የስኳር በሽታ—“ድምፅ የለሹ ቀሳፊ”
የስኳር በሽታ—“ድምፅ የለሹ ቀሳፊ”
ኬን 21 ዓመት ከሞላው በኋላ ምንም ያህል ውኃ ቢጠጣ ጥሙን መቁረጥ እየተሳነው በመምጣቱ ግራ ተጋባ። በተጨማሪም ቶሎ ቶሎ ይሸና ነበር። ወደኋላ ላይ በየ20 ደቂቃ መሽናት ጀምሮ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ክንዶቹ መዛል ጀመሩ። የማያቋርጥ የድካም ስሜት ይሰማው ነበር። አጥርቶ ማየትም እያቃተው መጣ።
በሽታው ምን እንደሆነ ያወቀው አንድ ዓይነት ቫይረስ በያዘው ጊዜ ነበር። ሐኪም ቤት ሄዶ ሲመረመር በሽታው ፍሉ ብቻ እንዳልሆነ ታወቀ። ዓይነት 1 የስኳር በሽታ ይዞት ነበር። ይህ ዓይነቱ የሰውነት ኬሚካላዊ ሚዛን መዛባት አካላችን በአንዳንድ ንጥረ ምግቦች፣ በተለይም በደም ውስጥ ባለው ስኳር የመጠቀም ችሎታው እንዲዛባ ያደርጋል። ኬን ስድስት ሳምንት ያህል ሆስፒታል ቆየና በደሙ ውስጥ ያለው ስኳር መጠን ተስተካከለለት።
ይህ የሆነው ከ50 ዓመት በፊት ሲሆን ከዚያ ወዲህ ሕክምና በብዙ ረገድ ተሻሽሏል። ቢሆንም ኬን አሁንም የስኳር ሕመምተኛ መሆኑ አልቀረም። በዛሬው ጊዜ እንደ ኬን በስኳር በሽታ የሚሠቃዩ ሰዎች ብዙ ናቸው። በመላው ዓለም 140 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች የስኳር በሽታ እንዳለባቸው ሲገመት የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ደግሞ ይህ ቁጥር እስከ 2025 ድረስ በእጥፍ ሊያድግ ይችላል። የበሽታው መስፋፋት በዘርፉ የተሰማሩትን ባለሙያዎች በጣም ማሳሰቡ አያስገርምም። በዩናይትድ ስቴትስ የአንድ ሕክምና ማዕከል ተባባሪ ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር ሮቢን ኤስ ጎላንድ “የበሽታው መስፋፋት አሁን በምናየው መጠን ከቀጠለ ትልቅ ወረርሽኝ ጀምሯል ማለት እንችላለን” ብለዋል።
ከዓለም ዙሪያ የተገኙትን እነዚህን አጫጭር ሪፖርቶች ተመልከት።
አውስትራሊያ:- የአውስትራሊያ ዓለም አቀፍ የስኳር ሕመም ተቋም እንደሚለው “የስኳር ሕመም 21ኛውን መቶ ዘመን ከሚፈታተኑ በጣም ከባድ የጤና ችግሮች አንዱ ሆኗል።”
ሕንድ:- ቢያንስ 30 ሚልዮን የሚደርሱ ሰዎች የስኳር ሕመምተኞች ናቸው። አንድ ዶክተር “ከ15 ዓመት በፊት ከ40 ዓመት በታች የሆኑ የስኳር ሕመምተኞች እምብዛም አይገኙም ነበር። ዛሬ ግን ከሁለት የስኳር ሕሙማን መካከል አንዱ በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ነው” ብለዋል።
ሲንጋፖር:- ከ30 እስከ 69 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት የስኳር በሽታ አለባቸው። ብዙ ልጆች፣ ከአሥር ዓመት የማይበልጥ ዕድሜ ያላቸው ሳይቀሩ የስኳር በሽታ እንዳለባቸው ታውቋል።
ዩናይትድ ስቴትስ:- ወደ 16 ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች የስኳር ሕሙማን እንደሆኑና በየዓመቱ 800, 000 የሚደርሱ አዳዲስ ሕመምተኞች በዚህ ቁጥር ላይ እንደሚጨመሩ ይገመታል። ከነዚህ ሌላ በበሽታው ቢያዙም መያዛቸውን ገና ያላወቁ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ።
አንድ ሰው ለረጅም ጊዜ ሳይታወቅለት ከበሽታው ጋር ሊኖር መቻሉ የስኳር ሕመምን ሕክምና ይበልጥ አስቸጋሪ ያደርገዋል። ኤዥያዊክ የተባለው መጽሔት “ብዙውን ጊዜ የመጀመሪያዎቹ የበሽታው ምልክቶች ጎልተው የሚታዩ ባለመሆናቸው የስኳር ሕመም ሳይታወቅ ለረጅም ጊዜ ይቆያል” ብሏል። በዚህም ምክንያት የስኳር በሽታ ድምፅ የለሹ ቀሳፊ የሚል ስም ሊሰጠው ችሏል።
ይህ በሽታ በጣም በመስፋፋቱና በጣም አደገኛ በመሆኑ በሚቀጥሉት ርዕሶች ለሚከተሉት ጥያቄዎች ማብራሪያ እንሰጣለን:-
● የስኳር በሽታ የሚመጣበት ምክንያት ምንድን ነው?
● ሕመሙ ያለባቸው ሰዎች እንዴት ሊቆጣጠሩት ይችላሉ?
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የስሙ አመጣጥ
የሕክምና ባለሙያዎች ለስኳር በሽታ የሰጡት ስም “ዳያቢቲስ ሜልተስ” ሲሆን ይህ ስም የተገኘው “መምጠጥ” የሚል ትርጉም ካለው የግሪክኛ ቃልና “እንደ ማር ጣፋጭ” የሚል ትርጉም ካለው የላቲን ቃል ነው። ለዚህ በሽታ ይህን የመሰለ ስም መሰጠቱ ተገቢ ነው። ምክንያቱም የስኳር በሽታ የያዘው ሰው በአፉ የገባው ውኃ በሽንት ቧንቧው ተመጥጦ የሚወጣ ያህል ብዙ ይሸናል። በተጨማሪም ሽንቱ ስኳር ስለሚኖረው ጣፋጭ ጣዕም ይኖረዋል። እንዲያውም ቀላል የሆነ የስኳር መመርመሪያ ዘዴ ከመገኘቱ በፊት የስኳር በሽታ መኖሩን ለመመርመር ከሚያገለግሉት ዘዴዎች አንዱ የሕመምተኛውን ሽንት በጉንዳን ጉድጓድ አጠገብ ማፍሰስ ነበር። ጉንዳኖቹ ሽንቱ በፈሰሰበት ቦታ ላይ ከተሰበሰቡ ስኳር መኖሩ ይታወቃል።