ውኃ ምትክ የማይገኝለት ፈሳሽ
ውኃ ምትክ የማይገኝለት ፈሳሽ
ኢየሱስ ከጉድጓድ ውኃ ስትቀዳ ላገኛት አንዲት ሳምራዊት ሴት የዘላለም ሕይወት ስለሚፈልቅበት የውኃ ምንጭ ነግሯት ነበር። (ዮሐንስ 4:14) ምንም እንኳ ኢየሱስ እዚህ ላይ የጠቀሰው ውኃ ምሳሌያዊ ቢሆንም የምንጠጣው ውኃም ከኦክሲጂን ቀጥሎ ለሕይወት በጣም አስፈላጊ የሆነ ፈሳሽ ነው። አንድ ሰው ያለ ምግብ ከሁለት ሳምንት በላይ መቆየት ይችላል፤ ያለ ውኃ ግን ከአምስት ቀን በላይ መቆየት አይችልም!
ከሰውነታችን ክብደት ሦስት አራተኛው ውኃ ነው። ለምሳሌ ያህል የአንጎላችን ከ75 እስከ 85 በመቶ እና የጡንቻዎቻችን 70 በመቶ ውኃ ነው። ውኃ ካሉት ጥቅሞች መካከል ምግብ በሰውነታችን ውስጥ እንዲፈጭና እንዲዋሃድ ያደርጋል፤ እንዲሁም ምግብን ወደ ሴሎቻችን ያጓጉዛል። መርዛማና ቆሻሻ የሆኑ ነገሮችን ከሰውነታችን ያስወግዳል፣ የመገጣጠሚያና የሆድ ድርቀት እንዳያጋጥም ይረዳል እንዲሁም የሰውነታችን ሙቀት የተስተካከለ እንዲሆን ያደርጋል። የሆነ ሆኖ በቂ ውኃ መጠጣት ውፍረት ለመቀነስ እንደሚረዳስ ታውቅ ኖሯል?
ውፍረት ለመቀነስ ውኃ መጠጣት
በመጀመሪያ ደረጃ ውኃ ስብና የምግብ ይዘት የሌለው ከመሆኑም በላይ በውስጡ ያለው የሶዲየም መጠንም ዝቅተኛ ነው። በሁለተኛ ደረጃ የምግብ ፍላጎትን ይቀንሳል። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ በሰውነታችን ውስጥ የተከማቸው ስብ ጥቅም ላይ እንዲውል ይረዳል። እንዴት? ኩላሊት በቂ ውኃ ካላገኘ በትክክል ሥራውን ማከናወን አይችልም። በዚህ ጊዜ ጉበት የኩላሊትን ሥራ መሥራት ይጀምራል። ይህ ደግሞ ጉበት ስብን በማቃጠል ጥቅም ላይ እንዲውል የማድረግ ሥራውን እንዳያከናውን እንቅፋት ይሆንበታል።
በዚህም የተነሳ ስብ በሰውነት ውስጥ ስለሚከማች እንወፍራለን። በስኮትስዴል፣ አሪዞና፣ ዩ ኤስ ኤ የሚገኘው የምግብ ጥናት ማዕከል ዶክተር የሆኑት ዶናልድ ሮበርትሰን “ውፍረትን ለመቀነስ በቂ ውኃ መጠጣት በጣም አስፈላጊ ነው። ውፍረት ለመቀነስ የሚፈልጉ ሰዎች በቂ ውኃ የማይጠጡ ከሆነ ሰውነታቸው በውስጡ የተከማቸውን ስብ በሚገባ ጥቅም ላይ ማዋል አይችልም” ሲሉ ተናግረዋል።እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ ውኃ በሰውነታችን ውስጥ ከመጠን በላይ ከተከማቸ ልንወፍር እንችላለን። በመሆኑም ብዙ ውኃ የመጠጣት ልማድ ያላቸው ሰዎች የሚጠጡትን ውኃ መጠን መቀነስ መፍትሄ እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ውጤቱ የተገላቢጦሽ ነው። ሰውነት የውኃ እጥረት እንደተፈጠረ ከተሰማው የሚያገኛትን እያንዳንዷን ጠብታ ውኃ እንደ እግርና እጅ በመሳሰሉት ቦታዎች ማከማቸት ይጀምራል። በዚህ ምክንያት የምግብ ጥናት ጠበብት ብዙ ውኃ መጠጣት እንደሚኖርብን ይመክራሉ። ከዚህም በላይ ብዙ ጨው በተመገብን መጠን ብዙ ውኃ መጠጣት እንደሚያስፈልገን መዘንጋት አይኖርብንም።
ሰውነትህን ውኃ አትንፈገው
በቆዳችን፣ በሳንባችን፣ በአንጀታችንና በኩላሊታችን አማካኝነት በየዕለቱ በአማካይ ሁለት ሊትር ውኃ፣ በመተንፈስ ብቻ ደግሞ በየቀኑ በግምት ግማሽ ሊትር ውኃ ከሰውነታችን ይወጣል። ይህን ውኃ መልሰን ካልተካነው ሰውነታችን ይጠማል። ራስ ምታት፣ ድካም፣ የጡንቻ መጓጎል፣ የሽንት መቅላት፣ መወበቅ እንዲሁም የአፍና የዓይን መድረቅ በሰውነታችን ውስጥ ከፍተኛ የውኃ እጥረት እንደተፈጠረ የሚጠቁሙ አንዳንድ ምልክቶች ናቸው።
ታዲያ ምን ያህል ውኃ መጠጣት ይኖርብናል? ውፍረትን ለመከላከልና ለማስወገድ በሚረዳ የሕክምና ዘርፍ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ሃዋርድ ፍሌክስ “አንድ ጤነኛ ሰው በቀን ቢያንስ ከስምንት እስከ አሥር ብርጭቆ (ከ2 ሊትር ያላነሰ) ውኃ መጠጣት አለበት። ስፖርት የምትሠራ ወይም ሞቃት በሆነ አካባቢ የምትኖር ከሆነ ከዚህ ይበልጥ መጠጣት ያስፈልግሃል። ወፍራም የሆኑ ሰዎች ከትክክለኛ ክብደታቸው በላይ ለሆነው ለእያንዳንዱ 10 ኪሎ ግራም አንድ ብርጭቆ ውኃ ተጨማሪ መጠጣት ይኖርባቸዋል” ብለዋል። ይሁን እንጂ ሲጠማህ ከጠጣህ በቂ ነው የሚል አመለካከት ያላቸው አንዳንድ ሰዎች አሉ። ሆኖም በጥም ከተቃጠልክ በሰውነትህ ውስጥ ያለው ውኃ ተሟጧል ማለት ነው።
ሌሎች ፈሳሾችን መጠጣት ውኃን ሊተካ ይችላልን? በውኃ የተበረዙ የፍራፍሬና የአትክልት ጭማቂዎችን መጠጣት ጥሩ ሊሆን ይችላል። ሆኖም እነዚህ ፈሳሾች በተወሰነም መጠን ቢሆን ምግብነት ስላላቸው ጭራሽ ውኃ ሊያስጠሙን ይችላሉ። በተጨማሪም ስኳርና ወተት በብዛት የሚገኝባቸውን ፈሳሾች መጠጣት ሰውነታችን እነዚህን ለመፍጨት ተጨማሪ ውኃ እንዲያስፈልገው ስለሚያደርጉ ይበልጥ ውኃ ሊያስጠሙን ይችላሉ። አልኮል እንዲሁም ካፌይን የተባለው ቅመም የሚገኝባቸው እንደ ቡናና ሻይ ያሉ መጠጦች ብዙ ስለሚያሸኑን ከሰውነታችን የወጣውን ፈሳሽ ለመተካት ብዙ ውኃ መጠጣት ያስፈልገናል። በአጭር አነጋገር ውኃን የሚተካ ፈሳሽ የለም። ታዲያ አሁን ለምን አንድ ብርጭቆ ውኃ አንጋብዝህም!
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ብዙ ውኃ እንድትጠጣ የሚያበረታቱ ጥቂት ምክሮች
● በሄድክበት ሁሉ ውኃ አይለይህ።
● ምግብ በበላህ ቁጥር አንድ ብርጭቆ ውኃ ጠጣ።
● ስፖርት ከመሥራትህ በፊት፣ በምትሠራበት ጊዜ እና ከሠራህ በኋላ ውኃ ጠጣ።
● በሻይ እረፍት ወቅት ከሻይ ወይም ከቡና ይልቅ ውኃ ጠጣ።
● የቧንቧው ውኃ ጣዕም እንዲኖረው ከፈለግህ ሎሚ ጭመቅበት ወይም የተጣራ ውኃ ጠጣ።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የሥዕል መግለጫ]
ፎቶ:- www.comstock.com