በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አሳዛኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙኝ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

አሳዛኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙኝ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

አሳዛኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙኝ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

“አሸባሪዎች እናቴን የገደሏት ለምንድን ነው?”​—ኬቨ *

“[ከመስከረም 11 በፊት] በውስጥ ለውስጥ መተላለፊያ መንገዶች መሄድ ያስደስተኝ ነበር። አሁን አሁን ግን ፈንጂ ፈንድቶ እዚያው እንዳልሞት እፈራለሁ።”​—ፒተር

የኬቨን እናት የሞተችው መስከረም 11, 2001 በኒው ዮርክ ሲቲ በዓለም የንግድ ማዕከል ላይ በተሰነዘረው ጥቃት ነበር። ፒተር እንደዚህ የመሰለ አሳዛኝ ሁኔታ ባያጋጥመውም አደጋው የማይረሳ ጠባሳ ጥሎበታል።

አንድ የዜና ዘገባ “በኒው ዮርክ የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆች መስከረም 11 የተሰነዘረው [ጥቃት] ጭንቀት ያስከተለባቸው ሲሆን ይህም በአብዛኛው እስከ ጉልምስና ዕድሜያቸው ሊዘልቅ ይችላል” ብሏል። “አደጋው በደረሰበት ቦታ ያልነበሩትም ጥቃቱን በቀጥታ እንደተመለከቱት ልጆች” እንደዚህ ያለው የስሜት መረበሽ እያጋጠማቸው መሆኑ ደግሞ ሁኔታውን አሳሳቢ ያደርገዋል። *

በእስራኤል የሚፈጸመው የአጥፍቶ ጠፊዎች ጥቃትም ሆነ በሌሎች ቦታዎች የሚከሰቱት ግድያዎች ተመሳሳይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። የስሜት መረበሽን በተመለከተ ጥናት ያካሄዱ አንድ ባለሞያ እንደዚህ ስላሉት ግድያዎች እንዲህ ብለዋል:- “[ልጆቹ] ጥቃቱ ከተሰነዘረበት ቦታ ወደ 3, 000 ኪሎ ሜትር ገደማ ያህል ርቀው ቢኖሩም እንኳ እነዚህ ሁኔታዎች ሊያስጨንቋቸው ይችላሉ።”

ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው? አንድ አደጋ ሲከሰት ልጆች ሁኔታው በመገናኛ ብዙኃን በተደጋጋሚ ሲቀርብ ይመለከታሉ። አሸባሪዎች ስለሰነዘሩት የቦምብ ጥቃት፣ በትምህርት ቤት ውስጥ ስለተፈጸመ ግድያ እንዲሁም የተፈጥሮ አደጋዎችን የሚያሳዩ አስፈሪ ምስሎች በተደጋጋሚ ስለሚቀርቡ ወጣቶች እነዚህን ነገሮች መርሳት ያስቸግራቸዋል። የኒው ዮርክ ሲቲ የትምህርት ቦርድ ያካሄደው አንድ ጥናት “ጥናቱ ከተካሄደባቸው 8, 266 ተማሪዎች መካከል 76 በመቶ የሚሆኑት የዓለም የንግድ ማዕከል ሕንፃዎች ከተደረመሱ ከስድስት ወራት በኋላም እንኳ በአሸባሪዎች የተሰነዘረው ይህ ጥቃት በተደጋጋሚ ወደ አእምሯቸው እየመጣ ይረብሻቸዋል” ብሎ መዘገቡ ምንም አያስገርምም።

የምንኖረው መጽሐፍ ቅዱስ “የሚያስጨንቅ ዘመን” ብሎ በሚጠራው ጊዜ ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) አሳዛኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙህ መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው? *

መጥፎ ነገሮች የሚከሰቱት ለምንድን ነው?

የሚያጋጥሙህን አሳዛኝ ሁኔታዎች ለመቋቋም የሚረዳህ አንደኛው መንገድ “ቅን አስተሳሰብ” መያዝ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:1 የ1980 ትርጉም ) ነገሮችን ከአምላክ አመለካከት አንጻር በማስተዋል ለማየት ሞክር። ለምሳሌ ያህል፣ አብዛኛውን ጊዜ ለሚከሰቱት አሳዛኝ ሁኔታዎች ምክንያት የሚሆነው ‘ጊዜና ያልታሰበ አጋጣሚ’ ነው። (መክብብ 9:11 NW ) ኢየሱስ ክርስቶስ በሰሊሆም ግንብ ስለተደረመሰባቸው ሰዎች በተናገረ ጊዜ ለዚህ የሚሆን ምሳሌ ጠቅሷል። በዚህ አደጋ አሥራ ስምንት ሰዎች ሞተዋል። ይሁን እንጂ ሰዎቹ አደጋ የደረሰባቸው አምላክ ስለፈረደባቸው እንደሆነ አድርገን ማሰብ እንደማይኖርብን ኢየሱስ ተናግሯል። እነዚህ ሰዎች የሞቱት አደጋው በደረሰበት ቦታና ሰዓት በአጋጣሚ በመገኘታቸው ነው። (ሉቃስ 13:1-5) በዚህ ሐቅ ላይ ማሰላሰልህ አደጋዎችን በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት ለመያዝ ይረዳሃል።

ቅን አስተሳሰብ መያዝህ ‘በእግዚአብሔር ላይ እንዳትቆጣና’ ለተፈጠረው አሳዛኝ ሁኔታ እርሱን ተወቃሽ ከማድረግ እንድትቆጠብም ይረዳሃል። (ምሳሌ 19:3) ይሖዋ “የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” እንጂ የመከራ ምንጭ አይደለም። (2 ቆሮንቶስ 1:3) አሳዛኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን በአምላክ ላይ ተቆጥተን ከእርሱ በመራቅ ፋንታ ወደ እርሱ መቅረብ ይኖርብናል። “ማንም ሲፈተን:- በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም” በሚለው በያዕቆብ 1:13 ላይ በሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ አሰላስል። *

ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት በመካከለኛው ምሥራቅ የደረሰ አንድ አሳዛኝ ክስተት ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ከዚህ አደጋ የተረፈው ብቸኛው ሰው “የእግዚአብሔር እሳት ከሰማይ ወደቀች፣ በጎቹንም አቃጠለች፣ ጠባቂዎችንም በላች” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 1:16) እንዴት ያለ አሰቃቂ አደጋ ነበር! በሁኔታው እጅግ የተደናገጠው ይህ ሰው አደጋውን አምላክ እንዳመጣው ተሰምቶት እንደነበረ ግልጽ ነው። ሆኖም ሁኔታው እንደዚያ አልነበረም። ኢዮብ 1:​7-​12 እሳቱን ያመጣው የአምላክ ጠላት የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ እንጂ አምላክ እንዳልሆነ ይገልጽልናል።

ይህ የሆነው በዓላማ ነበር፤ ሰይጣን የኢዮብን ታማኝነት እንዲፈትን ይሖዋ ፈቅዶለት ነበር። እንደ ኃይለኛ ንፋስና የጎርፍ መጥለቅለቅ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎችን በቀጥታ ሰይጣን እንደሚያመጣቸው አድርገን ማሰብ አይኖርብንም። * ያም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ” ይናገራል። (1 ዮሐንስ 5:19) በመሆኑም ሁከትና ጥፋት ለማድረስ በሰዎች ሊጠቀም ይችላል።

ይሁን እንጂ ምንም ተስፋ እንደሌለን ሊሰማን አይገባም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በ1 ሳሙኤል 22:​12-23 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ታሪክ ተመልከት። ታሪኩ ታማኝ የሆኑ ካህናትና ቤተሰቦቻቸው አረመኔያዊ በሆነ መንገድ እንደተጨፈጨፉ ይገልጻል። ክፉ የነበረው ንጉሥ ሳኦል እንዲህ ያለ የጭካኔ ድርጊት እንዲፈጽም በማነሳሳት ረገድ ሰይጣን የበኩሉን ሚና እንደተጫወተ ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም የኋላ ኋላ ንጉሥ የሆነው ታማኙ ዳዊት በ52ኛው መዝሙሩ ላይ አምላክ እንዲህ ያለ እኩይ ተግባር የሚፈጽሙ ሰዎችን እንደሚያጠፋቸው ያለውን ትምክህት ገልጿል።​—⁠መዝሙር 52:5

ዛሬም በተመሳሳይ አምላክ፣ በዲያብሎስ ገፋፊነት የሚፈጸሙ ግድያዎችንና የዓመፅ ድርጊቶችን የሚያስወግድበት ጊዜ እንደሚመጣ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በቅርቡ በልጁ በኢየሱስ በኩል “የዲያብሎስን ሥራ እን[ደሚ]ያፈርስ” ቃል ገብቶ የለም! (1 ዮሐንስ 3:8) ወደፊት ሰይጣን ያደረሰውን ጉዳት የሚያስታውስ ጠባሳ አይኖርም። አምላክ አሰቃቂ በሆኑ የዓመፅ ድርጊቶችና በሽብርተኞች ጥቃት ሳቢያ የሞቱትን እንኳ በትንሣኤ ያስባቸዋል።​—⁠ሥራ 24:15

አሳዛኝ ሁኔታዎችን መቋቋም የሚቻልበት መንገድ

መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ይህ ተስፋ በፍርሃት እንዳትዋጥ ሊረዳህ ይችላል። ሆኖም አንተም ልትወስዳቸው የምትችላቸው አንዳንድ እርምጃዎች ይኖራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በምሳሌ 12:​25 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት እንመልከት። የሚያጽናና “መልካም ቃል” ማግኘት የምትችለው ስሜትህን አውጥተህ ለሌሎች ስትናገር ብቻ ነው። እንደዚህ ማድረግህ መከራ ሲደርስብህ ከጎንህ የሚቆሙ ሰዎች እንዳሉ እንድትገነዘብ ይረዳሃል። እንግዲያው፣ የሚያስጨንቅህ ነገር ካለ ለወላጆችህ ወይም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ላለ አንድ የጎለመሰ ሰው ስሜትህን አውጥተህ ተናገር። *

በተጨማሪም አሳዛኝ ክስተቶችን የሚያሳዩ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን በተደጋጋሚ ከመመልከት ተቆጠብ። እነዚህን ፕሮግራሞች በተደጋጋሚ የምትመለከት ከሆነ ዘግናኝ የሆኑትን ምስሎች ከአእምሮህ ማውጣት ይቸግርሃል።​—⁠መዝሙር 119:37

ክርስቲያን ከሆንህ ደግሞ በተለመዱት ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ራስህን አስጠምድ። (ፊልጵስዩስ 3:16) ይህም ከክርስቲያን ባልንጀሮችህ ጋር መሰብሰብንና እምነትህን ለሌሎች ማካፈልን ይጨምራል። (ዕብራውያን 10:23-25) እንደዚህ ማድረግህ የሚረብሹ ነገሮችን ከማብሰልሰል ይጠብቅሃል። ራስህን ከሌሎች ማግለል ስሜታዊና መንፈሳዊ ጉዳት ያስከትላል።​—⁠ምሳሌ 18:1

በተለይ ደግሞ ማንኛውም ዓይነት የሚያስጨንቅ ሁኔታ ሲያጋጥመን መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የማንበብ ልማዳችንን አለማቋረጣችን ጠቃሚ ነው። የአንዲት ሎሬን የተባለች ወጣት እናት በካንሰር ትሠቃይ ነበር። ሎሬን እንዲህ ያለውን አሳዛኝ ሁኔታ ለመቋቋም የረዳት ምን እንደሆነ ስትናገር እንዲህ ትላለች:- “በዚያ አስጨናቂ ጊዜ የኢዮብን መጽሐፍ ደጋግሜ አነብብ እንደነበር አስታውሳለሁ። ከመዝሙር መጽሐፍም ብዙ መጽናኛ አግኝቻለሁ። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙትን የሚያጽናኑ ቃላት ሳነብብ በይሖዋ እቅፍ ውስጥ እንዳለሁ ሆኖ ይሰማኝ ነበር።” እህቷ ሚሼልም በተመሳሳይ እንዲህ ትላለች:- “መጽሐፍ ቅዱስን ሳላነብብ አንድ ቀን ካሳለፍኩ በጣም ይሰማኝ ነበር። የሚረብሹ ነገሮችን ማውጣት ማውረድ እጀምራለሁ። መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብብ እያንዳንዱን ዕለት ለማለፍ የሚያስችል መንፈሳዊ ምግብ አገኛለሁ።”

የምትወደውን ሰው በሞት አጥተህ ከሆነ የምትወዱት ሰው ሲሞት  * የተባለውን ብሮሹር ማንበብ በእጅጉ ሊያጽናናህ ይችላል። በብሮሹሩ ላይ የሚገኙትን ሁሉንም ጥቅሶች ካነበብክ በኋላ ጊዜ ወስደህ አሰላስልባቸው። እንዲሁም በትንሣኤ ተስፋ ላይ አሰላስል። ሎሬን “እናቴ ትንሣኤ አግኝታ እንደገና ስንገናኝ በዓይነ ሕሊናዬ ይታየኛል” በማለት ተናግራለች። “እማማ፣ ‘ተነሳሁ እኮ! ዛሬ እራት ምንድን ነው?’ ብላ ስትናገር የምሰማት ይመስለኝና ፈገግ እላለሁ።”

በጣም አሳዛኝ ሁኔታ በሚያጋጥምህ ጊዜ ወደ ይሖዋ በጸሎት መቅረብህ ሐዘንህን ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል ይሰጥሃል። ሎሬን እንዲህ ብላለች:- “እናቴ ስትሞት አጠገቧ ነበርኩ። ወዲያው ይሖዋ ሐዘኔን ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል እንዲሰጠኝ ጸለይኩ። በዚያው ቅጽበት በውስጤ የመረጋጋት ስሜት ተሰማኝ።” ወደ ይሖዋ በምትጸልዩበት ጊዜ የምትፈልጉትን ነገር ለይታችሁ ጥቀሱ። ምን እንደሚሰማችሁ ንገሩት። መዝሙራዊው “ልባችሁንም በፊቱ አፍስሱ” በማለት ተናግሯል።​—⁠መዝሙር 62:8

ከጊዜ ወደ ጊዜ በምድር ላይ የሚከሰቱት አስጨናቂ ሁኔታዎች እየተባባሱ መሄዳቸው አይቀርም። (2 ጢሞቴዎስ 3:13) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፤ . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል” የሚል ተስፋ ይሰጣል። (መዝሙር 37:9-11, 29) ይህ ተስፋ የሚፈጸምበትን ጊዜ በጉጉት መጠባበቅህ የሚያጋጥሙህን አሳዛኝ ሁኔታዎች ለመቋቋም ይረዳሃል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.6 የሥነ አእምሮ ጤና ባለሞያዎች እንደተናገሩት እንደ መፍዘዝ፣ መቃዠት፣ ራስን ማግለል፣ ዕለታዊ ተግባሮችን ማከናወን አለመቻል እንዲሁም የጥፋተኝነትና የቁጣ ስሜት ያሉት ምልክቶች ሊታዩባቸው ይችላሉ።

^ አን.9 ይህ ርዕስ ከባድ አደጋዎች ሲያጋጥሙን መቋቋም በሚቻልበት መንገድ ላይ ያተኮረ ቢሆንም ምክሮቹ የምንወደውን ሰው በሞት እንደማጣት ያለ አሳዛኝ ሁኔታ በሚያጋጥመን ጊዜም ተግባራዊ ሊሆኑ ይችላሉ።

^ አን.12 አምላክ ክፋትን በትዕግሥት ያለፈበትን ምክንያት ለማወቅ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 8 ተመልከት።

^ አን.14 በታኅሣሥ 1, 1974 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።

^ አን.18 ከፍተኛ የሆነ ውጥረት ወይም የመንፈስ ጭንቀት በሚያጋጥምበት ጊዜ ሐኪም ማማከር አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።

^ አን.22 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመገናኛ ብዙኃን የሚቀርቡትን አስጨናቂ ምስሎች በተደጋጋሚ መመልከት ጉዳት አለው