በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሌሎችን የሚጎዳ ንግግር አስወግዱ

ሌሎችን የሚጎዳ ንግግር አስወግዱ

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ሌሎችን የሚጎዳ ንግግር አስወግዱ

“ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ። ወንድሞቼ ሆይ፣ ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም።”​—⁠ያዕቆብ 3:10

የመናገር ችሎታ ከእንስሳት የሚለየን አንድ ልዩ ተሰጥኦ ነው። የሚያሳዝነው ግን አንዳንድ ሰዎች ይህን ስጦታ ያላግባብ ይጠቀሙበታል። ስድብ፣ እርግማን፣ ርካሽና ጸያፍ ንግግር እንዲሁም የብልግና ቀልዶች አንዳንድ ጊዜ ከአካላዊ ጉዳት የበለጠ ጎጂ ሊሆኑ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “እንደሚዋጋ ሰይፍ የሚለፈልፍ ሰው አለ” በማለት ይናገራል።​—⁠ምሳሌ 12:18

በሆነው ባልሆነው የሚሳደቡና የሚራገሙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። በጊዜያችን ልጆች የብልግና ንግግር በብዛት እንደሚጠቀሙ ትምህርት ቤቶች ሪፖርት አድርገዋል። ይሁንና አንዳንድ ሰዎች መጥፎ ቃላትን መናገር የታመቀ ስሜትን ለማብረድ ይጠቅማል የሚል አስተሳሰብ አላቸው። አንድ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “በየዕለቱ የምንጠቀምባቸው ቃላት ውስጣዊ ስሜታችንን ለመግለጽ የማያስችሉን ከሆነ ጸያፍ ንግግር መጠቀማችን ሐሳባችንን በሚገባ ለመግለጽ ያስ​ችለናል።” ክርስቲያኖች ጎጂ ቃላት መናገርን እንዲህ አቅልለው ሊመለከቱት ይገባል? በዚህ ረገድ አምላክ ያለው አመለካከት ምንድን ነው?

ጸያፍ ንግግርን አስወግዱ

ጸያፍ ቃላትን መናገር በዘመናችን የተጀመረ ነገር አይደለም። ከ2, 000 ዓመት ገደማ በፊት በሐዋርያት ዘመን ሰዎች ጸያፍ ንግግር ይጠቀሙ እንደነበር ስታውቁ ትገረሙ ይሆን? ለምሳሌ ያህል በቆላስይስ ጉባኤ ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች በሚናደዱበት ጊዜ ጸያፍ ቃላትን ይጠቀሙ ነበር። ይህን ያደረጉት ሆን ብለው ሌሎችን ለመጉዳት ምናልባትም አጸፋ ለመመለስ ብለው ይሆናል። በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ በርካታ ሰዎች በቁጣ በሚገነፍሉበት ጊዜ ጸያፍ ቃላትን ይሰነዝራሉ። በዚህም ምክንያት ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ ለዘመናችንም ጠቃሚ ነው። ጳውሎስ “እናንተ ደግሞ ቊጣንና ንዴትን ክፋትንም፣ ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር እነዚህን ሁሉ አስወግዱ” በማለት ጽፏል። (ቆላስይስ 3:8) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ክርስቲያኖች አብዛኛውን ጊዜ ከቁጣ ጋር ተያይዘው የሚመጡትን በንዴት ገንፍሎ መናገርንና ስድብን እንዲያስወግዱ በጥብቅ ተመክረዋል።

እርግጥ ነው፣ ብዙዎች ጸያፍ ቃላት የሚጠቀሙት ሌሎችን ለመጉዳት ብለው አይደለም። በአብዛኛው እንዲህ የሚያደርጉት በግድየለሽነት እንደሆነ የታወቀ ነው። ከዚህም የተነሳ ጸያፍ አባባሎች ይዋሃዷቸውና በዕለታዊ ንግግራቸው የሚጠቀሙባቸው ቃላት ይሆናሉ። እንዲያውም አንዳንዶች ያለ እነዚህ ቃላት ሐሳባቸውን መግለጽ እንኳ ያስቸግራቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ሌሎችን ለማሳቅ ብለውም ጸያፍ ቃላት ይናገራሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱን ልማድ ብዙም ጉዳት እንደሌለው ተራ ነገር አድርገን ልንመለከተው ይገባል? ቀጥሎ የቀረበውን ሐሳብ ተመልከት።

የብልግና ቀልድ ሌሎችን ለማሳቅ ተብሎ የሚነገር አስጸያፊ ንግግር ነው። ዛሬ ዛሬ የሚነገሩት የብልግና ቀልዶች አብዛኛውን ጊዜ ከወሲብ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያተኩሩ ሆነዋል። ጨዋ እንደሆኑ አድርገው ራሳቸውን የሚቆጥሩ ብዙ ሰዎች እንኳ እንዲህ ዓይነቱ ቀልድ ያስደስታቸዋል። (ሮሜ 1:28-32) ከዚህ አኳያ ብዙ ታዋቂ ኮሜዲያኖች ተፈጥሯዊም ሆነ ከተፈጥሮ ውጪ በሆኑ ፆታ ነክ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያተኩሩ ቀልዶችን የሚያዘወትሩ መሆናቸው ብዙም የሚያስገርም አይደለም። የብልግና ቀልድ በበርካታ ፊልሞች እንዲሁም የቴሌቪዥንና የራዲዮ ፕሮግራሞች ላይ ይቀርባል።

መጽሐፍ ቅዱስ የብልግና ቀልድን በተመለከተም ትምህርት ይዟል። ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ለነበሩ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፎላቸው ነበር:- ‘ለቅዱሳን እንደሚገባ ግን ዝሙትና ርኵሰት ሁሉ ወይም መመኘት በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ፤ የሚያሳፍር ነገርም የስንፍና ንግግርም ወይም ዋዛ [“ጸያፍ ነገር መናገር፣” የ1980 ትርጉም ] የማይገቡ ናቸውና አይሁኑ።’ (ኤፌሶን 5:3, 4) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ሰውን ለመጉዳት ተብሎም ሆነ ለቀልድ ጸያፍ ነገር መናገር በአምላክ ፊት የተጠላ ነው። ከሥነ ምግባር አንጻር ተቀባይነት የለውም። የሌሎችንም ስሜት ይጎዳል።

ሸካራ ቃላት አምላክን አያስደስቱም

መጥፎ ንግግር ሲባል የብልግና ቃላት መናገር ማለት ብቻ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ስድብ፣ አሽሙር፣ ፌዝና ዘለፋ ከባድ የስሜት ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ። ሁላችንም በአንደበታችን እንበድላለን፤ በተለይ በዚህ አሽሙርና ሐሜት በነገሰበት ዓለም ውስጥ ሌሎችን ልንጎዳ እንደምንችል የታወቀ ነው። (ያዕቆብ 3:​2) ሆኖም እውነተኛ ክርስቲያኖች ሌሎችን ለመጉዳት ተብሎ የሚሰነዘር ንግግርን አቅልሎ የመመልከት ዝንባሌ መያዝ የለባቸውም። ይሖዋ አምላክ ሌሎችን የሚጎዳ ማንኛውንም ዓይነት ንግግር እንደሚያወግዝ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል።

ለምሳሌ ያህል የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በሁለተኛ ነገሥት ላይ ነቢዩን ኤልሳዕን ስለተሳደቡ ልጆች የሚናገር ታሪክ ተጠቅሶ እናገኛለን። ዘገባው “አንተ መላጣ፣ ውጣ፤ አንተ መላጣ፣ ውጣ” በማለት ‘እንዳፌዙበት’ ይናገራል። የእነዚህን ልጆች ልብ ማንበብና ክፉ ሐሳባቸውን መረዳት የሚችለው ይሖዋ ነቢዩን መሳደባቸውን እንደ ቀላል ነገር አልተመለከተውም። በዚህም ምክንያት 42 የሚያህሉትን ልጆች እንዳጠፋቸው ታሪኩ ይናገራል።​—⁠2 ነገሥት 2:​23, 24

እስራኤላውያን “የእግዚአብሔር ቁጣ በሕዝቡ ላይ እስኪወጣ ድረስ፣ ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ፣ በእግዚአብሔር መልእክተኞች ይሳለቁ፣ ቃሉንም ያቃልሉ፣ በነቢያቱም ላይ ያፌዙ ነበር።” (2 ዜና መዋዕል 36:16) አምላክ በሕዝቡ ላይ የተቆጣበት ዋነኛ ምክንያት ጣዖት አምላኪ በመሆናቸውና እርሱን ባለመታዘዛቸው ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ በነቢያቱ ላይ ይሰነዝሩት ስለነበረው ስድብ ለይቶ መጥቀሱ አምላክ እንደዚህ ዓይነቱን ድርጊት እንደሚያወግዝ በግልጽ ያሳያል።

በዚህም ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ ለክርስቲያኖች “አረጋዊውን ሰው . . . በኃይለ ቃል አትናገረው” የሚል ምክር ይሰጣል። (1 ጢሞቴዎስ 5:1 አ.መ.ት ) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ከማንኛውም ሰው ጋር ባለን ግንኙነትም ይሠራል። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች “ማንንም የማይሰድቡ፣ የማይከራከሩ፣ ገሮች፣ ለሰው ሁሉ የዋህነትን ሁሉ የሚያሳዩ” እንዲሆኑ ያበረታታል።​—⁠ቲቶ 3:1

ከንፈራችንን መግታት ይኖርብናል

አንዳንድ ጊዜ አንድን ሰው በቃላት ለመወረፍ የሚገፋፋንን ውስጣዊ ስሜት መቆጣጠር ሊከብደን ይችላል። አንድ ግለሰብ በደል ሲፈጸምበት የበደለውን ሰው ፊት ለፊት ወይም በሌለበት ኃይለኛና ሸካራ ቃል በመናገር የመበቀል መብት እንዳለው ይሰማው ይሆናል። ቢሆንም ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነቱን ውስጣዊ ግፊት መቆጣጠር ይገባቸዋል። ምሳሌ 10:​19 “በቃል ብዛት ውስጥ ኃጢአት ሳይኖር አይቀርም፤ ከንፈሩን የሚገታ ግን አስተዋይ ነው” ይላል።

በዚህ ረገድ የአምላክ መላእክት ጥሩ አርአያ ይሆኑናል። የሰው ልጆች የሚፈጽሙትን ስህተት አብጠርጥረው ያውቃሉ። መላእክት በኃይልና በብርታት ከሰዎች የሚበልጡ ቢሆንም “ለይሖዋ ካላቸው አክብሮት የተነሳ” በሰዎች ላይ የስድብ ቃል አይሰነዝሩም። (2 ጴጥሮስ 2:​11 NW ) አምላክ ማንኛውም ሰው የሚሠራውን ስህተት የመመልከትና ነገሮችን የማስተካከል ችሎታ እንዳለው ስለሚያውቁ ከንፈራቸውን ይገታሉ። የመላእክት አለቃ ሚካኤል በዲያብሎስ ላይ እንኳ የስድብ ቃል ከመናገር ተቆጥቧል።​—⁠ይሁዳ 9

ክርስቲያኖች መላእክትን ለመኮረጅ ጥረት ያደርጋሉ። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር ይከተላሉ:- “ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ። ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። ተወዳጆች ሆይ፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፣ ለቊጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፣ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና።”​—⁠ሮሜ 12:17-19

የድምፃችን ቃናና መጠን እንኳ ሳይቀር የምንናገረው ነገር በሌሎች ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ሊያባብስ ይችላል። ባልና ሚስት እየተጯጯሁ በመጨቃጨቅ እርስ በርስ በቃላት ሲናቆሩ ማየት የተለመደ ነው። በርካታ ወላጆች ብዙውን ጊዜ በልጆቻቸው ላይ በቁጣ ይጮሃሉ። ይሁን እንጂ ስሜታችንን ለመግለጽ የግድ መጮህ አያስፈልገንም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘መራርነትና ንዴት ቊጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ . . . ከእናንተ ዘንድ ይወገድ’ ሲል ያሳስበናል። (ኤፌሶን 4:31) እንዲሁም “የጌታም ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር . . . ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም” በማለት ይናገራል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 2:24

መንፈስን የሚያድሱ ቃላት

በዛሬው ጊዜ መሳደብና ጸያፍ ቃላት መናገር የተለመደ ነገር ስለሆነ ክርስቲያኖች ይህን መጥፎ ተጽዕኖ የሚቋቋሙበት ዘዴ ሊኖራቸው ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ የሚረዳንን ጥሩ ዘዴ የሚያቀርብልን ሲሆን ይህም ባልንጀራችንን መውደድ ነው። (ማቴዎስ 7:​12፤ ሉቃስ 10:​27) ለባልንጀራችን ያለን ከልብ የመነጨ አሳቢነትና ፍቅር ምንጊዜም መንፈስን የሚያድሱ ቃላትን እንድንጠቀም ይገፋፋናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፣ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ” በማለት ይናገራል።​—⁠ኤፌሶን 4:29

እንዲሁም የአምላክ ቃል በአእምሯችን ውስጥ እንዲቀረጽ ማድረጋችን ሌሎችን ሊጎዳ የሚችል ንግግር ከመሰንዘር እንድንቆጠብ ያደርገናል። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና በዚያም ላይ ማሰላሰል “ርኩሰትን ሁሉ” እንድናስወግድ ይረዳናል። (ያዕቆብ 1:​21) አዎን፣ የአምላክ ቃል ቀና አስተሳሰብ እንዲኖረን ሊያደርግ ይችላል።