በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጉዞ ላይ ያለ ሠራዊት!

በጉዞ ላይ ያለ ሠራዊት!

በጉዞ ላይ ያለ ሠራዊት!

“የምንኖረው ቤሊዝ ውስጥ ገና በግንባታ ላይ ባለ መንደር ሲሆን አካባቢው በአረንጓዴ ተክል የተሸፈነ ነው። አንድ ቀን ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ቤታችን ተወረረ። ምግብ ፍለጋ የሚጓዙ ጉንዳኖች በበሩ ሥርና ባገኙት ስንጥቅ ሁሉ ወደ ቤቱ መጉረፍ ጀመሩ። ጉንዳኖቹ ቤታችንን በተቆጣጠሩበት ወቅት ለአንድ ወይም ለሁለት ሰዓት ያህል ለቀን ለመውጣት ተገደድን። ተመልሰን ስንገባ ቤቱ ውስጥ አንድም የነፍሳት ዘር አይታይም ነበር።”

እንደ ቤሊዝ ባሉ ሞቃታማ አገሮች ለሚኖሩ ሰዎች እንዲህ ዓይነቱ ክስተት የተለመደ እንዲያውም የሚፈለግም ነው። ይህ እንደ በረሮ የመሳሰሉትን ነፍሳትም ሆነ ሌሎች ተባዮችን ከቤት ጠራርጎ ማጥፋት የሚቻልበት መንገድ ነው። ደግሞም አቆሽሸውም ሆነ አበላሽተው የሚተዉት ነገር የለም።

እዚህ ላይ የተጠቀሱት ጉንዳኖች አርሚ አንት የሚባሉ ሲሆን በአኗኗራቸውና በእንቅስቃሴያቸው ከወታደሮች ጋር ይመሳሰላሉ። * በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ብዛት ያላቸው እነዚህ ዘላን ሠራዊቶች ቤታቸውን በአንድ ቦታ በመሥራት ፋንታ እግራቸውን በአንድ ላይ ያጠላልፉና እንደ መጋረጃ ሆነው ንግሥቲቱንና እጮቹን በመክበብ ጊዜያዊ መጠለያ ይሠራሉ። ከዚህ ጊዜያዊ መጠለያ የጉንዳን ሠራዊቶች ለምግብነት የሚያገለግሏቸውን ነፍሳትና እንደ እንሽላሊት ያሉ ትናንሽ ፍጥረታት ፍለጋ በረድፍ በረድፍ እየሆኑ ይወጣሉ። የሠራዊቱ መሪዎች ምግብ የሚሆናቸውን ነገር ከብበው ለማጥመድ ከከበባ የውጊያ ስልት ጋር የሚመሳሰል አካሄድ ይጠቀማሉ። ይህ ሁኔታ የሚከሰተው ከፊት ያሉት ጉንዳኖች የሚከተሉት ጠረን ሲያጡና ግራ ተጋብተው ወደፊት መጓዝ ሲያቆሙ ነው። ከኋላ ያሉት ጉንዳኖች ግን ወደፊት መጓዛቸውን ስለሚቀጥሉ በፊተኛው መሥመር በግራና በቀኝ በኩል ክምችት ይፈጠራል። ይህም ከከበባ የውጊያ ስልት ጋር የሚመሳሰል አካሄድ እንዲኖራቸው ያደርጋል።

እነዚህ ጉንዳኖች በ36 ቀን የተከፋፈለ ዑደት የሚከተሉ ሲሆን ለ16 ቀናት ያህል ይጓዙና ለ20 ቀናት ያህል በአንድ ቦታ ይሰፍራሉ። ንግሥቲቱ እንቁላል የምትጥለው በዚህ ወቅት ነው። ከዚያም መንጋው ረሃብ ስለሚያጠቃው በድጋሚ ጉዞ ይጀምራል። በሰልፍ የሚያደርጉት ጉዞ እስከ አሥር ሜትር የሚደርስ ስፋት ያለው ሲሆን ከጉንዳኖቹ የሚሸሹ ሸረሪቶች፣ ጊንጦች፣ ጢንዚዛዎች፣ እንቁራሪቶችና እንሽላሊቶች ከፊት ለፊታቸው ሲርመሰመሱ ይታያሉ። ከጉንዳኖቹ የሚሸሹትን እነዚህን ትናንሽ ፍጥረታት የሚመገቡ ወፎችም በዚያ ውር ውር ሲሉ መመልከት የተለመደ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በምሳሌ 30:24, 25 ላይ “እጅግ ጠቢባን” ተብለው ከተገለጹት አስደናቂ ፍጥረታት መካከል ጉንዳኖች ይገኙበታል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 በዚህ ርዕስ ላይ የተጠቀሰው የጉንዳን ዓይነት በማዕከላዊና በደቡብ አሜሪካ የሚገኘው ኤሲቶን የተባለው ዝርያ ነው።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አርሚ አንት ተብሎ የሚጠራው የጉንዳን ዓይነት

[ምንጭ]

© Frederick D. Atwood

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እግሮቻቸውን በማቆላለፍ ድልድይ ይሠራሉ

[ምንጭ]

© Tim Brown/www.infiniteworld.org