እንዲርቅ አጥብቀው ነግረውታል። ይህ ትምህርት የመጣው ከመጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን ከግሪኩ ፈላስፋ ከአርስቶትል ነበር።

ዘመናዊው ኮሚሽን አድካሚ የሆነ ምርመራ ካደረገ በኋላ ሊቀ ጳጳሱ በጋሊልዮ ላይ የተላለፈውን ብያኔ “በችኮላ የተደረገ አሳዛኝ ውሳኔ ነበር” ብለዋል። ታዲያ ይህ ሳይንቲስት ከተከሰሰበት ወንጀል ነጻ እንዲሆን ተደርጓል ማለት ነውን? አንድ ጸሐፊ “ታሪክ የሚያወግዘው ጋሊልዮን ሳይሆን የቤተ ክርስቲያኒቱን ፍርድ ቤት ስለሆነ አንዳንዶች እንደሚሉት ጋሊልዮ ከተከሰሰበት ወንጀል ነጻ እንዲወጣ ተደርጓል ብለን ማሰብ አንችልም” ብለዋል። ሉዊጂ ፊርፖ የተባሉት ታሪክ ጸሐፊ “አሳዳጆች ያሳደዱትን ሰው ከወንጀል ነጻ ማድረግ አይችሉም” በማለት ተናግረዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ ‘በጨለማ ስፍራ የሚበራ መብራት’ ነው። (2 ጴጥሮስ 1:​19) ጋሊልዮ ይህ መጽሐፍ በተሳሳተ መንገድ እንዳይተረጎም ተሟግቷል። ቤተ ክርስቲያን ግን በተቃራኒው ለሰዎች ወግ ስትል መጽሐፍ ቅዱስን ሽራለች።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.24 ሐቀኛ የሆነ አንባቢ ፀሐይ በሰማይ ስለመቆሟ የሚናገረው መግለጫ ሁኔታው ሲከሰት የተመለከተ ሰው ከሰጠው ምሥክርነት አንጻር እንጂ ሳይንሳዊ ትንታኔ ለመስጠት የተነገረ አለመሆኑን መቀበል አያዳግተውም። የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎችም ቢሆኑ ብዙውን ጊዜ ስለ ፀሐይ፣ ስለ ፕላኔቶችና ስለ ከዋክብት መውጣትና መጥለቅ ይናገራሉ። እንዲህ ሲሉ ግን እነዚህ የጠፈር አካላት ቃል በቃል በመሬት ዙሪያ ይዞራሉ ማለታቸው ሳይሆን በሰማይ ላይ የሚንቀሳቀሱ እንደሚመስሉ ማመልከታቸው ነው።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የጋሊልዮ የሕይወት ታሪክ

የፍሎሬንቲን ተወላጅ ከሆነው አባቱ በ1564 በፒሳ ከተማ የተወለደው ጋሊልዮ በዚያች ከተማ በሚገኘው ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ተከታትሎ ነበር። በዚህ የት​ምህርት ዘርፍ ለመቀጠል እምብዛም ፍላጎት ስላልነበረው ትምህርቱን አቋርጦ የፊዚክስና የሒሳብ ጥናቱን ቀጠለ። በ1585 በምንም ዓይነት ትምህርት የምሥክር ወረቀት ሳያገኝ ወደ ቤተሰቦቹ ተመለሰ። ቢሆንም የዘመኑን ታላላቅ የሒሳብ ሊቃውንት አክብሮት አትርፎ ስለነበረ በፒሳ ዩኒቨርሲቲ የሒሳብ አስተማሪነት ሥራ ለማግኘት ቻለ። አባቱ ከሞተ በኋላ ያጋጠመው የኢኮኖሚ ችግር ወደ ፓዱዋ እንዲሄድ ቢያስገድደውም የተሻለ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ አገኘ። የከተማዋ ዩኒቨርሲቲ የሒሳብ ሊቀ መንበር ሆነ።

በፓዱዋ በኖረባቸው 18 ዓመታት ቁባቱ ከነበረች ቬኒሲያዊት ሴት ሦስት ልጆች ወልዷል። በ1610 ወደ ፍሎረንስ ተመልሶ የተሻለ የኢኮኖሚ ደረጃ በማግኘቱ ለምርምር ሥራው የበለጠ ጊዜ ለመስጠት ቻለ። ይህን ሲያደርግ ግን በቬኒሲያ ሪፑብሊክ ግዛት ውስጥ የነበረውን ነጻነት አጥቷል። ታላቁ የቱስካኒ መስፍን “የመጀመሪያው ፈላስፋና የሒሳብ ሊቅ” የሚል ማዕረግ ሰጠው። ጋሊልዮ በ1642 በመናፍቃን ፍርድ ቤት በተበየነበት የቁም እስር እንዳለ በፍሎረንስ ከተማ ሞተ።

[ምንጭ]

From the book The Library of Original Sources, Volume VI, 1915

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጋሊልዮ ምድር የአጽናፈ ዓለሙ ማዕከል አለመሆኗን ያረጋገጠበት መነጽር

[ምንጭ]

Scala/Art Resource, NY

[በገጽ 12 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የምድር ማዕከልነት (ጂኦሴንትሪክ)

የፀሐይ ማዕከልነት (ሄልዮሴንትሪክ)

[ምንጭ]

Background: © 1998 Visual Language

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የሥዕሎቹ ምንጮች]

Picture: From the book The Historian’s History of the World