በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአንድ ጊዜ ለሁለት ጌቶች ለመገዛት ያደረግሁት ሙከራ

በአንድ ጊዜ ለሁለት ጌቶች ለመገዛት ያደረግሁት ሙከራ

በአንድ ጊዜ ለሁለት ጌቶች ለመገዛት ያደረግሁት ሙከራ

ኬን ፔን እንደተናገረው

የተወለድኩት በ1938 ሲሆን ያደግሁት በኒው ሜክሲኮ፣ ዩ ኤስ ኤ የሚኖረው አያቴ ጋር ነበር። ከብት አርቢ የነበረው አያቴ 9, 700 ሄክታር ስፋት ያለው ሰፊ የግጦሽ መሬት ነበረው። በሣር ከተሸፈነውና ጅረቶች ከሚፈሱበት ከዚህ መሬት ባሻገር ተራሮች ይታዩ ነበር። የበጎች፣ የከብቶችና የፈረሶች ድምፅ እንዲሁም በእረኞቹ ጫማ ላይ ያለው የፈረስ መኮርኮሪያ ብረት ሲያቃጭል የሚያወጣው ድምፅ አሁን ድረስ ትዝ ይለኛል። አንዳንድ ጊዜ ከቤት ወጣ ብዬ ነፋሱ በሣሩ ላይ ሲያልፍ የሚፈጥረውን ለስለስ ያለ የፉጨት ድምፅና በከብቶቹ የውኃ መጠጫ ገንዳ ዙሪያ የሚኮለኮሉት ኪልዲር የተባሉ ወፎች የሚያሰሙትን ጫጫታ መስማት ያስደስተኝ ነበር።

በልጅነታችን የምናየውና የምንሰማው ነገር በቀሪው ሕይወታችን ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። አብዛኛውን ጊዜዬን የማሳልፈው ከአያቴ ጋር ነበር። አያቴ ተረት ማውራት ይችልበት ስለነበር ስለ ምዕራባዊው አሜሪካ የሚነገሩ የድሮ ታሪኮችን እንዲሁም በ1881 በ21 ዓመቱ ስለተገደለው ቢሊ ዘ ኪድ ስለተባለው በነፍሰ ገዳይነትና በዝርፊያ የታወቀ ሽፍታና ስለ ግብረአበሮቹ ያጫውተኝ ነበር።

የይሖዋ ምሥክሮች የነበሩት ወላጆቼ ተራርቀው ወደሚገኙት የከብት አርቢዎች ቤቶችና ከሃንዶ ሸለቆ ማዶ ወዳሉት ደሳሳ የሸክላ ቤቶች ምሥራቹን ለመስበክ ሲሄዱ እኔንም ይወስዱኝ ነበር። ብዙውን ጊዜ በወንድም ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ የተሰጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን በሸክላ ማጫወቻ ያሰሙ የነበረ ሲሆን የወንድም ራዘርፎርድ ድምፅ እስካሁን ድረስ ከአእምሮዬ አልጠፋም። * በሸክላ የተቀዳውን ንግግሩን ሰው ሳንመርጥ ለከብት አርቢዎች፣ ለሜክሲኮ ገበሬዎችና እንደ አፓቼና ፕዌብሎ ላሉ የአሜሪካ ሕንዶች እናሰማ ነበር። በተለይ በጎዳናዎች ላይ እያገለገሉ መጽሔቶችን ማበርከት በጣም ያስደስተኝ ነበር። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በተፋፋመባቸው በእነዚያ ዓመታት እንኳን ብዙ ሰዎች አንድ ትንሽ ልጅ መጽሔት እንዲወስዱ የሚያቀርብላቸውን ግብዣ ይቀበሉ ነበር።

አዎን፣ ወላጆቼ በመንፈሳዊ በጥሩ ሁኔታ ኮትኩተው ነበር ያሳደጉኝ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም” በማለት የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ልብ ሳልል ቀረሁ። (ማቴዎስ 6:24) አብዛኛውን ሕይወቴን ያሳለፍኩት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመካፈል ቢሆን ምንኛ ደስ ባለኝ ነበር። ሆኖም ገና የሦስት ዓመት ልጅ ሳለሁ በውስጤ ያደረብኝ ሌላ “ጌታ” የማገልገል ምኞት ይህንን የሕይወት ጎዳና እንዳልከተል አደረገኝ። ይህ የሆነው እንዴት ነበር?

አብራሪ የመሆን ምኞት አደረብኝ

በ1941 ፓይፐር ከብ የምትባል አንዲት ትንሽ አውሮፕላን የከብቶቻችን በረት አጠገብ አረፈች። አውሮፕላኗ በጎቻችንን ይነጥቁ የነበሩትን ተኩላዎች ለማደን ታገለግል ነበር። የዚያኑ ጊዜ ማለትም በሦስት ዓመቴ አውሮፕላን አብራሪ የመሆን ምኞት አደረብኝ። እነዚያ የልጅነት ጊዜያት አልፈው 17 ዓመት ሲሞላኝ ከቤተሰቦቼ ተለይቼ በሆብስ፣ ኒው ሜክሲኮ በሚገኝ አንድ አውሮፕላን ማረፊያ መሥራት ጀመርኩ። በዚያም ጋራዥ በማጽዳትና በአውሮፕላን ላይ በመሥራት ለማከናውነው አገልግሎት የበረራ ሥልጠና ይሰጠኝ ነበር። በዚህ ወቅት ክርስቲያናዊ አገልግሎት በሕይወቴ ውስጥ ሁለተኛውን ቦታ ይዞ ነበር።

በ18 ዓመቴ ሚስት አገባሁና ሦስት ልጆች ወለድን። ቤተሰቤን የማስተዳድረው ፀረ ተባይ መድኃኒት መርጫ አውሮፕላኖችን፣ የኪራይ አውሮፕላኖችንና የአዳኝ እንስሳት ማደኛ አውሮፕላኖችን በማብረር እንዲሁም የአብራሪነት ሥልጠና በመስጠት ነበር። በዚህ ሁኔታ ስድስት ዓመታት ካለፉ በኋላ በዳላስ፣ ቴክሳስ በሚገኘው የቴክሳስ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ በአብራሪነት ተቀጠርኩ። ይህ ይበልጥ የተረጋጋ ሕይወት እንዲኖረኝ ስላደረገ በዴንተን ጉባኤ ውስጥ በሽማግሌነት አገለግል ነበር። እንዲሁም አንድ አብራሪና መላ ቤተሰቡን ጨምሮ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ነበሩኝ።

ከ1970 እስከ 1973 ድረስ በጋዝ በሚሠራ ተርባይን የሚንቀሳቀሱ አውሮፕላኖችን ካበረርኩ በኋላ ዲሲ-3 የተባለው አውሮፕላን ከአገልግሎት ውጭ ሲደረግ የእኔም የአብራሪነት ፍላጎት አብሮ ጠፋ። እውነቱን ለመናገር ወዳደግሁበት ወደ ኒው ሜክሲኮ ለመመለስ በጣም ጓጉቼ ነበር። ይሁን እንጂ የአብራሪነት ሥራዬን ካቋረጥኩ ቤተሰቤን በምን አስተዳድራለሁ?

ለሥነ ጥበብ ሥራ ፍቅር አደረብኝ

ከ1961 ጀምሮ ስለ ጥንታዊው ምዕራብ አሜሪካ የሚገልጹ ስዕሎችን አልፎ አልፎ ለጊዜ ማሳለፊያ ያህል እስል የነበረ ሲሆን ጥሩ ዋጋ ያወጡ ነበር። ስለዚህ የአብራሪነት ሥራዬን ለቀቅኩና ወደ ኒው ሜክሲኮ ተመልሼ በሰዓሊነት መተዳደር ጀመርኩ። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ሚዛኔን መጠበቅ አልቻልኩም። ለጥበብ የነበረኝ ፍቅር ሕይወቴን ተቆጣጠረው። ስዕል መሳል፣ ከጊዜ በኋላ የጀመርኩት የቅርጻ ቅርጽ ሙያና አልፎ አልፎ የምሠራው የአብራሪነት ሥራ ጊዜ አሳጡኝ። በቀን ከ12-18 ሰዓት እሠራ ነበር። ይህም ቤተሰቤንና አምላኬን ችላ እንድል አደረገኝ። ውጤቱስ ምን ነበር?

ትዳሬ ተናግቶ ለፍቺ በቃን። በስተ ሰሜን ወደሚገኘው ወደ ሞንታና ተዛወርኩና ችግሬን ለመርሳት ስል ጠጪ ሆንኩ። ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የጠቀሰው ኮብላይ ልጅ የተከተለው ዓይነት ክርስቲያናዊ ያልሆነ የሞኝነት ጎዳና መከተል ጀመርኩ። (ሉቃስ 15:11-32) ከዚያም አንድ ቀን የልብ ጓደኛዬ የምለው አንድም ሰው እንደሌለኝ ተገነዘብኩ። ችግር ውስጥ ያሉ ሰዎች ሲያጋጥሙኝ “የይሖዋ ምሥክሮችን አነጋግር፤ እነርሱ ሊረዱህ ይችላሉ” እላቸዋለሁ። “ታዲያ አንተ ለምን የይሖዋ ምሥክር አልሆንክም?” ብለው ይጠይቁኛል። እንደኔ ዓይነት ሕይወት እየኖሩ የይሖዋ ምሥክር መሆን እንደማይቻል እነግራቸዋለሁ።

በመጨረሻም በ1978 በኒው ሜክሲኮ ወደሚገኘው የቀድሞ ጉባኤዬ ተመለስኩ። ከበርካታ ዓመታት በኋላ በስብሰባ ላይ ስገኝ የመጀመሪያዬ ስለነበር እምባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም። ይሖዋ ምሕረቱን አልነፈገኝም። በጉባኤ ውስጥ የነበሩት ቀደም ሲል የማውቃቸው ወንድሞችና እህቶች አካሄዴን ከይሖዋ መንገዶች ጋር እንዳስተካክል በደግነት ረድተውኛል።

አዲስ የትዳር ጓደኛና አዲስ ሕይወት

በ1980 ከብዙ ዓመታት በፊት የማውቃትን ካረን የተባለች አንዲት ቆንጆ የይሖዋ ምሥክር አገባሁ። ከቀድሞ ባለቤቷ የወለደቻቸው ጄሰን እና ጆናታን የተባሉ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሯት። ካረን ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር የነበራት ሲሆን የተረጋጋ ሕይወት እንድመራ ረድታኛለች። እንዲሁም ቤንና ፊሊፕ የተባሉ ሁለት ወንዶች ልጆች ወለድን። ነገር ግን ሕይወት አልጋ ባልጋ ሆኖልኛል ማለት አልነበረም። ከፊታችን አንድ አሳዛኝ ገጠመኝ ይጠብቀን ነበር።

ከጊዜ በኋላ ሥነ ጥበብ ማጥናት ጀመርኩ። ስለ ሰዎችና እንስሳት የሰውነት አወቃቀር በተለይ ደግሞ ስለ ፈረሶች የሰውነት ቅርጽ እንዲሁም ንድፍ ለማውጣት አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች መሠረታዊ ነገሮችን በማጥናት ብዙ ጊዜ አሳልፍ ነበር። ከዚያም የሸክላ ቅርጻ ቅርጽ መሥራት ጀመርኩ። በተለይ ስለ ጥንቱ ምዕራብ አሜሪካ የሚያሳዩ ቅርጻ ቅርጾችን ይኸውም ፈረሶችን፣ በፈረስ ላይ የተቀመጡ ሕንዶችን፣ እረኞችን እንዲሁም በጋሪ ላይ ተቀምጦ የሚጓዝ የጥንት ጊዜ ሐኪም እሠራ ነበር። ጥሩ ገበያ ስለነበረኝ ሥራዎቼን ለሕዝብ የማሳይበትና የምሸጥበት ሱቅ ለመክፈት አሰብን።

በ1987 በሲዶና አሪዞና ውስጥ አንድ የስዕልና የቅርጻ ቅርጽ መሸጫ ሱቅ ገዛንና ካረን ባቀረበችው ሐሳብ መሠረት ማውንቴይን ትሬልስ ጋለሪ ብለን ሰየምነው። ካረን ሱቁ ውስጥ ስትውል እኔ ደግሞ እቤት ሥራዬን እየሠራሁ ልጆቹን እጠብቅ ነበር። ይሁን እንጂ ልጆቹ እየታመሙብን ተቸገርን። ገበያውም ቀዝቃዛ ነበር። በመሆኑም ካረን እቤት ሆና ልጆቹን ስትንከባከብ እኔ ደግሞ ሱቅ እንድውል ተስማማን። መሣሪያዎቼን ወደ ሱቅ ወሰድኩና እዚያው ደንበኞቼ ፊት መሥራት ጀመርኩ። ይህም በገበያው ላይ ትልቅ ለውጥ አመጣ።

ሰዎች ስለምሠራቸው የነሐስ ቅርጻ ቅርጾች ይጠይቁኝ ጀመር። ለጥያቄዎቻቸው መልስ ስሰጥና ዲዛይኖቹን ከየት እንዳገኘኋቸው ሳስረዳቸው በዚያውም ሳነብ ያገኘኋቸውን ስለ ጥንቱ ምዕራብ አሜሪካ የሚናገሩ ታሪኮችን ስምና ቦታ ሳይቀር እየጠቀስኩ እነግራቸው ነበር። ይህም ሰዎች ቅርጻ ቅርጾቹን የመግዛት ፍላጎት እንዲያድርባቸው ያደረገ ሲሆን እንዲያውም አንዳንዶቹ ገና በመሠራት ላይ ላሉ ቅርጻ ቅርጾች ቀብድ ይከፍሉና ሥራው ተሠርቶ ሲያልቅ ቀሪውን ከፍለው ይወስዱ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ንግዳችን አትራፊ በመሆኑ ሌሎች ተጨማሪ ሁለት ሱቆችና 32 ሠራተኞች ያሉት አንድ ትልቅ የቅርጻ ቅርጽ ፋብሪካ አቋቋምን። ይሁን እንጂ ሥራው ፋታ የሚሰጥ አልነበረም። ስለዚህ እኔና ካረን ማብቂያ የሌለው ከሚመስለው ከዚህ የሕይወት እሽክርክሪት እንዴት መውጣት እንደምንችል ማሰብ ጀመርን። በሁኔታው ላይ ጸለይንበት። በዚህ ወቅት በጉባኤያችን ውስጥ በሽማግሌነት አገለግል የነበረ ቢሆንም ይሖዋን ከዚህ የበለጠ ማገልገል እንዳለብኝ ይሰማኝ ነበር።

ለአንድ ጌታ ብቻ መገዛት

በ1996 የወረዳችን የበላይ ተመልካች ጉባኤያችንን ሊጎበኝ ሲመጣ ምሳ አብረነው እንድንበላ ጋበዘን። ምሳውን ከመጀመራችን በፊት ፈጽሞ ያልጠበቅነው ነገር አነሳብን። ለናቫሆ ሕንዶች ወደተከለለው አካባቢ ተዛውረን በቺንሌ ከተማ አዲስ ጉባኤ በማቋቋም እርዳታ እንድናበረክት ጠየቀን። እንዴት ያለ ፈታኝ ጥያቄ ነበር! ከዚህ ቀደም ወደዚህ ገለልተኛ የሆነ አካባቢ በተደጋጋሚ የሄድን ሲሆን በአንዳንድ ክልሎች ውስጥ ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ ተሳትፈን ነበር። ይህ ግብዣ አዲስ ግብ እንድናወጣ አጋጣሚ ፈጠረልን። ማብቂያ ከሌለው ሀብትን የማሳደድ ሩጫ ወጥተን ይሖዋንና ሕዝቦቹን ይበልጥ ማገልገል የምንችልበት አጋጣሚ ይህ ብቻ ነበር። በድጋሚ ለአንድ ጌታ ብቻ መገዛት ጀመርን።

አንድ ሽማግሌ ከነቤተሰቡ ከእኛ ጋር እንዲያገለግል ጥያቄ የቀረበለት ሲሆን ካረሴተስ ከሚባለው ከዚህ ቤተሰብ ጋር በጣም እንቀራረብ ነበር። ሁለታችንም ምቹ የነበሩትን ቤቶቻችንን ሸጠን በተመደብንበት አካባቢ የምንኖርባቸውን ተንቀሳቃሽ ቤቶች ገዛን። ከዚያም የስዕልና የቅርጻ ቅርጽ መሸጫ ሱቆቹን በኋላም ፋብሪካውን ሸጥኩ። አኗኗራችንን ቀላል በማድረግ ክርስቲያናዊ አገልግሎታችንን ለማስፋት የሚያስችለንን ዝግጅት ሁሉ አደረግን።

በጥቅምት 1996 አዲሱ የቺንሌ ጉባኤ የመጀመሪያ ስብሰባውን አደረገ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ምሥራቹን ለመላው የናቫሆ ሕዝብ ለማዳረስ ከፍተኛ ጥረት ያደረግን ሲሆን በጉባኤያችን ቋንቋውን መናገር የሚችሉ ጎበዝ አቅኚዎች አሉ። የናቫሆ ብሔር አባላት ባንሆንም በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት አስቸጋሪ የሆነውን ቋንቋ ቀስ በቀስ ለመማር ጥረት እያደረግን ነው። በአሜሪካ ሕንዶች ባለ ሥልጣናት ፈቃድ ቦታ አግኝተን አዳራሽ የሠራን ሲሆን በዚያው ዓመት ሰኔ ውስጥ ለአምላክ አገልግሎት ተወስኗል።

የገጠመን አሳዛኝ ሁኔታ!

በታኅሣሥ 1996 ካረን ከልጆቹ ጋር ለአጭር ጊዜ ቆይታ ወደ ሪዮዶሶ፣ ኒው ሜክሲኮ ሄደች። እኔ አብሬያቸው መሄድ አልቻልኩም ነበር። የ14 ዓመቱ ልጃችን ቤን የበረዶ ላይ ሸርተቴ ሲጫወት ከትልቅ ቋጥኝ ጋር ተጋጭቶ ሕይወቱ ያለፈ ሲሆን ይህም ምን ያህል እንዳስደነገጠንና እንዳሳዘነን መገመት ትችላላችሁ! ለሁላችንም ከባድ ፈተና ሆኖብን ነበር። ከደረሰብን ሐዘን መጽናናት የቻልነው የመጽሐፍ ቅዱስን የትንሣኤ ተስፋ በማወቃችን ነበር። ክርስቲያን ወንድሞቻችንም በእጅጉ ረድተውናል። የቀብር ንግግሩ ለበርካታ ዓመታት በኖርንበት በሲዶና ከተማ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች አዳራሽ በተሰጠበት ዕለት ጎረቤቶቻችን ናቫሆዎችን እንዲህ በብዛት አይተው ስለማያውቁ በጣም ተደንቀው ነበር። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ከ300 ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ ተጉዘው አጽናንተውናል።

የቤን ታናሽ ወንድም ፊሊፕ ያደረገውን መንፈሳዊ እድገት ማየቱ ለእኛ ትልቅ በረከት ነው። ግሩም መንፈሳዊ ግቦች በማውጣቱ በጣም ተደስተናል። አንድ አስተማሪውን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ አስጠንቷል። ሆኖም ሁላችንም ይሖዋ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ ቤንን ለማየት እንናፍቃለን።​—⁠ኢዮብ 14:14, 15፤ ዮሐንስ 5:28, 29፤ ራእይ 21:1-4

እርስ በርሱ በሚፋቀርና በሚረዳዳ ቤተሰብ ውስጥ በመኖራችን በጣም ደስተኞች ነን። የእንጀራ ልጄ ጆናታን ከባለቤቱ ከኬነ ጋር እንዲሁም ከመጀመሪያ ሚስቴ የወለድኩት ትንሹ ልጄ ክሪስ ከባለቤቱ ከሎሪ ጋር ይሖዋን በማገልገል ላይ ይገኛሉ። የልጅ ልጆቻችን ዉድሮው እና ጆናህ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የተማሪ ክፍል ማቅረብ ጀምረዋል። አባቴ የሞተው በ1987 ሲሆን 84 ዓመት የሆናት እናቴ ግን አሁንም ይሖዋን በማገልገል ላይ ትገኛለች። ወንድሜ ጆን እና ሚስቱ ቼሪም እንዲሁ የይሖዋ አገልጋዮች ናቸው።

“ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ . . . ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም” የሚሉት የኢየሱስ ቃላት እውነት መሆናቸውን ከራሴ ተሞክሮ ተምሬያለሁ። አሁንም ቢሆን የስዕልና የቅርጻ ቅርጽ ሙያዬ ጊዜዬንና ትኩረቴን ሊሰርቅብኝ ይፈልጋል። በመሆኑም ዳግመኛ ባሪያ እንዳያደርገኝ ሚዛናዊ የመሆንንና ጥንቃቄ የማድረግን አስፈላጊነት ተምሬያለሁ። “የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፣ ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፣ የማትነቃነቁም፣ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ” የሚለውን የሐዋርያው ጳውሎስ ምክር ተግባራዊ ማድረጉ በእጅጉ የተሻለ ነው።​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:58

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 ወንድም ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ በ1942 እስከሞተበት ጊዜ ድረስ የይሖዋ ምሥክሮችን ሥራ በበላይነት ይመራ ነበር።

[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1996 በቺንሌ ሳለሁ የነበረችኝ አውሮፕላን

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“በማመንታት የሚባክን ጊዜ የለም” የተሰኘው የነሐስ ቅርጽ

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለአዳራሽ መሥሪያ በተሰጠን ቦታ ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ ከካረን ጋር

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአንድ የናቫሆ መኖሪያ ቤት ስንሰብክ