በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ዕቃ ውስጥ የሚተከሉ ተክሎች ጠቀሜታ

በለንደኑ ዘ ታይምስ ላይ እንደተዘገበው አንድ ተመራማሪ “በትምህርት ቤቶች ውስጥ ዕቃ ውስጥ የተተከሉ ተክሎች በየቦታው እንዲቀመጡ ቢደረግ ኖሮ በሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት ማግኘት ይችሉ ነበር” ብለዋል። የሪዲንግ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ዴሪክ ክሌመንትስ ክሩም ተማሪ በሚበዛባቸውና በቂ አየር በማይገባባቸው ክፍሎች ውስጥ ያለው የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን መኖር አለበት ተብሎ ከሚታሰበው መጠን 500 በመቶ በላይ ስለሚበልጥ የተማሪዎቹ በትኩረት የመከታተል ችሎታ በጣም ይቀንስና የትምህርት እድገታቸው በጣም አዝጋሚ ይሆናል። ሲክ ክላስሩም ሲንድሮም የሚል ስያሜ በተሰጠው ለመማር ምቹ ባልሆነ የተፋፈገ ክፍል ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥር “ሲክ ቢልዲንግ ሲንድሮም” የሚል ስያሜ በተሰጠው የሠራተኞች ምርታማነትና የሥራ ቅልጥፍና እንዲቀንስ በሚያደርግ ምቹ ያልሆነ የሥራ ቦታ ከሚሠሩ ሠራተኞች ቁጥር በአምስት እጥፍ ይበልጣል። የአንድን ክፍል የአየር ጥራት ለማሻሻል እንዴት ያሉ ተክሎችን መጠቀም ይቻላል? በዩናይትድ ስቴትስ የተደረገ አንድ ጥናት ስፓይደር ፕላንት የተባለው ተክል በዚህ ረገድ በጣም ጠቃሚ እንደሆነ ገልጿል። በተጨማሪም ድራገን ትሪ፣ አይቪ፣ ራበር ፕላንት፣ ፒስ ሊሊና ዩካ የተባሉት ተክሎች የአየር ብክለትን በማስወገድ ረገድ በጣም ውጤታማ ናቸው። የቤት ውስጥ ተክሎች ካርቦን ዳይኦክሳይድን ወደ ኦክሲጅን በመለወጥ የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን እንዲቀንስ ያደርጋሉ።

የትላልቅ ከተሞች መቆሸሽ

ኤል ዩኒቨርሳል የተባለው የሜክሲኮ ሲቲ ጋዜጣ “ሜክሲኮ ሲቲ፣ ካራካስ፣ ቦጎታና ሃቫና በዓለም ተወዳዳሪ ያልተገኘላቸው ቆሻሻ የበዛባቸው ከተሞች ናቸው” በማለት ዘግቧል። ይህ ለንደን ታትሞ የወጣውና መርሰር የተባለ ድርጅት ያደረገው ጥናት ውጤት ነው። ብክለት በዓለም ከተሞች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት የመረመረው ይህ ጥናት እንደ አየር ጥራት፣ ፍሳሽ ማስወገድ፣ ደህንነት መጠበቅ፣ ቤት፣ ትምህርት፣ መጓጓዣና ሕዝባዊ አገልግሎት እንደልብ መገኘት የመሰሉትን ጉዳዮች ከግንዛቤ አስገብቷል። ከአውሮፓ ከተሞች መካከል በአጠቃላይ ለኑሮ አመቺ በመሆን ረገድ የአንደኛነቱን ቦታ የያዙት ዙሪክና ቪየና ናቸው። በጽዳት ረገድ የአንደኛነቱን ቦታ የያዙት ካልጋሪና ሆኑሉሉ ናቸው። በሪፖርቱ መሠረት በመላው ላቲን አሜሪካ የሳን ሁዋንን እና የፖርቶ ሪኮን ያህል ለመኖሪያነት የሚያመቹ ከተሞች የሉም።

የትዳር መፍረስ የሚያስከፍለው መዘዝ

ሲቪታስ የተባለው በጎ አድራጊ ድርጅት የቤተሰብ ጥናት ክፍል የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ረበካ ኦኒል ከሁለት አሥርተ ዓመታት በላይ የተደረጉ ከ100 የሚበልጡ ጥናቶችን ከመረመሩ በኋላ “ለብዙ እናቶች፣ አባቶችና ሕፃናት ‘አባት በሌለበት ቤት’ ማደግ ድህነት፣ የስሜት ቁስለት፣ የጤንነት መታወክ፣ በጥሩ አጋጣሚ ለመጠቀም አለመቻልና አለመረጋጋት አስከትሏል” ሲሉ ዘግበዋል። የለንደኑ ዘ ሰንዴይ ቴሌግራፍ በዘገበው መሠረት “አባትና እናታቸው የተፋቱባቸው ልጆች በጤና የመታወክ ዕድላቸው 50 በመቶ፣ ከቤት የመጥፋት ዕድላቸው ሁለት እጥፍ፣ የመደፈርና የመጎሳቆል እድላቸው አምስት እጥፍ እንደሚጨምር” ኦኒል ገልጸዋል። ጋዜጣው በማከል “ከወላጅ አባታቸው ጋር የማይኖሩ ልጆች ከሰዎች ጋር ለመግባባትና ትምህርት ለመቀበል የመቸገር ዕድላቸው በሦስት እጥፍ” እንደሚበልጥ ገልጿል። ወደ ጉርምስና ዕድሜ ሲደርሱ ደግሞ የመስከር፣ የማጨስ፣ አደንዛዥ ዕፅ የመውሰድ . . . ወንጀል የመፈጸም፣ ከዕድሜያቸው በፊት ሩካቤ ሥጋ የመፈጸምና ልጅ የመውለድ ዕድላቸው በሁለት እጥፍ ይጨምራል።” ሪፖርቱ እንደገለጸው ባልና ሚስቱ ችግረኞች በሚሆኑበት ጊዜ እንኳን ልጆቻቸው እንዲህ ላሉ ችግሮች የመጋለጥ ዕድላቸው ከትዳር ጓደኛቸው የተለዩ ወላጆች ካሏቸው ልጆች ያነሰ ነው።

ራስን መግደል ከነፍስ ግድያ ምክንያቶች የአንደኛነቱን ቦታ ይዟል

ዚ ኢንዲፔንደንት የተባለው የለንደን ጋዜጣ “በመላው ዓለም ዋነኛው የግድያ ምክንያት ራስን መግደል ነው” ሲል ዘግቧል። የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ዘገባ ላይ የተመሠረተው ይህ ጽሑፍ በ2000 1.6 ሚልዮን ሰዎች ተገድለው እንደሞቱ ገልጿል። ከእነዚህ ውስጥ ራሳቸውን የገደሉ ሰዎች ብዛት 815, 000 ሲደርስ በሰው የተገደሉት 520, 000፣ በጦርነትና በተለያዩ ግጭቶች የተገደሉት 310, 000 ነበሩ። በ2000 ከተፈጸሙት ግድያዎች መካከል አብዛኞቹ “የተከናወኑት በታዳጊ አገሮች ሲሆን በበለጸጉ አገሮች የተገደሉት ሰዎች ብዛት ከ10 በመቶ ያነሰ ነው” በማለት ጋዜጣው ገልጿል። በቤላሩስ፣ በኢስቶንያና በሊቱዋኒያ ራሳቸውን የገደሉ ሰዎች ብዛት ከብሪታንያው በአራት እጥፍ ይበልጣል። በአፍሪካ፣ በደቡብና ሰሜን አሜሪካ በሰው የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ራሳቸውን ከገደሉት በእጥፍ የሚበልጥ ሲሆን በአውስትራሊያ፣ በአውሮፓና በሩቅ ምሥራቅ ግን ሁኔታው የዚህ ተቃራኒ ነው።

እንቅልፍ የተነፈጉ ልጆች

ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት የተባለው መጽሔት እንቅልፍ ማጣት በልጆች ጤንነት ላይ ከፍተኛ ችግር በማስከተል ላይ መሆኑን ገልጿል። እንቅልፍ የተነፈጉ ልጆች በትምህርታቸው ደካማ ሲሆኑ ከሌሎች ሰዎች ጋር መግባባት ያስቸግራቸዋል። ጋዜጣው “በቂ እንቅልፍ የማያገኙ ልጆች አብዛኛውን ጊዜ በትኩረት የመከታተል አቅማቸው ደካማ ሲሆን ብስጩዎች፣ ቅብጥብጦችና ግልፍተኞች ናቸው” በማለት ዘግቧል። ለእነዚህ ሁሉ ችግሮች ዋነኞቹ ተወቃሾች ወላጆች መሆናቸው ሐኪሞችን አሳስቧቸዋል። የሕፃናት ሥነ አእምሮ ሐኪም የሆኑት ብራውን ማክዶናልድ “ቤተሰቡ አንድ ላይ ሆኖ እንዲጫወት ብላችሁ ልጆቻችሁን እስከ ምሽቱ 5 ሰዓት የምታቆዩዋቸው ከሆነ አኗኗራችሁን መለወጥ ይኖርባችኋል” ብለዋል። ልጆቹ ጤናማ የሆነ የእንቅልፍ ልማድ እንዲኖራቸው ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ በአንድ የተወሰነ ሰዓት እንዲተኙና እንዲነሱ እንዲያደርጉ ወላጆች ተመክረዋል። ከመተኛታቸው በፊት እንደማጠብ፣ ማቀፍ ወይም ታሪክ ማንበብ የመሰሉ አንድ ዓይነት ድርጊት እንዲያስለምዷቸውና ሊተኙ አንድ ሰዓት ሲቀራቸው ጀምሮ ቴሌቪዥን እንዳያዩ ወይም በኮምፒውተር እንዳይጠቀሙ እንዲከለክሏቸው ተጨማሪ ምክር ተሰጥቷቸዋል።

“ጨዋታ፣ ምግብና ደም”

“የጃፓን ወጣቶች ነፃ ፊልም የሚታይባቸው፣ የኮምፒውተር ጨዋታዎች የሞሉባቸውና ምግብና የእግር እሽት ሳይቀር በነፃ የሚሰጥባቸው የተንጣለሉ አዳራሾችን ማዘውተር ጀምረዋል” ሲል አይ ኤች ቲ አሳሂ ሺምቡን ዘግቧል። “የሚፈለግባቸው አንድ ነገር ብቻ ነው። ደም መለገስ ይኖርባቸዋል።” ምክንያቱም እነዚህ አዳራሾች የጃፓን ቀይ መስቀል ማኅበር ያዘጋጃቸው የደም መቀበያ ማዕከላት ናቸው። ጋዜጣው “ሰዎች እንደ ድግስ ቤት ባለ አካባቢ ደም ይሰጣሉ” ይላል። “ብዙ ወጣቶች እንደነዚህ ባሉት አዳራሾች ደም ከሰጡ በኋላ በነፃ ብስኩት እየበሉ፣ ጭማቂ እየጠጡና የኮምፒውተር ጨዋታ እየተጫወቱ መቆየት ያስደስታቸዋል። ሌላው የሚስባቸው ነገር ደግሞ በሣምንቱ ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚሰጠው የጥንቆላ አገልግሎት ነው።” በተጨማሪም የቁንጅና ትምህርት፣ የአኩፓንክቸር፣ የእሽት፣ የሙዚቃና የሸቀጦች ሽያጭ አገልግሎት ይሰጣል። ቀይ መስቀል በጣም እየቀነሰ የመጣውን የደም ለጋሾች ቁጥር ለማሳደግ በአገሪቱ በሙሉ ያሉትን ማዕከላት በመለወጥ ላይ ነው። በአንድ ወቅት “በአስፈሪነታቸውና በማስጠላታቸው ይታወቁ የነበሩት እነዚህ ማዕከላት በአሁኑ ጊዜ “ወጣቶች የሚያዘወትሯቸው የመዝናኛ ቦታዎች ሆነዋል” በማለት ጋዜጣው ዘግቧል።

ለወገባችሁ ጥንቃቄ አድርጉ!

ኤል ፓይስ ሰመናል የተባለው የስፓንኛ ጋዜጣ “ጥሩ ያልሆነ የሰውነት አቋም፣ ውፍረትና በቂ አካላዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ ቀስ በቀስ ወገባችን እንዲጎዳ ያደርጋል” ይላል። በበለጸጉ አገሮች ከሚኖሩ ሰዎች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት በሕይወታቸው ውስጥ የወገብ ችግር ገጥሟቸው እንደሚያውቅ ተገምቷል። በወገብ በሽታዎች ላይ የሚያተኩረው የስፔይኑ ኮቫክስ ክሊኒክ የወገብ በሽታ እንዳይዘን ለመከላከልም ሆነ ከበሽታው ለመዳን አቀማመጣችንንና አቋቋማችንን ማስተካከል እንደሚኖርብን ይመክራል። ሊወሰዱ ከሚገባቸው ቀላል እርምጃዎች መካከል:- ወገብን ቀጥ አድርጎ በጎን መተኛት፣ ጀርባን መደገፊያ ላይ አስደግፎ መቀመጥ፣ ኮምፒውተር ላይ በምንሠራበት ጊዜ ትከሻችን የተፈጥሮ ቦታውን እንዲይዝ ማድረግ፣ ጎንበስ ማለት አስፈላጊ ከሆነ ከወገብ ሳይሆን ከጉልበት በርከክ ማለት፣ ለረዥም ጊዜ መቆም አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ አንዱን እግር በደረጃ ወይም በትንሽ መቀመጫ ላይ አሳርፎ ክብደትን በአንድ እግር ላይ ማሳረፍ ይገኝበታል።

ውፍረት፣ አሳሳቢ እየሆነ የመጣ ዓለም አቀፍ ችግር

የትላልቅ ሰዎችም ሆነ የሕፃናት ውፍረት “በመላው ዓለም አስደንጋጭ ደረጃ ላይ የደረሰ ችግር” ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በድሆቹ አገሮች ጭምር የሚታይ ችግር እንደሆነ ዘ ላንሰት የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። የሰሜን ካሮላይና ኢኮኖሚስትና የሥነ ምግብ ኤፒድዮሞሎጅስት የሆኑት ባሪ ፖፕኪን የዚህ መንስኤው በከፊል በቴክኖሎጂ መስክ በተደረገው እድገት ምክንያት እንደ በቆሎ፣ አኩሪ አተርና ጥጥ ከመሰሉት ሰብሎች በቀላሉ የምግብ ዘይት ማውጣት መቻሉ እንደሆነ ተናግረዋል። “በእስያና በአፍሪካ አገሮች እነዚህ ዘይቶች በዕለታዊ ምግብ ላይ ስለሚጨመሩ የምግቦቹ የካሎሪ መጠን ከፍ ሊል ችሏል” ይላል ዘ ላንሰት። በተጨማሪም መንግሥታት የሚያወጧቸው የእርሻና የንግድ ፖሊሲዎች ስኳር በጣም ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ ወደ ውጭ አገሮች እንዲላክ አስችሏል። በዚህም ምክንያት የምግብ አምራቾች ምርታቸውን የሚያጣፍጡበት ርካሽ ዘዴ እንዲያገኙ አስችሏል። በተጨማሪም በብዙ መስኮች የተደረገው የቴክኖሎጂ እድገት ጉልበት የሚጠይቁ ሥራዎችንና አድካሚ እንቅስቃሴዎችን በመቀነሱ ሰዎች እየወፈሩ መጥተዋል። የሥነ ምግብና የጤና ባለሞያዎችን የሚያሳስባቸው ውፍረት እንደ ስኳር በሽታ፣ ደም ብዛትና የልብ ሕመም የመሰሉትን ከባድ የጤና ችግሮች ሊያስከትል የሚችል መሆኑ ነው።