በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የስኳር ሕመምተኞችን ሊረዳ የሚችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ የስኳር ሕመምተኞችን ሊረዳ የሚችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ የስኳር ሕመምተኞችን ሊረዳ የሚችለው እንዴት ነው?

የስኳር ሕመምተኞች ጤንነታቸውና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ራሳቸውን መግዛታቸውና አዎንታዊ አመለካከት መያዛቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ሕመምተኞቹ እነዚህን ባሕርያት እንዲያዳብሩ ግን የማያቋርጥ ድጋፍ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። ስለሆነም ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው ‘ለዛሬ ብቻ፣ ምንም አይልህም’ በማለት ለጤናቸው የማይበጅ ምግብ እንዲበሉ ሊፈትኗቸው አይገባም። የልብ ሕመምና ዓይነት 2 የስኳር በሽታ ያለበት ሃሪ “ከባለቤቴ ጥሩ ድጋፍ አገኛለሁ” ብሏል። “ልበላቸው የማይገቡ ምግቦችን ቤት ውስጥ አታስቀምጥም። አንዳንድ ሰዎች ግን አይገባቸውም። እንዴት ያለ ችግር እንደሚፈጥርብኝ አይገነዘቡም” ይላል።

የስኳር ሕመምተኛ ከሆነ ሰው ጋር አዘውትረህ የምትገናኝ ከሆነ የሚከተሉትን ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓቶች አስታውስ። “እያንዳንዱ የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ አንድ ስንኳ የራሱን ጥቅም አይፈልግ።” እንዲሁም ‘ፍቅር የራሱን ጥቅም አይፈልግም።’​—⁠1 ቆሮንቶስ 10:​24፤ 13:​4, 5

ስለ ጤንነታቸው የሚያስቡ ሁሉ፣ የስኳር ሕመምተኞች ሆኑም አልሆኑ፣ በምግብ ረገድ ራሳቸውን መግዛት ያስፈልጋቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ሁላችንም ራስን የመግዛት ባሕርይ እንድናዳብር ስለሚመክረን በዚህ ረገድ ይረዳናል። በሕይወትህ ውስጥ ይህን ባሕርይ ለመኮትኮት ቆርጠሃል? (ገላትያ 5:​22, 23) በተጨማሪም እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች የብርታት ምንጭ ሊሆኑልን ይችላሉ። አንዲት የስኳር ሕመምተኛ ጳውሎስ “ሊወገድ ያልቻለ የሥጋ መውጊያ ነበረው። ቢሆንም አምላክን በታማኝነትና በተሟላ ሁኔታ አገልግሏል። እኔም እንደርሱ ማድረግ እችላለሁ” ብላለች።

አዎን፣ ጳውሎስ ሊያስቀረው የማይችለውን ችግር ተቀብሎ በመኖሩ የተሳካለት ሚስዮናዊ ሆኗል። (2 ቆሮንቶስ 12:​7-9) የ18 ዓመት ወጣት የሆነው ደስቲን ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ ማየት የተሳነው ከመሆኑም በላይ ከ12 ዓመቱ ጀምሮ የስኳር ሕመምተኛ ነው። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በዚህ ዓለም ሁሉ ነገር የተሟላለት አንድም ሰው እንደሌለ አውቃለሁ። ከስኳር ሕመም የምገላገልበትን የአምላክ አዲስ ዓለም በጉጉት እጠባበቃለሁ። ለኔ ይህ ሕመሜ ጊዜያዊ ነው። እንደ ጉንፋን ወይም እንደ ፍሉ ቶሎ አይተወኝ ይሆናል። አንድ ቀን ግን ይተወኛል።”

ደስቲን ይህን የጻፈው በአምላክ መንግሥት በምትተዳደር ምድራዊ ገነት ውስጥ ፍጹም የሆነ ጤንነት እንደሚገኝ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ በማሰብ ነው። (ራእይ 21:​3, 4) የአምላክ ቃል መለኮታዊ አገዛዝ በሚሰፍንበት በዚያ ዘመን ‘ታምሜአለሁ የሚል እንደማይኖር’ ይናገራል። (ኢሳይያስ 33:​24፤ ማቴዎስ 6:​9, 10) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተመሠረተው ስለዚህ ተስፋ ይበልጥ ለማወቅ ትፈልጋለህ? በአካባቢህ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን አነጋግራቸው ወይም በገጽ 5 ላይ ከሠፈሩት አድራሻዎች የሚመችህን መርጠህ ለዚህ መጽሔት አታሚዎች ጻፍ።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ራስን መግዛትና አዎንታዊ አመለካከት መያዝ በጣም አስፈላጊ ነው