በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለጎብኚዎች ክፍት ሆኖ የቆየ አንድ ቅርንጫፍ ቢሮ የብዙዎችን አድናቆት አተረፈ

ለጎብኚዎች ክፍት ሆኖ የቆየ አንድ ቅርንጫፍ ቢሮ የብዙዎችን አድናቆት አተረፈ

ለጎብኚዎች ክፍት ሆኖ የቆየ አንድ ቅርንጫፍ ቢሮ የብዙዎችን አድናቆት አተረፈ

በጀርመን የሚገኝ የንቁ! ዘጋቢ ያጠናቀረው

“በጣም ደስ ይላል! ሁሉም ነገር በጣም የሚያስደንቅ ነው!” “በጥሩ ሁኔታ ስለተቀበላችሁንና ስላስጎበኛችሁን እናመሰግናችኋለን። በጣም ደስ ብሎናል።” ብዙ ጎብኚዎች እነዚህን የመሳሰሉ የአድናቆት ቃላት እንዲናገሩ የገፋፋቸው ምን ነበር? በጀርመን በዜልተርስ-ታውነስ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ መቶኛ ዓመቱን ሲያከብር ከዓርብ ግንቦት 24 እስከ እሁድ ግንቦት 26, 2002 ለጎብኚዎች ክፍት ሆኖ ነበር። በዚህ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ከ1, 000 በላይ ፈቃደኛ ሠራተኞች ያገለግላሉ።

በቅርንጫፍ ቢሮው አቅራቢያ ያሉ የይሖዋ ምስክሮች ጉባኤዎች ጎብኚዎችን በመጋበዙ ልዩ ዘመቻ ከፍተኛ ተሳትፎ አድርገዋል። ከዚህ ልዩ በዓል በፊት በነበሩት ሁለት ሳምንታት 100, 000 የሚሆኑ መጋበዣ ወረቀቶች ለሰዎች ታድለዋል። ይህን የጉብኝት ፕሮግራም የሚገልጹ ማስታወቂያዎችም በጋዜጦችና በተለያዩ የራዲዮ ሥርጭቶች በሰፊው እንዲቀርቡ ተደርጓል። ለቅርንጫፍ ቢሮው ሥራ ዕቃ አቅራቢ ለነበሩ ነጋዴዎችና ቸርቻሪዎች፣ እንዲሁም ባለ ሥልጣኖች መጋበዣው በግል ታድሏቸዋል። በአጠቃላይ ከ7, 000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ይህን ግብዣ የተቀበሉ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ሰዎች ናቸው።

ጎብኚዎች ማተሚያውን፣ የመጽሐፍ መጠረዣውን፣ የጽሑፍ መላኪያ ክፍሉን፣ የተለያዩ የጥገና ክፍሎችንና የልብስ ንጽሕና መስጫውን እንዲሁም በአስተዳደር ሕንፃው ላይ የሚገኙ የተለያዩ ክፍሎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። የቀረቡት ኤግዚቢሽኖች የይሖዋ ምስክሮች በጀርመን ውስጥ በናዚና በኮሚኒስት አገዛዝ ሥር ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የነበራቸውን ጽኑ አቋም የሚያሳዩ ነበሩ። ይሖዋ የሚለውን መለኮታዊ ስም የያዙ ከ700 የሚበልጡ የተለያዩ መጽሐፍ ቅዱሶችም ለሕዝብ እይታ ቀርበው ነበር። ሁሉንም የአድናቆት መግለጫዎች በዚህ ርዕስ ላይ ደግመን ማቅረብ ባንችልም የተወሰኑትን እነሆ:-

“እዚህ ያሉት ሁሉ ተግባቢዎች ናቸው። ሁሉም ነገር በጣም ንጹሕና በሥርዓት የተቀመጠ ነው። ሰዎቹም ሆኑ በአካባቢው የሚታየው ነገር ውብና ማራኪ ነው። የእናንተን የወዳጅነት አቀራረብ በመጠኑም ቢሆን መኮረጅ እንችላለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን።”​—⁠አንድ አረጋዊ ባልና ሚስት።

“ላቀረባችሁልን ግሩም ምግብም ሆነ ላደረጋችሁልን አስደሳች መስተንግዶ ከልብ እናመሰግናለን። ሁሉንም ነገር ወድደነዋል፤ እንደገና ብንመጣ ደስ ይለናል። እዚህ ያሉት ሰዎች በጣም፣ በጣም ጥሩዎች ናቸው።”​—⁠የመስተዋት ቴክኖሎጂ ተማሪዎች በሐሳብ መስጫ መዝገቡ ላይ ያሰፈሩት አስተያየት።

“ስላደረጋችሁልን የሞቀ አቀባበል በጣም እናመሰግናለን። በጉብኝቱ በጣም በጣም ተደስተናል። በልብስ ንጽሕና መስጫ ክፍሎች ለሚሠሩት ምስጋናችን ይድረስ። ምክንያቱም እንደዚህ ያለ ንጹሕና ሥርዓታማ ቦታ አይተን አናውቅም።”​—⁠የሣሙናዎችና የእጥበት ዕቃዎች አምራች ኩባንያ ተወካይ በኢ ሜል የላከው መልእክት።

እንግዶችን ታስጎበኝ የነበረችው ኢቫ “መኝታ ቤቶቹን እያዞርኩ ሳስጎበኝ በእያንዳንዱ ጉብኝት ላይ ‘ጓዛችንን ጠቅልለን መጥተን ለመግባት ዝግጁዎች ነን!’ የሚሉኝ ጎብኚዎች ነበሩ” በማለት ገልጻለች።

በኤሌክትሪክ በሚሠራ ተሽከርካሪ ወንበር የምትንቀሳቀስ አንዲት የአካል ጉዳተኛ የቅርንጫፍ ቢሮውን ንድፍ በትኩረት እየተመለከተች ሳለች አንዲት ፈቃደኛ ሠራተኛ ልትረዳት የምትፈልገው ነገር እንዳለ ጠየቀቻት። ሴትዬዋ “አይ፣ ምንም አልፈልግም!” በማለት መለሰች። ግቢው ውስጥ ከገባች አምስት ሰዓት እንደሆናትና ከዚህ በኋላ ግን ቀጥ ብላ መቀመጥ እንደተሳናት ተናገረች። በመሠረቱ ሴትዬዋ የአልጋ ቁራኛ የነበረች ስትሆን አሁንም ሕመሙ እያሠቃያት ነው። ሆኖም “መቼም ቢሆን ቤቴ ሄጄ መተኛት እችላለሁ፤ ጉብኝቱን ግን ያለዛሬ አላገኘውም” ስትል ገልጻለች። አክላም “ሁሉም ነገር በጣም ደስ ይላል፤ ያልጎበኘሁት ምንም የለም!” ብላለች።

የአምስት ዓመቱ ጆርጅ ከሁሉም የወደደው ምኑን እንደሆነ ተጠይቆ ነበር። ግዙፍ በሆነው የማተሚያ መሣሪያ እንደተደሰተ ሲገልጽ “የወረቀት ጥቅልሎቹን በአንዱ ጫፍ ሲያስገቧቸው በሌላው ጫፍ ተጽፎባቸው ይወጣሉ! በጣም ያስገርማል!” በማለት ተናግሯል።

አንዲት እህት ያልጠበቀችው አስደሳች ተሞክሮ አጋጥሟታል። አንድ ጊዜ ብቻ በጉባኤ ስብሰባ ላይ የተገኘው የይሖዋ ምሥክር ያልሆነው ባሏ ቅዳሜ ዕለት አብሯት ሄዶ ጎብኝቶ ነበር። እሁድ ዕለት ሚስቱ ከጉባኤ ስብሰባ ስትመለስ ልብሱን ለባብሶ ዝግጁ ሆኖ ጠበቃት። “ምነው?” ብላ ስትጠይቀው “ትናንትና ሁሉንም ነገር ለማየት ጊዜ አልበቃኝም” በማለት መልስ ሰጣት። “ስለዚህ ተዘጋጂና ወደ ዜልተርስ እንሂድ። እንደገና በደንብ ላየው እፈልጋለሁ” አላት።

የመጽሐፍ ቅዱስ ኤግዚቢሽን በሚታይበት ቦታ ጥሩ አለባበስ ያላት በዕድሜ ጠና ያለች አንዲት ሴት ፈራ ተባ እያለች ስልክ መደወል ትችል እንደሆነ ጠየቀች። በኋላ ስንሰማ ለካስ ባሏ ያረጁ መጻሕፍትን ወደቀድሞ ሁኔታቸው በመመለስ የተካነ መጽሐፍ ጠራዥ ነበር። እሷና ባሏ የመጻሕፍት አፍቃሪዎች ከሆኑ ሰዎች ጋር አዘውትረው ይገናኙ የነበረ ሲሆን ከእነርሱም አንዱ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን መሰብሰብ የሚወድ አንድ የፕሮቴስታንት ቄስ ነበር። በስልክ ልትጠራው የፈለገችው እሱን ነበር። ቤት ስላላገኘችው በስልክ ማሽኑ መልእክት ተወችለት። “ከቻልክ ዛሬውኑ ለመምጣት ሞክር። እንዲህ ዓይነት ነገር አይተህ እንደማታውቅ እርግጠኛ ነኝ። ይኼ ሊያመልጥህ አይገባም!”

በአቅራቢያው ከነበረው ሊምበርግ ከተማ ከሴት ልጃቸው ጋር ሊጎበኙ የመጡ ባልና ሚስት ነበሩ። የግብዣ ጥሪው እቤታቸው እስኪደርሳቸው ድረስ ስለ ይሖዋ ምስክሮች ሰምተው አያውቁም ነበር። እነዚህ ባልና ሚስት በዜልተርስ ያለውን ይህን ትልቅ ድርጅት ለማየት ወሰኑ። ማርሎንና ሊላ የተባሉት የጀርመን ቅርንጫፍ ቢሮ ፈቃደኛ ሠራተኞች ስለ ይሖዋ ምስክሮችና በቅርንጫፍ ቢሮው ስላለው ሕይወት አብራሩላቸው። በጣም ስለተደነቁ አንድ ሰው ቤታቸው መጥቶ በቋሚነት መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስጠናቸው ጠየቁ።

“እዚህ ያለው ሁሉም ነገር ማራኪና አስደሳች ነው። ያየሁት ማተሚያውን ብቻ ቢሆንም እጅግ አስደናቂ ነው። እናንተ በጣም ጥሩና ተግባቢ ሰዎች ናችሁ። የማረከኝም ይህ ባሕርያችሁ ነው።”​—⁠የ12 ዓመቷ እስቴፋኒ በጎብኚዎች መዝገብ ላይ ያሠፈረችው።

ከአጎራባቹ መንደር የመጣች አንዲት ሴት እንዲህ አለች:-“አንድ ነገር ልንገራችሁ። እኔ ሙስሊም ብሆንም እዚህ ያለውን ነገር ለማየት ሁልጊዜ እመኝ ነበር። እናንተ ሁላችሁም በጣም ደስ የምትሉና ዘና ያለ መንፈስ ያላችሁ ሰዎች ናችሁ። እኛን [የውጭ አገር ሰዎችን] በጀርመን አገር ውስጥ ባይተዋርነት እንዳይሰማን አድርጋችኋል። ሰው ወዳዶች ናችሁ። ይህ በጣም ግሩም ነገር ነው! ነገ ከባለቤቴ ጋር እንደገና እመጣለሁ።” ለጎብኚዎች በተዘጋጀው መዝገብ ላይ “ግሩም ነው! ገነት ውስጥ እንዳለሁ ሆኖ ተሰምቶኛል” በማለት ጽፋለች።

ከመኪና ማቆሚያው እስከ በሩ ድረስ ሰዎችን የሚያመላልስ አንድ የአውቶቡስ ሹፌር አንዱ መንገደኛ ከሌላው ጋር “እንዴት ያለ የወዳጅነት አቀባበል ነው! እስከዛሬ ድረስ እዚህ ቦታ ምን እንደሚሠራ ምንም አላውቅም ነበር። እነዚህ ሰዎች እዚህ ምን እንደሚሠሩ ያወቅኩት ገና ዛሬ ነው። እንዴት ጥሩ ጠባይ እንዳላቸው ተመልከት። ይህ መቼም ከሚሰጣቸው ሃይማኖታዊ ትምህርት የመነጨ መሆን አለበት” ሲባባሉ ሰምቷል።

ጉብኝቱ ካለቀ ከሁለት ሰዓት በኋላ አንድ ሰው በአስተዳደሩ ሕንፃ ፊት ለፊት ባለው አደባባይ ወዲያ ወዲህ ይል ነበር። በሐሳብ ተመስጦ ራሱን እየነቀነቀ ወደ ሕንፃው ይመለከት ነበር። ከዚያም ወደ አንዱ የቅርንጫፍ ቢሮው ፈቃደኛ ሠራተኛ ቀረበና “ሁሉንም ነገር በፍቅር ተገፋፍታችሁ እንዳደረጋችሁት ግልጽ ነው። እኔ የይሖዋ ምስክር ባልሆንም ይሖዋ እንዲባርካችሁ እመኛለሁ” በማለት ተናገረ።

አንዲት እህት ደግሞ እንዲህ በማለት ጽፋለች:-“በዚህች አጭር ደብዳቤ አማካኝነት ልባዊ ምስጋናዬን ልገልጽላችሁ እወዳለሁ። ይህን የጉብኝት ፕሮግራም አስደሳች ለማድረግ ምን ያህል እንደደከማችሁ ይገባኛል። . . . ሁሉም ነገር ወደፊት የሰው ዘር በሙሉ በአንድነት የሚኖርበትን ጊዜ የሚያሳይ ናሙና ነው ለማለት ይቻላል። . . . ይህ የጉብኝት ፕሮግራም ለአምላካችን ለይሖዋ ተጨማሪ ክብር እንዳመጣ ምንም ጥርጥር የለውም።”​—⁠ሳንድራ።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዕድሜ ለገፉ፣ የአካል ጉዳተኛ ለሆኑ ወይም ለአቅመ ደካሞች የመጓጓዣ አገልግሎት ሲሰጥ

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባለፉት ጊዜያት እንጠቀምባቸው የነበሩት የስብከት ዘዴዎች ሲታዩ

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወደ ጉብኝቱ እንኳን ደህና መጣችሁ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጽሐፍ ቅዱስ ኤግዚቢሽን

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፈቃደኛ ሠራተኞች የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በቀላል አገላለጽ ሲያስረዱ