በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕክምናው አስቸጋሪነት

የሕክምናው አስቸጋሪነት

የሕክምናው አስቸጋሪነት

“ቀላል የሚባል የስኳር በሽታ የለም። ሁሉም ከባድ ነው።”​—⁠አን ዴሊ የአሜሪካ የስኳር በሽታ ማኅበር

“የደም ምርመራው ውጤት አንዳንድ ችግሮች እንዳሉ ያመለክታል። አስቸኳይ የሕክምና ክትትል ያስፈልግሻል።” ዲቦራ ይህን የዶክተሯን ቃል ስትሰማ አናቷን በዱላ እንደተመታች ሆኖ ተሰማት። “ያን ዕለት ሌሊቱን በሙሉ ላቦራቶሪው ተሳስቶ መሆን አለበት ብዬ ሳስብ አደርኩ” ትላለች። “እንዴት ልታመም እችላለሁ? ፈጽሞ ሊሆን አይችልም አልኩ።”

ዲቦራ እንደ ብዙዎቹ ሰዎች ጤነኛ እንደሆነች ይሰማት ስለነበረ አንዳንድ የሕመም ምልክቶች ቢኖሯትም እምብዛም ትኩረት አልሰጠቻቸውም። ሁልጊዜ ውኃ የሚጠማት ለአለርጂ በምትወስደው መድኃኒት ምክንያት ይመስላት ነበር። ቶሎ ቶሎ ሽንቷ የሚመጣው ደግሞ ብዙ ውኃ ስለምትጠጣ እንደሆነ አድርጋ ታስብ ነበር። ድካሙም ቢሆን የልጆች እናት ሆና ሥራ ውላ እየገባች ቢደክማት ምን ያስደንቃል?

የደም ምርመራ ሲደረግ ግን ይህ ሁሉ የሚሰማት በስኳር በሽታ ምክንያት እንደሆነ ታወቀ። የምርመራውን ውጤት መቀበል ለዲቦራ ከባድ ነገር ሆነባት። “ስለበሽታዬ ለማንም አልተናገርኩም” ትላለች። “ማታ ማታ፣ መላው ቤተሰብ ሲተኛ ጨለማውን ፍጥጥ ብዬ እየተመለከትኩ አለቅሳለሁ።” አንዳንዶች የስኳር በሽታ እንዳለባቸው ሲያውቁ እንደ ዲቦራ የስሜት መረበሽ ያጋጥማቸዋል። ቁጣና ጭንቀት ይሰማቸዋል። “እንዲህ ያለው ነገር በኔ ላይ ሊደርስ አይገባም እያልኩ አለቅስ ነበር” ትላለች ካረን።

ይህ ሁሉ በድንጋጤ ምክንያት የሚመጣ የስሜት መረበሽ ነው። ቢሆንም የስኳር ሕመምተኞች ድጋፍ ከተሰጣቸው ከችግራቸው ጋር ተላምደው መኖር ይችላሉ። ካረን “ነርሴ ያጋጠመኝን ሁኔታ ተቀብዬ እንድኖር ረድታኛለች” ብላለች። “ባለቅስ ምንም ችግር እንደሌለው ነገረችኝ። ውስጣዊ ስሜቴን በልቅሶ ማውጣቴ እንድስተካከል ረዳኝ።”

ከባድ በሽታ የሆነው ለምንድን ነው?

የስኳር በሽታ “የሕይወት ሞተር መታወክ ነው” ተብሏል። ይህም አለበቂ ምክንያት አይደለም። ሰውነት በግሉኮስ መጠቀም ሲያቅተው በርካታ ውስጣዊ ሂደቶች ይታወካሉ። የእነዚህ ሂደቶች መታወክ ደግሞ እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል። ዶክተር ሃርቬ ካትሴፍ “የስኳር በሽታ ማንንም በቀጥታ አይገድልም። ሰዎችን የሚገድለው በስኳር በሽታ ምክንያት የሚመጣው አካላዊ ቀውስ ነው። ይህ ቀውስ እንዳይደርስ በማድረግ ረገድ የተሳካልን ቢሆንም ቀውሱ ከደረሰ በኋላ ግን የሚፈለገውን ሕክምና መስጠት ገና አልቻልንም” ብለዋል። *

ታዲያ የስኳር በሽታ የያዛቸው ሰዎች በእርግጥ ተስፋ አላቸው? አዎን፣ የበሽታቸውን አሳሳቢነት ከተገነዘቡና ሕክምናቸውን በሚገባ ከተከታተሉ ተስፋ አላቸው። *

አመጋገብና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ

ዓይነት 1 የስኳር በሽታን መከላከል ባይቻልም ሳይንቲስቶች ለበሽታው የሚያጋልጡ የጂን ባሕርያትን በማጥናት የሰውነት በሽታ የመከላከል ኃይል በቆሽት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ለማድረግ በመሞከር ላይ ናቸው። (በገጽ 8 ላይ የሚገኘውን “የግሉኮስ ድርሻ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) “ዓይነት 2 የስኳር በሽታን በተመለከተ ያለው ሁኔታ ግን የተሻለ ነው” ይላል ዳያቢቲስ-ኬሪንግ ፎር ዩር ኢሞሽንስ አስ ዌል አስ ዩር ሄልዝ የተባለው መጽሐፍ። “በዘራቸው በስኳር በሽታ የመያዝ አዝማሚያ ያላቸው ብዙ ሰዎች የተመጣጠነ ምግብ በመመገብና አዘውትረው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ጥሩ አካላዊ ጥንካሬ እንዲኖራቸው ስላደረጉና ውፍረታቸውን ስለተቆጣጠሩ የበሽታው ምልክቶች እንዳይታዩባቸው ለማድረግ ችለዋል።” *

ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሴሽን አካላዊ እንቅስቃሴ የሚያስገኘውን ጥቅም ለማስገንዘብ በሴቶች ላይ ስለተደረገ ሰፊ ጥናት ዘግቧል። ጥናቱ “ለአጭር ጊዜ የሚደረግ ጉልበት የሚጠይቅ እንቅስቃሴ [የሰውነት ሴሎች] በኢንሱሊን አጋዥነት የሚቃጠለውን ግሉኮስ ከ24 ሰዓት ለሚበልጥ ጊዜ በአግባቡ መጠቀም እንዲችሉ እንደሚረዳ አረጋግጧል።” በመሆኑም ሪፖርቱ “በእግር መሄድም ሆነ ጉልበት የሚጠይቅ እንቅስቃሴ የሴቶችን በዓይነት 2 የስኳር በሽታ የመያዝ አጋጣሚ በጣም ይቀንሳል” ሲል ደምድሟል። ተመራማሪዎቹ ከተቻለ በየቀኑ፣ አለዚያም በአብዛኞቹ የሳምንት ቀናት ቢያንስ ለ30 ደቂቃ ያህል መጠነኛ የሆነ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ጥሩ እንደሆነ መክረዋል። ይህ አካላዊ እንቅስቃሴ በእግር እንደመሄድ ያለ ቀላል እንቅስቃሴ ሊሆን ይችላል። አሜሪካን ዳያቢቲስ አሶሴሽን ኮምፕሊት ጋይድ ቱ ዳያቢቲስ “በእግር መሄድ ከሁሉ የተሻለ፣ አደጋ የሌለውና ብዙ ወጪ የማይጠይቅ የእንቅስቃሴ ዓይነት ሳይሆን አይቀርም” ይላል።

ይሁን እንጂ የስኳር ሕሙማን አካላዊ እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ጊዜ የባለሙያ ክትትል ያስፈልጋቸዋል። ይህ አስፈላጊ የሚሆንበት አንደኛው ምክንያት የስኳር በሽታ በደም ሥሮችና በነርቮች ላይ ጉዳት በማድረስ የደም ዝውውር እንዲታገድና የመደንዘዝ ስሜት እንዲሰማ ስለሚያደርግ ነው። በዚህ ምክንያት በእግር ላይ ትንሽ ጭረት ቢኖር ሳይታወቅ ቆይቶ በጣም ሊቆስልና ቶሎ ብሎ ሕክምና ካላገኘ እግር እስከመቆረጥ ሊያደርስ ይችላል። *

ይሁንና አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ የስኳር በሽታን ለመቆጣጠር ሊረዳ ይችላል። አሜሪካን ዳያቢቲስ አሶሴሽን ኮምፕሊት ጋይድ “ተመራማሪዎች የሚዘወተር አካላዊ እንቅስቃሴ የሚያስገኘውን ጥቅም ይበልጥ በመረመሩ መጠን ይበልጥ ጥሩ ዜና እያመጡልን ነው” ይላል።

የኢንሱሊን ሕክምና

የስኳር በሽታ ያለባቸው ብዙ ሰዎች የአመጋገብ ጥንቃቄና አካላዊ እንቅስቃሴ ከማድረግ በተጨማሪ በየቀኑ የስኳራቸውን መጠን መመርመርና በተለያዩ ሰዓቶች ኢንሱሊን መወጋት ያስፈልጋቸዋል። ዓይነት 2 የስኳር በሽታ ከያዛቸው ሰዎች አንዳንዶቹ ጥሩ የአመጋገብና የአካል እንቅስቃሴ ልማድ በማዳበራቸው ጤንነታቸው ከመሻሻሉም በላይ ለጊዜውም ቢሆን ኢንሱሊን መወጋት አቁመዋል። * ዓይነት 1 የስኳር በሽታ የያዛት ካረን የአካል እንቅስቃሴ ማድረጓ በመርፌ የምትወስደው ኢንሱሊን በሰውነቷ ውስጥ በተሻለ ሁኔታ እንዲሠራ እንደሚረዳት ተገንዝባለች። በዚህም ምክንያት በየቀኑ የምትወጋውን ኢንሱሊን መጠን በ20 በመቶ መቀነስ ችላለች።

ይሁን እንጂ ኢንሱሊን መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ ቢገኝ ሕመምተኛው ተስፋ የሚቆርጥበት ምክንያት የለም። “ኢንሱሊን መውሰድህ ድክመት እንዳለብህ አያሳይም” ይላሉ ለበርካታ የስኳር በሽተኞች የሕክምና ክትትል የሚያደርጉት ሜሪ አን። “ምንም ዓይነት የስኳር በሽታ ይኑርህ የደምህን ስኳር መጠን በጥንቃቄ ከተቆጣጠርክ ወደኋላ የሚመጡ የጤና ችግሮችን በአብዛኛው ልትቀንስ ትችላለህ።” እንዲያውም በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት የደማቸውን ስኳር መጠን በጥንቃቄ የተቆጣጠሩ ዓይነት 1 የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች “በስኳር በሽታ ምክንያት የሚመጡ የዓይን፣ የኩላሊትና የነርቭ በሽታዎችን በእጅጉ” መከላከል እንደቻሉ አረጋግጧል። ለምሳሌ በዓይን ሕመም (ሬቲኖፓቲ) የመጠቃት ዕድላቸው በ76 በመቶ ቀንሷል። ዓይነት 2 የስኳር በሽታ ያለባቸውም ቢሆኑ የደማቸውን ስኳር መጠን በጥንቃቄ በመቆጣጠር ተመሳሳይ ጥቅም አግኝተዋል።

የኢንሱሊንን ሕክምና ይበልጥ ቀላልና የማያሳምም ለማድረግ በጣም የተለመዱት የኢንሱሊን መውጊያ መሣሪያዎች፣ ማለትም ሲሪንጆችና የኢንሱሊን ብዕሮች በጣም ቀጭን መርፌዎች እንዲኖሯቸው ተደርጓል። አብዛኛውን ጊዜ በጣም የሚያሳምመው “የመጀመሪያው መርፌ ነው” ይላሉ ሜሪ አን። “ከዚያ በኋላ ግን ምንም እንደማይሰማቸው አብዛኞቹ በሽተኞች ይናገራሉ።” ሌሎች ኢንሱሊን የመውጊያ መሣሪያዎችም አሉ። በማያሳምም መርፌ ቆዳ ላይ ጠቅ ካደረጉ በኋላ ኢንሱሊን የሚረጩና ሆድ ላይ ወይም ሌላ ቦታ ላይ ተሰክተው ለሁለት ወይም ለሦስት ቀናት የተመጠነ ኢንሱሊን ወደ ሰውነት የሚያስገቡ መሣሪያዎች ይገኛሉ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይህ የትንሽ ተንቀሳቃሽ ስልክ መጠን ያለው የኢንሱሊን መርጫ መሣሪያ የበለጠ ተወዳጅነት አትርፏል። ይህ ራሱን በራሱ እየተቆጣጠረ ሰውነት በሚያስፈልገው መጠን ኢንሱሊን የሚያስተላልፍ መሣሪያ የኢንሱሊንን አወሳሰድ ይበልጥ ትክክለኛና አመቺ አድርጎታል።

እውቀት መሰብሰባችሁን ቀጥሉ

ያም ሆነ ይህ ለሁሉም የሚሠራ አንድ ወጥ የሆነ የስኳር በሽታ ሕክምና የለም። እያንዳንዱ ግለሰብ ስለሚወስደው ሕክምና በሚያስብበት ጊዜ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት ከግንዛቤ ሊያስገባቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ። ሜሪ አን “ክትትል የሚያደርጉልህ የሕክምና ባለሙያዎች ቢኖሩም የመጨረሻው ወሳኝ አንተ ነህ” ይላሉ። እንዲያውም ዳያቢቲስ ኬር የተባለው መጽሔት “ወጥ የሆነ የግል እንክብካቤ ትምህርት ያልታከለበት ማንኛውም የስኳር በሽታ ሕክምና ያልተሟላና የሥነ ምግባር ደንብን ያልጠበቀ እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ ይችላል” ይላል።

የስኳር ሕመምተኞች ስለበሽታቸው ይበልጥ ባወቁ መጠን ጤንነታቸውን ለመንከባከብና ረዥምና ጤናማ ሕይወት የመምራት አጋጣሚያቸውን ከፍ ለማድረግ የበለጠ ብቃት ይኖራቸዋል። ይሁን እንጂ ውጤታማ ትምህርት መቅሰም ትዕግሥት ይጠይቃል። ዳያቢቲስ​—⁠ኬሪንግ ፎር ዩር ኢሞሽንስ አስ ዌል አስ ዩር ሄልዝ የተባለው መጽሐፍ “ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ለማወቅ ብትሞክር ግራ ልትጋባና ባገኘኸው ትምህርት መጠቀም ሳትችል ልትቀር ትችላለህ። ከዚህም በላይ በጣም ጠቃሚ ከሆኑት መረጃዎች አብዛኞቹ ከመጻሕፍት ወይም ከበራሪ ጽሑፎች የሚገኙ አይደሉም። በጣም አስፈላጊ የሆኑት መረጃዎች . . . የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴህ በደምህ ስኳር ላይ የሚያስከትለውን ለውጥ በመከታተል የሚገኙ ናቸው። ይህ ደግሞ የሚታወቀው በረዥም ጊዜና ከብዙ ሙከራ በኋላ ነው” ይላል።

ለምሳሌ በጥንቃቄ በመከታተል ውጥረት በሰውነትህና በስኳርህ መጠን ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ ማወቅ ትችላለህ። ኬን “የስኳር በሽታ ለ50 ዓመት አብሮኝ ኖሯል። ሰውነቴ የሚነግረኝን አውቃለሁ” ብሏል። ኬን ሰውነቱን “ማዳመጡ” ጠቅሞታል። በአሁኑ ጊዜ 70 ዓመት ያለፈው ቢሆንም ሙሉ ቀን ሠርቶ መግባት ይችላል።

ቤተሰብ የሚሰጠው ድጋፍ አስፈላጊነት

በስኳር በሽታ ሕክምና ረገድ ቤተሰብ የሚሰጠው ድጋፍ ችላ ሊባል አይገባም። እንዲያውም አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ለልጆችም ሆነ ለወጣቶች የስኳር በሽታን በመቆጣጠር ረገድ “ከሁሉ የሚበልጠውን አስተዋጽኦ የሚያበረክተው የቤተሰብ አንድነትና መረዳዳት ሳይሆን አይቀርም” ይላል።

የቤተሰብ አባሎች ስለ ስኳር በሽታ ቢያውቁና እንዲያውም በሽተኛው የሐኪም ቀጠሮ በሚኖረው ጊዜ በየተራ አብረው እየሄዱ የሚነገረውን ቢሰሙ በጣም ጠቃሚ ይሆናል። በዚህ መንገድ የሚያገኙት እውቀት ድጋፍ እንዲሰጡ፣ ቸል ሊባሉ የማይገባቸውን የሕመሙን ምልክቶች ለይተው እንዲያውቁና ምን እርዳታ ሊሰጡ እንደሚችሉ እንዲገነዘቡ ያስችላቸዋል። ከአራት ዓመቷ ጀምሮ የዓይነት 1 ስኳር በሽተኛ የሆነች ሚስት ያለችው ቴድ “የባርብራ የስኳር መጠን በጣም ዝቅ ሲል አውቃለሁ። በጨዋታ መካከል ዝም ትላለች። ብዙ ያልባታል፣ አላንዳች ምክንያት ትቆጣለች እንዲሁም ትፈዝዛለች” ብሏል።

በተመሳሳይም የኬን ሚስት ካትሪን ባሏ ገርጥቶና አልቦት ከተመለከተች እንዲሁም አለምክንያት መነጫነጭ ከጀመረ ቀላል የሆነ የሂሣብ ጥያቄ ትጠይቀዋለች። ኬን ግራ የተጋባ መልስ ከሰጠ ኃላፊነት ወስዳ በአፋጣኝ መደረግ የሚገባውን ታደርግለታለች። ኬንም ሆነ ባርብራ ስለችግራቸው የሚያውቁ፣ የሚወዷቸውና የሚተማመኑባቸው የትዳር ጓደኞች ስላሏቸው አመስጋኞች ናቸው። *

አፍቃሪ የሆኑ የቤተሰብ አባላት ደግ፣ ታጋሽና ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ ሆነው ለመገኘት መጣር ይኖርባቸዋል። እነዚህ ባሕርያት ሕመምተኛ የሆነ ሰው የሚያጋጥሙትን የኑሮ ችግሮች እንዲቋቋም ብሎም ያደረበትን በሽታ እንዲያሸንፍ ሊረዱት የሚችሉ ናቸው። የካረን ባል ሚስቱን እንደሚወዳት በተደጋጋሚ ይገልጽላታል። ይህ ደግሞ ትልቅ እርዳታ አበርክቶላታል። ካረን እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “ናይጀል ‘ሁሉም ሰው ለመኖር ምግብና ውኃ ያስፈልገዋል። አንቺ ደግሞ ምግብና ውኃ እንዲሁም ትንሽ ኢንሱሊን ያስፈልግሻል’ አለኝ። ያስፈልጉኝ የነበሩት እንደ እነዚህ ያሉ ተግባራዊ ጠቀሜታ ያላቸው የፍቅር ቃላት ናቸው።”

በተጨማሪም ቤተሰቦችና ወዳጆች የደም ስኳር መጠን ከፍና ዝቅ ሲል የበሽተኛው ጠባይም እንደሚቀያየር መረዳት ያስፈልጋቸዋል። አንዲት ሴት “በስኳር መጠን መቀነስ ምክንያት ትካዜ ሲሰማኝ ዝምተኛ፣ ግልፍተኛና ብስጩ እሆናለሁ። በኋላ ግን እንዲህ ያለ የሕፃንነት ባሕርይ በማሳየቴ በጣም አዝናለሁ። ይሁን እንጂ ለምን እንዲህ እንደሚሰማኝ ሰዎች እንደሚረዱልኝ ሳውቅ በጣም እጽናናለሁ” ብላለች።

የስኳር በሽታን በተለይ ሕመምተኛው የወዳጆቹንና የቤተሰቡን አባሎች ትብብር ካገኘ፣ በተሳካ ሁኔታ ማስታመም ይቻላል። በዚህ ረገድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችም ሊጠቅሙ ይችላሉ። እንዴት?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.8 የስኳር በሽታ ከሚያስከትላቸው አካላዊ ቀውሶች መካከል የልብ በሽታ፣ በአንጎል ውስጥ ደም መፍሰስ፣ የኩላሊት መታወክ፣ የደም ቧንቧዎች በሽታና የነርቭ መጎዳት ይገኙበታል። ደም በበቂ ሁኔታ ወደ እግር መድረስ ሲያቅተው ቁስል ይፈጠርና እስከመቆረጥ ሊያደርስ ይችላል። በተጨማሪም ለትላልቅ ሰዎች መታወር ዋነኛው ምክንያት የስኳር በሽታ ነው።

^ አን.9 ንቁ! ለየትኛውም ዓይነት ሕክምና አይወግንም። የስኳር በሽታ እንዳለባቸው የሚጠራጠሩ ሁሉ ይህን በሽታ በመከላከልና በማከም ረገድ በቂ ልምድ ያለው ሐኪም ማማከር ይኖርባቸዋል።

^ አን.11 በሆድ አካባቢ መወፈር በዳሌ አካባቢ ከመወፈር የበለጠ አደገኛ ነው።

^ አን.13 በዚህ ረገድ አጫሾች ራሳቸውን ለበለጠ አደጋ ያጋልጣሉ። ምክንያቱም የማጨስ ልማድ በልብና በደም ዝውውር ላይ ጉዳት የሚያደርስ ከመሆኑም በላይ የደም ሥሮችን ያጠባል። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ በስኳር በሽታ ምክንያት የአካል ክፍላቸውን ከተቆረጡ ሰዎች መካከል 95 በመቶ የሚሆኑት አጫሾች ናቸው ይላል።

^ አን.16 ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ የሚዋጥ መድኃኒት እንዲወስዱ ማድረግ ተችሏል። አንዳንዶቹ መድኃኒቶች ቆሽት ብዙ ኢንሱሊን እንዲያመነጭ የሚያደርጉ፣ ሌሎቹ በደም ውስጥ ያለው ስኳር መጠን ቶሎ እንዳይጨምር የሚቆጣጠሩ፣ ሌሎቹ ደግሞ ኢንሱሊን ያለመቀበልን ባሕርይ የሚቀንሱ ናቸው። (አብዛኛውን ጊዜ ለዓይነት 1 የስኳር በሽታ የሚዋጥ መድኃኒት አይታዘዝም።) ባሁኑ ጊዜ ኢንሱሊን በአፍ ሊወሰድ አይችልም። ምክንያቱም ወደ ደም ከመግባቱ በፊት የኢንሱሊኑ ፕሮቲን በጨጓራና በአንጀት ውስጥ ይፈርሳል። ኢንሱሊንም ሆነ የሚዋጥ መድኃኒት አካላዊ እንቅስቃሴ የማድረግንና ጤናማ የአመጋገብ ልማድ የመከተልን አስፈላጊነት አያስቀርም።

^ አን.26 የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች ሁሉ የስኳር በሽተኛ መሆናቸውን የሚገልጽ መታወቂያ ካርድ ምንጊዜም ሊለያቸው እንደማይገባ የሕክምና ሊቃውንት ይመክራሉ። ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ ይህ መታወቂያ ሕይወታቸውን ሊያተርፍላቸው ይችላል። ለምሳሌ የስኳር መጠን በጣም ዝቅ በማለቱ ምክንያት የሚደርሰው ችግር ሌላ ዓይነት የጤና ችግር፣ አልፎ ተርፎም የስካር ምልክት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ይህ በሽታ ወጣቶችንም ያጠቃልን?

እውቅ ኢንዶክራይኖሎጂስት እና በኒው ዮርክ የማውንት ሳይናይ የሕክምና ትምህርት ቤት ዲን የሆኑት ዶክተር አርተር ሩበንስታይን የስኳር በሽታ “የልጆች በሽታ እየሆነ መጥቷል” ይላሉ። የስኳር በሽታ የሚጀምርበት አማካይ ዕድሜ በእርግጥም እየቀነሰ መጥቷል። የስኳር በሽታ ስፔሽያሊስት የሆኑት ዶክተር ሮቢን ኤስ ጎላንድ ስለ ዓይነት 2 የስኳር በሽታ ሲናገሩ “ከአሥር ዓመት በፊት የሕክምና ተማሪዎችን ይህ በሽታ ከ40 ዓመት በታች በሆኑ ሰዎች ላይ አይታይም ብለን እናስተምር ነበር። አሁን ግን 10 ዓመት እንኳን ባልሞላቸው ልጆች ላይ ማየት ጀምረናል” ብለዋል።

በስኳር በሽታ የሚያዙ ልጆች ብዛት እየጨመረ የመጣው ለምንድን ነው? አንዳንድ ጊዜ ወላጆቻቸው የስኳር በሽታ ያለባቸው በመሆናቸው ምክንያት በስኳር በሽታ የመያዝ አዝማሚያ ወርሰው የሚወለዱ ልጆች ይኖራሉ። ይሁን እንጂ በሰውነት ክብደትና በአካባቢ ሁኔታ ምክንያት የሚመጣበት ጊዜም አለ። ባለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት በጣም ወፍራም የሆኑ ልጆች ቁጥር ከእጥፍ በላይ ጨምሯል። ምክንያቱ ምንድን ነው? “ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ በአመጋገብና በሰውነት እንቅስቃሴ ረገድ ብዙ ለውጥ ታይቷል” ይላሉ የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ ቁጥጥርና መከላከያ ማዕከላት ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ዊልያም ዲትስ። “በምግብ ቤቶች የሚዘጋጁ ምግቦችን አዘውትሮ መመገብ፣ ቁርስ ያለመብላት ልማድ እየተስፋፋ መሄድ፣ ለስላሳ መጠጦችንና ለሰውነት እምብዛም የማይጠቅሙ አሸር ባሸር ምግቦችን ማብዛት፣ በትምህርት ቤቶች የሚሰጠው [የአካል ማጠንከሪያ ትምህርት] እየቀረ መምጣትና በትምህርት ክፍለ ጊዜ መካከል የሚኖር የጨዋታ ጊዜ መቅረት ከእነዚህ ለውጦች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።”

የስኳር በሽታ ሊድን አይችልም። ስለዚህ የስኳር ሕመምተኛ የሆነ አንድ ወጣት የሰጠውን ቀላልና ግልጽ ምክር መከተል ይበጃል:- “ለሰውነት እምብዛም ጥቅም ከማይሰጡ አሸር ባሸር ምግቦች ራቁ፣ የአካል ጥንካሬያችሁን ጠብቁ።”

[በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የግሉኮስ ድርሻ

በትሪልዮን የሚቆጠሩት የሰውነታችን ሕዋሳት የኃይል ምንጫቸው ግሉኮስ ነው። ይሁን እንጂ ግሉኮስ ወደ ሕዋሳት መግባት የሚችልበት “ቁልፍ” ያስፈልገዋል። ይህ “ቁልፍ” ኢንሱሊን የሚባለው ከቆሽት የሚመነጭ ኬሚካል ነው። ዓይነት 1 ስኳር በሽታ በሚኖርበት ጊዜ ኢንሱሊን ፈጽሞ አይኖርም። ዓይነት 2 የስኳር በሽታ በሚኖርበት ጊዜ ደግሞ በአብዛኛው ሰውነት የሚያመነጨው ኢንሱሊን በቂ ሳይሆን ይቀራል። * ከዚህም በላይ ሕዋሳቱ ኢንሱሊኑን አላስገባ ይላሉ። ሁለቱም ዓይነት የስኳር በሽታዎች የሚያስከትሉት ውጤት ተመሳሳይ ነው። ሕዋሳቱ በቂ ግሉኮስ ሳያገኙ ይቀራሉ፣ በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ደግሞ በጣም ከፍ ብሎ አደገኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል።

አንድ ሰው በዓይነት 1 የስኳር በሽታ በሚያዝበት ጊዜ የሰውዬው በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት በቆሽት ውስጥ የሚገኙትን ኢንሱሊን አመንጪ ቤታ ሕዋሳት ያጠቃሉ። ስለዚህ ዓይነት 1 የስኳር በሽታ በሰውነት የበሽታ ተከላካይ ሕዋሳት መቃወስ ምክንያት የሚመጣ ሲሆን በበሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ምክንያት የሚመጣ የስኳር በሽታ ተብሎ የሚጠራበት ጊዜ አለ። በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ላይ ቀውስ ከሚፈጥሩት ነገሮች መካከል ቫይረሶች፣ መርዛማ ኬሚካሎችና አንዳንድ መድኃኒቶች ይገኛሉ። በተጨማሪም ዓይነት 1 የስኳር በሽታ አብዛኛውን ጊዜ ከወላጅ ወደ ልጅ የሚተላለፍ በመሆኑና ነጮችን በብዛት የሚያጠቃ በመሆኑ የዘር ውርስ አንደኛው ምክንያት ሊሆን ይችላል።

የዘር ውርስ በዓይነት 2 የስኳር በሽታ ላይ የበለጠ ድርሻ ያለው ቢሆንም በይበልጥ የሚታየው ነጮች ባልሆኑ ሰዎች ላይ ነው። በዚህ ዓይነቱ የስኳር በሽታ የአውስትራሊያ አቦርጅኖችና የአሜሪካ ሕንዶች በብዛት ይጠቃሉ። በተለይ የአሜሪካ ሕንዶች በዓይነት 2 ስኳር በሽታ በመጠቃት ረገድ ከዓለም የአንደኛነቱን ቦታ ይዘዋል። ተመራማሪዎች በዘር ውርስና ከመጠን ባለፈ ውፍረት መካከል ያለውን ዝምድና እንዲሁም በዘር ውርስ ምክንያት በስኳር በሽታ የመያዝ አዝማሚያ ያላቸው ሰዎች ብዙ ስብ ሲኖራቸው ይበልጥ ለስኳር በሽታ ስለሚጋለጡበት ምክንያት ጥናት እያደረጉ ነው። * ዓይነት 2 የስኳር በሽታ ከዓይነት 1 በተለየ መንገድ አብዛኛውን ጊዜ የሚይዘው ከ40 ዓመት በላይ የሆናቸውን ሰዎች ነው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.44 ከስኳር በሽተኞች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ያለባቸው የስኳር በሽታ ዓይነት 2 ነው። ይኸኛው ዓይነት የስኳር በሽታ “ኢንሱሊን የማያስፈልገው” ወይም “ከዕድሜ ጋር የሚመጣ” የስኳር በሽታ ተብሎ ይጠራ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ አጠራር በሽታውን በትክክል አይገልጸውም። ምክንያቱም ዓይነት 2 የስኳር በሽታ ከያዛቸው መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት ኢንሱሊን መውሰድ ያስፈልጋቸዋል። ከዚህም በላይ ቁጥራቸው በሚያስደነግጥ ሁኔታ እየተበራከተ የመጣ ገና ጉርምስና ዕድሜ ላይ እንኳን ያልደረሱ ብዙ ልጆች በዓይነት 2 ስኳር በሽታ እየተያዙ ነው።

^ አን.46 አንድ ሰው አብዛኛውን ጊዜ ከመጠን በላይ ወፍራም ነው የሚባለው ሊኖረው ከሚገባው ትክክለኛ ክብደት 20 በመቶ ብልጫ ሲኖረው ነው።

[ሥዕል]

የግሉኮስ ሞሊክዩል

[ምንጭ]

Courtesy: Pacific Northwest National Laboratory

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የቆሽት ድርሻ

ቆሽት የአንድ ሙዝ ያህል መጠን ያለው ከጨጓራ በስተጀርባ የሚገኝ ብልት ነው። ዚ አንኦፊሽያል ጋይድ ቱ ሊቪንግ ዊዝ ዳያቢቲስ የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው “ጤነኛ የሆነ ቆሽት በደም ውስጥ የሚኖረው የግሉኮስ መጠን ከፍና ዝቅ በሚልበት ጊዜ ሁሉ አስፈላጊውን የኢንሱሊን መጠን እያመነጨ ከትክክለኛው መጠን ያልወጣ የግሉኮስ መጠን እንዲጠበቅ በማድረግ የማያቋርጥ የማስተካከል ተግባር ይፈጽማል።” ኢንሱሊን የተባለውን ሆርሞን የሚያመነጩት በቆሽት ውስጥ የሚገኙት ቤታ ሕዋሳት ናቸው።

ቤታ ሕዋሳት በቂ ኢንሱሊን ማመንጨት ሲያቅታቸው ግሉኮስ በደም ውስጥ ይጠራቀምና የስኳር መጠን ከፍ ይላል። ከመጠን ያለፈ ኢንሱሊን በሚያመነጩበት ጊዜ ደግሞ የስኳር መጠን በጣም ይቀንሳል። ጉበት ከቆሽት ጋር በመተጋገዝና ትርፍ የሆነው ግሉኮስ በግላይኮጅን መልክ ተጠራቅሞ እንዲቆይ በማድረግ ትክክለኛ የስኳር መጠን እንዲጠበቅ ከፍተኛ እርዳታ ያበረክታል። ከቆሽት ትእዛዝ ሲደርሰው ደግሞ ግላይኮጅኑ ወደ ግሉኮስ እንዲቀየር በማድረግ አካል እንዲጠቀምበት ያደርጋል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የስኳር ድርሻ

ስኳር ማብዛት የስኳር በሽታ ያመጣል የሚል የተሳሳተ ግምት አለ። ስኳር በሉም አልበሉ፣ በዘር ውርስ ምክንያት በስኳር በሽታ የመያዝ አዝማሚያ ያላቸው ሰዎች በጣም ከወፈሩ በበሽታው የመያዛቸው ዕድል በጣም ከፍተኛ ይሆናል። ይሁን እንጂ ስኳር ማብዛት በጤና ላይ ጉዳት ማድረሱ አይቀርም። ምክንያቱም ስኳር ሰውነት የማይገነባ ምግብ ከመሆኑም በላይ ለውፍረት አስተዋጽኦ ያደርጋል።

ሌላው የተሳሳተ አስተሳሰብ ደግሞ የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች ስኳር ከመጠን በላይ ያምራቸዋል የሚለው ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የስኳር በሽተኞች ለጣፋጭ ምግቦች ያላቸው አምሮት ከአብዛኞቹ ሰዎች የተለየ አይደለም። የስኳር በሽታ ቁጥጥር ካልተደረገበት ሊያስርብ ይችላል እንጂ የስኳር አምሮትን አይጨምርም። የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች ጣፋጭ ነገር ሊበሉ ቢችሉም ከጠቅላላው ምግባቸው ጋር እንዲመጣጠን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች ፍሩክቶስ፣ ማለትም ከፍራፍሬዎችና ከአትክልቶች የሚገኝ ስኳር የሚበዛባቸው ምግቦች በእንስሳት ሕዋሳት ላይ ኢንሱሊንን ያለመቀበል ችግር እንዲከሰት እንደሚያደርጉ፣ አልፎ ተርፎም የስኳር በሽታ እንደሚያስከትሉ አረጋግጠዋል።

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ሥዕሎች]

የስኳር በሽታ በቀላሉ ሲተነተን

ቆሽት

ጤነኛ ሰው

ምግብ ከተበላ በኋላ በደም ውስጥ የሚኖረው የግሉኮስ መጠን ከፍ ስለሚል ቆሽት ትክክለኛ መጠን ያለው ኢንሱሊን ያመነጫል

የኢንሱሊን ሞሊክዩሎች በጡንቻና በሌሎች የሰውነት ሕዋሳት ላይ በሚገኙ ተቀባይ ሞሊክዩሎች ላይ ይጣበቃሉ። ይህ ደግሞ የግሉኮስ ሞሊክዩሎች ወደ ሕዋሳት እንዲገቡ የሚፈቅዱትን በረኞች ይቀሰቅሳል

ግሉኮስ የጡንቻ ሕዋሳት ውስጥ ይገባና ይቃጠላል። በዚህ መንገድ በደም ውስጥ የሚኖረው የግሉኮስ መጠን ወደ ትክክለኛው መጠን ይመለሳል

ዓይነት 1 የስኳር በሽታ

በቆሽት ውስጥ የሚገኙት ኢንሱሊን አመንጪ ቤታ ሕዋሳት በሰውነት የበሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ይጠቃሉ። በዚህ ምክንያት ቆሽት ኢንሱሊን ማመንጨቱን ያቆማል

የግሉኮስ ሞሊክዩሎች የኢንሱሊንን እገዛ ካላገኙ ወደ ሕዋሳት መግባት አይችሉም

ዓይነት 2 የስኳር በሽታ

አብዛኛውን ጊዜ ቆሽት የተወሰነ መጠን ያለው ኢንሱሊን ያመነጫል

ተቀባዮች በኢንሱሊን ቶሎ የማይቀሰቀሱ ከሆነ ግሉኮሱን ከደም ወደ ሕዋሳት የሚያስገቡት በረኞች አይቀሰቀሱም

በደም ውስጥ የሚኖረው ግሉኮስ መጠን ከፍ ይልና አስፈላጊ የሆኑ የሰውነት ሂደቶች ይስተጓጎላሉ፣ የደም ሥር ግድግዳዎችም ይጎዳሉ

[ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ሕዋስ

ተቀባይ

በረኛ

ኢንሱሊን

ኒውክሊየስ

ግሉኮስ

[ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ቀይ የደም ሥር

ቀይ የደም ሕዋሳት

ግሉኮስ

[ምንጭ]

ሰው:- The Complete Encyclopedia of Illustration/J. G. Heck

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለስኳር ሕመምተኞች ጤናማ አመጋገብ በጣም አስፈላጊ ነው

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የስኳር ሕመምተኞች በተለያዩ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ሊካፈሉ ይችላሉ